Tuesday, September 17, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ በመጪው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ አስታወቀ


semayawi-party

 ኢሳት ዜና :-አዲስ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ምንም እንኳ የአዲስ አበባ መስተዳደር ለሰልፉ  በ12 ሰአታት ውስጥ መልስ የመስጠት ሀላፊነት የነበረበት ቢሆንም ይህን አላዳረገም።  ፓርቲው የሚጠበቅበትን ሁሉ ለሚመለከተዉ አካል የማሳወቅ ግዴታ በአግባቡ ስለተወጣና ለሰልፉም የሚያስፈልጉ ስራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም በታቀደው መሰረት ሰልፉ ይካሄዳል ብሎአል፡፡
በዚህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ የምናነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሲቪክ ማሕበራትና ዜጎች በአጠቃላይ በሰልፉ ላይ በመሳተፍ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ፓርቲ ጥሪውን አቅርቦ ፣ ሰላማዊ ሰልፉን በመቆጣጠርና የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ የሚያውክን ሁኔታ በማስወገድ የሰላማዊ ሰልፈኞች መብቶችን ለመጠበቅ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎች የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ተግባር በአግባቡ እንዲያከናውኑ ጠይቋል።
አንድነት ፓርቲ ለመስከረም 19 የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱና ፈቃድ ማግኘቱ ይታወቃል።

 734 ሚሊዮን 600 ሺ ብር የመዘብሩ የስራ ሃፊዎች አለመቀጣታቸውን መረጃዎች አመለከቱ
ኢሳት ዜና :-አዲስ ከስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሺን የተገኝው መረጃ እንደሚያመለክተው ከተለያዩ የፌደራል መስሪያ ቤቶች 734 ሚሊዮን 6 መቶ ሺ ብር የመዘብሩ የስራ ሃፊዎች በተጣራ መረጃ ክስ ቢመሰረትባቸውም የውሳኔ ቅጣት እንዳልተላለፈባቸው ታውቋል።
ለረጅም ጊዜ በተደረገ ምርመራ ተጣርቶና መስረጃ ተገኝቶባቸው ከ2004 ዓም ጀምሮ ክስ የተመሰረተባቸው የተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የውሳኔ ሀሳብ እንዳልተላለፈባቸው ከመሰሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ላይ  94 ሚሊዮን 300 ሺ ብር  ከትምህርት ተቋማት ግንባታ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ የሙስና ወንጀል ምርመራ ተጠናቆ ክስ ቢመሰረትም በቂ ውሳኔ ሳያገኝ ቀርቷል።
ከአራዳ ክ/ከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ  ህገወጥ የካሳ ክፍያ በመፈጸሙ ሦስት የምርመራ መዝገቦች ተጠናቀው በ2004 ዓ.ም ክስ ቢመሰረትም የቅጣት ውሳኔ አላገኝም።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀራጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የ12 ሚሊዮን ብር እና የ34 ሚሊዮን ብር ህገወጥ ብድርን እንዲፈፀም ያደረጉ አካላት በቂ የሰነድ ማስረጃ እንደተገኘባቸው ቢገለጽም እርምጃ ሳይወሰድ ቀርቱዋል፡፡
በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ከመመሪያና አሰራር ውጪ ለግለሰቦች የስልክ መስመር እንዲዘረጋ በማድረግ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር ስልክ በማስደወል በመስሪያ ቤቱ ላይ 14 ሚሊዮን ብር ጉዳት መድረሱን የተመለከተ  ሁለት ምርመራዎች ተጠናቀው በክስ ሂደት ላይ ሲሆኑ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በሚፈጥሩት ጫና ክሱ እየተጓተተ ነው።
በትግራይ ክልል የሚገኘው በሼባ የብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ለፋብሪካው የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ፍጆታ ቆጣሪ መሳሪያ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ በማድረግ መብራት ሀይል ከሽያጭ ማግኘት ይገባው የነበረውን ገቢ በማስቀረት በአገር ላይ  65 ሚሊዮን 300 ሺ ጉዳት በመድረሱ ምርመራው ተጣርቶ ለወሳኝ አካል ቢተላለፍም ውሳኔ ሳያገኝ ቀርቷል።
በተመሳሳይ በኦሮምያ ክልል በደብረዘይት የሚገኝ የግል የብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ለፋብሪካው የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ፍጆታ ቆጣሪ መሳሪያ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከሽያጭ ማግኘት ይገባው የነበረውን ገቢ በማስቀረት በአገር ላይ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረሱ ምርመራው አጣርቶ የፀረ ሙስና ኮሚሺን ቢልክም የፍትህ መጓተት ታይቶበታል።
በመብራት ሀይል አላግባብ በ 248 ሚሊዮን 900 ሺ ብር የተፈጸመ የ4 ሺ4 መቶ 70 ትራንስፎርመሮች አለም አቀፍ ግዢ በሁለት የምርመራ መዝገቦች የተጣራ ቢሆንም ውሳኔ አልተሰጠበትም።
ንብረቱ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የብረት ማኑፋክቸሪንግ ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ የሆነ ግምቱ  4 ሚሊዮን 7 መቶ ሺ የሆነ የብርና የነሃስ ሜዳልያ ከግምጃ ቤት በመጥፋቱ ተመርምሮ የተረጋገጠ ቢሆንም ውሳኔ አላገኘም።
በተንዳሆ ፕሮጀክት ከግብር ጋር በተያያዘ በመንግስት ላይ     ጉዳት በመድረሱ ምርመራው ተጠናቆ ክስ ተመስርቷል። በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ በሊዝ እንዲስተናገድ የተወሰነለትን የመኖሪያ ቤት ኅ/ሥ/ማ ያለ ሊዝ በማስተናገድ የተሰጠ 30 ሺ 3 መቶ 32 ካ/ሜ ቦታ ምርመራ ተጠናቆ ክስ የተመሰረተ ቢሆንም ውሳኔ አላገኘም።
ለብሄራዊ ባንክ በሽያጭ ከሚቀርብ ወርቅ ጋር በተያያዘ የባንኩ ሰራተኞችና ነጋዴዎች በመመሳጠር 63 ሚሊዮን ብር በመመዝበር አስቀድሞ ተከሰው የነበሩ አሁን ጥፋተኛ ተብለው ጉዳዩ ለቅጣት ውሳኔ ተቀጥሯል።
በቂርቆስ ክ/ከተማ በልማት ተነሺዎች ስም ከመመሪያ ውጪ ግምቱ 13 ሚሊዮን 3 መቶ ሺ የሆነ 2, ሺ 1 መቶ 45 ካ/ሜትር ትርፍ መሬት አላግባብ በተሰጣቸው እና ከካሳ ክፍያም ጋር በተያያዘ  5 ሚሊዮን 2 መቶ ሺ ብር በትርፍ የተከፈላቸው ግለሰቦች ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ሀዋሳ ቅርንጫፍ በእምነት ማጉደል ወንጀል ግምቱ ብር 1 ሚሊዮን 7 መቶ ሺ የሆነ መድሃኒት ተመዝብሮ ለግል ጥቅም መዋሉ እና በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በተደረገ የ100 ሚሊዮን የእህል ግዢ ጨረታ ግለሰቦች ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ጨረታውን ያሸነፉ መሆኑ በተደረገው ምርመራ በመረጋገጡ ጨረታው እንዲሰረዝና በግለሰቦቹ ላይ ክስ እንዲመሰረት የተደረገባቸው በጥቅሉ ከህዝብ በግብር የተሰበሰበ በርካታ ገንዘብ በአንድም በሌላ መልኩ በከፍተኛ አመራሮች ተጽእኖ በ2004 እና በ2005 ዓ.ም ተጣርቶ ለፍርድ ሰጭው አካል ቢተላለፍም ውሳኔ ሳይሰጥባቸው ቀርተዋል፡፡
ከ 7 መቶ ሚሊዮን  ብር በላይ የመዘበሩ የስራ ሃፊዎች አልተቀጡም ሲል ከፀረ ሙስና ኮሚሺን የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ አሀዙ በ2005 የተፈጸመውን ሙስና አላካተተም።
ባለፉት 22 የኢህአዴግ የአገዛዝ አመታት የተፈጸሙና በጸረ ሙስና ኮሚሽን ያልተጣራ በሙስና የተዘረፈ ገንዘብ በቢሊዮኖች እንደሚቆጠር ይገመታል።

የኢንዱስትሪው ዘርፍ የወጪ ንግድ አሽቆለቆለ

ኢሳት ዜና :-አዲስ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፈው ዓመት የተመዘገበው የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) አፈጻጸም እጅግ አነስተኛ እንደነበር ከኢንዱስትሪ ሚ/ር የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡
በ2005 የኢትዮጵያዊያን በጀት ዓመት ከጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ከአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ከፋርማሲዩቲካልስና ከኬሚካል የወጪ ንግድ 542 ሚሊዮን  4 መቶ ሺ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 281 ሚሊዮን  2 መቶ ሺ  ዶላር ወይንም 52 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው፡፡ ዘርፉን ባለፉት ሁለት ዓመታት በ18 በመቶ ለማሳደግ በመንግስት በኩል እቅድና ፍላጎቱ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ይህን እቅድ ማሳካት የተቻለው በ12 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ለዚህ ከተሰጡ ምክንያቶች መካከል የአቅም ውሱንነት፣የምርት ጥራትና ምርታማነት ማነስ፣ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠር አለመቻልና የተገኙትንም አሟጦ መጠቀም አለመቻል እንዲሁም የሰው ኃይል እጥረት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ከ2003-2007 ዓም መንግስት ባወጣው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ቀደም ሲል ኢኮኖሚው ግብርና መር ነው በሚል ሙጭጭ ያለበትን አቋሙን በማስተካከል እስከ 2007 ዓ/ም ድረስ ኢንዱስትሪው መሪነቱን ከግብርና የሚረከብበት ሁኔታ እንደሚኖር በእቅዱ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡
ሆኖም የአጠቃላይ ኢኮኖሚው ደካማ አፈጻጸም ኢንዱስትሪን እና ግብርናን በማዳከም በአንጻሩ ከእቅድ ውጪ  የአገልግሎትን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ደካማ አፈጻጸም አንድ ዓመት ገደማ የቀረውን የመንግሰት የትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደማይሳካ ከወዲሁ ጠቋሚ ሆኗል፡፡

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ተጠየቀ።

መስከረም ፮(ስድት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አዲስ ከዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ለ14 ወራት በቃሊቲ እስርቤት ከታሰሩ በኋላ  ተፈተው የወጡት ስዊድናውያን ጋዜጠኞች  ማርቲን ሺቢ እና ዩዋን ፐርሹን እንዲሁም ዓለምዓቀፍ የሰብዓዊና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተወካዮች፡ ጋዜጠኞችና በስዊድን የሚኖሩ በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ስዊድናውያን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባዘጋጀው ደብዳቤ ላይ ፊርማቸውን በማኖር  ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ  የታሰሩ ጋዜጠኞችን እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሳለፉትን የእስር ህይወት የሚተርከውን እና በቅርቡ ለህትመት የበቃው 438ቱ ቀናት የሚለው መጽሃፋቸው ኢትዮጵያውያንን የህሊና እስረኞችን ለማስታወስ በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ይፋ እንዲሆን የወሰኑት   በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው በከፍተኛ ስቃይ ለሚንገላቱት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች እና ሌሎች የህሊና እሰረኞች የገቡትን ቃል ለማደሰ እንደሆነ በዝግጅቱ ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በአሸባሪነት ተወንጅለው በእስር ላይ የሚገኙ የስራ ባልደረቦቻቸው በዓለም ዓቀፉ ሚዲያ በመዘንጋታቸው እና ይሄንን በመላው ዓለም ዘንድ ትኩረት እያጣ የሚገኘውን ከጊዜ ወደጊዜ  እየተባባሰ የመጣውን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና አፈና እንዲቆም እርዳታ ለጋሽ አገሮች፡ አህጉራዊ እና ዓለምዓቀፍ ድርጅቶች በኢህአዴግ መንግስት ላይ ግፊት በማድረግ በቃሊቲ፡ በቂሊንቶ፡ ዝዋይ እና ሌሎችም እስርቤቶች የሚገኙ ጋዜጠኞች፡የተቃዋሚ ፖርቲዎች መሪዎች እና በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች እንዲፈቱ ለማሰብ መጽሀፋቸውን በዝግጅቱ ላይ ይፋ ለማድረግ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በህይወት ከተለዩ  በኋላ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና አፈና ይሻሻላል ሲባል ጭርሱን ተባብሶ መቀጠሉን በመጠቆም በቅርቡ ከማርቲን እና ዩዋን ጋር በተመሳሳይ ወራት እና ወንጀል ታስራ አሁንም በቃሊቲ እስርቤት ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባት ያለችውን  ርዕዮት ዓለሙን እንደዓብነት አንስተዋል።
ርዕዮት በእስር ላይ በምትገኝበት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እየተፈጸመባት ያለውን ኢሰብዓዊና ኢህጋዊ በደሎች ለመቃወም ከመስከረም ፩ ጀምሮ በረሃብ አድማ ላይ መሆኗን በመጠቆም ይህ በገዥው ስርዓት ሎሌዎች በህሊና እስረኞች ላይ የሚካሄደው በደል እና ግፍ ቅጥ እያጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ውብሸት ታዬ ከእስር እንዲፈታ ያቀረበው የይቅርታ ደብዳቤ በገዥው መንግስት ተቀባይነት ካለማገኝቱም ባሻገር ከአራት ወራት በፊት ከቂሊንጦ ወደ ዝዋይ እስርቤት ሆን ተብሎ በመዛወሩ ልጁ እንዲሁም እድሜያቸው ከሰማኒያ ዓመት በላይ የሆናቸው ወላጆቹ ተመላልሰው ሊጠይቁት እንዳልቻሉ ተገልጿል።
ኤቢፍ የተባለው የስዊድን የሲቪክ ተቋም፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ድንበርየለሹ የጋዜጠኞች ማህበር በስዊድን መስከረም 4፣ 2006 ዓም የተካሄደውን ዝግጅት በጋራ በመሆን ማዘጋጀታቸውን  ቴዎድሮስ አረጋ  ከስቶክሆልም ዘግቧል።
በሌላ ዜና ደግሞ መንግስት በስዊድን ስቶክሆልም ያዘጋጀው የቦንድ ሽያጭ መርሀግብር በተቃውሞ እንዲጨናገፍ ተድርጓል።
በኢትዮ ስዊድን መርሃግብር አስተባባሪነት ከጎትምበርግና ስቶክሆልም የተሰባሰበዉ የተቀዋሚ ኃይል  የአዳራሹን መግቢያ በሰዉ በመዝጋትና የራሳቸዉን  ቀስቃሽ ሙዚቃዎችን በማጫወት  የአዳራሹን መግቢያና አካባቢዉን ተቆጣጥረዉት ስለነበር ይህን ጥሶ የሚገባ ባለመኖሩ አዳራሹ ከቦንድ አዘጋጆች በቀር ባዶዉን እንዲዉል መደረጉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በምሽቱ የሙዚቃ ፕሮግራም ላይ በተፈጠረ ረብሻም የሙዚቃ ዝግጅቱ እንደተጠበቀው አለመካሄዱን መረጃው አመልክቷል። በስዊድን መንግስት ያዘጋጀው የቦንድ ሽያጭ ሲከሽፍ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

 

የአንበሶች መጋቢው -በአንበሳ መበላታቸው ተዘገበ።

 ኢሳት ዜና :- አዲስ አበባ በተለምዶ አንበሳ ግቢ ተብሎ በሚጠራው የአንበሶች ማቆያ ማእከል ውስጥ ዛሬ ከጠዋቱ 1:30 ላይ  የአንበሶች መጋቢ የነበሩ ግለሰብ በ አንበሳ መበለታቸውን ራዲዮ ፋና ዘገበ።
እንደራዲዮጣቢያውዘገባአደጋው የተከሰተው   በዛሬው እለት ተረኛ ተንከባካቢ የነበሩት እና አቶ  አበራ ሲሳይ የተባሉትየአንበሶቹ መጋቢ፥ የአንበሶቹን ማዳሪያ እያጸዱ ባሉበት ወቅት ነው።
ከጥንቃቄ ጉድለት ባልተዘጋው በር የገባውና  መጋቢውን ለህልፈተ ህይወት የዳረጋቸው አንበሳ ስሙ-ቀነኒሳ እንደሆነም ራዲዮው ጨምሮ ዘግቧል።
የግለሰቡን ህይወት ለማትረፍ በወቅቱ በስራ ላይ የነበሩ የግቢው ሰራተኞች ጥረት ቢያደርጉም-ሳይሳካ መቅረቱንም ለማወቅ ተችሏል።
የሟች አስከሬን ከመንከባከቢያ ስፍራው ወጥቶ ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ተወስዷል። የዚህ አይነት አደጋ  በ19 89 ዓ.ም መከሰቱ የሚታወስ ነው።
ESAT

No comments:

Post a Comment