Monday, September 16, 2013

በገላን ጉራ ፈለገ ግዮን ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከሰማይ ስለወረደው መስቀል

KeSemay Yeworedew Meskel
ከሰማይ ወረደ ተብሎ በጳጳሳት የተጎበኘው መስቀል ለሕዝብ ይታያል

በአቃቂ ቃሊቲ በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ፣ ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በቀስተ ደመና፣ በመብረቅ እና በነጎድጓድ ታጅቦ ከሰማይ እንደወረደ የተነገረው መስቀል፣ በጳጳሳት የተጎበኘ ሲኾን፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለሕዝብ እይታ እንደሚቀርብ ተገለጸ፡፡
መስቀሉን ከወረደበት ለማንሣት የሞከረ ወጣት ተስፈንጥሮ ከወደቀበት ለአራት ቀን ራሱን እንደሳተ የሚናገሩ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ፣ ከምሽቱ 9፡00 ከፍንዳታ ጋራ አካባቢው በብርሃን ተሞልቶ ስናይ የእሳት ቃጠሎ መስሎን ነበር ብለዋል፡፡ እያንጸባረቀ በኃይለኛ ግለት ያቃጥል ነበር የተባለው መስቀሉ፣ በጳጳሳት እና በማኅበረ ቅዱሳን መሪዎች የተጎበኘ ሲኾን የኢየሱስን ስቅለት የሚያሳይ ወርቃማ ቅርጽ ያለው ነው፡፡
ወደ አቃቂ ከተማ ከሚያስገባው ዋናው የአስፋልት መንገድ በስተግራ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ገላን ጉራ በሚባለው ስፍራ የዛሬ አምስት ዓመት የተቋቋመው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም [የቅድስት] ክርስቶስ ሠምራ ክብረ በዓል እየተከናወነ ሳለ ከሌሊቱ 9፡00 የኾነው ክሥተት ነው የዚህ ሁሉ መነሻ፡፡ ከባድ የፍንዳታ ድምፅ የሰሙና የቀስተ ደመና ቀለማትን የተላበሰ ብርሃን የተመለከቱ ነገሩን ከዝናባማው የአየሩ ኹኔታ ጋራ በማያያዝ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር የሚሉት የደብሩ መጋቢ፣‹‹በነጎድጓድና በኢትዮጵያ ባንዴራ የታጀበ መስቀል ከሰማይ ሲወርድ አይቻለኹ፤›› ብለዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ መስቀሉን ለማየት ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚጎርፉ ምእመናን በርክተዋል፡፡
ባለፈው ኀሙስ ከአቃቂ ከተማ በማለዳ ተነሥተን ከሁለት ሰዓታት የእግር ጉዞ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኑ ስንደርስ፣ ጥቂት ምእመናን በተገኙበት የዕለቱ ቅዳሴ እየተከናወነ ነበር፡፡ ከቆይታ በኋላ ቅጽሩ የመስቀሉን ታሪክ ሰምተው ከአቅጣጫው በሚመጡ ምእመናን ተሞላ፡፡ ‹‹መስቀሉ ከሰማይ ሲወርድ አይቻለኹ›› የሚሉት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፣ ስለ መስቀሉ አወራረድ ገለጻ ማድረግ የጀመሩት ከጸሎተ ቅዳሴው ፍጻሜ በኋላ ነው፡፡
በቅጽሩ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ መስቀሉ ወርዶ ያረፈበትን ስፍራ እያመለከቱ ይናገራሉ፡- ቦታው በቆርቆሮ ታጥሮ ድንኳን ተተክሎበታል፡፡ መስቀሉ ዐርፎበታል ከተባለው ስፍራ ‹‹አፈር›› እየተቆነጠረ የሚቀርብላቸው ምእመናን፣ ‹‹አፈሩን›› እየተመለከቱ የመጋቤ ሐዲስን ገለጻ ያዳምጣሉ፡፡
ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በዓል ነሐሴ ፳፫ ቀን የጸሎት ሥርዐት ከምሽቱ 5፡00 አካባቢ እንደተጀመረ የሚያስታውሱት መጋቤ ሐዲስ፣ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ አካባቢው በቀስተ ደመና ብርሃን ደምቆ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን ለዚህ ልዩ ክሥተት ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር፡፡ ከዝናባማው የአየር ጠባይ ጋራ አዛምደው አቅለለው ነው የተመለከቱት፤›› ብለዋል መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፡፡ የቀስተ ደመናው ብርሃን አንዴ ሲደምቅ፣ አንዴ ሲደበዝዝ መቆየቱን መጋቤ ሐዲስ ጠቅሰው፣ ‹‹ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ነፋስ ለማግኘት በካህናት መውጫ በር በኩል ስወጣ ግን ደብዛዛ የነበረው ብርሃን የበለጠ ደምቆ እንደ ቀን ብርሃን ወገግ ብሎ ታየኝ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሻቅቤ ስመለከት ሰማዩ በነጭ ደመና ተከቦ ተመለከትኩ፡፡ አፍታም አልቆየ፣ በኢትዮጵያ ባንዴራ ቀለማት የተጠቀለለ አንዳች ነገር በዝግታ ከሰማይ እየተገለባበጠ ሲወርድ አየኹ፡፡››
ከቤተ ክርስቲያኑ ቤተ ልሔም አጠገብ ያለውን የአገር አቋራጭ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መሥመር ተሸካሚ ማማ እያመለከቱ፣ ‹‹ከሰማይ እየተጠቀለለ የሚወርደው ነገር ከማማው አካባቢ ሲደርስ ነጎድጎዳማ ድምፅ ማሰማት ጀመረ›› የሚሉት መጋቤ ሐዲስ፣ ‹‹መሬት ላይ ሲያርፍ በከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ አካባቢው የእሳት ንዳድ የመሰለ ብርሃን ሞላው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ቤተ ልሔሙ ተቃጠለ እያልኹ ብጮኽም ድምፄን የሰማ ሰው አልነበረም፤ ለደቂቃዎች ያህል ለሰዎች እንዳይሰማ ኾኖ ታፍኖ ነበር፡፡ ድምፄ መሰማት ሲችል ግን፣ ካህናቱ ጩኸቱን ሰምተው ተደናግጠው ወደ ውጭ ወጡ፤›› ብለዋል፡፡ አንዳች አደጋ ደርሶ እሳት ተቀጣጥሎ ሊኾን ይችላል በሚል ድንጋጤ ሁሉም እሳቱን ለማጥፋት እንደተሯሯጠ ጠቅሰው፣ ነገር ግን ከአካባቢው ብርሃን በቀር የእሳት ቃጠሎ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል፡፡
‹‹አንድ የቤተ ክርስቲያናችን ወጣት አገልጋይ ወደ ደመቀው ብርሃን ተጠግቶ ለማየት ሞከረ፤ አንዳች ነገር ወደላይ አስፈንጥሮ መሬት ላይ ጣለው፤ ምእመናን ተደናገጡ፤ የኤሌክትሪክ መሥመር ተበጥሶ ኮንታክት ፈጥሮ ይኾናል የሚል ጥርጣሬ ነበር ያደረብን›› ሲሉም ተርከዋል፡፡ ‹‹የወደቀው ወጣት ምላሱ ተጎልጉሎ በወደቀበት ራሱን ስቶ ተዘርግቶ ነበር›› የሚሉት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፣ ከወደቀበት በጥንቃቄ አንሥተን ጠበልና ቅብዐ ቅዱስ ብናደርግበትም አልተሻለውም ብለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ካህናቱ እንደምንም ወደ ብርሃኑ ተጠግተው የተመለከቱት፡፡ እናም በብርሃን የታጀበ መስቀል መሬት ላይ ዐርፎ አዩ ብለዋል፡፡
ካህናቱና ምእመናኑ በአግራሞት ሲመለከቱ ቢቆዩም የእሳቱ ወላፈን ይፋጃል ያሉት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፣ በርቀት መጎናጸፊያ ተወርውሮበት እንዲለብስ እንደተደረገ ይገልጻሉ፡፡ የተቋረጠው ሥርዐተ ማሕሌት ከ10፡00 በኋላ የቀጠለ ሲኾን በካህናቱ ትእዛዝ መስቀሉ ወርዶ ካረፈበት ሥፍራ ላይ ማለዳ 12፡30 ድንኳን ተተከለ፤ ብፁዓን አባቶችም በስልክ እንዲያውቁ ተደረገ ብለዋል፡፡ ይኹን እንጂ በማግስቱ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ክብረ በዓል ስለነበር ብዙዎቹ ጳጳሳት ወደ ደብረ ሊባኖስ፣ ቀሪዎቹም ወደ የአድባራቱ ሄደው ስለነበር በዕለቱ መምጣት አልቻሉም ብለዋል፡፡
‹‹ከበላይ አካላት በተነገረን መሠረት ለወረዳው ፖሊስ ካሳወቅን በኋላ የፖሊስ ኃይል አካባቢውን ተቆጣጠረ፤›› የሚሉት መጋቤ ሐዲስ ቅዳሜ ዕለት የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መጥተው መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚያው ዕለት ከሰዓት በኋላ ለመምጣት ቀጠሮ የሰጡ ጳጳሳት ግን ከአንድ ሰዓት በላይ በረዶ የቀላቀለ ዝናም በመጣሉና ጭቃው የማያስገባ በመኾኑ ከመንገድ ተመልሰዋል፡፡ በማግሥቱ እሑድም አክራሪነትን ለመቃወም ሰልፍ የሚካሄድበት ቀን በመኾኑ መምጣት አልቻሉም፡፡
ሰኞ ዕለት፣ ነሐሴ ፳፯ ቀን በርካታ ጳጳሳት በቦታው ተገኝተው፣ መስቀሉ ዐርፎ ከቆየበት ስፍራ ተነሥቶና በበርካታ ምእመናን ታጅቦ ወደ መቅደስ እንዲገባ መደረጉን መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ ተናግረዋል፡፡ በደረሰበት አደጋ ራሱን ስቶ የቆየው አገልጋይ፣ በአራተኛው ቀን መንቃቱንና በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ ወጣቱ ሲጠየቅም፡- ሊያነሣው እጁን ሲሰነዝር ከኋላው አንዳች ሕፃን ልጅ የመሰለ ነገር ጎትቶ መሬት ላይ እንደጣለውና ከዚያ በኋላ የኾነውን እንደማያውቅ መግለጹን መጋቤ ሐዲስ ተናግረዋል፡፡
መስቀሉ ከወደቀበት መሬት ተነሥቶ ሲገባ ከፍተኛ ግለት እንደነበረውና [ያከበሩት] አባት ‹‹እያቃጠለኝ ነው›› እያሉ ሲናገሩ እንደነበር ተገልጧል፡፡ መስቀሉ የሰው ሥራ እንዳይኾን የተጠራጠሩ መኖራቸውን የጠቀሱት መጋቤ ሐዲስ ፍሥሓ፣ ‹‹መስቀሉ ከምን እንደመጣ የሚያውቀው ፈጣሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ እንግዳው የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ፣ መስቀሉ ከሰማይ ሲወርድ እንዳልተመለከቱ ጠቅሰው፣ ‹‹በጳጳሳቱ ካረፈበት ተነሥቶ ወደ መቅደስ ሲገባ ወርቃማ ብርሃን ነበረው›› ብለዋል፡፡ አንዳንድ የአካባቢው ሰዎችም ሌሊቱን ነጎድጓዳማ ድምፅ መስማታቸውንና በማግሥቱም ስለ ክሥተቱ ከቤተ ክርስቲያኑ ካህናት እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ለአካባቢው ጸጥታ በማሰብ መስቀሉ በየዕለቱ ለምእመናን እንዳይታይ ከቤተ ክህነት ትእዛዝ እንደተላለፈ ጠቅሰው፣ መስከረም ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር መስቀሉን ለእይታ ለማወጣት ቀጠሮ መያዙን መጋቤ ሐዲስ አስታውቀዋል፡፡
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 13 ቁጥር 713፤ ቅዳሜ መስከረም ፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)

 https://freedomofspeech4.wordpress.com/2013/09/16/53-3/

No comments:

Post a Comment