አቶ ከፍያለው ሃይሉ
፡ የቀድሞ አየር ወለድ አሰልጣኝና የበረራ ደህንነት ባለሙያ አጭር የህይወት ታሪክ
አቶ ከፍያለው ኃይሉ ከአባታቸው ከአቶ ኃይሉ ተሰማ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጉዳይ ዓለሙ ግንቦት 29 ቀን 1942 ዓ.ም. በጎጃም ክፍለ ሀገር በደብረ ማርቆስ ከተማ ተወለዱ፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በደብረ ማርቆስ ከተማ የቀድሞ ስሙ ንጉስ ተክለሀይማኖት እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እያሉ ሀገራቸውን ለማገልገል በነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1959 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የምድር ጦር አየር ወለድ ክፍልን ተቀላቀሉ፡፡ ከዚያም ተገቢውን ወታደራዊ ስልጠና በፍቼ ማሰልጠኛ ጣቢያ ከአጠናቀቁ በኋላ ደብረዘይት በሚገኘው የአየር ወለድ ክፍል የመጀመሪያ የዝላይ ስልጠና ትምህርት አጠናቀው በቀጣይነት የ9ኛው ኮማንዶ ኮርስ ስልጠናቸውን እና ሌሎችንም ወታደራዊ ትምህርቶች በብቃት አጠናቀቁ፡፡ ከዚያም አየር ወለድ ጦር በተሰማራባቸው የስራ መስኮች ሁሉ ፣ አቶ ከፍያለው በብቃት ግዳጃቸውን ተወጥተዋል።
አቶ ከፍያለው በተሰለፉበት የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ባሳዩት ንቁ ተሳትፎና ወታደራዊ ብቃት ከሌሎች ዕውቅ ጓዶቻቸው ጋር ለ3ኛው የአየር ወለድ የፓራ ኮማንዶ አሰልጣኝነት ኮርስ ተመርጠው በአጥጋቢ ውጤት አጠናቀዋል፡፡ በጊዜው አብረዋቸው ከአጠናቀቁት ታዋቂና ብቁ የኮማንዶ አስተማሪዎች ውስጥ እብስቱ አያሌው፣ ድንበሩ በኩረ፣ ታዬ ቶላ፣ ተስፉ ተፈራና ፀጋዬ ሳይንቴ ይጠቀሳሉ፡፡ ዛሬ ሁሉም በተለያየ መስክ ተሰልፈው ለሀገራቸው መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
አቶ ከፍያለው በደብረዘይት ከተማ የፓራ ኮማንዶ አስተማሪ በመሆን ብዙ የሀገር ገንቢ ወጣት የሰራዊት አባላትን በማፍራትና የሌሎችን ነፃ አውጭ ሰራዊት አባላት በማሰልጠን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ቀጥሎም በዕድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ተሰማርተው በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ወገናቸውን አገልግለዋል፡፡
ከ1970 – 1982 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ደህንነት ስራና በአሰልጣኝነት ተመድበው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጋቸው በላይ በተለያዩ የውጭ እና ወዳጅ አገሮች ጥያቄ የበረራ ደህንነት ትምህርት ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ከሰጡባቸው አገሮችም ውስጥ የመንና ጋና ይገኙበታል፡፡
በታሪካዊው የሕዝብ ለሕዝብ የኪነት ቡድን አባል በመሆንም አብረው ተጉዘዋል፡፡ በአጠቃላይ ለ24 ዓመታት ባገለገሉበት ከላይ በተጠቀሱት አርአያነት ባለው ተግባሮቻቸው የተለያዩ ሽልማቶችንና የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል፡፡
አቶ ከፍያለው ኃይሉ ከወ/ሮ የኔነሽ ጥላሁን ጋር ህጋዊ ጋብቻ ፈጽመው 37 ዓመታት በፍቅርና በመተሳሰብ ኖረው 3 ልጆችን አፍርተው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡ ወደ አሜሪካ በመምጣት ኑሮአቸውን በመጀመሪያ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከዚያም ወደ ካሊፎርኒያ ግዛት በመዛወር በሳንሆዜ ከተማ ኑሮ መስርተው እስከዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ ከሀገሩና ከወገኑ ርቆ በውጭ የሚኖር ወገናቸው በማሰባሰብ፣ በማፅናናትና በመርዳት የሚታወቁ ነበሩ፡፡
አቶ ከፍያለው ኃይሉ ፈርሀ እግዚአብሔር ያደረባቸው ለተቸገሩ ደራሽ ቅንና ሩህሩህ በሁላችንም ዘንድ ሲታወሱ የሚኖሩ ባህሪያቸው በመሆኑ በአበረከቱት ቅን አገልግሎትና በጎ ተግባር ከሀዘናችን እንጽናናለን፡፡
ለባለቤታቸው ለወ/ሮ የኔነሽ ጥላሁን ፣ ለልጆቻቸው፣ ለመላ ቤተሰባቸውና ወዳጅ ዘመድ መጽናናትን እንመኛለን ቸሩ አምላክ ነፍሳቸውን ይማርልን፡፡
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.
No comments:
Post a Comment