ዲ/ን ዳንኤል ክብረት: ‹‹ይህች ቤተ ክርስቲያን ተጠብቃ፣ ሥርዐቷን ይዛ ወደሚቀጥለው ትውልድና ዘመን መሻገር አለባት›› የሚሉትን አካላት ነው ‹‹አክራሪ›› ማለትና ዝም ማሰኘት የሚፈለገው፡፡ እነዚህን ሰዎች ዝም ማሰኘት ግን አይቻልም፡፡ ሃይማኖት የህልውና ጉዳይ ነው!!
(ዕንቊ መጽሔት፤ ቅጽ 6 ቁጥር 101፤ መስከረም ፳፻፮ ዓ.ም)
መንግሥት የተወሰኑ አክራሪዎች የሚላቸው አካላት የሙስሊሙን ማኅበረሰብ እያወናበዱት ነው ሲል መግለጹ
የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚሁ ጉዳይ ጋራ በተያያዘ የተወሰኑ ሙስሊሞችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ይኸው አጀንዳ አሁንም
የሙስሊሙን ማኅበረሰብ በሚያረካና ዘላቂ አገራዊ ሰላም በሚያመጣ ኹኔታ መቋጫ አላገኘም፡፡ ይልቁንም መንግሥት
‹‹ሚዛን ለመጠበቅ›› በሚመስል መልኩ ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አካባቢም አክራሪዎች አሉ፤
መረጃው አለን›› እያለ መወንጀል ጀምሯል፡፡ ለመኾኑ በኢትዮጵያ አክራሪነትን የሚያበረታታ ታሪካዊና ማኅበራዊ መሠረት
አለን?
መንግሥት በተለየ መልኩ ትኩረት አድርጎበታል የሚባለውን የማኅበረ ቅዱሳን ሓላፊዎችን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ባለመሳካቱ የማኅበሩን አስተያየት ማካተት አልቻልንም፡፡
የዚህ እትም የመጽሔታችን እንግዳ ደራሲና ሰባኪ ዳንኤል ክብረት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያንን በሚመለከቱ ጉዳዮችና በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ በርካታ መጻሕፍትን
ከጻፉት ምሁር ጋራ በአክራሪነት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ባልደረቦቻችን ፈቃዱ ማኅተመ ወርቅና ሰሎሞን ለማ
ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ዕንቊ፡- ጽንፈኝነት ምንድን ነው? አክራሪነትስ?
ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፡- አንድን ነገር ወደ ጥግ ወይም ወደ መጨረሻው ጠርዝ ላይ መውሰድ ጽንፈኝነት
ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ አክራሪነት ይኹን ጽንፈኝነት በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብዙም ልዩነት ያላቸው ጉዳዮች
አይደሉም፡፡ ልዩነታቸው በአፈጻጸም ላይ ነው፡፡ ጽንፈኞቹ ‹‹ይሄ እና ይሄ ብቻ›› የማለት ጠባይ አላቸው፡፡
አክሪዎቹ ደግሞ ‹‹ይሄ እና ያ ካልኾነ እንዲህ እናደርጋለን›› ወደሚልና ወደ ተግባሩ ርምጃ የሚያዘሙት ናቸው፡፡
ጽንፈኝነት በየትኛውም ጠባይ ሊኖር ይችላል፡፡ በማንኛውም ጉዳይ በቅርብ ስትመጣ ለዘብተኝነት፣ ወደ መሐል ሲኾን ወግ አጥባቂነት፣ ወደ ዳር ሲሄድ ጽንፈኝነት ይኖራል፡፡ በባህልም
ቢኾን ለዘብተኛ ሰው አለ፤ ማንኛውም ባህል ምንም የማይመስለው፡፡ ባህሉን የሚያጠብቅም አለ፤ ‹‹ባህሌን
እወደዋለኹ፤ አከብረዋለኹ፤ ለምን ትነካብኛለኽ? ለምንስ ትበርዝብኛለኽ? ሳይበረዝና ሳይከለስ እንዲሁ እንዲኖርልኝ
እፈልጋለኹ. . .›› ብሎ የሚያስብ ሰው አለ፡፡ ወደ ዳር ያለው ደግሞ ‹‹ከዚህ ውጭ ያለውን ፈጽሞ ማየትም ኾነ
መስማት አልፈልግም!. . .›› ባይ ነው፡፡ የሌላውን ህልውና የሚክድ ነው፡፡ ይህ ለእኔ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ከባዱ
ነገር አክራሪነት ነው፡፡ ወደ አክራሪነት ስትመጣ ‹‹ይሄኛውን ካልተቀበለ…›› ከሚል ይነሣና ርምጃ እስከ መውሰድ
ጥግ ድረስ ይሄዳል፡፡
ዕንቊ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- በአገራችን ‹‹አክራሪነት የለም›› ብለን መደምደም አንችልም፡፡ በተወሰነ ደረጃ አለ፡፡ የሚለያየው በምን ያህል ደረጃና የት ነው ያለው? የሚለው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የመኖሩን ምልክት ሰዎች ከእምነታቸው የተነሣ ሲገደሉ፣ የእምነት ቦታዎች ሲቃጠሉ፣ የእምነት አባቶች መቃብራትና የተለያዩ ነገሮች እንዲፈርሱ ሲደረጉ. . . አይተናል፡፡ ጽንፈኝነትን ብቻ ሳይኾን ወደ ኃይል ርምጃው የመሄዱን ነገር አይተናል፡፡
የዛሬ ሰባት ዓመት ከተመለከትነው የጅማው ድርጊት ብንነሣ እንኳ አክራሪነት መኖሩን እንረዳለን፡፡ እነዚያ የጅማ ክርስቲያኖች የተገደሉት ምንም መጥፎ ነገር አድርገው አልነበረም፡፡ ብዙዎች ኾነው ነውጥ ፈጥረው ነው እንዳይባል በቁጥራቸው ትንሽ ናቸው፡፡ የነበሩትም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በገባበት ከኻያ ዓመት በፊት በነበሩት ሰሞናት በአሰቦት ገዳም እነ ጃራ አል እስላሚያ
የፈጸሙትም በምሳሌነት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ እነዚያ መነኮሳት ተራራ ላይ በነበረ አንድ ገዳም ይኖሩ የነበሩ
ናቸው፡፡ ሌላ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ የተገደሉት መነኩሴ ወይም ክርስቲያን በመኾናቸው ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲታይ
የአክራሪነት ጠባዕያት በአገራችን የለም ለማለት ያስቸግራል፡፡
ዕንቊ፡- ከመቼ ወዲህ ነው ይህ ዝንባሌ በኢትዮጵያ መስተዋል የጀመረው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ይህ የመገዳደል ኹኔታ ማለትም አንድ ሰው ክርስቲያን በመኾኑ የመግደል፣ ሙስሊም
በመኾኑ የመግደል ወይም የሙስሊምን መሰጊድ፣ የክርስቲያኑን ቤተ መቅደስ በማቃጠል የሚገለጸው ድርጊት በቅርብ ጊዜ
ታሪክ ውስጥ ከ1980ዎቹ በኋላ መታየት የጀመረ ነው፡፡ የተመዘገቡት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከ1980 ዓ.ም ወዲህ
ነው፡፡ ይህም ከአካባቢያዊ ኹኔታዎችና በመላው ዓለም ከተስዋለው የተከተለና ችግርን የመፍቻ አንድ አማራጭ አድርጎ
ከመመልከት የመነጨ ነው፡፡
ዕንቊ፡- በአገር ውስጥ እንዲህ ዐይነት ነገሮች እንዳይከሠቱ ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አንድ፡- መንግሥት፣ ሁለት፡- ከሃይማኖት ተቋማት፣ ሦስት፡- ከሌሎች አካላት በኩል ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ መንግሥት
በሕገ መንግሥቱ፣ ‹‹ሃይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ ናቸው›› ብሏል፤ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ፖሊስ
እንኳ የለም፡፡ ይሄ ባለመኖሩ መንግሥት ሃይማኖቶችን እንዴት ነው የሚያያቸው? ለሚለው መልስ ለማግኘት አስቸጋሪ
ይኾናል፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል ያለው ለሌላው ያደላል፣ በሌላ በኩል ያለውም ለሌላው ያደላል እያለ እንዲያማርር
ኹኔታው በር ከፍቷል፡፡ አሠራሮች ላይ የሚፈጠሩ ነገሮች አሉ፤ በምዝገባውና በሌላውም፡፡ አንዳንዶቹ የተጨቋኝነት፣ ሌሎቹ የጨቋኝነት፣ ደግሞ አንዳንዶቹ የተገላጋይነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ናቸው፡፡
የሃይማኖት አስተሳሰቦች የሚመሩትን ብዙኀን ሕዝብ እንዴት ነው፤ በምን መልኩ ነው፤ እምነቱን
ከአገሪቱ ዕድገት፣ ከአገሪቱ የፖሊቲካ አስተሳሰብ ጋራ በማይጣላበት ኹኔታ ማስኬድ የሚቻለው በሚለው ላይ በደንብ
የተጠና ፖሊስ በአገሪቱ አልነበረም፡፡ የተሠራ ሥራ አልነበረም፡፡ አሁንም አለ ለማለት ይከብደኛል፡፡ ዛሬ በሃይማኖት
ጉዳዮች አንድ የሃይማኖት ዳይሬክቶሬት ነው ያለው፡፡ ግን አገሪቱ ውስጥ ትልልቅ ቦታ የሌላቸው፣ ታላላቅ ጉዳዮችን
የማይወስኑ፣ በትልቅ ፖሊሲ፣ በትልቅ ሚኒስቴር ደረጃ ይታያሉ፡፡ ይህ ለቦታው የተሰጠውን ግምት ያንጸባርቃል፡፡
ብዙውን ውኃ በትንሽ ኮዳ ለመያዝ የመሞከር አሠራር ነው የሚስተዋለው፡፡ ስለዚህ በእምነቱ ጉዳይ ከኮዳው አቅም በላይ
ሲኾን የሚፈጠሩ ዐይነት ችግሮች እየተመለከትን ነው፡፡
ዕንቊ፡- አክራሪነትን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አኳያ እንዴት ታየዋለኽ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አክራሪነት ቦታ የለውም፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት፣ ከቀኖናው ስንነሣ ይህች ቤተ ክርስቲያን ለሌሎች ዕውቅና የመንፈግ ችግር አልነበረባትም፡፡ ዕውቅና ስትሰጥ ነው የኖረችው፡፡
የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ አገሪቱ ሲመጡ፣ በወቅቱ የነበሩት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናን ባይቀበሉት ኖሮ
ንጉሡ ብቻውን ምንም ሊያደርግ ባልቻለ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የነገሥታቱ ሥልጣን፣ ከእምነት
አባቶች ተቀባይነት ማግኘት የሚመነጭ በመኾኑ ነው፡፡ ያ ሳይኾን ሲቀር በአገሪቱ የተፈጠሩትን ችግሮች ቀረብ ካሉት
ጊዜያት በእነ ዐፄ ቴዎድሮስ፣ በእነ ዐፄ ሱስንዮስ ከኾኑት ድርጊቶች ማየት እንችላለን፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ግጭቶች ይፈጠሩ የነበሩት፣ ሌሎች ለእርሷ ዕውቅና መስጠት ሲያቅታቸው ነው፡፡
ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ሺሕ ዘመናት ስትቀድስ፣ ስታስተምር የኖረችበትና በ6ኛው መ/ክ/ዘ በእጅ የተጻፈው ወንጌል
የተገኘው በዐድዋ እንዳባ ገሪማ ገዳም ነው፡፡ ከእርሱ የቀደመ እስከ አሁን ሊገኝ አልቻለም፡፡ እንደዚህ ያለ የክርስትና ታሪክ የተገኘባትንና አስቀድማ ወንጌል ስታስተምር የነበረችን ቤተ ክርስቲያን ‹‹ወንጌል ስታስተምሪ አልነበረም›› የሚልና ለሥራዋ፣ ለአገልግሎቷ ዕውቅና የመንፈግ ችግር አለ፡፡ ይህን ኃይል በመጠቀም፣ ድንበሯን በመሻገር፣ እርሷው ቤት ድረስ ገብተው ካህናቷ ካሉበት፣ ቅኔ ማሕሌቷና መቅደሷ ውስጥ የመዝለቅ ፍላጎት ያላቸው ሲመጡ ችግር ነው የሚኾነው፡፡
በ17ኛው መ/ክ/ዘ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ በካቶሊኮችና በኦርቶዶክሶች መሐል የተከሠተው ግጭት
መንሥኤው አስቀድሜ የገለጸኹት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሮማ አልሄደችም፡፡ ሮም ናት እዚህ የመጣችው፡፡ እዚህ
መምጣቷ ብቻ አልነበረም ችግሩ፣ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ከበሮው፣ ታቦቱም፣ የካህናቱ አልባሳትም ይውጣ! የዘመን አቆጣጠሩም እንደ ጎርጎሮሳውያን ይኹን! በዓላቱም ይቀየሩ! የዓመቱ መጀመሪያ መስከረም መኾኑ ቀርቶ ታኅሣሥ ይኹን!›› በሚል በቀጥታ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ውስጥ ገቡ፡፡ ይህን የመሰለው ግፊትና ዕውቅና የመንፈግ ኹኔታ ሲመጣ ወደ ጦርነት ደረጃ ታለፈ፡፡
በስተኋላ የዐፄ ሱስንዮስ ዘመን አልፎ የዐፄ ፋሲል ዘመን ሲመጣና ችግሩ ቆሞ ኢትዮጵያውያን አባቶች፣ እነዚህ ሰዎች ምን ይደረጉ ሲባሉ ‹‹ጉባኤ ይጠራና እንከራከር›› ነው ያሉት፡፡ ጉዳዩን ከጉልበት ወደ ዕውቀት አቅጣጫ ነው የወሰዱት፡፡ ‹‹የሐሳብ ክርክር እናድርግ፤ በጉባኤው የረታ ይሂድ›› አሉ እንጂ ሌላ ነገር አላሉም፡፡ ይህም የሊቃውንቱን ጠባይ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ አክራሪነትን ሊያበቅል የሚችል መሬት አይገኝም፡፡
ዕንቊ፡- በቅርቡ የመንግሥት ወኪሎችና ሌሎች የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት አገር ዓቀፍ የኾነ ጉባኤ፣ አባ
ዮናስ የተባሉ ሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለይ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ‹‹የአክራሪነት
ችግር አለ›› የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በርግጠኝነት በቤተ ክርስቲያኒቱ የአክራሪነት ችግር
ስለመኖሩ ለማሳወቅ የደፈሩ የፖሊቲካ ሰዎችም ነበሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአንተ አስተያየት ምንድን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- በቅድሚያ፣ አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሦስት ከፍለን ማየት አለብን፡፡ አንደኛ፡- የሌሎች መሣርያ በመኾን መሣርያ ያደረጓቸውን ወገኖች ጉዳይ የሚያስፈጽሙ አሉ፡፡ እነዚህ ሰይጣን ወደ ገነት መግባት በቻለበት ኹኔታና መንገድ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ እንደሚታወቀው ሰይጣን ራሱ ወደ ገነት አልገባም፡፡ ወኪል ነበረው፡፡ ወኪሉም እባብ ነበር፡፡
በእባብ ውስጥ አድሮ ነው ወደ ገነት የዘለቀው፡፡ ምክንያቱም የሰይጣን ባሕርይም ጠባይዕም ስለማይፈቅደለት ራሱ ወደ
ገነት አይገባምና ነው፡፡ በአባቶቻችን መጽሐፍ እንደሚነገረው፣ እባብ ተንኮለኛ፣ ውብና ትክለ መልካም ነበረች፡፡
ስለዚህ ሰይጣን ክፉ ሐሳቡንና ሤራውን በተዋበውና በማራኪው የእባብ ውበትና ተክለ ሰውነት ሸፍኖ ወደ ገነት ገባ፡፡
ሔዋንም ልትሳሳት የቻለችው የምትነጋገረው ከእባብ ጋራ ስለመሰላት ነው፡፡ ከእባብ ጀርባ ያለውንና የእባብን ሐሳብ
የቀየረውን ነገር መመልከት አልቻለችም፡፡
ልክ እንደዚሁ ሁሉ ገነት በኾነችው ቤተ ክርስቲያን የሌላውን ሐሳብ ይዘው የመጡ ወገኖች ገብተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በምንኩስና፣ በቅስና፣ በዲቁና፣ በመምህርነት፣ በዘማዊነት አለባበስ ውስጥ ሁሉ የሚገኙ ናቸው፡፡ ግን ሐሳባቸው የእነርሱ አይደለም፡፡
ሁለተኛ፡- ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት ስትቃወመው የነበረችውን የለዘብተኛ ማለት የሊበራል ክርስትና
አስተሳሰብ ተጭነው በመምጣት ያን የሚያራምዱ ሰዎችም አሉ፡፡ ከእኒህ ጋራ ሊታዩ የሚችሉ ግን ደግሞ ለምንም ነገር
ግድ የሌላቸው ሰዎችም አሉ፡፡ በዐርባና በሰማኒያ ቀናቸው ከመጠመቃቸው በቀር ለምንም ኾነ ለምን ቤተ ክርስቲያኒቱ
ውስጥ ግድ የሌላቸው መኖራቸው አይካድም፡፡
ሦስተኞቹ ደግሞ፣ ‹‹የለም፣ ይህች ቤተ ክርስቲያን የራሷ የኾነ በጣም ብዙ ጠንካራ ነገሮች
አሏት፡፡ በዶግማ፣ በቀኖና፣ በትውፊት፣ በቅርስ፣ በባህል ሀብታም ነች፡፡ በዓለም ላይ የጠፉ ቅርሶችን ጠብቃና
ተከባክባ የቆየች ናት፡፡ የዓለም የባህል ሙዝየም ናት. . .›› ብለው የሚያምኑ፣ የሚሟገቱላትም ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡-
ሰንበቴ ይህች ቤተ ክርስቲያን ይዛው የቆየችው የዓለም ባህል ነው፡፡ የዓለም ክርስትና ሲጀመር ሰንበቴ ነበር፡፡
ሲጠፋ ግን ጠፋ፡፡ እርሷ ዘንድ ግን አለ፡፡ ጽዋ በሌላም ቦታ ነበር፤ ግን ጠፋ፡፡ ዛሬ የአውሮፓን ካታኮምብ
(ጥንታዊ ከርሰ መቃብሮች) ቁፋሮ ሲካሄድ የሚገኙ ሥዕሎች ሰንበቴ ተሰብስበው ሲበሉ፣ ጽዋ ሲጠጡ የሚታዩባቸው
ናቸው፡፡ እነርሱ አሁን የድሮ ክርስቲያኖች እንዲህ ነው የሚበሉት፣ የሚጠጡት ይሉኻል እንጂ ዛሬ ህልውናው የለም፡፡
እኛ ጋራ ግን ከነሕይወቱ ተጠብቆ ታገኘዋለኽ፡፡
ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፤ [በዓለ]መስቀል እኛ ጋራ አልነበረም የተጀመረው፡፡ ሌሎች ጋራ የነበረ ነው፡፡ ግን እኛ
ጋራ ነው ሕያው ኾኖ የሚገኘው፡፡ በሌሎች ቦታዎች ታስቦ ነው የሚውለው፡፡ [በዓለ]ጥምቀትም ታስቦ ነው የሚውለው፡፡
የግብጽን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስታይ፣ እስከ ስምንትና ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በዓለ ጥምቀትም በዓለ መስቀልም
በዐደባባይ ይከበር ነበር፡፡ ዛሬ ግን አልኾነም፡፡ ይኸው እኛ ጋራ ግን በህልውናው አለ፡፡ ስለዚህ ነው ይህች ቤተ
ክርስቲያን የራሷ ብቻ ሳትኾን የዓለም ባለ አደራ ናት የምንለው፡፡ ከዓለም ከኦሪት ታቦታቱን፣ ከሐዲስ መስቀሉን
ጠብቃ በአደራ አስቀምጣ የቆየች አደራ የማትበላ ናት፡፡
‹‹ይህ ቤተ ክርስቲያን አደራዋን እንደጠበቀች፣ ሃይማኖትን እንደ አባቶቻችን፣ አሠራሩን እንደ ዘመናችን አድርጋ መሄድ አለባት›› የሚሉ ወገኖችም ያሏት በመኾኑ፣ በእነዚህ ወገኖችና የሌላውን ሐሳብ ተጭነው በሚመጡ ሰዎች መሐል ትግል አለ፡፡ ክርክር አለ፡፡ ሰውዬውን በአካል ባላውቃቸውም ሲናገሩ ባላዳምጥም አሉ የተባለውን ሰምቻለኹ፡፡ ምናልባት ስማቸው የተነሣው አባት የተባለውን ሐሳብ ይዘው መጥተው ሊኾን ይችላል ብዬ አምናለኹ፡፡
የኾነው ኾኖ፣ የሌላውን ሐሳብ ይዘው የሚመጡ ሰዎች ትልቁ ችግራቸው ምንድን ነው? ዘመኑን ከመዋጀት ይልቅ (መጽሐፉ ‹‹ዘመኑን ዋጁ›› ይላልና) ዘመኑን የመጠቀም ስልት መከተላቸው ነው፡፡
የኮሚዩኒስት ሐሳብ ሲራመድ ካዩ፣ ራሳቸውን ኮሚዩኒስት ሌላውን ካፒታሊስት ያደርጋሉ፡፡ የካፒታሊስት ሐሳብ በዘመኑ
ሲራመድ ሲያዩ ደግሞ ራሳቸውን ካፒታሊስት ሌላውን ኮሚዩኒስትነት ፈርጀው ማስመታት ይፈልጋሉ፡፡ ይህን መሰል ተግባርም
በየዘመኑ ይፈጽማሉ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተ ወደ ኻያ ዓመት በላይ ኾኖታል፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ይሰጡት የነበረውን
ስሞች ብንመለከት የሚያስገርምና የሚያስደንቅ ነው፡፡ መአሕድ በአገሪቱ ትልቅ መነጋገርያ በኾነበት ጊዜ ‹‹መአሕድ
ነው›› ተባለ፡፡ አገሪቱ ቅንጅት፣ ቅንጅት በምትሸትበት ጊዜ ደግሞ ‹‹ቅንጅት›› ተባለ፡፡
ዕንቊ፡- ለምንድን ነው እንደዚህ የሚባለው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ምክንያቱ አስቀድሜ ባቀረብኹት ምሳሌ መሠረት በዘመኑ የመጠቀም ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጠባይና ባሕርይ የሚመጣ ነው፡፡ አንተ በሐሳብ ስትሸነፍ ማስመታት መቻል አለብኽ፡፡ በእኛ አገር የተለመደ ሦስት ዐይነት አሠራር አለ፡፡ አንድን ነገር መጀመሪያ ታውቀዋለኽ፡፡ ቀጥለኽ ስም ትሰጠዋለኽ፡፡ ሠልሰኽ ትመታዋለኽ፡፡ ስም ካላወጣኽለት አይመታልኽም፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለምን ነበር ‹‹መአሕድ›› ይባል የነበረው? የሚያደርገው እንቅስቃሴ በመታወቁ ነው፡፡ እንደዚህ
የሚወነጅሉትም ሰዎች እኮ ያውቁታል፡፡ ግን ለመምታት የሚያስችላቸውን ስም ማውጣት አለባቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ግን እስከ አሁን ድረስ አክራሪ ኹኖ ያመጣው ነውጥ፣ ያሥነሳው ነገር፣ የደበደበው፣ የገደለው ሰው፣ ያቃጠለው ቤተ እምነት የለም፡፡
ዕንቊ፡- ሰው ሕይወቱን፣ እምነቱን፣ ትምህርቱን፣ የዕውቀትና የኑሮ ምርጫውን በተመለከተ የራሱ ሐሳብና
ከሐሳቡም የሚመነጭ ውሳኔ አለው፡፡ የሌላውን መብት እስካልተፃረረ ድረስ በራሱ ለራሱ የመመራት መብት ባለቤት ነው፡፡
‹‹ለምንድን ነው እኛ ወዳደራጀነው ተቋም፣ ማእከል የማትመጣው›› የሚሉ ‹‹አልመጣም›› ሲል በአክራሪነት ወይም
በሌላ የሚፈርጁ ሰዎችና ቡድኖች ደግሞ አሉ፡፡ ይህን ኹኔታ በጠራና የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር ደረጃ ለኅብረተሰቡ
ማስተማር የሚቻልበት መንገድ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አስቀድሜ ለማንሣት እንደፈልግኹት፣ ለዘብተኛው አካል መሥዋዕትነት ለመክፈል ወይም
ደግሞ አንዳች ሱታፌ ለማድረግ ፍላጎት የለውም፡፡ ያኛው ደግሞ የሌላው ወኪል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህች ቤተ
ክርስቲያንኮ በሦስት ደረጃ ማለትም ወይ ለማፍረስ! ወይ ለመጠምዘዝ (ከምትሄድበት አቅጣጫ ወደ ሌላ መሥመር
ለመውሰድ) ይህ ካልኾነ ደግሞ ለማደንበሽ ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ማደንበሽ ማለት ምንም እንቅስቃሴ እንዳታደርግ፣
ዝም ብላ እንድትኖር ማድረግ ማለት ነው፡፡ ለአንድ ሰው ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ ተሰጥቶት ግን በአእምሮው ምንም
ዕውቀት እንዳይኖረው የማድረግ ዐይነት ነው፡፡ እንደዚህ ዐይነቱ ሰው አንድ ሰፈር ውስጥ ቁጭ ብሎ የፈለገውን ፊልም፣
የፈለገውን ሙዚቃ እያየና እያደመጠ፣ በዚህ ብቻ እየተደሰተና እየጨፈረ እንዲኖር ቢደረግ ይህ ኑሮ አይደለም፡፡ ያ
ሰው ምንም የሚያስበው፣ የሚሠራው፣ የሚፈጥረው ነገር የለውም፡፡ በቃ ሰፈሩ ብቻ መኖርያው ነው፡፡ የምግብ፣ የልብስ
ችግር የለበትም፡፡ እንግዲህ ይሄ ነው መደንበሽ የሚባለው፡፡
በእኒህ በሦስቱ የማጥፊያ ስልቶች ይህች ቤተ ክርስቲያን ተሞክራለች፡፡ ግን የእግዚአብሔር ኃይል፣ የቅዱሳን
ጸሎት በውስጧ ስላለ የተመኙላትን ልትኾን አልቻለችም፡፡ በርግጥ የተወሰኑ ሰዎችን መማረክ ይቻል ይኾናል፤ ግን
ይህች ቤተ ክርስቲያን ከማናችንም ኃይል በላይ ናት፡፡ ያልታወቀና ማንም የማይደርስበት ኃይል ያላት ነች፡፡ ባትኾን
ትጠፋ ነበር፡፡ ግራኝ አንድ ዐሥረኛ ምእመኗ እስኪቀር ጭፍጨፋ አካሂዶባታል፡፡ ብዙዎቹን መቅደሶቿን አቃጥሎባታል፤ ግን አልጠፋችም!
ፋሽስት ኢጣልያ ብዙ ነገር አድርጓል፡፡ የፋሽስት ኢጣልያ ወራሪ ጦር እንደገባ ወደ አራዳ ቅ/ጊዮርጊስ በመሄድ
የቤተ ክርስቲያኑን ቅጽር በወታደሮች ነው ያስከበበው፡፡ ቀጥሎም የቅ/ጊዮርጊስ ታቦት ‹‹ወታደራዊ ፍርድ ቤት››
በሚለው ችሎት እንዲቀርብ በማድረግና ‹‹ሞት ሊፈረድበት ይገባል!›› የሚል ውሳኔ በማስወሰን ዙሪያውን ተኩስ
እንዲከፈትበት አድርጓል፡፡ የተኩሱ አሻራ አሁንም ድረስ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ውስጥ አለ፡፡ ግን ይህ ለምን
ተደረገ? የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ታቦቱ አገር በመጠበቁ ካልኾነ ምን ወንጀል ነበረበት? ከአራዳ ጊዮርጊስ
አልፈው ደብረ ሊባኖስ በመሄድ መነኮሳቱን የገደሉት ለምንድን ነው? ቅርሷንስ ጭነው የሄዱት? ያኔ ብዙ መነኮሳት
ተገድለዋል፡፡ ከሞቱት መሐል እነ አቡነ ጴጥሮስ የዚህች ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ራስ ናቸው፡፡ ግን
የሚጠብቃት ኃይል ስላለ ምንም ሊያደርጓት አልተቻላቸውም፡፡
ዕንቊ፡- ይህ ‹‹አክራሪ›› የሚባለው ስያሜ የመነጨው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፍረስ፣ ለመጠምዘዝ ወይም ለማደንበሽ ከሚፈለገው መንፈስ ነው ማለት ይቻላል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ታድያስ! እርሱ እኮ ነው ‹‹ይህችን ቤተ ክርስቲያን እንጠብቅ›› የሚሉትን የሚፃረረው፡፡
ዕንቊ፡- ‹‹መንፈሱ መኖር አለበት›› በሚሉና ‹‹መንፈሱ መኖር የለበትም›› በሚሉ መካከል ነው ትግሉ ያለው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ነው!. .
.ትግሉ እርሱ ነው፡፡ ‹‹ይህች ቤተ ክርስቲያን ተጠብቃ፣ ሥርዐቷን ይዛ ወደሚቀጥለው ትውልድና ዘመን መሻገር
አለባት›› የሚሉትን አካላት ነው አሁን ‹‹አክራሪ›› ማለትና ዝም ማሰኘት የሚፈለገው፡፡ እነዚህን ሰዎች ዝም
ማሰኘት ግን አይቻልም፡፡ ሃይማኖት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
ዕንቊ፡- ዝም ማሰኘት ካልተቻለ ግቡ ምን ሊኾን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እርሱን በሂደት የምናየው ነው፡፡ የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማንም በዕቅድ፣ በስትራተጂ፣ በምን ሊተምነው አይችልም፡፡ ታሪኳ የእግዚአብሔር ሥራ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹እገሌ ነው እርሷን የሚመራት›› ሊባል አይችልም፡፡ አስተዳደራዊ አመራር ይኖራታል እንጂ መንፈሳዊ አመራሯን ከፈጣሪ የምታገኝ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚህ እኛ የተባሉት ሰው(አባ ዮናስ) ይህን ዓላማ ይዘው መጥተው ተናግረውት ካልኾነ በቀር ማኅበረ ቅዱሳንን አክራሪ ለማሰኘት የሚያበቃ ምንም፣ አንድም መከራከሪያ ሊያመጡ አይችሉም፡፡
ለነገሩ እርሳቸውም ቢኾኑ ማስጠንቀቂየ ሰጡ እንጂ ይሄ፣ ይሄ፣ ይሄ ብለው በዝርዝር ያመጡት ምንም ነገር የለም፡፡
ከሳቸውም በፊት የነበሩት ሌሎች ሰዎች እንደ እርሳቸው ብለዋል፡፡ ማናቸውም ግን ማስረጃ ብለው የሚያቀርቡት ነገር
የላቸውም፡፡ በበኩሌ አራት፣ አምስት ነገሮች ሲነገሩ እሰማለኹ፡፡ ‹‹አንዲት አገር አንዲት ጥምቀት››፤ ‹‹አንድ
አገር አንድ ሃይማኖት›› ብለዋል የሚል፡፡ ይህን ከብዙኀን መገናኛ እሰማዋለኹ እንጂ ከየትኛውም የቤተ ክርስቲያን
መጽሐፍ ላይ ተጠቅሶ አይቼ አላውቅም፡፡
እንዴ ‹‹አንድ አገር አንድ ሃይማኖት›› የሚለው እኮ ከራሷ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋራ የሚጋጭ ነው፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ አንድ ቁጥር ስምንት ላይ የሚለው ‹‹በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እስከ ዓለም ዳርቻ
አስተምሩ›› ነው፡፡ አንድ አገር ውስጥ ተቀመጡ አላለም፡፡ የሚባለውን የማንቀበለው ከእኛ አስተምህሮ ጋራ ስለሚጋጭ
ነው፡፡ ቢቻል ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማልያ፣ ታንዛንያ፣ ጋና፣ ጃማይካ ሄደን አስተምረን ክርስቲያን ማድረግ ነው
የሚጠበቅብን፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ የኾኑ አሜሪካውያን፣ ጃማይካውያን፣
እንግሊዛውያን፣ ጀርመናውያን አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ እንዴት ወደ አንድ አገር መጥቅለል ይቻላል? ሊኾን አይችልም፡፡
ፈጽሞ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋራ የማይሄድ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በዜግነት ኢትዮጵያውያን ያልኾኑ የእምነት አባቶች ያሏት ነች፡፡ የመጀመሪያው ጳጳስ አቡነ
ሰላማ ግሪካዊ ነው፡፡ ዘጠኙ ቅዱሳን የሶርያ፣ የግሪክ፣ የሮም ሰዎች ናቸው፡፡ ወደዚህ ቀረብ ስንል አቡነ ገብረ
መንፈስ ቅዱስ ግብጻዊ ናቸው፡፡ የደብረ ሊባኖሱ 11ኛ ዕጨጌ አቡነ ዕንባቆም የመናዊ ነው፡፡ እንዴት ተደርጎ በአንድ አገርና በአንድ ሕዝብ መወሰንና ማስተማር የሚቻለው፡፡ በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እኮ ዕድሉ የለም፡፡
ዕንቊ፡- ጽንፈኝነትን ይኹን አክራሪነትን የሚያበረታታ ታሪካዊ መሠረት በአገራችን ታሪክ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ከዚህ ጥያቄ አንጻር ሦስት ነገሮችን ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡ አንደኛ፡-
የእምነቶቹ ግንኘነት በመተዋወቅና በመግባባት እንዲኾን የተሠራ ሥራ የለም፡፡ ይሄ ባለመሠራቱ አንዳንድ ወገኖች
ሁልጊዜ የተጨቋኝነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ግን እነዚህን በቀላሉ ማጥፋት የሚቻልበት
መንገድ፣ እርስ በርስ የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲኖራቸው የማድረጉ ዕድል አለ፡፡
ለምሳሌ አንዱ ስለሌላው ሲናገር መኾን ስለሚኖርበት ኹኔታ ተቀራርቦ በመወያየት አንድ የሚያግባባ ነጥብ ላይ
መድረስ ይቻላል፡፡ በመሠረቱ ስለሌላው እምነት ማስተማር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ አንተ ‹‹እኔ ትክክል ነኝ›› ስትል ሌላው
‹‹ስሕተት ነው›› ማለት በፍጹም ችግር ያለበት ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ ሙስሊም ‹‹እስልምና ትክክለኛ የመዳን
ሃይማኖት ነው›› እስካለ ድረስ ‹‹ክርስትና ስሕተት ነው›› ብሎ ስሕተት ናቸው ብሎ ስለሚያምንባቸው ነገሮች
ቢያስተምር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ለምን ይህን አደረግኽ ልንለው አንችልም፡፡ አለበለዚያ ‹‹ክርስትናም እስልምናም ትክክል
ነው›› ማለት መቻል አለበት፡፡ አንድ ክርስቲያንም ስለ እስልምና ‹‹ቊርዓን እዚህ ጋራ ተሳስቷል፤ ነቢዩ መሐመድ
እዚህ ላይ ተሳስተዋል፤ አካሄዳቸው ስሕተት ነው›› ቢል ለእኔ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ግን እርሱ አይደለም ችግሩ፡፡ ይህን
ስታስተምር ምን ዓይነት ሥነ ምግባራዊ መርሕ መከተል አለብህ፤ አንዱ ወደ አንዱ እንዲመጣ ሳይኾን አንዱ በሌላው
ላይ የጥላቻ ስሜት እንዳያድርበት ማድረግ የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን የሚያይበት አሠራር መስተካከል አለበት ባይ ነኝ፡፡ በአንድ
ሚኒስቴር ሥር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው ያለው፡፡ ፖሊሲ የለውም፡፡ አሁን ተቋቋመ የተባለው ጉባኤ በራሱ
ሲታይ ሕዝቡ በሚገባ የተረዳው ዐይነት አይደለም፡፡ የምንመሠርታቸው ተቋማት ለምን እንደ ሐበሻ መድኃኒት ድብቅ
እንደሚኾኑ ይገርመኛል፡፡ ሲኾን እንደዚህ ዐይነቱ ተቋም መቋቋም የሚገባው በላይኛው አካል አልነበረም፡፡ ከታች
ከአጥቢያ ጀምሮ አብያተ ክርስቲያንና መስጊዶች ባሉበት አካባቢ የሚገኙ ምእመናን ተሰብስበው ‹‹እንዴት ነው ሁሌ
ከምንቧቀስ፣ ከምንጋጭ በጋራ በሚያገናኝን ጉዳይ ላይ የማንነጋገረው? የሚያስማማን ኹኔታ የማንፈጥረው?›› የሚለውን
ጥያቄ በማንሣት መወያየት ይኖርባቸዋል፡፡ የምንለያይበት ነገር ቢኖርም የጋራችን በኾነው ጉዳይ መነጋገር፣
የተለያየንበትን በየራሳችን አስቀምጠን ጊዜ የሚፈጅ ቢኾንም የፈጀውን ያህል ጊዜ ፈጅቶ ይሄን፣ ይሄን፣ ይሄን እያልን
ወደላይ መድረስ አለብን፡፡
በእኛ በኢትዮጵያውያን ጠባይ ምንም ነገር ቢኾን ሊሠምር የሚችለው ከላይ ወደታች ሲኾን ነው፡፡ እምነት ከታች
ወደላይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ያለጳጳስ ኖረው ያውቃሉ፡፡ ያለምእመናኑ ግን ጳጳሳቱ ኖረው
አያውቁም፡፡ ስለዚህ ወሳኞቹ ምእመናን ናቸው፡፡ ያለእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ብዙ ሙስሊሞች ኖረዋል፡፡
የእስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት የተቋቋመው በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ብዙ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡
ሙስሊሞች ባልነበሩበት ዘመን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ኖሮ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ወሳኞቹ ሙስሊሞቹ ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት የእምነቱ ነገር ከታች ወደላይ እንጂ ከላይ ወደታች ኾኖ አይኾንም፡፡ በቃ አይኾንም! የኢትዮጵያ
እምነት ጠባዩ እርሱ አይደለም፡፡ ይህን ጠባይ እኛ እንሻገረው ብንል ብሎኑ ጭራሽ አይገጥምም፡፡ የሚመጣው ስድስት
ቁጥር ብሎን ነው፤ ማስገባት የሚፈለገው ግን አራት ቁጥር ብሎን ነው፡፡ ና ግባ፤ ቢባል እሺ አይልም፡፡ ስለዚህ ምን
ይደረጋል. . . ልኬቱ መመጠን አለበት፡፡ ቀዳዳውን ላስፋው ሲሉ ግን ግጭቱ ይፈጠራል፡፡
ዕንቊ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› አለ ትላለኽ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እኔ ከመቻቻል ያለፈ መገንዘብ ነበረ እላለኹ፡፡ ‹‹መቻቻል›› የሚለውን
አልቀበለውም፡፡ ለምን? መቻል ውስጥ እህህ አለበት፡፡ አሁን ባልና ሚስትን ብዙ ጊዜ ስናስታርቅ ‹‹እኔኮ ችዬው ነው
የኖርኩት›› ብለው ሲሉ ተስማምቶኝ ነው ማለታቸው አይደለም፡፡ ምን ይደረግ ብዬ፤ ልጅ ለማሳደግ ብዬ፤ ችዬው፣
ተሸክሜው እያሉ ነው የተበደሉት ሚስቶች፡፡ አንደኛው ተሸካሚ ኾኖ እህህ…ብሎ የመቻል ነው፡፡ ጭነት የበዛበት ነው፡፡
የማይፈለግ ነገር ያለበት ነው፡፡ ቻለው ተብለህ የምትኖረው ኑሮ ማለት ነው፡፡ መገንዘብ ማለት ግን አንዱ የሌላውን
ችግር፣ ብርታት ተገንዝቦ በዚያ ውስጥ መኖር ማለት ነው፡፡
ዕንቊ፡- ይኼ የምትለው መገናዘብስ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሕዝብ ዘንድ አለ፡፡ አሁን አለና የለምን በቃላት ደረጃ
ስናገረው ተግባራዊ መመዘኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የእስልምና እምነት፣ ምን ያህልስ የክርስትና እምነት
ተከታዮች አሉ ብለን ስንጠይቅ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሁለት እምነት ተከታዮች ቁጥር ከኢትዮጵያ
ሕዝብ አብላጫው ነው፡፡ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ ይኸው መገናዘብ አለ፡፡ በርግጥ በጥቂቶች ዘንድ ላይኖር
ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድን ሙስሊም ‹‹እንኳን ለመውሊድ በዓል አደረሰኽ›› ስትለው ተገንዝበኸዋል ማለት ነው፡፡
በዚያ በዓል ላይ ተስማምተኸ ላይኾን ይችላል፡፡ እንደውም ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ ብዙኀን መገናኛዎች ለሙስሊሞች
‹‹እንኳን ለዒድ አል አረፋ በዓል አደረሳችኹ››፤ ለክርስቲያኖች ‹‹እንኳን ለጥምቀት በዓል አደረሳችኹ›› ሲሉ
ይደመጣሉ፡፡ ግን ለምንድን ነው እንዲህ የሚሉት? እኔ በኢትዮጵያዊነቴ የሙስሊም ወገኔን በዓል ገዝቼዋለኹ፡፡
ሙስሊሙም የእኔን በዓል ገዝቶታል፡፡ እርሱም በእኔ እምነት እድናለኹ፤ እኔም በእርሱ እምነት እድናለኹ፤ አላልንም
እንጂ በባህላችን አንዳችን የሌላችንን በዓል ገንዘብ አድርገነዋል፡፡
ስለዚህ በብዙኀን መገናኛ በኩል መባል የሚኖርበት ‹‹ለኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለዒድ አል አረፋ፤ እንኳን
ለብርሃነ ጥምቀቱ በዓል አደረሳችኁ›› ነው፡፡ ሚዲያው ይለየናል? እኛ ያልተያየነውን ለምን የኢትዮጵያ ሬዲዮና
ቴሌቪዥን ድርጅት የሚለያየን እላለኹ፡፡ ብዙውን ጊዜ እኔ ጓደኛዬን ‹‹እንኳን አደረሰን›› ነው የምለው፡፡ ለምሳሌ
እርሱ የመውሊድን በዓል ሲያከብር የሚያገኘው ሃይማኖታዊ በረከት እንዳለ አስቦ ነው፤ ልክ እኔ ጥምቀት በማከብርበት
ጊዜ እንደማደርገው፤ ግን እርሱን እንኳን አደረሰኽ ስለው እርሱ በዓሉን ሰላማዊ ኾኖ፣ ነጻ ኾኖ፣ ደስ ብሎት
የሚያከበርበትን ከባቢያዊ ኹኔታ መፍጠር ግዴታዬ ነው፡፡
ዕንቊ፡- ‹‹እንኳን አደረሰኽ›› እና ‹‹እንኳን አደረሰን›› በሚለው መሐል ልዩነት አለ እያልኽ ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ስንኾን አዎ፣ ልዩነት አለው፡፡ ለምን? እኔም አስተዋፅኦ
አድርጌአለኹ፡፡ ሙስሊሙ ሃይማኖታዊ በዓሉን ደስ ብሎት፣ ነጻ ኾኖ እንዲያከብር፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔም
የጥምቀት በዓሌን ደስ ብሎኝ በሰላማዊ ኹኔታ ለማክበሬ የሙስሊሙ አስተዋፅኦ አለበት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን
‹‹እንኳን ለመውሊድ፣ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን፤ አደረሳችኁ›› ማለት ወይም መባባል ነው ያለብን፡፡
የሁላችንም አስተዋፅኦ ያለበት ነገር እኮ ነው፡፡
እስኪ ፈጣሪ ያሳይኽ. . .ለጥምቀት፣ ለፋሲካ. . .ቀን በግ ይዞ የሚመጣውን ሰው ሙስሊም ይኹን ክርስቲያን
በምን ታውቀዋለኽ? ለይተኽ የምታውቅበት ልዩ ዘዴ አለኽ እንዴ? እርሱ ይዞ ባይመጣ አንተ ከየት ነበር የምታገኘው?
ይህ ሰው እኮ ለፋሲካ ይህን ነገር ማድረስ አለብኝ ብሎ ከሠራ ትልቅ ተግባር ነው ያከናወነው፡፡ እና የእነዚህ
ወገኖቻችን አስተዋፅኦ በእኛ በዓል አከባበር ላይ አለበት፡፡ ለምን ታድያ የሥራውን ቀን ዝግ እናደርጋለን?
የማይገባኝ ነገር እርሱ ነው፡፡ ጥምቀት ዕለት ሙስሊም ወገናችን ለምን ሥራ እንዲገባ አይደረግም? የመውሊድ ዕለትስ
እኛ ሥራ እንዳንገባ የሚደረገው ለምንድን ነው? መገናዘቡ የለም ከተባለ፣ አንዱ ለሌላኛው ያበረከተው አስተዋፅኦ
የለም አልነበረም የሚባል ከኾነ ሥራው ሲዘጋ በከፊል ነው መዘጋት የሚኖርበት፡፡ የመውሊድ በዓል ሲኾን ሙስሊም
የኾናችኹ ወደ ሥራ አትምጡ፤ የስቅለት ዕለት ሲኾን ደግሞ ክርስቲያን የኾናችኹ ወደ ሥራ አትግቡ፤ ሌሎቻችኹ ግን ወደ
ሥራ መግባት አለባችኹ መባል ነበረበት፤ በዓሉ የእነርሱና የእኛ ብቻ ከኾነ፤ ግን የሁላችንም ነው፡፡ በሕግ ደረጃ
ብሔራዊ በዓል ነው ተብሎ ከተደነገገ በኋላ በሚዲያ በኩል ልዩነቱ ለምን ይመጣል? ይሄ ነው በተግባር መልስ ማግኘት
ያለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሥር ኾነን ያዳበርነው ከወደላይ ትልቅ ችግር ይፈጠርበታል፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኹት
በኢትዮጵያ ውስጥ እምነት ከታች ወደላይ ነው፡፡ ታች ያለው ያለበላዩ መኖር ይችላል፡፡ በስተላይ ያለው ግን ያለበታቹ
መኖር አይችልም፡፡
ቤተ ክህነት መኖሯን ሳያውቁ የሚኖሩ ብዙ ምእመናን አሉ፡፡ ጋምቤላ፣ ጎጃም፣ አሶሳ ጠረፍ ሄደኽ፣ ጎንደር ገጠር
ወርደኽ. . .ፓትርያርኩ ማን ናቸው? ብለኽ ጠይቅ፤ የት ያውቃል! የእስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢ ማን ናቸው? ብትለው
እስኪ የት ያውቅልኻል! እግዚአብሔርን፣ የአጥቢያውን ታቦት፣ ቃዲውን ነው የሚያውቀው፡፡ ወይም ደግሞ በሰፈሩ
ያለውን ዑሏማ ‹‹አሏህ ወ አክበር›› የሚያሰኘውን ሰው ነው የሚያውቀው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋራ፣ ከአላህ ጋራ
የሚያገናኘው ያ በቅርቡ ያሉት የሃይማኖቱ ተጠሪ ናቸው፡፡ እርሱ ካለለት በቂ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ያለው ትርፍ
ነው፡፡ እኔ ታች ያሉት ከተግባቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ችግር የለም ባይ ነኝ፤ የሃይማኖት መሠረቶች እነርሱ
ናቸውና፡፡ ሌላው ዓለም ስንሄድ ከላይ ወደታች ነው፡፡ ለዚህም ነው ለኢትዮጵያውያን በሃይማኖታቸው ጸንተው መኖር
እምነቱ ከታች መኾኑ ዋነኛው መሠረት ነው፡፡
ዕንቊ፡- እምነቱ ከላይ ወደታች ቢኾን ምን ችግር ይገጥመዋል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ግብጽ ስንት ጊዜ ጳጳስ ስታስቀር ምን ይውጠን ነበር? በዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ፣ በዚህ
ሁሉ ክርክር በንጉሡም በደርግ ዘመንም እንይ፤ አሁንም እንመልከት፡፡ ስለ እምነት ተቋማት የተለያየ አመለካከት ነው
የነበረው፤ ያለውም፡፡ በየዘመኑ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ከመንግሥት ጋራ ናቸው አይደሉም የሚለው ክርክር አለ፡፡
ይህ ክርክር ግን ታች ያለውን ሰው አይነካውም፡፡ ጥፍጣፊው አይደርስበትም፡፡ ለምን? ብለን ስንል ጉዳዩ ከላይ
ነው፡፡ እርሱ ከታች አንድ የንስሐ አባት፣ አንድ ቁርዓን የሚያስቀራው ካለ በቂው ነው፡፡ ታቦቱ አጠገቡ ካለ እዚያው
ሄዶ ያስቀድሳል፤ ክርስትና ያሥነሳል፤ ሲሞት እዚያው ይቀበራል፡፡ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ የምለው መገናዘብ፣
መግባባት ይህን ነው፡፡
ዕንቊ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ህልውና ለመጠበቅ፣ ዕሴቶቿን በነበረበት
ለማቆየት የሚደረገውን መንፈሳዊ ትግል ወይም ይህን የመሰለውን ተነሣሽነትና መንፈሳዊ አስተምህሮ እንደ አክራሪነት
ተግባር የሚመለከቱትን ለመከላከል ምን መደረግ ይኖርበታል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አንደኛ፡- መገንዘብ አለባቸው! በደንብ ስለማውቀው ክርስትና ልናገር፡፡ ክርስትና የሚጠይቅኽ አንተ አምነኽ፣ ተጠምቀኽ ብቻ እንድትኖር አይደለም፡፡ ይሁዳ በመልእክቱ ቁጥር ሦስት ላይ ‹‹ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እመክራችኋለኹ›› ነው ያለው፡፡ እንድትጋሉ እንጂ አምናችኹ፣ ተጠምቃችኹ እንድትቀመጡ አላለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት ላይ ‹‹ሩጫዬን ፈጽሜአለኹ፤ ሃይማኖቴን ጠብቄአለኹ፤ መልካሙን ገድል ተጋድዬአለኹ››
ብሏል፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት መጠበቅ አንድ ነገር ነው፡፡ ብዙ ሰው እንደሚለው ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም፡፡
መልካሙን ገድል መጋደል ደግሞ ይኖርብናል፡፡ ያ መልካሙ ገድልም ደግሞ ከሦስት አካላት ጋራ የሚደረግ ነው፡፡ አንደኛ፡-
ከራስ ጠባይዕ ጋራ፣ ሁለተኛ፡- ከሰይጣን ጋራ፣ ሦስተኛ፡- ከተለያዩ አካላት ማለትም ሃይማኖትኽን፣ ቤተ
ክርስቲያንኽን ወይም እምነትኽን ለማፍረስ ከተነሡ ወገኖች ጋራ፣ ከመናፍቃን፣ ከከሐድያን፣ ከአላውያንና ከሌሎች
አካላት ጋራ የምታደርገው ተጋድሎ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- መናፍቃን ከውስጥ የሚወጡ ናቸው፡፡ አላውያን የምንላቸው ኃይልና ሥልጣን ተጠቅመው የሚመጡ
ሲኾኑ ከሐድያን ደግሞ ወጥተው የሚሄዱ ናቸው፡፡ መልካሙ ገድል የሚባለውም ከእኒህ ጋራ የሚደረግ ተጋድሎ ነው፡፡
ይሄ ከሌለ ተጋድሎ አለ ሊባል አይችልም፡፡ ስለኾነም በክርስትና የመጋደል ግዴታ አለ፡፡ ስለዚህ የክርስትና ተጋድሎ
በሚሰጠው ግዴታ ውስጥ አንድ ክርስቲያን አንዱን የተጋድሎ ዐይነት መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ‹‹ቀኝኽን ለሚመታኽ ግራኽን
ስጥ›› የሚል ክርስትናን የምንከተል በመኾናችን እስከ አሁን አባቶቻችን ሞተዋል እንጂ አልገደሉም፡፡
ሃይማኖትን የመጠበቅና የመጋደል ግዴታ በክርስትና አለ፡፡ በዚህ መሠረት የሚጋደሉትን አክራሪ የሚሉ
ሰዎች ካሉ ያልተገነዘቡት ነገር አለ፡፡ አክራሪነት ይሄ ከኾነ በክርስትና አክራሪነት የሚጀምረው በቅዱስ ጴጥሮስ
ዘመን ከነበሩት ሐዋርያት ነው ማለት ነው፡፡ እነዚያ ሁሉ አክራሪዎች ከኾኑ የምናወራው ስለ ክርስትና ነው ማለት
ነው? ስለዚህ ስም በሌላው ላይ ከመለጠፋቸው በፊት ማወቅ፣ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የሚሰነዘሩ ሐሳቦች ምንጫቸው መታየት አለበት፡፡ ለምንድን ነው ያ ሰው እንደዚያ ያለ ሐሳብ ያቀረበው፤ በምን ፍላጎት ላይ ተመርቶ ነው የሚለው መጤን ይኖርበታል፡፡
ከዚህ በፊት መንግሥት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚል ትልቅ አጀንዳ አንሥቶ በነበረ ጊዜ የኾኑ አካላት ተነሥተው
‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ኪራይ ሰብሳቢ ነው›› ብለዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ አካላት ነገ ሌላ ስም ቢመጣ የመጣውን ስም
ከማለት አይመለሱም፡፡
ዕንቊ፡- ማኅበረ ቅዱሳን እንደዚህ ዐይነቱን ነገር ለመከላከል ምን ማድረግ አለበት?
ዲ/ን ዳንኤል፡- የተለየ ነገር ማድረግ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ እያደረገ ያለውን መቀጠል ነው፤
ምክንያቱም ለሚነሣው ሁሉ መልስ በመስጠት ራስን ከሠራተኛነት ወደ ተዋጊነት መለወጥ አያስፈልግም፤ እውነት ነውና
የሚያሸንፈው፡፡ በአገራችን ይትበሃል ‹‹ቂጣም ከኾነ ይጠፋል፤ ሽልም ከኾነ ይገፋል›› እንደሚባለው በተያዘው ሐቅ
መቀጠል ነው፡፡ አንድ ሰው እርግዝና መኾኑን ባወቀው ጉዳይ ‹‹አይ ይሄ ቦርጭ ነው›› ላሉት ሰዎች ሁሉ ለማስረዳት
በመድከም ጨጓራውን መላጥ የለበትም፡፡ ሲወለድ ይታወቃል፤ ያኔ ይደርሳል፡፡
በበኩሌ አንድ የተባለ ነገር ብቻ ዐውቃለኹ፡፡ በዓለም ላይ ተከሥቶ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን አላደረገውም›› የተባለውን ነገር፡፡ የመስከረም 11ዱን የአሸባሪዎች ተግባር ማኅበረ ቅዱሳን አደረገው አልተባለም፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት ነገሮች ግን ተመልክተውታል፡፡ እናም
ክፉ ነገር ሲመጣ መለጠፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ግን የሚመለከታቸው አካላት ጊዜ ሰጥቶ፣
መዛግብቱን ይዞ ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ እንደውም ማኅበሩ አንድ የሚጎድለው ነገር ቢኖር ማስረዳት ነው፡፡ መልስ
መስጠት እንጂ ቀድሞ የማስረዳት ነገር ውስጥ ብርቱ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቀድሞ ጉዳዮቹን የማስረዳት፣ የመንገር
ሓላፊነት አለበት፡፡ የሚያስረዳውም ሰዎች እንዲገባቸው ብቻ አይደለም፡፡ መረዳት፣ አለመረዳት ግን የእነዚያ አካላት
ድርሻ ነው፡፡
ዕንቊ፡- በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ወንጃይ ጣቶች የሚቀሰሩት ለምንድን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖታዊ ዕሴቷ በተጨማሪ ለብዙ ዘመናት ሁለት ለአገሪቱ የሚጠቅሙ ዕሴቶችን ይዛ የኖረች ነች፡፡
አንደኛ፡- የኢትዮጵያዊነት ዕሴት ማለትም አገርን የመውደድ፣ አገርን ከአጥቂዎች
የመከላከል፣ የአገር ፍቅር ስሜት በደም ሥር እንዲዘዋወር የሚያደርግ፣ ለአገር የመሞት ዕሴትን የያዘች ነች፡፡ ይሄ
በግልጽ ይታያል፡፡ በተለያየ ዘመን የመጡ የአገሪቱ ጠላቶች መጀመሪያ ማፍረስ የሚፈልጉት ይህችን ቤተ ክርስቲያን
ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም አገሪቱ በጠላቶቿ ስትወረር ከግንባር ቀድማ የምትደርሰው ይህች ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡
ለምን? ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን አገራዊ አደራንም የተረከበች ቤተ ክርስቲያን በመኾኗ፡፡
ሁለተኛ፡- የአገር፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የእምነት፣ የቅርስ ባለአደራ ናት፡፡ ቤተ
ክርስቲያኒቱን ያቃጠለውና ብዙ ምእመን የፈጀው የግራኝ መሐመድ ካባ የሚገኘው በመርጡለ ማርያም ቤተ ክርስቲያን
ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያንን ካባ ያስቀመጠችው እርሱን በመሳምና በመሳለም በረከት ይገኛል ብላ እንዳልኾነ
ይታወቃል፤ ግን የአገር ታሪክ ነው፡፡ የብዙ ነገሥታት፣ የአያሌ መኳንንት፣ የሚወዷትና የሚጠሏት ሰዎች ቅርስ ያለው
በቤተ ክርስቲያኗ ነው፡፡ ባለአደራ ስለኾነች፣ እርሷን የሚመለከቱም የማይመለከቱም መጻሕፍት ይገኙባታል፡፡ በጭራሽ
ከእርሷ ጋራ የማይሄዱ የእነአርስቶትል፣ የእነሶቅራጥስ የእነፕሌቶ መጽሐፎች ሁሉ አሉ፡፡ ይህችን አገር የማድከም
ፍላጎት ያለው፣ በዓለም ላይ አንገቷን ቀና አድርጋና ከፍ ብላ እንድትሄድ የማይፈልግ ማንኛውም ኃይል መጀመሪያ
መምታት ያለበት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ምክንያቱም አገሪቱን አገር የሚያሰኟት ሁለት ትልልቅ ዕሴቶች ውስጧ
ያሉ በመኾኑ፡፡
በብዙ ዓለም አገሮች ዞሬአለኹ፡፡ በኢትዮጵያ የሚደሰቱ አላየኹም፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ በእኛው አገር ውስጥ
አንድ የውጭ ማኅበረሰብ ት/ቤት አለ፡፡ ይህ ት/ቤት ከውጭ በሚመጣ የትምህርት ቁሳቁስ እየተረዳ የትምህርት
ሥርዐቱን የሚያስኬድ ነው፡፡ በታሪክ ማስተማርያ መጽሐፉ ላይ(አንድ ተማሪ አምጥቶ እንዳሳየኝ) ስለ አፍሪካ
በሚገልጸው ክፍል ‹‹ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ቅኝ አልተገዙም›› ይልና ምክንያቱን ሲያብራራ ‹‹ላይቤሪያ በአሜሪካ የበላይ ጠባቂነት ሥር ስለነበረች ሲኾን ኢትዮጵያ ደግሞ መሬቷ አስቸጋሪ ስለኾነ ነው›› ይላል፡፡ አየኽ! ያን ሁሉ ከዐድዋ የተጀመረ የፀረ ቅኝ አገዛዝ መሥዋዕትነት ድምጥማጡን አጥፍተውታል፡፡
ይህን የሚለው የትልቋ አገር የአሜሪካ የታሪክ ማስተማርያ መጽሐፍ ነው፡፡ እነርሱ ሳያውቁት ቀርተው ነው ማለት
ይቻላል፡፡ ኾን ብለው ኢትዮጵያን የማንኳሰስ ዘመቻ ግን በብዙ ቦታ ይታያል፡፡ የቀደመውን ተወው፤ ሰሞኑን የኾነውንና
የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ ያስቆጠረውን ጉዳይ በምሳሌ ላምጣልኽ፡፡ ኃይሌና ቀነኒሳ ከሞ ፋራኅ ጋራ ያደረጉትን ልዩ
ውድድር አስታውሱ፡፡ ቢቢሲ ይህን ውድድር ምን ብሎ ዘገበ…‹‹ሞ ፋራኅ ተሸነፈ›› አለ፡፡ እንዲህ ያለው ቀነኒሳ
አሸነፈ ላለማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሚገርመው ራሱ ቢቢሲ ‹‹የኬንያው አትሌት ቀነኒሳ አሸነፈ›› አለ፡፡
ይህ ትልቅና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያለው የዜና ማሰራጫ ተቋም እንዴት ነው ቀነኒሳን ኬንያዊ የሚያደርገው?
‹‹ኢትዮጵያዊ›› የሚለው መጠሪያ፣ መለያ እንዴት ሊጠፋው ቻለ? ከዚህ ጀምሮ ስታይ ይህችን አገር ኾን ብሎ የማዳከም
ነገር እንዳለ በብዙ መንገዶች እንዳለ ትገነዘባለኽ፡፡
እኔ ከፍተኛ ድጋፍ የምሰጠው ‹‹ይህችን አገር በምንም በምንም ብለን በኢኮኖሚውም ይኹን በሌላው ራሷን የቻለች
አገር ማድረግ አለብን›› የሚለውን የዚህን መንግሥት አቋም ነው፡፡ ከሕዳሴው ግድብ ጀምሮ ያለውን ነገር ሁሉ
የማንንም ድጋፍ ሳንጠይቅ መሥራት አለብን የሚለው ይስማማኛል፡፡ ለምን? ማንም በጎአችንን አይፈልግም፡፡ የትም
ስለኢትዮጵያ ተብሎ የሚሰጠውን ትምህርት እንመልከት፤ በሁለት የአውሮፓ አገሮች የታሪክ ማስተማርያ መጻሕፍት
አይቻለኹ፡፡ ስለአፍሪካ የሚገልጸው ንኡስ ክፍል ‹‹ግብጽ›› ይልና ‹‹መርዌ›› ይመጣል፡፡ በጭራሽ ስለ አክሱም
ማውራት አይፈልግም፡፡ ለምን? ምን አደረገች? የኾነ ነው፡፡ የሐቅ ጥያቄ ነው፡፡ የምርጫ ጥያቄ አይደለም፡፡
ዕንቊ፡- እንደ ጀርመን የግዕዝን ቋንቋ በትምህርት ሥርዐታቸው ውስጥ ያስገቡትስ አገሮች?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እርሱ በጣም ጥቂት በኾኑ በጎ አድራጊዎች የኾነ ነው፡፡ እንደዚያም ቢኾን ያ
የተደረገበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ለእኛ ተብሎ የተደረገ አይደለም፡፡ ከዚህ የሚሄድና የሄደ ስንት ጥበብ አለ፤
ነበር፡፡ ግእዙ የሄደውና የሚሄደው ጥበብን የመፍቻ ቁልፍ ስለኾነ ነው፡፡ እንደ ‹‹ባየር›› ያሉ የመድኃኒት
ፋብሪካዎች ከየት ተነሥተው የመድኃኒት ማምረቱን ሥራ አሐዱ እንዳሉት፣ ምንን ወስደው አስተርጉመው እንደጀመሩት
ይታወቃል፡፡ ያ ለራስ ጥቅም ሲባል የተደረገ ነው፡፡ የዚህችን አገር የዕድገትና የብልጽና ከፍታ የሚያመጣ
አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያመጣ ነገር ሲሞከር ግን፣ አገራችን ስትመታ ነው የሚታየው፡፡ ኢትዮጵያ በኢጣልያ
ስትወረር ማን አብሯት ነበር? በወቅቱ የነበረው እውነት ጠፍቷቸው ነው? አይደለም፡፡ እና ይህችን ቤተ ክርስቲያን
ከዚህች አገር ጋራ የማየት ጉዳይ ስላለ ምንጊዜም ቢኾን ሰበብ ፈጥረው መምታት ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በውጭዎቹ ብቻ
የሚፈጸም አይደለም፤ ወኪሎችም አሏቸው፡፡ ትግሉ ከሁለቱ ጋራ ነው የሚኾነው፡፡ ዓላማቸው መበተን ሳይኾን ይህችን
ቤተ ክርስቲያን ማጥፋት ነው፡፡ ይህን ካልቻሉ ማደንበሽ!
ዕንቊ፡- በኢትዮጵያ ያለው የፖሊቲካ ነው የሃይማኖት አክራሪነት?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እኔ የሁለቱም አለ ብዬ አምናለኹ፡፡ የእምነት አለ፡፡ የፖሊቲካ እንኳ ባንል
የአስተሳሰብ አክራሪነት ይኖራል፡፡ በእኛ አገር የተለመደው የፓርቲ ፖሊቲካ ነው፡፡ አንዱም ትልቅ ችግር እርሱ
ነው፡፡ ይህ ስላለ ‹‹እገሌ እንደዚህ ነው›› ሲባል ‹‹እገሌ መአሕድ ነው››፣ ‹‹እገሌ እንደዚህ ብሏል›› ሲባል
‹‹ኢሕአዴግ ነው፤ ቅንጅት ነው›› ይባላል፡፡ ለስላሳ ወይም ቢራ ይመስል የኾነ ሣጥን ውስጥ ካልገባኽ ብቻኽን
አስተሳሰብኽን ሊመዝነው ወይም ሊያደምጠው አይፈልግም፡፡
በነገራችን ላይ እንዲህ ዐይነቱ ጠባይዕ ከባህላችንም የመጣ ነው፡፡ በገበያው ላይ ያታያል፡፡ የኾነ ነገር
ለመግዛት ስትጠይቅ ‹‹በደርዘን ካልኾነ፣ ከነሣጥኑ ካልወሰድኽ፤ የጠርሙስ ማስያዣ ካላመጣኽ ወይም ይህን ያህል
ክፈል›› ይልኻል፡፡ ነጥሎ ማየት አይወደድም፡፡ ጠቅልሎ የማየት በሽታ አለብን፡፡ ስለዚህ ከመኖር የመጣ የአክራሪነት
አመለካከት አለ፡፡ አክራሪ ሰዎችም አሉ፡፡ ከጠቅላላው ማኅበረሰብ አንጻር ሲታዩ ግን ኢምንት ናቸው፡፡ ኾኖም
አንዳንዴ የማኅበረሰቡን ሐሳብ የማግኘት ዕድል ያላቸው ሲኾኑ፣ ይህንንም ዕድል የምናመቻችላቸው እኛው ነን፡፡ ሰዎቹ
አቅም ኖሯቸው አይደለም፡፡ በማንኛውም ሰዓት በአቅራቢያው ጉንፋን አማጭ ቫይረስ ሊኖር ይችላል…ያ ሰው ሲደክም፣
በጉዞ ወይም በከባድ የሥራ ጫና ሊኾን ይችላል በዚያን ጊዜ እርሱ በሽታ ኾኖ ይመጣል፡፡ የሰውዬው መድከም ነው
ለበሽታው መከሠት አስተዋፅኦ ያደረገው፡፡ ሰውዬው ጠንካራ ከኾነ ግን በአካባቢው የፈለገው ነገር ቢኖር ምንም
ሊያደርገው አይችልም፡፡ የአክራሪነትን ጉዳይ የማየው እንደዚህ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ አመኔታ ያለው ሕዝብ ተቋም የለም፤ ጠንካራ እምነቶች ግን አሉ፡፡
ጠንካራ የእምነት ተቋምና አስተዳደራዊ ኹኔታዎች የሉም፤ አንዱ ትልቁ ችግር ይህ ነው፡፡ ተአማኒነት ያለው ተቋም
አለመኖር፡፡ ቤተ ክህነቱንም የእስልምና ጉዳዮችንም ፕሮቴስታንቱንም በምሳሌነት ብንወስድ ምእመናኑ በፍርሃት በጥርጣሬ
የሚያዩት እንጂ የሚወዱት የሃይማኖት ተቋም የለም፡፡ ከምእመናኑ ጋራ በጣም ተቀራርቦ የሚሠራ የሃይማኖት ተቋም
አይታይም፤ ምክንያቱም በዚህች አገር ላይ ብዙዎቹ ምእመናን ናቸው፡፡ ጳጳሳቱ ኀምሳ ያህል ናቸው፡፡ ካህናቱ ተሰፍረው
ወይም ተቆጥረው የሚደረስባቸው ናቸው፡፡ ሕዝቡ ግን ብዙ ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች በሚገባ፣ በታማኝነት፣
ከሙስና፣ ከዘረኝነት፣ ከፖሊቲካ አቋም የጸዳና ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ጠንካራ የሃይማኖት ተቋም ቢኖር ኖሮ አሁን
አሉ የምንላቸውን የአክራሪነት ዝንባሌዎች በጣም እንቀንሳቸው ነበር፡፡ ይህ ባለመኖሩ ከሃይማኖት ተቋሙ
የሚነሣውን የአስተዳደር ችግር በሙሉ ሰውን የመገፋት፣ የመጨቆንና አደጋ ውስጥ የመግባት ስሜት እንዲያድርበት
አድርጎታል፡፡ ይህ ለእነማን ዕድል ይሰጣል? የአክራሪነት ስሜት ላላቸው አካሎች ነው፡፡
ስለዚህ ትልቁ ነገር፣ የእምነት ተቋማት ተጠያቂነት፣ ግልጽነት ባለበት ኹኔታ በየራሳቸው ሃይማኖት
ሥርዐት መሠረት የሚኾንና በሌላ የማይቀየር፣ የእምነቱን ታሪክ መነሻ ያደረገ፣ ግን ለማንኛውም ሰው ግልጽ የኾነ
ራሳቸውን በራሳቸው ማረምና ማስተካከል የሚያስችላቸውን አሠራር መዘርጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ዛሬ ስለእምነት ተቋማት
ጉዳይ ተነሥቶ ጨዋታ ሲጀመር ምእመናኑ÷ ስለሙስና፣ ስለገንዘብ፣ እገሌ በዘመድ ተሾመ፣ እገሌ ገንዘብ ተቀበለ፣ እገሌ
የእነ እገሌ ወገን ነው የሚለውን ነው አብዝተው የሚናገሩት፡፡ እና ነገሩ ይጽዳ፤ ይወገድ ከተባለ ከዚህ ነው
መጀመር የሚኖርበት፡፡
http://haratewahido.wordpress.com
የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
ReplyDeleteእነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.