Monday, December 9, 2013

ሽፋኑ የጋረደው መጽሀፍ


ድሮ ድሮ ክረምት በመጣ የምልበት ምክንያት ከትምህርት ቤት መዘጋት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን እረፍት በመናፈቅ ነበር፡፡ አሁን አሁን ክረምቱን ከምናፍቅባቸው ምክንያቶች አንዱ ከመፃህፍት ህትመት ጋር የተያያዘ እየሆነ መጥቷል። አመቱን አድፍጠው የቆዩ መጻህፍት በክረምት ብቅ ማለታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ ከእረፍት ቀናት በአንደኛው የክረምት ሲሳይ ከሆኑ መፃህፍት አንደኛው በእጄ ከገባ ቆየ፡፡ የመፃህፍት አዟሪው ደንበኛዬ “ቀሽት የሆነ ስለቺክ የሚተርክ መጽሀፍ” ብሎ አቀበለኝ፡፡ ያቀበለኝ መጽሀፍ ርዕስ እንግዳ አልሆነብኝም፡፡ በሽፋኑ ዙሪያ በማህበራዊ ድረ ገፆች (ፌስቡክ) ላይ የሞቀ ክርክር አድርገናል፡፡ አንድ ወዳጄ በፌስቡክ ገፁ ላይ ሽፋኑን ለቆት ስለነበር፣
በዚሁ መነሾ ከጓደኞቻችን ጋር ስንነጋገር ቆይተናል፡፡ (በነገራችን ላይ በፌስ ቡክ መፃህፍትን ማስተዋወቅ እጅጉን ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ፌስ ቡክን ለቁም ነገር ማዋል ይኼ ነው!) … በመጽሀፍ ሽፋን ላይ የሴትን ልጅ ዳሌ አጉልቶ በማሳየት፣ ከጭን ጋር በተያያዘ በተሰጠው የመጽሀፉ ርዕስ … ዙሪያ ኩነና የበዛበት ውይይት አደረግን፤ እውነት ለመናገር ከኮናኞቹ መካከል ዋነኛው እኔ ነበርኩ፡፡ … እና ከመፅሀፍ ሻጩ ደንበኛዬ የተቀበልኩትን መፅሀፍ እንደቀልድ ገለጥ አድርጌ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ … ማቆም አቃተኝ!!! “ውሸትን ፍለጋ …” የሚለው መፅሀፉ መግቢያ ላይ የተሰደረው አጭር ትርክት በግርምት አንገቴን እንድወዘውዝ አደረገኝ፡፡ እንዲህ በመሰለ የሚገርም የታሪክ አውዶች ለተከበበ መጽሀፍ የተመረጠለት የሽፋን ምስልና የመጽሀፉ ርዕሰ ጭምር ተገቢ ናቸውን? ብዬ እንድጠይቅ ሆንኩኝ፡፡
“የመጀመሪያው ጫማ…” የሚለው የመጽሀፉ ሁለተኛ አጭር ትርክት ስለ መጽሀፉ ሚዛን ደፊነት እንዳረጋግጥ አደረገኝ። ይኼ ሁሉ ሲሆን መፅሀፉን ከመጽሀፍ አዟሪ ወንድሜ አልገዛሁትም ነበር፤ ታሪኮቹ አጫጭርና በአንድ ትንፋሽ የሚጨረሱ አይነት ስለሆኑ እሱም አልተከፋብኝም፡፡ የማታ ማታ መጽሀፉን ገዝቼ በቅርብ ባገኘሁት የአንድ ካፌ ወንበር ላይ አረፍ ብዬ ማንበቤን ቀጠልኩ፡፡ “ኩመላና ሊቀመንበር መንግስቱ” የሚለውን ትርክት ሳነብ ውስጤ በጥያቄ ጠነከረ፡፡ ትርክቱ ከጨርቆስ የካቲካላ መንደር ተነስቶ፣ በፕሬዚዳንት መንግስቱ ቤት በኩል አድርጎ … የህይወትን ነፀብራቅ የሚያሳይ ግሩም ስራ ነው፡፡ ህይወትን ከጭቃ አቡኪነት አንፃር የሚመረምረው ይኼው ትርክት፤ አንድ ጭቃ አቡኪ በራሱ ዓለም ውስጥ እየኖረ የሚያጋጥመውን የኑሮ ሁነት የሚያስቃኝ ነው። ስንት ሰዎች አሉ በራሳቸው ህይወት ዛቢያ ላይ የሚሽከረከሩ? ስንት ሰዎች አሉ የህይወት ግባቸው የተሰጣቸውን ህይወት መኖር ብቻ የሆነ … እያልኩ በሀሳብ እንድማስን ያደረገኝ ሥራ ነበር፡፡ ከዚሁ በተፃራሪው በህይወት ያሉ ሰዎችን (ሊቀመንበር መንግስቱንም ሆነ ባለቤታቸው ወ/ሮ ውባንቺ ቢሻውን) መጽሀፉ ውስጥ ማካተቱ ተገቢ መስሎ አልታየኝም፡፡ የኔ ነገር … ስለመጽሀፉም ሆነ ስለ ደራሲው ሳልናገር ዘልዬ ስለ ይዘቱ ማውራት ጀመርኩ አይደል? የመፅሀፉ ርዕሰ “በአራጣ የተያዘ ጭን” ይሰኛል፡፡ ደራሲው ደግሞ ዮፍታሔ ካሣ፡፡ በሊትማን ጀኔራል ትሬዲንግ አማካኝነት የሚከፋፈል መጽሀፍ ሲሆን፤ 234 ገፆች አሉት። እንደምታዩት የመፅሀፉ ሽፋን ላይ ሞንዳላ ሴት ትታያለች፡፡ ከመጽሀፉ ርዕስ ጋር የሽፋን ፎቶውን ስታስተያዩ የሚመጣባችሁ ምስል “ሮማንቲክ” እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡
የተለመደ የገበያ ጫጫታ ለመፍጠር እንደሚሞክሩ መጽሀፍት አድርጋችሁ ብትወስዱትም “ለምን?” የሚል አይኖርም፡፡ ምክንያቱም በዚህ መልኩ የቀረቡ መጻህፍትን ተሻምተን ገዝተን ቆሽታችንን ያሳረርንበት ጊዜ በዛ ያለ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ይህን የመሰለ የፅሁፍ በረከት በሽፋኑ “ቀሽምነት” ሳይነበብ ቢያልፍ ኪሳራው የጥበብ ጭምር ነው፡፡ መፅሀፉን በአንድ ትንፋሽ “ጭልጥ” ካደረግሁት በኋላ ጠቃሚ ሀሳብ ለምን አላነሳም በሚል ስሌት ይኼንን ጽሁፍ ወደ ማዘጋጀቱ ገባሁ፡፡ “በአራጣ የተያዘ ጭን” 19 ትረካዎችን ይዟል፡፡ ዳጎስ ያለው “ስድስት ኪሎ ካምፓስ” የሚለውና መቼቱን በስድስት ኪሎ ካምፓስ ያደረገው ትረካ ነው፡፡ ትረካው ከተለመደው የዩኒቨርስቲ ህይወት አፃፃፍ በተለየ መልኩ፤ የዩኒቨርስቲ ህይወት ከከባቢው ማህበራዊ ህይወት ጋር ያለውን መስተጋብር ለማነፃፀር ሞክሯል፡፡ ሙከራው ግን ብዙም የተሳካ አይመስልም፡፡ የዚህን ትርክት መሰረታዊ ጭብጥ ለማግኘት ብባዝንም ይህ ነው የሚባል ጭብጥ ለማግኘት አልታደልኩም፡፡
ይልቁንም በዘፈቀደ የተፈጠሩ በሚመስሉ ገፀ-ባህሪያት ፈገግ የሚያሰኙ እና ዘና የሚያደርጉ የዕለት ገጠመኞች ፈታ ብያለሁ። እንደኔ እንደኔ የመጽሀፉ ደራሲ የ6 ኪሎ ካምፓስ የሚለውን ትረካ ሲጽፍ ስሜቱን ከመከተል ውጪ እኛን አንባቢዎቹን ያሰበን አይመስለኝም። አንባቢው ይኼንን ጽሁፍ ሲያነብ ከመዝናናት ውጪ ምን ጭብጥ ያገኝበታል የሚለው ብዙም አላስጨነቀውም፡፡ ይህ ሁኔታ ምናልባት የዘመናዊ ልቦለድ አፃፃፍ መሰረታዊ መርህ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ ዊልያም ብሩስለን የተባሉት እንግሊዛዊ ሀያሲ፤ ይኼንኑ የሚያጠናክር ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ እንዲህ ይላሉ … The authors of the modern short story “no longer attempt to make daily life more entertaining by inventing exotic plots. Instead, modern short story writers have tended to base their narratives on their own experience; here the focus is much more on the less spectacular aspects of life, on the significance underlying what is apparently trivial. The result of such perceptive writing is perfection of form, harmony of theme and structure, and precision of style to reveal the subtleties of the human mind and of human behaviour. (የዘመናዊ አጭር ትረካ ፀሀፊዎች አዳዲስ የህይወት ዘይቤዎችን እና መሳጭ የሆኑ የታሪክ መዋቅሮችን ለመፍጠር ላይ ታች የሚሉበት ጊዜ አብቅቷል፡፡ ይልቁንም ዘመናዊ ጸሀፍቱ በራሳቸው የህይወት ልምምድ ላይ ይመሰረታሉ፤ ይህ ልምምድ በህይወት ያልታዩ ገፆች ላይ ያተኮረና ተራ ተርታ የሚባል ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ አፃፃፍ ይትብሀል ውጤት ደግሞ የቅርፅ ፍፁምነትን፣ የጭብጥ አለመዛነፍን እንዲሁም የሰውን የህይወት እና የህሊና ስርቻ እንዲሁም የባህሪ ውስጠት የሚገልፅ ይሆናል።) መጽሀፉ ላይ ያገኘሁት ትልቁ ነገር ግጥም መሰል የአጭር ልቦለድ አፃፃፍ ይትብሀልን ነው። በመጽሀፉ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ትረካዎች እንደ ግጥም በአንድ ቁጭታ የሚያልቁ፣ እንደ ግጥም ምጥንነት የሚታይባቸው፣ እንደ ግጥም የማይሰለቹ ናቸው። There is a close connection between the short story and the poem as there is both a unique union of idea and structure. የሚለውን የአንዳንድ ምሁራን አተያይ ያረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለነገሩ በመጽሀፉም ውስጥ ግጥምን ከአጭር ትረካ ጋር አሰናስሎ የማቅረብ ቅርጽ አስተውያለሁ፡፡
“የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ ተስፋዬ ገብረአብ እንደተጠቀመበት ያለ ማለት ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ይህ አይነቱ የአፃፃፍ ቅርፅ ከሁለቱም የአፃፃፍ ዘውጎች የሚገኘውን ኪነታዊ እርካታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ልክ ሙዚቃዊ ድራማ በነጠላው ከሚቀርብ ድራማ በበለጠ የመግለጽ እና ኪነታዊ ለዛው ከፍ እንደሚል ሁሉ፡፡ ለዚህ አባባል ዋቢ ካስፈለገ በመጽሀፉ ውስጥ “ሴትን ተከትዬ…” የሚለው ትርክት ማሳያ ይሆናል፡፡ “ሴትን ተከትዬ …” የሁላችንንም የልጅነት ህይወት የሚተርክ፣ አንድ ወጣት በሴት ልጅ ፍቅር ልቡ በተሞላበት ወቅት ሊደርስ የሚችልበትን ከፍ ያለ ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዛ ሁሉ በላይ ፀሀፊው የተከተለው የአፃፃፍ መንገድ፣ የአገላለጽ ውበት፣ የአቀራረብ ቅርፅ … ለኔ የተለየ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በአማርኛ የአጫጭር ትረካዎች ውስጥ ብርቅ የሆነብን የታሪክ ድርቀት፣ የቋንቋ ስብራት … “በአራጣ የተያዘ ጭን” ውስጥ ታክሞ እናገኘዋለን። አንድ ወጣት ጸሀፊ “የአማርኛ ትረካዎቻችን በጣም ስለሚጎተቱ ታሪካቸው እንዲፈጥንልኝ እያነበብኩ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ እገባለሁ፤ ፍጥነት ባገኝ ብዬ” ብሎ ነበር፡፡ በዚህ መጽሀፍ ውስጥ የትረካው ፍጥነት እጅግ ከመሰጡኝ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። ፍጥነቱ ግን የመዋከብ ሳይሆን የመዝናናት ስሜት ይፈጥራል፡፡ እንደ ድክመት የማነሳው ከመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት የመጽሀፉ ሽፋን እጅግ አወዛጋቢ ሆኖብኛል፡፡ ለምን ዓላማ እንደዚያ ማድረግ እንዳስፈለገ እራሱ አልገባኝም፡፡
የአንድ ሴትን ገላ በማየቱ ብቻ መጽሐፉን የሚገዛ “ጅል” አንባቢስ ይኖር ይሆን? እንጃ ለኔ ግን አይመስለኝም! ከዛ ውጪ በመጽሀፉ ውስጥ የሚታየው የፊደላት ግድፈት የአርትዖት ሥራውን የይድረስ ይድረስ ያስመስለዋል። ቀጣይ ህትመቶች ላይ እነዚህ ነገሮች ቢታዩ፡፡ በማጠቃለያነት፡- A short is a piece of prose fiction which can be read at a single sitting. ታዋቂው አሜሪካዊ ደራሲ ኤድጋር አላን ፖ የተናገረው ነው፡፡ ለኔ ግጥም እና አጭር ልቦለድን ማጣጣም ከሌሎች የስነፅሁፍ ቅርፆች ይበልጡብኛል። በአንድ ቁጭታ የምጨርሰው ነገር ስለምፈልግ ይሆናል። እንጃ ብቻ … በአሁኑ ጊዜ እንደአሸን የፈሉ በሚያስብል ደረጃ የግጥም መፃህፍት በቀናት ልዩነት በሚወጡበት ከተማችን፤ የግጥምን ያህል ባይሆንም የተሻለ የረጅም ልብወለድ ስራ እየተበረከተ ባለበት ወቅት፤ የአጫጭር ልቦለድ እና ትረካዎች መጽሀፍት ከገበያ መውጣት የሚያነጋግር ነው፡፡ ሀሳብ ያለው አንድ ሁለት ቢል ጥሩ ነው፡፡ … በተረፈ የጀመሩትን ስናበረታታ የሚሞክሩት ይጀምራሉና ነውና ዮፍታሔ ካሳ ባለህበት በርታልን!!! በአንድ መጽሀፍ ብዕርህን አስትቀል (ከመፅሀፉ ባገኘሁት አባባል) እሰናበታለሁ!

addis admas

No comments:

Post a Comment