Monday, December 23, 2013

ከችሎቱ ጀርባ ያለው ጥቁር ዳኛ ማነው? – (በስለሺ ሐጎስ)


ክፍል አንድ
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር አስር ቀን 2004 ዓ.ም በእነ ርዕዮት አለሙ ላይ ያስተላለፈው የጥፋተኝነት ውሳኔ በችሎቱ የተሰየሙት ዳኞች በነጻ ህሊና የሰጡት ፍርድ ነው ብሎ ያመነ ሰው አልነበረም፡፡ እዚህም እዚያም ሲወራ የነበረው ውሳኔው በመንግስት ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን ጨምሮ በርካታ ሰወች ይህንኑ በአደባባይ ጽፈውታል፡፡ ቆየት ብሎ ግን ዳኛው የተጻፈለትን እንዳነበበ የሚገልጹና ተጨማሪ ነገር ለማወቅ የሚገፋፉ መረጃዎች ወደኔ መምጣት ጀመሩ፡፡
እርግጥ የኢትየጵያ የፍትህ ስርአት በተደጋጋሚ ተፈትኖ የወደቀና ነጻነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ አይነት የጥርጣሬ ድምጾች መሰማታቸው በራሱ ብዙ የሚገርም አይደለም፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የምር እንዳስብ የሆንኩት ዳኛው የተጻፈለትን እንዳነበበ በመስማቴ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከዚያ በፊት በነበረው የፍርድ ሂደት ያስተዋልኳቸው ሦስት አጠራጣሪ ክስተቶቸ ናቸው እንደ ጋዜጠኛም ሆነ እንደ ርዕዮት የቅርብ ሰው ስለ ጉዳዩ ብዙ ለማወቅ እንድታትር የገፋፋኝ፡፡
የመጀመሪያው፣ ርዕዮት በማዕከላዊ ምርመራ ላይ እያለች የታዘብኩት ነው፡፡ ርዕዮት በተያዘች በማግስቱ አራዳ ፍርድ ቤት ቀርባ ፖሊስ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ አባቷና ጠበቃዋ የሆኑት አቶ አለሙ ደግሞ ቤተሰብ እንዲጠይቃትና የህግ ምክር እንድታገኝ አመለከቱ፡፡ ዳኛዋም ፖሊስ ይህንኑ እንዲፈጽም አዘውና የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ሰጥተው ችሎቱ አበቃ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ርዕዮት፣ ጠበቃም ሆነ ቤተሰብ ሳታገኝ 28ቱ ቀን አለፈ፡፡
የነበረው አማራጭ የቀጠሮው እለት ጠበቃዋ ገብተው ድጋሜ እንዲያመለክቱ ማድረግ ብቻ ነበር፡፡ እኛም ፍርድ ቤት ስትመጣ ጠብቀን ቢያንስ አይኗን ለማየት ጓጉተናል፡፡ በዕለቱ የሆነው ግን በጣም አስገራሚም አሳዛኝም ነበር፡፡
ቀጠሮው ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ነበረ፡፡ በዚያን ዕለት ጠዋት 2፡30 ቁርስ ላደርስላት ወደ ማዕከላዊ ስሄድ ከዚያን ዕለት በፊትም ሆነ በኋላ አይቻት የማላውቃት አንዲት ልጅ “ርዕዮትን በሌሊት ወደ ፍርድ ቤት ወስደዋታል ሮጠህ ድረስባት” ብላኝ ካጠገቤ ብን አለች፡፡ ለአቶ አለሙ በስልክ ይህንኑ ነግሬ ወደ ፍርድ ቤቱ አመራሁ፡፡ ቦታው ቅርብ በመሆኑ 10 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ደረስኩ፡፡ እኔ ወደ ግቢው ስገባ ርዕዮት በፒካፕ መኪና ተጭና እየወጣች ነበር፡፡
የፍርድ ቤቱ የቀጠሮ ሰዓት የተለወጠው ባጋጣሚ ወይም በስህተት ሊሆን ይችላል በሚል ይህ ለምን እንደሆነ መዝገብ ቤቱን ጠይቀን የተረዳነው  ኬዙን ያየችው ዳኛ በህመም ምክኒያት ለረጅም ጊዜ ስራ የምትገባው ከሰዓት በኋላ ብቻ መሆኑንና ሁኔታው ለእነሱም እንግዳ ነገር መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም የቀጠሮው ሰዓት ለውጥ በፖሊስ ፍላጎት ሆን ተብሎ ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት በፍርድ ቤቱና በፖሊስ መሀከል ሊኖር የሚገባው መስመር ላይ ችግር አለ ማለት ነው፡፡
ሌላው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለ5 ወራት ያህል ግራና ቀኙን ሲያከራክር ሰንብቶ ታህሳስ 17 2004 ዓ.ም የመጨረሻውን ፍርድ ለመስጠት በተሰየመበት ዕለት የነበረው ሁኔታ እንዲሁ ጥርጣሬውን የሚያጠናክር ነው፡፡ ቀጠሮው ከጠዋቱ 3፡00 የነበረ ቢሆንም በዚያን ዕለት ይሰጣል የተባለውን ፍርድ ለመስማት የተገኙ ሰዎች የችሎቱን አዳራሽ የሞሉት ቀደም ብለው ነበር፡፡ ዳኞቹ 1 ሰዓት አርፍደው 4፡00 ላይ ችሎቱ ተሰየመ፡፡ ወዲያውኑ ውሳኔው ማለቁንና ይሁን እንጂ በኮምፒውተር ተጽፎ ስላላለቀ ከሰዓት በኋላ እናርገው አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የእነውብሸት ጠበቃ አቶ ደርበው “ከሰዓት ሌላ ቀጠሮ ስላለኝ አልችልም” ብለው ከአራት ቀን በኋላ ለታሀሳስ 21 እንዲሆን አማራጭ አቀረቡ፡፡ ዳኛው ግን አልተቀበሉትም፡፡ “እነዚህ ሰወች ያሉት በማረሚያ ቤት ነው፤ ቀጠሮው ከሚራዘም 7 ሰዓት እንገናኝና እስከ 8፡00 እንጨርሳለን” የሚል አማራጭ አቅረቡና በዚሁ ተስማሙ፡፡
የዳኛው ንግግር የሆነ ጥሩ ነገር ሊኖር ይችላል የሚል ተስፋ ስላጫረብን ሁላችንም ከዚያው ሳንወጣ ሰዓቱ እስኪደርስ መንቆራጠጥ ያዝን፡፡
አይደርስ የለ ሰዓቱ ደርሶ ችሎቱ በሚሰየምበት አዳራሽ ተኮለኮልን፡፡ ዳኞቹ ግን በሰዓቱ የሉም፡፡ ግማሽ ሰዓት አለፈ፤ አልመጡም 8 ሰዓት ሲሆን ሁላችንም ቀጠሮ አለኝ ያሉትን ጠበቃ ደርበውን እያየን መሳቀቅ ያዝን፤  ሰዓቱ እየነጎደ ነው፤ 9 ሰዓት ሆነ፡፡ ዳኞቹም አልመጡም ጠበቃ ደርበውም አልሄዱም፡፡ 9፡45 ላይ ዳኞቹ መጡ፡፡ አቶ ደርበው ግን ቀሩ፡፡
ዳኛው ስለማርፈዳቸው ምንም ሳይሉ አሁንም ጽሁፉ ስላልደረሰ በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት አጀንዳቸውን ማገላበጥ ያዙ፡፡ “አራት ቀን ምን ሲደረግ ይራዘማል” ያሉት ዳኛ ከ23 ቀን በኋላ ለጥር 10 2006ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተው ዕለቱና ችሎቱ አበቃ፡፡ ተስፋችንም እንዲሁ፡፡
ይህ ሁኔታ አንዳች ደስ የማይል ነገር እየተከናወነ እንዳለ የሚናገር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ቀደም ሲል ያነሳነውን ጥርጣሬ ወደ እውነት የሚገፋው ተጨማሪ ክስተት፣ ለቀጠሮው መራዘም ምክኒያት ሆኖ የቀረበው ነገር ነው፡፡ የታህሳስ 17ቱ ቀጠሮ ወደ ጥር 10 የተሻገረው ውሳኔው በኮምፒውተር ተጽፎ አለማለቁ ሆኖ ሳለ ዳኛው ጥር 10 ያነበቡት በኮምፒውተር ያልተተየበ የእጅ ጽሁፍ ነበር፡፡ ስለዚህም የቀጠሮ ለውጡ የተካሄደው ከችሎቱ ጀርባ ባለ ሌላ ምክኒያት እንጂ ዳኛው እንዳሉት የኮምፒውተር ጽሁፍ ጉዳይ አይደለም ለማለት ይቻላል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ትንንሽ የሚመስሉ በርካታ ትዝብቶች ዳኛው የተጻፈለትን እንዳነበበ ከሚገልጸው መረጃ ጋር ተደምረው ሲታዩ የሚሰጡትን ትርጓሜ በማስረጃ ለማረጋገጥ መጠነኛ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
ይህን ለማረጋገጥ ሁነኛና ቀላል ዘዴ ሊሆን የሚችለው በእለቱ ዳኛው ያነበበውን የእጅ ጽሁፍና የዳኛውን ትክክለኛ የእጅ ጽሁፍ አግኝቶ ማመሳሰል ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ማስረጃዎች ተገኝተዋል፡፡ ማስረጃዎቹ ዳኛው በዕለቱ ያነበበው ጽሁፍ በራሱ በዳኛው የተጻፈ አለመሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ቀጣዮቹን ሁለት ምስሎች ይመልከቱ
pic 1
pic 2                                                                                                                   መልስ የሚያስፈጋቸው ጥያቄዎች
ጥያቄ 1 የግራ ወይም የቀኝ ዳኛው ሊጽፉት አይችሉም?
    በፍጹም፡፡
ጥያቄ 2 ከፊደል አጣጣሉ በተጨማሪ የፅሁፎቹን ልዩነት የሚያመለክቱ ሌሎች ማስረጃዎች አሉ?
እንዴታ!
ጥያቄ 3 ምናልባት የዳኛው ጽሁፍ የማይነበብ ሆኖ ወይ ደክሞት ወይ በሌላ ምክኒያት ከቅርብ ሰዎቹ አንዱን አጽፎት ቢሆንስ?
እሱም ሊሆን አይችልም፡፡
እኔ የደረስኩበት ድምዳሜ የሚያመለክተው ከዚህ የተለየ ነው፡፡
ከእኔ ድምዳሜ በፊት አንባቢያን እንዲመራመሩበት የሁለት ቀናት ዕድል ልስጥና ከነገ በስቲያ በክፍል ሁለት
  • ጽሁፉ ከዳኞቹ በአንዳቸው ወይም በእነሱ ሰዎች አለመጻፉን የሚያመላክቱ ነጥቦችን
  • በዚህ ጽኁፍ ከጠቀምኳቸው ሁለት ገጽ ማስረጃዎች በተጨማሪ ባለው (የጥፋተኝነት ውሳኔውን ዝርዝር የሚያትና የቅጣት ውሳኔው የተጻፈበት በድምሩ 29 ገጽ የእጅ ጽኁፍ) ላይ ያስተዋልኩትን
  • የጸሀፊውን ማንነት ለመገመት የሚያስችሉ ምልከታዎቼን ጨምሬና እና ሙሉውን ማስረጃ አያይዤ እመለስበታለሁ፡፡
እስከዚያው ከዛሬው ጨለማ ለሚለደው፣ ለነገው በሩህ ቀናችን                                                            ቺርስ!! ብያለሁ፡፡
ስለሺ ሐጎስ – ታህሳስ 14 2006ዓም

No comments:

Post a Comment