Thursday, September 19, 2013

ሰዶ ማሳደድ- በዲሲ ጎዳና (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

ዲሲ ከሚገኝ የሃበሻ መንደር ምሳ ቀምሰን ስንወጣ ከፊት ለፊቴ አንድ አእምሮው እንደተነካ የሚያስታውቅ ሃበሻ ጮክ ብሎ ሲናገር አስተዋልኩ። ሰውነቱ ወፍራም ሲሆን፣ ለአእምሮው የሚወሰደው ኪኒን በሰውነቱ ላይ ውፍረት ሳያስከትል እንዳልቀረ ነው። አሜሪካ ከመጣ 10 አመት አልፎታል፤ በዲሲ መታየት ከጀመረ ቅርብ አመት ቢሆንም በርካታ ሃበሾች በሁለት ነገሮች ጠንቅቀው ያውቁታል። ይኸውም፥ በየቀኑ የዲሲ ጎዳናዎችን ሲያካልል የሚናገራቸው ቃላቶች « ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ይውደም፤ ይጥፋ..» የሚልና ሌላው ደግሞ ሰብሰብ ብሎ ያያቸውን ሃበሾች « እናንተ የፈረንጅ አሽከሮች፤ አገራችሁ እየተዋረደች፣ ዜጎቿ እየተራቡና እየተሰቃዩ፥ እናንተ የነጭ አሽከር ሆናችሁ ታገለግላላችሁ፤ ውርደታሞች..» እያለ በመናገር ይታወቃል።…. በመኪና መተላለፊያ ዋና መንገድ ውስጥ ገብቶ « ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ይውደም፤ ..» እያለ ሲናገር፣ አንድ ቦርጩን ያንዘረጠጠና እድሜው በሃምሳዎቹ የሚገመት ሃበሻ ወደ አእምሮው በሽተኛ ተጠግቶ « አንተ ራስህ ጥፋ፤ ትርፍራፊ ለቃቃሚ» ብሎ ጮሆ ሲናገረው አደመጥኩ። አእምሮ በሽተኛው ቱግ ብሎ « ማነው ትርፍራፊ ለቃሚ?..» እያለ ማንባረቁን ቀጠለ። ..ሰውዬው የገዢው ፓርቲ ደጋፊ አሊያም አባል እንደሆነ አልተጠራጠርኩም፤ ጠጋ ብዬ ጥያቄ ሰነዘርኩለት ፥ « ይህ ወገን የአእምሮ በሽተኛ ነው፤ ለምን ትናገረዋለህ?..» አልኩት፤ ፊቱን አጨማዶ፥ « ለምን እርሱ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግን ይሳደባል?..ይጥፋ ይላል?…» ሲለኝ በጣም አስገረመኝ፤ « ትሰማለህ…ይህ አሜሪካ ነው!! ኦባማ የሚብጠለጠልባት አገር ናት። አገር ቤት በነእስክንድር፤ ርእዮት፣ አቡበክር፤ አንዱአለም…አትናገሩ ተብለው የሚፈፀምባቸው አፈናና የእስር ስቃይ አልበቃ ብሎ…እዚህ በነፃነት አገር ፓርቲዬ ተሰደበ ትላለህ?..አሜሪካ ምግብ የሚደፋባት አገር ናት፤ ትርፍራፊ የሚለቅም የለም፤ ትርፍራፊ ያለው ሕሊና ሸጠው በሚያድሩበት መንደር ነው፤..» ንግግሬን አላስጨረሰኝም…እየገላመጠኝ ሄደ።….የአእምሮ በሽተኛ ወገኔ ጮክ ብሎ መለፍለፉን ቀጥሏል። ..እንዴት ነው ነገሩ!?…በገዛ አገራችን ነፃነት ተነፍገን ተሰደድን። ያሰደዱን ሰዎች መልሰው በስደት አገር እንዲህ ሲፈነጩ ማየት አያበግንም?….ወገኖቼ ምን ትላላችሁ?..
( የአእምሮ በሽተኛ ወገኔ ገፅታውን የቆረጥኩት ምንአልባት ቤተሰቡ ያለበትን ሁኔታ ላያውቅ ይችላል ከሚል ነው። ..)
 
https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/09/19/09-3/

No comments:

Post a Comment