Wednesday, September 11, 2013

ሕሊና አይረታም

ሕሊና አይረታም

( ለመታችና አስመታቾች በሙሉ)

ሞግተህ ላትረታው ሕሊናህን ክደህ፣

በጻድቅ ምላስህ ውስጥህን ደብቀህ፣

እባብነትህን በእርግብ ላባ ከድነህ፣

እጅግ በጠለሸው በነወረ አእምሮህ፣

ቅዱስ ነኝ ትላለህ መላዕክ ነኝ ትላለህ፣

ይህ ጭራቅነትህ አይገለጥ መስሎህ፡፡

በወርቅ የለበጥከው ቀፋፊ ልብህ፣

የማታ የማታ ሲገፈፍ ጭምብልህ

መገለጡ አይቀርም የውስጠህ ሲኦል፣

ያለፍክበት ሕይወት ያደለብከው በደል፡፡

በስውሩ ሴራህ ወዳጅህ ሲቃትት፣

ቃልህ አይዞህ ይላል እጅህ መርዝ ሲግት፡፡

እንዲህ ሆኖም ሞቶ በመቃብሩ ላይ፣

ያዘነ ለመምሰል ለሰዎች እንዲታይ፣

ደረት ትደቃልህ ፀጉር ትነጫለህ፣

ጮቤ እየረገጠ እየሳቀ ውስጥህ፡፡

መቼም ለአንተም አትቀር ያቺ የቁርጥ ቀን፣

ዋጋህ መሰፈሩ በሰራህው መጠን፡፡

ጭራቅነትህን ቀድመህ አስብበት፣

ሕሊና አይረታም ዝንተአለም ቢሞገት፡፡

. ሠርፀ (J. Sertse), 2001 ዓም

D.Sertse Desta

No comments:

Post a Comment