Friday, December 20, 2013

ባዶ ሳጥን። ከሥርጉተ ሥላሴ



ኢትዮጵያዊነት ለሄሮድስ መለስ በሽታቸው ነበረ። ደፍረን እንናገረው …..
ቀልዴን እንዳይመስላችሁ የእውነቴን ነው። ተረብ እንዳይመስላችሁ ነው የምር። ከልቤ ሙዳይ ያለችውን ሚስጢር ዘክዘክ አድርጌ ላጋራችሁ እንሆ ዛሬ ወደድኩ። የታደለቸው ኩኑ በ15.12.2013 የነገ የሰላም መዲና ሆነች። የአፓርታይድን ግብዕት ለመፈጸም ፍሬ አፍርታ ዘር አንዘርዝራ ጎታዋን በእኩልነት ሞላልታለችና እንደ ጎለጎታ ዎህ ብላ በልበ -ሙሉሉነት ሰከነች። እንሆ … ኩኑ ሰላማዊ ቅዱሳዊ እረፍት ለልጇና ለወዳጇ በክብር ሸለመች። ይጋባታል! ይህ የዓለም ፊኖሚናና አጀንዳ የሆነ የበኽረ አስራታት እናት ናትና ዬምርት ጎታዋ ተትረፈረፈ – በዕውቅና። አደናቆትም በአርቱ ማዕዘናት ተቸራት። ኩኑዬ ልበላት ትቆላመጥ አይደል? ቢያስፈልግም ዬወርቅ ቀለበት አስርቼ ላክ ነው የማደርግላት። የሰላም አባት የእረፍት ቦታ ለትውልዱ፤ የነገም የአፍሪካ ትውፊት። ማለት ቅርስና ውርስ የቅብብል አድባር በመሆን አፈሯ ከበረ – ተባረከ – ተመረቀ። የነፃነት ራህብተኞች ሁሉ ስብከቱን፤ ማህሌቱንና ቅኔውን ከቦታዋ በመሄድ ያጣጥማሉ … ከዛሬ ጀምሮ። ለማግስት ወደ ምስራቃዊዋ የኬፕ ገጠራማ ወደ ኩኑዬ ሚሊዮኖች ይተማሉ ….. ዕምነት – ፅናት – ቅንነት – ይበቃኛል – ቤዛነት – ፍቅር  የሰበለባት ደግ ሰፈር። ማህደረ – ዕሴት! ትልቅ የተግባር ሙዚዬም ይገነባባታል። ዩኒስኮም ይሄኔ አጭቶት ይሆናል። ጽድቅ።
መስታውቷ ኩኑ ተልዕኳውን በተግባር ትማ፤ ለትውልድ አደራን አቅልማ አስማምታ ዳረች። ትንሿ የደቡብ እፍሪካዊቷ መንደር ልክ እንደ ጎለጎታ ፍቅርን በአግልግሏ በአደራ አመሰጥራ ታሪክን በዕንቁ አንቆጥቁጣ አስቀመጠች። የታደለች! መርቋታ! የምን ዝም እዬበሉ እዬጠጡ። ኩኑ – ኩሩ ምህረትን ፈትላ ነገን በተዋበ ጃኖ አለበሰች። ሰላምን ጠርታ ቅንነትን ለድል አቀለመች። መታባበርን ጋብዛ ዓለምን በአንድ ቀለበት በኪዳን አዋውላ ጠመቀች። ፍላጋ አስምራ ለፍትኃት ናፍቆትን ታጠቀች። አማረባት!  አስተሳሰረች …. ኩኑ አስናች – አስቀችም። አንድ ቀን ሄጄ አያታለሁ። እኔም የድርሻዬን ሁለቱን መስኮቶቼ ከፋፍቼ እንዲተነፍሱ አደርጋለሁ። የነፃነት እምነቴንም ቆጣጥሬ ስቀበር አብሮኝ እንዲሆን እናዘዛለሁ …. ታደልኩ።
በመጤ እንደራሴ ሲባክኑ፤ ማንነታቸው አምልጧቸው እንደ ግዑዝ ሞትን ሳያስቡ ያለፉት ሄሮድስ መለስ በመላጣና በተጠ ገጠመኝ ሲወዛወዙ፤  ከተኮፈሱበት ወረድ ብለው በዓለም አደባባይ „ጊዜ ገቢረ ለእግዚአብሄር“ ሆነና በባተሌ ትንታግ፤ የዕንባም ሰማያዊ መልክተኛ፤ መክሊተኛም ግራማቸው ሸሽቶ በቅፅበት ከሰሉ። በጉልበታሙ ዬነፃነት ስንኛዊ ድምፅ ብቻ በርግገው ክብራቸው ለአፍታ ተኖ ተገፈፈ። ጥቂትም ሳይቆዩ ከል ዕንባ የተላኩ የመላእከ ሞት ወታደሮች መንፈሳቸውን በክርኒ ሰልቀው ለህልፈት ዳረጓቸውና ሥጋቸውም ሆነ መንፈሳቸው አፈር ሆነ። እሳቸውን አፋችነን ሞልተን ሞቱ ማለት እንችላለን። አፍር ሆኑ – በሐምሌ 7.2012። በሽታቸው ቀኑ የተሰበረበት፤ አሟሟታቸው ቀኑ የተጣፈበት፤ ቀብራቸው ደግሞ እሬሳ የሌለው ባዶ ሳጥን።  እንዲህ ዓይነት ታሪክ በዬትኛው ሀገር በዬትኛው መሪ ደርሶ ያውቃል?!  ይህ ብቻ በራሱ ቆሞ የሚመሰክረው አንድ የነጠረ ሃቅ አለው። ለኃጥ የወረደ ለፃድቅ ሆኖ ተወዳጁ የጋናው መሪም ወጨፎ ደረሳቸው። ቀን ጠበቃ ነው። ቀን ጥግ ነው። ቀን ለቀን ሰጥቶ ጥቃትን ያወጣል። የበቀል አምላክም እርግማኑን ካለይቅርታ ልኮ ዕንባን ይታደጋል። …. ሊቀ – ሊቃውንቱ አልፃፉትም እንጂ ታምሩስ ታምር ነበር። ለዓለም ህዝበ -ክርስትያን በብራናቸው ከተብው ማወጅ ነበረባቸው። እኛ የትናንትናውን ብቻ እናዘክራለን፤ የትናንት አምላክ ዛሬም አለ፣ የዛሬም አምላክ ነገም ይኖራል፣ በዘመናችን በዓይናችን ያዬነው ገድል ነበር …. እንደ ታምረ ማርያም … እንደ ገድለ ጊዮርጊስ ….

አወና! እኔ እላለሁ በቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ተቀበረ የተባለው የሄሮድስ መለስ አስከሬን ፈጽሞ የለበትም ባዶ ሳጥን ነው እላለሁ። ወያኔ ማለት እኮ ጉድጓድ ነው። መንፈሱና ሚስጢሩ የከተሙት ከሸሩ መቃብር፤ ከተንኮሉ ጎጆ ውስጥ ከዛ ነው። እንደምታውቁት ሄሮድስ መለስ ሀገር አልነበራቸውም። ብሄራዊ መዝሙርም አልነበራቸውም፤ ብሄራዊ ሰንደቅዓላማም አልነበራቸውም፤ የእኔ የሚሉት የነጠረ ማንነት አልነበራቸውም፤ እሳቸው የእኛ – እኛም የእሳቸው አልነበርነም። ስለሆነም በድናቸው እንኳን መሬቷን እንዳይነካ ጎሳን የከዘነው መንፈሳቸው አይፈቅድላቸውም።  አምላካችንም ይህን አያደርገውም። ገዳዮዋን እንዴት … ተብሎ ነው እቴ … ምን በወጣት ጦቢት ተሸከሚ ተብላ የሚበዬንባት? ስለሆነም የመለስ በድን ቅድስተ ሥላሴ ላይ የለም ባይ ነኝ። ዬት ገባ? የቆዬ ሰው ይዬው …

በታመቀው ጥላቻ ከርፍቶ ለኑዛዜ ሳይበቁ መቅረታቸው ሆነ መታመማቸው ላይበቃ በመሞታቸው ፍንክች ሳንል ሳይሞቀን ወይም ደግሞ ሳይቀዘቅዘን ያሳለፍን ሚሊዮኖች ነበርን። የዓለም ሚዲያም ሆነ ህዝቡም እንዲሁ። የተከበሩ ማንዴላም የሀዘን መግለጫ የላኩ አይመስለኝም። የተከደነ ሚስጢር ይላችኋል ይህ ነው። ሄሮድስ መለስ ጠላት ጣሊያን ቢገዛ ሊያደርስ ከሚችለው በላይ ኢትዮጵያን በመከራ የጠበሱ፤ ኢትዮጵያዊነትን በጋለ ብረት ያቃጠሉ፤ ማንነትን አጋደመው ያረዱ፤ ዜግነታቻን ያለርህራሄ በቋሳ የቀቀሉ፤ ታሪክን አንጠልጥለው የሰቀሉ የበቀል አጋፋሪ ነበሩና ….  የተጠቀጠቀው የአርበኞቻችን አፅምም ይቅር አይልም – እኛም።

ሄሮድስ መለስ እንደ ጠላት የሚያዮትን ታሪካዊት ቀደምት ሀገር ኢትዮጵያን በድፍረትና በልበ ሙሉነት አንድም ቀን ኢትዮጵያ ሀገሬ፤ መኩሪያና መመኪያ፤ የምወዳችሁና የማከብራችሁ ህዝቦቼ ሳይሉ ሰንደቅዓላማችን እንደተጸዬፉት፤ ኢትዮጵያዊነትን ፊት እንደነሱት፤ ዜግነታቸው እንደ ቀፈፋቸው አለፉ። የነጠረው ውስጣችንም ቃር …  ቃር እንዳላቸው። ግን ከእናት ሀገር ጥሪት፣ ቅርስና ውርስ ሞጥጠው ከድቀት ተነስተው ለእርሳቸው፤ ለቤተሰባቸውና ለጋሼ ጃግሬዎቻቸው በምልዕት ዘርፈው ሳይበሉት ለአንድ ሰኔል፣ ለጥቂት ቹቻና ለስንዝር ገመድ ዲታነት ሳይወዱ ተገደው አደገደጉ …. ተመስገን!

ሄሮድስ መለሰን አወቂ ነበሩ የሚሉ የነፃነት ቤተኛ ጋዜጠኛዎችን ሳደምጥ እኔ ይገርመኛል። የእውቀት መለኪያ የክብር መሰረት ብሄራዊ መግለጫ ትራስ ሲኖረው ነው። እሳቸው በዚህ ህይወት አልኖሩበትም። ቅርፊትን ተማፅነው ልጥን ተማማነው በመንደር ትርምስ ሲቀብጡ ሲለጠጡ ተበጠሱ እውቀት ሆነ ለእኔ የህዝብ መሪነት ብቃት መለኪያው  ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር ለመቀበል የመወሰን አቅም። የህዝብን አንጡራ የመንፈስ ኃብት በቅንነት ሸምቶ ለህዝብ ጠቀም ተግባር ማዋል። ዜግነቱን ግርማ ሞገሱ በማደረግ ከራሱ ባላይ ከፈጣሪው በታች አድርጎ መቀበል። ብሄራዊ ስሜቱ ወላፈኑ ከሩቅ ጠረኑ የሚጠራ ሲሆን፤ ወስጡን በውስጥ አጣጥሞ እኔነቱን የዋጠ። በራሱ የሚኮራ። ቅልውጥ የማያምረው እራሱን ለባእድ መንፈስ ጥገኛ ያለደረገ። ክህዝብ ቅምጥ ሃብት ትውፊትና ታሪክ ለመማር የፈቀደና የወሰነአንጡራ ጥሪቷና ሚስጢሯ የማያሰፍረው፤ ተፈሪነቷ አንገቱን የማያስደፈው። የማያነበብ ግን የሚነበብ። እውነት ለማናገር ኢትዮጵያ እኮ ባለቤት እረኛ የሌላት ሀገር እኮ ናት። እውቀት የሚባለውም ነገር ለዚህ የኃላፊነትን ብቃት በሰገደ መንፈስ ማስተናገድ የሚችል የላቀ ህሊና ይመስለኛል። ከዚህ አንፃር አቶ መለስ ነበራቸው ለሚባለው ዕውቀት እኔ እንደ ልዝ እንጨት ወይንም ማገዶ ነው የማዬው፤ ማፍረስ – መናድ ይህ እውቀት …?! የተተረተረ ውስጥ የነበራቸው የጎሳ መሪ አዋቂ ሲባሉ ያማል። እባካችሁ እንተዛዘን – የሀገሬ ጋዜጠኞች

ቀድሞ ነገር ዜጋ ያልሆነ ያልተቀበለውም፤ ዜግነቱን የናቃ የተሳለቀ … ያዋረደ እኮ ነው ኢትዮጵያዊነትን ሲመራ የነበረው። ኢትዮጵያዊነት ለሄሮድስ መለስ በሽታቸው ነበር – ንዳድ ወይንም ወባ። የሚያንደፈድፍ የሚያንዘፈዝፍ። ደፍረን እንናገረው። ውስጣቸው ከዚህ ቅዱስ መንፈስ በጣሙን የራቀ ጎሳ ላይ የጎደበ በድን። ሌላው ውስጤ ሲስቅበትም ሲያዝንበትም የነበረው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ ከመንደር ጉርኖ ያለወጣ ስንኩል መንፈስ አህጉራዊ የሆነ ውክልና ሲሰጠው ነበር። ይህን ሳሳላ ውስጤ በግራሞት ተቆናጦ ይህን ልብጥ የመቋቋም አቅማችን ሳስቶ ያን ያህል ጊዜ እናታችን በመጤ እንደራሴ፤ በሚባዝን ባዕድ መንፈስ ተረግጣ መመራቷ የመንፈሴን ሰሌዳ እዬቆሰቆሰ ያቆሳስለው ነበር። ከዚህ አንፃር ነው እኔ ለጋዜጠኛ አበበ ገላው የላቅ ክብርና ዘመን የማይሽረው ልዩ ፍቅር ያለኝ። ጥቃቴን ስላወጣ። አቤ ተጋድሎውን በድል ቋጭቷል። ቀሪው የእኛ ጣጣ ነበር ተግባርን ቀልበን ማታ እንዲያበቃ ማደረግ ….

ከዚህ በተጨማሪም መንደር ላይ ያለ ፍልስፍና ለዘመኑ ደረጃውን ያልጠበቀ ወርደ ጠባብ ቅንጥብጣቢ የዘበጠ ግንዛቤ ነው። እውነት ቁመህ ተናገር ቢባል በ23 ዓመት ውስጥ አዋቂ መሪ ኢትዮጵያ እንዳልነበራት አሳምሮ በገለጸ። ስብከቱንም የምንምነት ናዳ በለቀቀበት። እኔ አይገባኝማ የሄሮድስ  መለስ የአዋቂነት እጀ ጠባብ። ስለዚህ ለእኔ ሄሮድስ መለስ ውስጥ ያለው የዕውቀት እንጥፍጣፊ በራሱ ጊዜ ተኖ ካለታሪክ ያስቀራቸው የተላጠ ነገር ነው – አሰር። ይልቅ ትውልድንና ታሪክን በመሻርና በመደምሰስ፤ እንዲሁም በማጥፋት ብቸኛው መሪ የነበሩት ሄሮድስ መለስ በቋሳ ተሞሽረው፤ በትዕቢት ተነፍተው፤ በማንአለብኝነት ተራራ ላይ ቁጢጥ እንደ አሉ ለሁሉ በእኩልነት ድልድል ወደ ሚሆንበት የንበት ጉዞ እንደ ተሉ መሄዳቸው የእጃቸውና ድርሻቸው ይመስለኛል። ጨዋን ህዝብን በማዋረድና በመናቅ፤ ህግ የሆነን ምልዕት በማንጓጠጥና በማጣጣል የሚታወቁት ሄሮድስ መለስ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ትናትን ገልበው፤ ዛሬን በጎጥ ዲዲቲ በመጋለብ ሀገርና ትውልድን አፈርሰው በድንገት ፈረሱ። የፈለሱ።

መራራው የሄሮድስ ዘመን ስጋትንና ሰቀቀን በባዕት በገፍ አምርቶ፤ ወርቅና ብር ተለይቶበት፤ የክትና የዘወትር ተበጅቶበት፤ የልጅ እና የእንጀራ ልጅነት ልዩነት ሰግሮበት፤ በማይገፋ ጥቋቁር የቀን ሌሊቶች፤ አዘውትረው ደም ባነቡ የሌሊት ድቅድቆች ወደ 21 ዓመት አካባቢ የአፍሪካን ቀንድ ፍርሰትን ዓውጆ፤ ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እናት ሀገርን እንዳወጣ ቸብችቦ፤ የአባቶቻችንና የእናቶቻችነን የአርበኝነት አብነታዊ ውሎ ደመ ከልብ በማደረግ በአደራ ላይ ጦር የመዘዘ፤ ጥቃትን ያወጀ እኩይ አስተዳደር ነበር …. የጉዲት መሳ  …

ዘመኑ ለሚሊዮኖች የወስጥ ሰላም አመክኖ፤ በሀገሩ ዜጋ ባይታዋር ሆኖ፤ ተገፍትሮ በፍርኃት ተሰቅዞ፤ በልዩነት ተወግሮ፤ በጥርጣሬ ተቃብቶ፤ አሳሩን የባላበት የራህብና የፍዳ ነበር። በመለስ የተመለሰ ምንም ቅርስና ጥሪት የለንም። ይልቁንም ዕንባ በማምረትና በማከፋፈል ብቸኛው የህማማትና የምድራዊ የሲኦል ጊዜ ነበር። ዳር ድንበራችንም ለባዕድ በችሮታ የታጨበት … ጭጋጋማ … ጢሳማ ….

ስለሆነም ባዶ ሳጥኑ የተቀበረበት የቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል በራሱ ፍትኃት፤ ጥምቀተ – ትንሳኤ ያስፈልገዋል ባይ ነኝ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ በድፍረት። ጸበል መረት አለበት። በስሙ የተሰዬመው ባዶ ሳጥን፤ ፀላዬ ሰናይ የከተመበት ነውና። ባዶ ሳጥኑ ያረፈበት ቦታ እንኳንስ ሺዎች ሚሊዮኖች እንደ ደቡብ አፍሪካዊት የምህረት አባት፤ የይበቃኛል ልዑል ኔልሰን ያረፋባት ኩኑዬ ለዝክረ ነፃነት የሚተሙበት ሳይሆን ይልቁንም ነገ የሚወቀስበትና የሚነቀስበት ይሆናል። በዚህ ሥርዓት በተባባሪነትና በመሪነት የተሳተፉ ሁሉ አንገታቸውን የሚደፉበት ጠቀራማ። ከሀገር በላይ ምን ፍቅር – ምን ዕምነት – ምን ጌጥ – ምን መኖር – ምን ትምክህት – ምን ፍላጎት – ምን ህልም ምን ትዳር – አለና!? ማረራችን ከስሎ መንፈሳችን ወስጥ አመድ ሆኗል። ቁስለታችን ምግለቱ ውስጣችነን መድረሻ አልባ አድርጎታል። ወስጣችን ማረተ – በለዘ። የዘመኑ ታዳሚ ነንና …. አንሸሸው ነገር …. ተ – ቃ – ጠ – ል – ን!

ዘመነ ሄሮድስ መለስ አይዋ አብሮነት አዘውትሮ ደመር* (በቀጠሮ የሚካሄድ የወል የለቅሶ ቀን) የዋለበት ነበር፤ ሌላው ቀርቶ መርዙ በአንድ ቤተሰብ በእናትና በልጅ፤ በእህትና ወንድም፤ መሃከል ለነበረው እትብታዊ ፍቅር እንኳን ያላዘነ ፈጽሞም ያልራራ የዲያቢሎስ ዘመን ነበር። የፍቅር ተቋማት ተንደው፣ የልዩነት አረም የበቀለበት ዘመነ – ክህደት። ዘመነ – ፍልሰት። ዘመነ – ጥፋት። ፍደሰት። እኛነታችነን በጅራፍ የተቀጣበት ዘመን። የወዬበ ዘመን ነበር የሳጥናኤል መለስ ዘመን። ዛሬም አለቀቀም … ለነገም መለስ ብዙ የጥፋት ሴራዎችን ኮልኩለው አፍልተውና ዘርተው ነው ያለፉት …. አሜኬላ። መከራችን ማለቂያ መክተቻም የለውም።

ትውልዱ የችግራችን ሥሩን በመመርምር ጥናቱን በራሱ ላይ በውስጥነት ሰርቶ ቅንነትን ቢመገብ፤ ተግባርና ኃላፊነታችን ለመወጣት ቢያንስ የማሰብ አቅም ይኖረናል። እያንዳንዱ ዜጋ ሌላ ቦታ ሄዶ አይደለም የጥናት ተግባሩን መከወን ያለበት ከራሱ ይጀምርው። ውጭ ያለነው በልተን አድረን ሊሆን ይችላል። ግን የብዙ ነገሮች ተጠቂ ሆነናል። ቤታቻን ተቀምተናል። እናታችን ተዘቅዝቃ ከእነ-ተስፋዋ ተንጠልጥላላች። በትን ታግታለች። ወገኖቻችን በነፃነት ራህብና በእህል ውኃ እራብ እስኪበቃቸው እዬተወቁ ነው። ዛሬ የጠራው የትናንቱ ባህላችን የለም። አዲስ ቅይጥ ባህል እንጂ።  ግለኝነቱ ብቻ አይደለም መሬታችን እንደ እንሳሳ ለሚኖሩ መጤዎች ታድሏል። መኖር ጋብቻን ያመጣል። ጋብቻው ትውልድን ይፈጥራል። ነገ የእኛ አይደለም። ነገ የእኛ አንጡራ ጠረኑኑ እንዲፈልስ ሄሮድስ መለስ ረቂቅ ደባ ፈጽመዋል። የኛን ወዝ ተቀምተናል። ያ … መደበኛ የውስጥ ጠረን ተሰርቀናል። መከራው ያመረቀዘ ነው። ፍዳው የመገለ ነው። ስቃዩ የሚያርመጠምጥ ነው። ተስፋውም – የተሰቀዘ።

መሬቱ ለባዕድ በመሰጠቱ በኬሚካል እዬተቃጠለ ነው። አዬሩም የብክለት ታዳሚ ሆኗል። ስለሆነም ነገ ገና ከመምጣቱ አሯል። ሄሮድስ ያሰለጠናቸው በእግር ተተኪዎች በሀገር ውስጥና በውጭ መጠነ ሰፊ የመማር ልዩ ዕድል ስለነበራቸው በአረም የበቀለው የሄሮድስን የበቀል ዶክተሪን የጎጥ ፍልስፍና ለማግሥት ነቀረሳን ተክሏል። የአርበኝነት ታሪክ የነፃነት ታሪክ „የጀብደኝነት““ የሚሉ ማፈሪያ ተባዮችን አፍርቷል። ጥቁር አንበሳ እኮ የመጀመሪያው የተደራጀ የሽምቅ ውጊያ ሰንደቅ ነው። ዓለምን በድርጊት የመራም ያስተማረም ታላቁ ኢትዮጵያዊነት ነው። እንኳንስ ሌላው … ቅኝ ለማደረግ የተመኙት እንኳን የማይሉትን ነው የሄሮድስ አረማዊ ችግኞች ሲሉ የሚደመጡት።

ከ15 ቀን በፊት ቃሌ ሩም ነበርኩኝ። እንግሊዝ ሀገር የሚኖር “እምነት ወይንም ነጋድራስ ባይከዳኝ“ በሚባል የፓል ሥም የሚጠራ ወጣት በድፍረት ዓለምን ያስደመመውን ግሩሙን የተጋድሎ የነፃነት ታሪካችን ትቢያ በማልበስ ሎቱ ስብኃት ስለ ቃሉ „የጀብደኝነት“ ሲል በቦጅቧጇ የድምጽ ቃና ነበር እንደ መሪው እንደ ሄሮድስ በመታበይ የገለጸው። ስሰማ ተንዘፈዘፍኩ። በርቀትም የቤት ሥራችን ምን ያህል ውስብሰብ እንደ ሆነ ተልምኩት … ይህ ሰው ሀገራችነን አንድ ጊዜ ከዩጎዝላብያ፤ ሌላ ጊዜ ከአልባንያ ጋር ወስዶ እዬቀረቀር መርዙን ሲረጫጭ „ልጅ ሰለሞን“ በሚል የፓል ስም የሚጠራ ጥሩ ተናጋሪና ስለ አውሮፓ ሀገሮችም ጠንቅቆ ያነበበ የቤቱ አድሚን የተገባውን ቅጣት አስታጠቀው። መመከተም አልቻለም ነበር። በምን ስሌት ነው የሰው ልጅ መገኛ፤ የአፍሪካ አርማ ከነአልባንያ ከነኮዘቦ … ዬምታዳበለው … ዝብርቅ ባለ መንፈስ ሲላተም የሚመክት ወንድም በመኖሩ መርዙን ከጅራቱ ነቅሎ ለራሱ አወራረደለት። በዚህ መልክ ስንት ነፍስ ከማእዱ ወጥቶ ይሆን? „ትምህርት ዜግነት“ የወቅቱ የትኩረት አቅጣጫችን ሊሆን ይገባልም እላለሁ … ለነገም የሚመረቁበት ሙያ እንዲሆን ምኞቴ ነው። ያልተበከለ ማሳ፤ አረም ያልነከው መሬት የለነም …

በክርክር ወይንም በዲቤት ወቅት ስድብ ሳይሆን ፋይዳው፤ ነጥቦችን እንዲህ በፋክት አፋጦ፤ በእውነት መክቶ ሃሰትን ጠርቦ፤ በወጥ አምክንዮ ትራስነት በብልጫ አቅም መርዛዊ የሄሮድስን ሰደድ መመከት ያስፈልጋል። ለኢትዮጵያዊነት ሌላ የማማሳከሪያ ሰነድ ወይንም ሀገር፤ ሌላ የሪፈረንስ ሊንክ አያስፈልገንም። ባህረ መዝገቡ ማውጫ ሰነዱ እሱ እራሱን በራሱ ተርጉሞ ያመሳጠረ ነውና – ኢትዮጵያዊነት። ለነገሩ ማማሳጠር የተሰጣቸው ብቻ ልዩ መክሊት ነው። ያልተሰጠውን ከአረም የበቀለ ችግኝ በምን አቅሙ …. መንጠራራቱ በራሱ ይገርማል …

ወገኖቼ የመለስ ዶክተሪን መርዝ ዕዳው ከትውልዱ አቅም በላይ በመሆኑ በእጥፍ፤ በድርብ በፍቅርና በስምምነት ተግተን ብንሰለፍ እንኳን ያችን የትናንቷን ንፁህ ሀገር፤ ቅዱስ መንፈሷን ከእነ-ልቧ ለማግኘት ዳገቱ – ዳገት ነው። – ተራረውም የጨው ውሃን ያዘለ። እኛን የሚጠብቀን ድርሻ በእናቱ ማህፀን ዓይን ያልተፈጠረለትን፤ የዓይን ቦታውም ድምስስ የሆነውን ልጅ ሲወለድ ዓይናማ ማደረግ ነው።

የእኔ ጸጋዎች፤ የሀገሬ ልጆች …  በእናቱ ማህጸን የዓይን ቦታ ያልነበረውን በምን ታምርና በምን ረቂቅ ትንግርት ነው ዓይናማ ማደረግ የምንችለው?! በምን ጉልበትና የስበት ኃይል ነው ይህን ተልዕኮ ተውጥተን የተቀበልነውን የአደራ ጸጋ ቅብብሎሹን በመራረቅ ለቀጣዮ የምናስረክበው?! ልብ ብንለው የትውልዱ የፊት ለፊት ተግባር ይህን ያህል ጥልቅ ነው። ስለሆነም ዛሬ አዎን ዛሬ አደራ በላ ሳንሆን የውስጥ ለውጥ በማምጣት ቅንነትን ፈቃድ እንስጠው። በአውንታዊ ዕይታ መንፈሳችን እናናው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳልና ያለንን ጥቅም ላይ ለመዋል ወታደራችን፤ ዘበኛችን፤ ጠበቃችን፤ አጋፋሪ ሊጋባችን መሪያችንም ቅንነትን እናድርግ በስተቀር ደርቀን እንቀራለን።

ከሄሮድስ የተረከብነው ባዶ ሳጥን ነው። … መንፈሱ የተሰደደ። እኛ ግን ሁሉ አለን። ሁሉንም ለመሆን እንፈቃቀድ … እንደ ዕዬምነታችንም ቃሉን ለድርጊታችን መሪነት እንፍቀድለት። …. መፍትሄው ያለው ከዛ ላይ ነው። …. ለእኔ ከፍቅር ይልቅ ቅንነት ይበልጥብኛል። ቅንነት ጥገት ነው። ጋቱ ሙሉዕ የሆነ። ቅንነት ካለ ምቀኝነት ይሰባራል። ቅንነት ካለ ፍቅር ለመስጠት ንፉግ አይኮንም። ቅንነት ካለ ጥላቻ ይሞታል። ቅንነት ካለ አቅማችን አቅደን ወደ ተግባር በመለወጥ  የአደራችን ባለቤት መሆን እንችላላን። ቅንነት የእስር ቤት ዳኛ ነው። ቅንነት ምህረተኛ በመሆኑም ንዑዳን ተግባራት ካለመሰናክል ገቢራዊ በማድረግ ፍሬዎች እንዳሻቸው ይፈነጥዛሉ …. ነገም ከዛሬ ይጀምራል። ፍሬም ከዘሩ ይበቅላል። የአሉታ ዕይታ ለአውንታ እጁን ይሰጣል ዳኛው ቅንነት ከሆነ …. መጠራጠር ለመተማማን ይሰግዳል … የጎሸው ይጣራል የከረረው ይለዝባል። ፍላጎታችን አንድ ከሆነ ኃብታችን አቅም እንዲኖረው እንፍቀድ ….

አንድ ሰው ብዙ ነው። መንፈሱና አካሉን ንፉግ ሳይሆን ለነፃነት ትግሉ ከለገሰ እንደአሰብነው እንሆናለን። እንደ ተፈጥሯችን እናመራለን። የጋዜጠኛ አበበ ገላው አንድ ስንኝ እኮ ነው ያን ያህል ጉልበት ኖሮት መተንፈሻ ቧንቧችን በመክፈት ጥቃትን አውጥቶ ለሄሮድስ መለስ ቅጣትን ያስታጠቀ። አቤ ችሎት – ጠበቃ – አቃቢ ህግ – ዳኛም ነው። ሚሊዮኖች የተገፉ ህዝቦች በአንድ ላይ ቢነሱ ወያኔ እኮ ምንም ነው። ጠርሙስ። ከባህር የወጣ አሳ። የተግባር ጥግና ከለላ የሌለው … ብን … ትን — ብትን ….. የሚል። ይ ቻ ላ ል ….. እንደ ገና እንረባረብበት እንችላለን።

በተን ብላ በቀረበችው የባዶ ሳጥን የብዕር ጠብታ ካበዛሁባችሁ ይቅርታችሁን እጠይቃለሁ። አቀናሁ። ሸምቱ። እንደገናም አቅኑልኝ። …. እንፈቃቀድ …. እንደማመጥ …. ህመሙ እንዲመረምረን ይለፍ እንስጠው። …. ስቃዩም ሥር ሰዶ መንፈሳችን እንዲንው በቂ የርስት ማሳ ህሊናችን ይሰጠው። …. ቆጥቆጥ ሲያደርገን ቆረጥ፤ ቆረጥ ስናደርግ በቃን እንወልዳለን። …. ጉልበተኛን አንባገነን እየተጋፉ መሄድ ደስ ይላል ~~~ የአሸናፊነትን ዋዜማ ነውና!


ኑሩልኝ እኔ ካለ እናንተ ምንም ነኝና ….. ትቢያ …

ኣራት ዓይናማው መንገዳችን ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው!
እልፍ ነና እልፍነታችነን በተግባር እልፍ እናድርገው!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
sreate1 
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

No comments:

Post a Comment