Wednesday, September 11, 2013

ለሁሉም ምቹ ግን ጥቂቶች የሚኖሯት እውነት!



 ለሁሉም ምቹ ግን ጥቂቶች የሚኖሯት እውነት!

ለራስ ያልቀደመ ስለሌላው መኖር፣

ላጡት ተስፋ መሆን ለሌላው መቸገር፣

የዚች ፍልስፍና የዚች ጥበብ አገር፣

ምንጯ ከየት ይሆን ሥረ መሠረቷ፣

የፍቅር መኖሪያዋ የቅንነት ቤቷ፡፡

ለማገዝ የመሻት የሌላውን ሸክም፣

ስለሌላው መኖር ስለሌላው መድከም፣

ለሌላው መጨነቅ ለሌላው መታመም፣

የዚች ፍልስፍና የዚች ልዩ ጥበብ የዚች ልዩ ሚስጢር፣

የት ይሆን ቀዬዋ ያለችበት መንደር፡፡

ስስትን የማታውቅ ሞልቶ የተረፋት፣

በረከቷ የማይነጥፍ ሰጥታ የማያልቅባት፣

የክፋት መቃብር በቀሏ ምኅረት፣

እውን የምትታይ ያለፈጠራት ምናብ፣

የአእምሮ ምቾት/ሠላም የሕሊና ምግብ

የሐሴት አፍላጋት የሚመነጩባት ይቺ ልዩ ጥበብ፣

አገሯ ወዴት ነው ሥረ መሠረቷ፣

የከተመችበት የመኖሪያ ቤቷ፡፡

. ሠርፀ J. Sertse -የካቲት 2005 . (February, 2013)

D.Sertse Desta

No comments:

Post a Comment