Thursday, September 26, 2013

“አጐቶቼ ሙስሊሞች ናቸው” – ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም


“ኢትዮጵያዊ አሸባሪ አለ ብዬ አላምንም”
“የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የምሆነው ፓርቲዎች ከተዋሐዱ ብቻ ነው”
“አጐቶቼ ሙስሊሞች ናቸው”

ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም

ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ለሁለት ወራት በአሜሪካ ቆይታ አድርገው ተመልሰዋል፡፡ ስለቆይታቸው እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች “በተለይ” ከሎሚ መጽሔት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች በሃገር ቤት የሚታተመውን የሎሚ መጽሄት ለማንበብ እድሉ ካልገጠማቸው በሚል የዶ/ር ያ ዕቆብን ቃለ ምልልስ እንደወረደ አስተናግደነዋል።
Dr yakobሎሚ፡- እንኳን በሰላም ተመለሱ!
ዶ/ር ያዕቆብ፡- እንኳን ደህና ቆያችሁኝ፡፡
ሎሚ፡- የአሜሪካ ቆይታዎ ምን ይመስል ነበር;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አሜሪካ የሄድኩት ከፊል ቤተሰቤ እዛ ስለሚገኝ ነው፡፡ እነሱን ለመጠየቅና እነሱን ለማየት ነው የሔድኩት፡፡ በአሜሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያኖች እንደመኖራቸው መጠን ከእነሱ ጋር መገናኘቴ አልቀረም፡፡ ውይይቶችም የማድረግ አጋጣሚ ነበረኝ፡፡ በ”ቴሌ ኮንፍረንስ፣ ፓልቶፕ” አማካይነት በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጊያለሁ፡፡ እንደሚታወቀው እኔ በአሁኑ ወቅት የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ እራሴን ወክዬ ነው ከነዚህ ወገኖች ጋር ውይይት ያደረኩት፡፡ በሀገር ውስጥ ለዴሞክራሲና፣ ለፍትህ የሚደርጉትን እንቅስቃሴዎች ማወቅ ከሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ በቆየሁበት ጊዜያት በዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ዙሪያ እንቅልፍ እንደሌላቸው ተመልክቻለሁ፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች አሉ፡፡ የብዙዎቹ ምልከታ በሀገር ውስጥ ለዴሞክራሲ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ ለምሣሌ ማንሣት ካለብኝ “ኢትዮጵያዊነት” የሚባል አንድ ድርጅት አለ፡፡ ይህ ድርጅት ሲቪል ድርጅት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን መስራት ይፈልጋሉ፡፡ ሌሎች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች አሉ፡፡ ከእነሱም ጋር በሀገራችን የሚደረገውን የዴሞክራሲና የፍትህ እንቅስቃሴ አስመልክቶ በውይይት መልክ ተነጋግረናል፡፡ እናም በአብዛኛው ቆይታዬ ያተኮረው በነዚህ ጉዳዮች ላይ ነበር፡፡
ሎሚ፡- በአሜሪካ ቆይታዎ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ዓይነት መንፈስ እናዳላቸው ተገነዘቡ;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ለሰላማዊ ትግል የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ተገንዝቢያለሁ፡፡ ከኔ ጋር መገናኘት የቻሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በእውነቱ በሀገራችን ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ፍትህ እንዲሰፍን ፍላጐት አለን ሲሉ ገልፀውልኛል፡፡ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው፡፡ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ድጋፍ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ፈቃደኛም ናቸው፡፡ በአብዛኛው እንግዲህ ሰላማዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በሌላ መስመር የሚሄዱ ይኖራሉ፡፡ እኔ ከእነሱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረኝም፡፡ ግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጭንቀቱ በሀገራችን ሰላም ይኖራል ወይ; የሚል ነው፡፡ ጥያቄም ብቻም አይደለም፤ “ጭንቀትም ጭምር ነው” በዚህ በኩል ይህንን የማያስብ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ብዙ አይነት ድርጅቶች አሉ፤ ብዙ ሲቪክ ድርጅቶች አሉ፡፡ አሁን አንዱን ጠቀስኩ እንጂ ሌሎችም አሉ፡፡ በነገራችን ላይ በአሜሪካ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ያ ሁሉ ታዲያ በሀገሩ ጉዳይ ያገባኛል ይላል፡፡ እኔ በተለያዩ ሀገራት ኖሪያለሁ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ የሀገሩ ጉዳይ የሚቆረቁረው ሕዝብ አይቼ ግን አላውቅም፡፡ ምናልባት የአቅም አለመኖር ተዳምሮ ብዙ አስተዋጽኦ ላያደርግ ይችላል፡፡ ግን በሀሣብ ደረጃ እንደ ኢትዮጵያዊነት ሁሌም የሚቆረቆር ሕዝብ ነው፡፡
ሎሚ፡- በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ይሁንና ግን የአቋም ልዩነት አለ፡፡ በቅርቡ ኦነግ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ኢህአፓም ቢሆን አመራሮቹን በማሰናበት መግለጫ አውጥቷል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሣቸውን ችግር ሳይፈቱ፣ ለሀገር ችግር የሚኖራቸው ፋይዳ ምን ዓይነት ይሆናል ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ርግጥ ነው፤ ክፍፍሉ ለማንም እንደማይጠቅም ግልፅ ነው፡፡ ሁላቸውም ይረዱታል፡፡ በአገኘሁት አጋጣሚ ያነሣሁት ዋናው ነጥብ መተባበር አለብን፣ አንድ ላይ መስራት አለብን የሚል ነው፡፡ ከተቻለ መዋሐድ አለብን፡፡ በሀገር ደረጃና በአደራ መልክ ጭምር ሁሉም ለምን ፓርቲዎቹ አይተባበሩም; አብረው አይሰሩም; አይዋሃዱም; የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ ዓላማችን ለሀገራችን ዴሞክራሲና ብልፅግና ማስፈን እስከሆነ ድረስ ምን ያለያየናል? የሚለው ጥያቄ ነው ወሳኙ፡፡ ከባህላችንም ይሁን ከፀባያችን ከየት እንደተገኘ ባላውቅም በሀገራችን አብሮ መስራት በጣም አስቸጋሪ ነገር ሆኗል፡፡ በፖለቲካዊ ብቻ ሣይሆን በማህበራዊ ሕይወት ጭምር፡፡ ይህ ነገር ደግሞ እዛም አለ፡፡ ይህ ተቀርፎ አንድ ላይ መሰባሰብ አለብን፤ ተቃዋሚዎች ተሰባስበን፣ ውጭም፣ ውስጥ ያለነው በአንድ ልብና ቃል ከቆምን ኢህአዴግን በምርጫ ማሸነፍ እንደሚቻል እንገነዘበዋለን ይላሉ፡፡ ቅንጅት ያሸነፈው እኮ በፓርቲዎቹ ውህደት ምክንያት ነው፡፡ እነሱ ፓርቲዎች ተዋህደው እስከሰሩ ድረስ በገንዘባችን፣በጉልበታችን ምንም ሣንቆጥብ እንረዳለን ነው እያሉ የሚናገሩት፡፡ እንደሚታወቀው ብዙ ድርጅቶች አሉ ግን በየፊናቸው መካሰስ፣ መወቃቀስ፣ መነቋቆር አለ፡፡ ለቆሙለት አላማ ገፍተው ከመሄድ ይልቅ በመጨቃጨቅ ጊዜያቸውን ያሣልፋሉ፡፡ አሁን እንደተባለው ኢህአፓ ለሁለት ተከፍሏል፤ እንዲሁም ኦነግ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ሌሎችም ፓርቲዎች ከነዚህ ውጭ ያሉ ተከፋፈሉ ሲባል ነው የምንሰማው፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ይሄ ነገር የባህልም ይሁን የታሪክም የምን ውጤት እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ይሄ እንደውም ሶሲዮሎጂስቶች በሰፊው ሊያጤኑት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያት ከተባለ “ለምንድ ነው ኢትዮጵያውያኖች አብረን በጋራ መስራት የማንችለው;” ለዚህ ጥሩ ምሣሌ ላንሣ፤ በውጪ አንድ የጥብቅና ቢሮ 1800 ጠበቆች አሉት፡፡ እኛ ጋር አንድ ቢሮ ውስጥ ሁለት ጠበቆች አብረው መስራት አይችሉም፡፡ ርግጥ ነው በሀገራችን ሽርክናን ሕጉ አይፈቅድም፡፡ በጣም አስገራሚ ነው! ለምን እንደማይፈቅድ አይገባኝም፡፡ ይህም ሆኖ ሁለት ጠበቃ አብሮ የሚሰራ የለም፡፡ የሕግ ስራ ደግሞ አብሮ ውይይት ተደርጐ ተመክሮበት የሚሰራ ስራ ነው፡፡ ሆኖም ግን እኔ የማውቃቸውና አብረው የሚሰሩ ሁለት ሦስት የሚሆኑ ጠበቃዎች የሉም፡፡ የሀገራችን አንድ ትልቁ ድክመት መከፋፈሉ ነው፡፡ መከፋፈል ባይኖር ይህንን ሁሉ ተቃዋሚ አንድ ላይ ማሣለፍ ቢቻል ኢህአዴግን በምርጫ በቀላሉ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ሕዝቡ የተከፋፈሉ ፓርቲዎችን አይፈልግም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ ነበር የሚለው፡፡ ውጭ ያሉትም ቢሆን ትልቁ ችግራቸው የትኛውን ፓርቲ እንደግፍ? ሰማያዊ? አንድነት? መኢአድ… የትኛውን እንደግፍ ነው የሚሉት፡፡ በተከፋፈለ ኃይል ግን የትም ቦታ ላይ ሊደረስ አይቻልም፡፡
ሎሚ፡- በቆይታዎ ከሰብዓዊ መብት ተቋማትና ከአሜሪካ መንግስት አንዳንድ ኃላፊዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ነበርዎት;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አልነበረኝም፡፡ ሊያገናኘኝም የሚችል ሁኔታም አልነበረም፡፡ እንዳልኩህ እኔ የፖለቲካ ፓርቲን ወክዬ አይደለም የሄድኩት፡፡ ስለዚህ ምንም ሊያገናኘኝ የሚችል ነገር የለም፡፡
ሎሚ፡- ወደ አሜሪካ ከመሄድዎ በፊት ለጠ/ሚ ኃ/ማርያም አንድ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ጉዳዩም በቤንሻንጉል (ጉራፈርዳ) በተባለ አካባቢ የተፈናቀሉ ዜጐችን የሚመለከት ነበር፡፡ እናም ከአሜሪካ ሲመለሱ ክስ እንደሚመሰርቱ ገልፀው ነበር፡፡ የክሱን ይዘት ምንድን ነው? ተከሣሾቹስ እነማን ናቸው;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- መጀመሪያ ክስ ከመመስረቱ በፊት፣ ለተከሣሹ ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ልትከሰስ ነው፣ ይሄንን ነገር አስተካል የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡ ይሄንን አስመልክቶ ለጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሣለኝ በጉራፈርዳና በቤንሻንጉል ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በተባረሩት ኢትዮጵያውያን ምክንያት የእነሱን መብት ለማስከበር ክስ እንደምንመሰርት ማስጠንቀቂያ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ደብዳቤ ፅፌላቸዋለሁ፡፡ ለዛ ደብዳቤ መልስ አላገኘንም፡፡ የዛን ደብዳቤ መልስ ለማግኘት ትንሽ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ጊዜም ሰጥተናቸው ነበር፡፡ በቀጣይ ደግሞ ክሱን ወደመመስረት ነው የምንሔደው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የነዚህ ሰዎች መፈናቀል ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡ በሰው ዘር ላይ የሚፈፀም ወንጀል “Crime against humanity” ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ይይዛል፡፡ ማፈናቀልን፣ ሰዎችን መደብደብን፣ የመሳሰሉትን ይይዛል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ በተለይ በዘር ላይ ተመስርቶ ከተደረገ በአለም አቀፍ ደረጃ ሊያስጠይቅ የሚችል ወንጀል ነው፡፡ በአለም አቀፍ ፍ/ቤት ክስ ከመመስረት በፊት በሀገር ውስጥ ያለውን የፍትህ ሁኔታ ማስጨረስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ክስ ለመመስረት የምንዘጋጀው፡፡ የክሱም ይዘት፣ ሰዎች ከቀያቸው ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መፈናቀላቸውን ተከትሎ፣ ይህ ጉዳይ በሚመለከታቸው ባለስልጣናት ላይ ክስ መመስረት ነው፡፡ክሱ ሲመሰረት ማመልከቻ እናስገባለን፤ ማመልከቻው ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ፣ አቃቤ ሕግ ካመነበት ወደ ፍርድ ቤት ሊሄድ ይችላል፡፡ ሌላው በተፈናቀሉ ጊዜ ብዙ ንብረቶቻቸው ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ንብረቶቻቸውን ጥለው ነው የሄዱት፡፡ ዘር ሊያመርቱ አልቻሉም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ በፈለገበት አካባቢ የመዞርና፣ ኑሮ የመመስረት መብት አለው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ብቻ ሣይሆን በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች አዋጅ የተከበረ ሕግ ነው፡፡ አንድ ዜጋ በሀገር ውስጥ በፈለገበት ቦታ ሄዶ የመኖርና፣ ንብረት የማፍራት መብት አለው፡፡ ይሄ ህግ ነው የተጣሰው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ የተዘረፈው ንብረታቸው እንዲመለስላቸው፣ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሣ እንዲከፈላቸው እነኚህን ጥያቄዎች እናቀርባለን፡፡ ፍ/ቤቱ ይህን ተቀብሎ ሊያስተናግደን ከቻለ ጥሩ፤ ካልሆነ ግን ወደ አለም አቀፉ መድረክ መሄዳችን የማይቀር ነገር ነው፡፡ አሁን ክሱን በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን፡፡ ክስ መመስረት የማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብት ነው፡፡ የተፈፀመባቸው ነገር ግን እጅግ አሣፋሪ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚያሣፍር ነው፡፡ ትናንት የተመሠረተች ሀገር አይደለችም፡፡ የብዙ ሺህ አመት ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ አንዱ ዜጋ በፈለገው አካባቢ መኖር አይችልም ብሎ ማፈናቀል…በእውነት በኢትዮጵያ ላይ ከዚህ የበለጠ ውርደት ያደረሰ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
ሎሚ፡- ክሱ እነማንን ያጠቃልላል;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ኃላፊዎች ይህንን ጉዳይ ሣያውቁ፣ እነዚህ ሰዎች ከቀያቸው ተባረሩ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ባያውቁ እንኳን ማወቅ ነበረባቸው ተብሎ መክሰስ ይቻላል፡፡ ኃላፊነታቸው የነዚህን ሰዎች መብት ማስከበር ነው፡፡ ይሄ የክልሉ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፡፡ የፌዴራል መንግስትም ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ በአንደኛ ደረጃ ተከሳሾች የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ይሆናሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የክልሉን አስተዳደሮች…ከፕሬዚዳንቱ አንስቶ ሌሎችንም ሊያጠቃልል ይችላል፡፡
ሎሚ፡- እርስዎ በአሜሪካ በነበሩበት ወቅት በፀረ ሽብር ሕጉ ዙሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት አድርገው ነበር፡፡ እርስዎ የፀረ ሽብር ሕጉን እንዴት ይመለከቱታል;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለኔ ኢትዮጵያዊ አሸባሪ የለም፡፡ ምናልባት ከውጭ የሚመጣ አሸባሪ ሊኖር ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ድንበርን አጠናክሮ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ እኔ በበኩሌ ኢትዮጵያዊ አሸባሪ አለ ብዬ አላምንም፡፡ እስከዛሬም ድረስ አልታየም፡፡ እንደኔ አስተሳሰብ አሸባሪነት እኮ የራሱ ትርጉም አለው፡፡ የፖለቲካ ዓላማ አድርጐ ተነስቶ ሕዝብን ለመበጥበጥ፣ ለማስረበሽ፣ የሕዝብን ሰላም ለማናጋት የሚደረግ ድርጊት ነው፡፡ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ጫና ማድረግ፣ ጥያቄ ማቅረብ አሸባሪነት አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሕጉ ራሱ አሣፋሪ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዚህ ዓይነት ሕግ አይሰራም፡፡ አንድ ሰው ፃፈ፣ተናገረ ተብሎ ወህኒ ቤት አይገባም፡፡ ብዙዎቹ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ሰዎች ቦንብ አልወረወሩ፣ የመንግስት መዋቅር አላበላሹ፣ የመንግስት መዋቅር አላወደሙ፤ ለምን ተናገራችሁ፣ ፃፋችሁ በሚል ነው የታሰሩት፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ በሕገ መንግስቱ የተቀመጠውን ነፃነትን ይገድባል፡፡ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ይገድባል፡፡ ይሄ ሕግ አንድ ሰው አሰበ ብሎ እንኳን የሚቀጣበት ሁኔታ አለ፡፡ አንድ ነገር ማሰቡን በምን ማረጋገጥ ይቻላል? ማረጋገጫ መንገድ የለም፡፡ ማንም የፈለገውን ነገር ማሰብ ይችላል፡፡ አንተ ከፈለክ እኔን ለመግደል ልታስብ ትችላለህ፡፡ ወንጀል ሰራህ ማለት ግን አይደለም፡፡ እኔን ለመግደል አስበህ እንደሆነ እንዴት አድርጌ ነው የማውቀው፡፡ እና በእውነት የፀረ ሽብር አዋጁ የሀገሪቱን የሕግ አካሄድ፣ የፍትህ አካሄድ የበለጠ ይጐዳል እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡ የወንጀል ሕጉ ወንጀለኛን ለመቅጣት በቂ አንቀፆች አሉት፡፡ ይሄን አዋጅ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በአብዛኛው ያወገዙት ነው፡፡ ይህ በእውነት ለኢትዮጵያ ጥሩ ስም አይደለም፡፡ የዚህ አይነት ህግ የውጭ ባለሀብቶች እዚህ ሀገር መጥተው እንዳይንቀሣቀሱ ይከለክላቸዋል፡፡ ይሄ ሕግ በጣም ፅንፈኛና አላስፈላጊ ሕግ ነው፡፡ አሸባሪነትን መከላከል ካስፈለገ በሀገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊና የሕዝቡ መብት መከበር አለበት፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲ ካለ፣ ሕዝቡ የኔ መንግስት ነው ብሎ ካመነ ራሱ ሽብርተኝነትን ይከላከላል፡፡ ከሕዝቡ በላይ ማንም የለም፡፡
ሎሚ፡- ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማመልከት ነው የሚያስፈልገው፤ እንጂ መንግስት የመከልከልም ሆነ የመፍቀድ መብት የለውም ይላል-ሕጉ፡፡ ይሁን እንጂ ሰማያዊ ፓርቲ ለሁለተኛ ዙር የጠራው ሰልፍ ታግዷል፤ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ሰላማዊ ሰልፍ መከልከል ተገቢ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም ቢሆን በወቅቱ ለሚመለከተው ክፍል አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱ ሕግ ወይም በሕገ መንግስቱም ይሁን በሌላው አለም አቀፍ ሕግ ማስታወቅ እንጂ ማስፈቀድ አያስፈልግም፡፡ ይሄ ሰብአዊ መብት ነው፡፡ መብቴ ይከበር ብለህ አታስፈቅድም፤ ትጠቀምበታለህ እንጂ፡፡ መብት እንደተገሰሰ ታስታውቃለህ እንጂ መብቴ ይጠበቅልኝ ማለት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በጊዜው አስታውቆ ነበር፡፡ መልስም የተሰጠው አልመሰለኝም፡፡ “ጉዳዩን በርግጥ በዝርዝር አላውቅም፡፡ አልነበርኩም፡፡” መልስ ተሰጠውም አልተሰጠውም በ48 ሰዓት ውስጥ ምላሽ ካላገኘ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርግ ይችላል ይላል ሕጉ፡፡ ከዛ ባለፈ ግን ቢሯቸው ድረስ ሄዶ መደብደብ፣ ማንገላታት፣ ሰላማዊ ሰልፍን መከልከል ቀጥታ ሕገ መንግስቱን ቃል በቃል የሚፃረር ድርጊት ነው፡፡ መንግስት ያላከበረውን ሕገ መንግስት ማን ሊያከብረው ይችላል? መጀመሪያ መንግስት አርዓያ መሆን አለበት፤ መንግስት ካመፀ በምን ልትከላካል ነው? ይሄ የመንግስት አመፅ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተዘጋጁ ሰዎችን መደብደብ ቢሯቸውን መበርበር አመፅ ነው፡፡ ይሄ በእውነት አሣፋሪ ድርጊት ነው፡፡ ከዚህ አይነት ድርጊት መውጣት አለብን፡፡ ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመፃፍ፣ የመናገር መብት የትም ሀገር ያለ ነው፡፡ ቱርክ፣ ፈረንሣይ፣ እንግሊዝ ይደረጋል፡፡ ለምንድነው እኛ ሃገር ሰላማዊ ሰልፍ በዱላና በግድያ የሚስተናገደው? ከእንደዚህ አይነት ነገር መውጣት አለብን፡፡ እንደሌሎች ሕዝቦች ሁሉ መብቶቻችን እንዲከበሩልን እንፈልጋለን፡፡ ሰዎች ነን፤ እንደሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ዴሞክራሲ እንፈልጋለን፡፡ ፍትህ እንፈልጋለን፣ ቅር ሲለን የመንግስት ፖሊሲ ሣይስማማን ሲቀር ወጥተን በሰላማዊ መንገድ መቃወም እንፈልጋለን፡፡ ይሄን መከልከል አያስፈልግም፡፡
ሎሚ፡- መንግሰት “አክሪራነት” የሚለውን ቃል ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ጋር የማያያዝ አዝማሚያ ታይቶበታል፡፡ ይሄ ለጉዳዩ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ወይ;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የማንኛውም ሕዝብ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ካልሆነ በስተቀር በጉልበት ሊፈታ አይችልም፡፡ በመንግስት በኩልም ኃይል ተጠቅሞ የሕዝብን ጥያቄ ማዳከም አይቻልም፡፡ የሚሻለው ምንጊዜም ቢሆን ወደ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመራውን ውይይት መምረጥ ነው፡፡ እነኚህ ሰዎች መንግስት በኃይማኖታችን ውስጥ ጣልቃ አይገባ ማለታቸው ትክክል ነው፡፡ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ይሄንን ነገር ማቆም አለበት፡፡ ዋናው ነገር ግን ኢትዮጵያ በኃይማኖት ተቻችሎ በመኖር በጣም ዝናን ያተረፈች ሀገር ነች፡፡ ይሄ አሁንም ሊቀጥል ይችላል፡፡ ግብፅ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉት ሙስሊሞች ብቻ ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች አስር ፐርሰንት ናቸው፡፡ ሶሪያ ሙስሊም ብቻ ነው ያለው፤ ሊቢያም እንደዛው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ከዚህ የተለየች ነች፡፡ እኔ አጐቶቼ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ዘመድ የሌለው የለም፡፡ ስለዚህ ዘመዶቼ ናቸው፡፡ ታዲያ በኔ ላይ ነው የሽብር ተግባር የሚፈፅሙት; አያደርጉትም፡፡ አስታውሳለሁ፤ ከሆኑ የቅርብ ጓደኞቼ ጋር ስንጨዋወት ሙስሊም ዘመድ የሌለው ኢትዮጵያዊ የለም በሚለው ተማመንን፡፡ በሀገራችን የሙስሊም አሸባሪነት የሚያስፈራ ነገር አይደለም፡፡ መብታቸው እስከተከበረ ድረስ ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡ ዋናው ነገር ተግባብቶ ከሙስሊሞቹ ጋር መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ መብታችን ይከበር ብለው ጥያቄ ያቀረቡትን የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ሰዎችን ቃሊት ሄጄ አነጋግሪያቸዋለሁ፡፡ “እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ለሀገራቸው በጐ ነገር የሚመኙ፣ ሰላምና ዴሞክራሲን የሚመኙ ሰዎች ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚለዩበትን ሁኔታ አላየሁም፡፡
ሎሚ፡- ኢህአዴግ ላለፉት አንድ አመታት “የመለስ ራዕይ” በሚለው መርሁ ቀጥሏል፡፡ አንድ ፓርቲ በአንድ ሰው ወይም በሕይወት በሌለ የቀድሞ መሪው ሀገር መምራት ይችላል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በእውነት በጣም የሚገርም ነው፡፡ ሰው ከሞተ በኋላ በሬሳው ይግዛን ብሎ ይሄን ያህል ማጋነን፣ ማቅ ለብሶ ማዘን ተገቢ አይደለም፡፡ በጣም ኋላቀርነት ነው፡፡ እኔ እንደማየው “ሰው ስራው ታሪኩ ነው” ታሪክ ደግሞ ለማንም አያዳላም፡፡ የአቶ መለስ ስራ ታሪኩ ነገ ከነገ ወዲህ ይወጣል፤ እንጂ ዛሬ የተሰሩ ነገሮች (ጥሩ ተሰርተውም ይሁን መጥፎ) ሊደመሰሱ አይችሉም፡፡ ብዙ የማይደመሰሱ ነገሮች አሉ፡፡ በ1997 ዓ.ም. በመንግስት አባባል እንኳን 200 ሰዎች ሞተዋል /ተገድለዋል/፡፡ በዚህ ዙሪያ ማነው ተጠያቂው? ተብሎ የተፈረደበት አመራር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ ወደብ አልባ እንድትሆን ተደርጓል፡፡ ይሄን ሁሉ ታሪክ የሚፈርደው ነገር ነው፡፡ ዛሬ “ራዕይ፣ራዕይ” ስለተባለ እነኚህ ድርጊቶች ይሰረዛሉ ማለት አይደለም፡፡ በጐውም፣ መጥፎውም፣ ስህተቱም ተደብቆ አይቀርም፤ ይወጣል፡፡
ሎሚ፡- ሀገሪቱ ወዴት አቅጣጫ እየሄደች ይመስልዎታል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የዚህች ሀገር የወደፊት መፃኢ ዕድል ሁሉንም የሚያሳስብ ነው፡፡ የብዙዎች ጭንቀትም ይሄ ነው፡፡ ሀገሪቱ በብሔረሰብ ተከፋፍላ በአንዳንድ አካባቢ ከፍተኛ ጥላቻ እየተፈጠረ ነው፡፡ ልንሸሸው የማንችለው ነገር ነው፡፡ ተረባርቦ ሀገሪቱን ማዳን ሕዝቡን ማዳን ያስፈልጋል፡፡ ጥላቻ ሲፈጠር እያየን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ወደ መጥፎ አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል፡፡ ጥላቻው የለም ማለት፣ አውሎ ነፋስ ሲመጣ ሰጐን አንገቷን ቀበረች የሚሉት ተረት ዓይነት ቢጤ ነው የሚሆነው፡፡ ጥላቻ ስለመኖሩ ከጉራፋርዳና ከቤንሻንጉል የበለጠ ምን ማስረጃ ያስፈልጋል? ይሄ በፍጥነት እልባት ማግኘት አለበት፡፡ ምንም ጥርጥር የሌለውም፤ ሀገሪቱ በብሔር ተከፋፍላለች፡፡ ስም ባልጠቅስም፤ አሜሪካ በነበርኩበት ወቅት የአንድ ብሔር ቀን ብለው ሲያከብሩ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህንን ስናይ ወዴት ነው የምንሄደው? የዚህች ሀገር መፃኢ ዕድልስ ምን ይሆን? በዚህ ዓይነት አካሔድ ሀገር እንደ ሀገር ሊቀጥል ይችላል ወይ? የሚል ስጋት አዘል ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም፡፡ ርግጥ ነው፤ የአንዱ ጐሣ መብት አይከበር አይባልም፡፡ ቋንቋው መከበር አለበት፤ በቋንቋው መናገር መቻል አለበት፤ ግን በጎሳው ኢትዮጵያዊነቱን ሊሰርዝ አይችልም፡፡ አሜሪካ ውስጥ “ኢትዮጵያዊነት በግድ ተጫነብኝ፤ እኔ የዚህ ጐሣ ተወላጅ ነኝ” ሲሉ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይሄ ምንን ያመለክታል? የወደፊቷን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚጥል ነው፡፡
ሎሚ፡- በጥብቅና ሞያ በመስራት ላይ ይገኛሉ፤ አሁን ያለውን የፍ/ቤቶች አሰራር እንዴት ያጤኑታል? ቢሮክራሲያዊ አሠራሮችስ ምን ያህል ተንሰራፍተዋል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ቢሮክራሲያዊ አሠራሩ በፍርድ ቤት ብቻ ሣይሆን በአጠቃላይ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ያለ እንከን ነው፡፡ በርግጥ ዳኞችም በጣም ስራ ይበዛባቸዋል፡፡ ብዙ ክርክሮችና ብዙ ጭቅጭቆች አሉ፡፡ ግን መንግስትን በሚመለከት ጉዳይ (ኢትዮጵያ) ውስጥ ፍትህ አገኛለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ ምናልባት ሁለት ግለሰቦች ተካስሰው ፍትህ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ የመንግስት እጅ ያለበት ጉዳይ ከሆነ ግን ፍትህ አገኛለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ ሙስና መንሰራፋቱን መንግስት ራሱ ተቀብሎታል፡፡ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቷል፡፡ በፍ/ቤት ብቻ ሣይሆን ሀገሪቱንም የወረር ክስተት ነው፡፡ ሙስና እንደ ነቀዝ ኢትዮጵያን እያጠቃ ነው፡፡ ዛሬ ያለገንዘብ ጉዳይህን የሚያይልህ የለም፡፡
ሎሚ፡- ዶ/ር ያዕቆብ እስከመቼ ነው ከየትኛውም የፖለቲካ ፖርቲ ጋር የማይሰሩት? የፖለቲካ አቋማቸውስ ምንድነው;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አንድ ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ በፖለቲካ አመራሩ ወጣቶች መተካት አለባቸው፡፡ እኔ ያለሁበት ወይም የነበርኩበት ሁኔታ አክትሟል፤ ማለትም ጊዜው አልፏል፡፡ ሌሎች መረከብ አለባቸው፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ እኛ እኮ የተቀረፅነው በማርኪስዝም ሌኒንዝም ነበር፡፡ ዛሬ ማርክሲዝም ሌኒንዝም የትም አይሰራም፡፡ ዛሬ ለዴሞክራሲ የተማሩ፣ ለፍትህ ግንዛቤ ያላቸው ወጣቶት በአመራር ደረጃ መተካት አለባቸው፡፡ ይሄ ደግሞ አማራጭ የሌለው እውነታ ነው፡፡ ብቻችንን ከ40 አመት በላይ ነው በፖለቲካ ውስጥ የቆየነው፡፡ አስታውሳለሁ፤ መሬት ላራሹ ብለን ሰልፍ የወጣነው የዛሬ 43 አመት ነው፡፡ በዛ ጊዜ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፕሬዚዳንት ነበርኩ፡፡ እስካሁን ድረስ አልተውኩትም፡፡ በአመራር ደረጃ ፖለቲካ በቂዬ ነው፡፡ ኃላፊነት ግን አለብኝ፤ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ይህቺ ሀገር ብዙ ብዙ ዕድል ሰጥታኛለች፡፡ መካስ አለብኝ፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ለዴሞክራሲና ለፍትህ በሚደረገው እንቅስቃሴ የምችለውን አደርጋለሁ፡፡ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ጥሩ ቅርበት አለን፤ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ቅርበት አለኝ፡፡ ከመኢአድም ጋር ቅርበት አለኝ፡፡ አንዳንዴም ሲጋብዙኝ ካለኝ ተሞክሮ በመነሣት ንግግር አደርጋለሁ፡፡ ትምህርት ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ አመራሩ ግን በወጣቶች መተካት አለበት፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የምሆነው ፓርቲዎቹ ከተዋሃዱ ብቻ ነው፡፡ ይህን ካደረጉ የአባልነት ቅፅ ለመሙላት ዝግጁ ነኝ፡፡ በዚህ በተከፋፈለ ሁኔታ ግን መቀላቀል አልፈልግም፡፡ በኔ እምነት የተከፈለ ፓርቲ የትም ይደርሳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ አባል የመሆን ፍላጐት የለኝም፡፡
 http://www.zehabesha.com/amharic/archives/7748

No comments:

Post a Comment