Wednesday, September 11, 2013

አስተታያየት ለዶ/ር ፍቅሬ ቶሎ(ላ)ሳ፣ ዶ/ር በያን አሶባና ለየደጋፊዎቻቸው

 

እኔ የታሪክም የፖለቲካም ሰው አይደለሁም፡፡ ግን ታሪክ አዋቂ ነን ፖለቲከኛም ነን የሚሉት ሰዎች ለሕዝብ በሚያካፍሏቸው እነሱ ታሪክ ነው ለሚሉት ፅሁፋቸውና አሰትምሮታቸው፣ ምሁራዊ ነው ለሚሉት ትንታኔያቸውና አስተያየታቸው፣ ስኬትን ያመጣል ለሚሉት ንድፈሀሳባቸውና ዕቅዳቸው ለዘመናት የእኔና የመሰሎቼ አእምሮ ለመቀበል እየተቸገረ እራሱ መልሶ እነሱ እኮ ምሁር ናቸው፣ ብዙ ያወቃሉ ስለዚህ ትክክል ናቸው በሚል ሲሸነገልና ሲሸነፍ ኖሯል፡፡ ዛሬ ግን ቢያንስ የእኔ አእምሮ እነሱን መሐይብ/ም ምሁራን ብሎ ሊፈርጃቸው ፍቃደኛ ሆኗል፡፡ ታሪክም (ፅሑፎቹን ማለቴ ነው)፣ፖለቲካም መነሻቸው ጥላቻ በመረዛቸው ፍራቻ ባሸማቀቃቸው አእምሮዎች ተፈብርኮ ታሪክ ወይም ፖለቲካ ከሆነ ምሁርነትን የሚጠይቅ ሆኖ አላያየውም፡፡ በተሻለ እኔ አና እኔን መሰል አንብበንም (ቢያንስ ማንብ እንችላለን) ይሁን የሰማንውን እውነት ወይም ማጣቀሻ ባለው የሀሳብ መነሻ ታሪካዊም ሆኑ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን ብንሰጥ ምሁር ነን ከሚሉት የተሻለ ተፎካካሪ እንደምንሆን ስለደመደምኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከተለው ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ሙከራ አደርጋለሁ (ይህ ሙከራ ነው)፡፡ ሰሞኑን ዶ/ር ፍቅሬ (የታሪክ ሰው እንደሆኑ የሚናገሩ) የተባሉ ሰው ለአንድ ዶ/ር በያን ለተባሉ ሌላ ሰው (የኦሮሞ ብሔርን መሠረት ያደረገ የአንድ ፓርቲ አባል) ግልጽ ደብዳቤ በሚል የጻፉት ጽሑፍ ምክንያት የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ አይቼ (በኢንተርኔት) እኔስ ብሞክር ምን ይለኛል ከሚል ነው፡፡ በዶ/ር ፍቅሬ ቶሎ(ላ)ሳ ደብዳቤ በተባለው ብጀምር፤ ከመሠረታዊ ሐሳብና (አንድነትን የመሻት) በአንዳንድ ታሪካዊ እውነታዎች አኳያ ሲታይ መልካም የሚባል ነው፡፡ ሆኖም ግን በአጻጻፉ ምሑራዊ ማሳመኛዎችን በማቅረብ ለማስረዳት ከተሞከሩት ትንታኔዎች ይልቅ ልምምጫንና እኛ እኮ ወንድማማቾች ነን በሚል ምሁራዊ ባልሆኑ ይልቁንም ማባበያ በሚመስሉ አረፍተ ነገሮች የታጀበ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል ከብዙዎች በተለይም ኦሮሞ ነን ወይም እንወክላለን በሚሉ ለዚህ ደብዳቤ የተሰጠው አስተያየት ጥሩ ያልነበረው፡፡ በእርግጥም አስተያየት ሰጭዎቹ እንደሚሉት እነሱን ለማታለል የተጻፈ እነሱ እንደሚሏቸው የዘመናዊ ደበተራዎች ጽሑፍ አሰመስሎታልና፡፡ 

 ልምምጫው (ሌሎች እንዳሉት ማባበያው ሊሆን ይችላል) ከተራ የግል ሥም ማመሳከር እስከ የተወሳሰበ የታሪካዊ ማንነት ማመሳሰል ነበር፡፡ እኔ ከአንድ ምሁር ሰው የአንድን ሰው ስም አንስቶ ከሆነ ሕዝብ ቋንቋ ጋር የሥሙ ትርጉም ተያያዥነት ስላለው አንተ የእንደዚህ ያለ ሕዝብ አባል ለመሆንህ ማስረጃ ነው፤ እኔም እንደዚሁ ስለሆንኩ እኔና አንተ አንድ ቤተሰብ ነን ብሎ ለማቀራረብ መሞከር አይመችም፡፡ የሥም ትርጉም በሆነ ሕዝብ ቋንቋ ውስጥ መገኘቱ የታሪክ አመላካችነት ፋይዳ የለውም እያልኩ አይደለም፡፡ አጠቃቀሙ የመለማመጥንና ሰዎችን ለመሸንገል የዋለ ስለመሰለኝ እንጂ፡፡ ሊያውም አንድ ምሁር ነኝ ከሚል ለሌላ ምሁር ለሆነ ሰው እንደማስረጃነት ማቅረብ፡፡ ደግሞ ዶ/ር ፍቅሬም ሆኑ ዶ/ር በያን ኦሮሞ ለመሆናቸው ወይም ላለመሆናቸው ጥያቄ ባልተነሳበት የሀሳብ ትንታኔ ውስጥ፡፡ ጉዳዩ ትልቅ የሀገር ጉዳይ መስሎ መጨረሻ አንተና እኔ እኮ እንዲህ ነን ለማለት፡፡ በአጠቃላይ አይመጥንም! ሌሎች የተነሱ የታሪክ መረጃ ናቸው የሚሏቸው ነገሮች በመዝገብ ካሉ ጥሩ ግን እነሱንም ምሁሩ ራሳቸው የፈበረኳቸው እንዳይሆኑ እመኛለሁ፡፡ የሚቀጥለውን ጉዳይ ከማንሳቴ በፊት እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ እንጂ የተኛውንም ብሔረሰብ ሆነ ፖለቲካ እንደማልወክል

እንድታውቁልኝ እወዳለሁ፡፡ ጀበደኛው ኢትዮጵያዊ ሆኜ አይደለም በእርግጥም ውስብሰብ ቤተሰብና እኔ ከዚህኛው ነኝ ብሎ ለመናገር ከማያስችል ኢትዮጵያዊነት እንጂ፡፡ እኔ ብቻም ሳልሆን ብዙዎች አለን፡፡ ወደ ጉዳዬ ልመለስና ዶ/ር ፍቅሬ እንትና እንትናን ወለደ በሚለው ትንታኔያቸው አማራ ማራ የተባለ የኦሮሞ ዘር… ይላል፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጲ የሚባልም ሰው በእውን በኢትዮጵያ ታሪክ የነበረ ሰው ሊኖርም ይችላል፡፡ ይህን ታሪክ ደግሞ ጸሐፊው የተጠቀሙት በአብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብን ጥንታዊ ኢትዮጵያዊነትን ለማመልከት ነው፡፡ ጥሩ ግን ያነሷቸውን የታሪክ መረጃዎች አሁን ላይ ላለው ነባራዊ ሁኔታ በአያያዥነት ያቀረቧቸው የመካከለኛ ወይም ከዚያም በኋላ የተከሰቱ ታሪኮችን ለማየት አላስቻለኝም፡፡ ለካ እንዲህ ነበር የሚያሰኝ አዲስ ዕውቀት ሳይሆን ሊሆን ይችላል የሚል ታሪኩን ለጸሐፊው ይሁንልህ እንደማለት አይነት ስሜት ነው የፈጠረብኝ፡፡ ምክነያቱም ተረት ተረት ወይም አፈታሪክ አይነት ስለሆነብኝ፡፡ ግን አንድ ሰው ነው ካለ እኔም ላለመሆኑ ማረጋገጫ ማቅረብ እስካልቻልኩ ድረስ እሱም መብቱ ነው እኔም አለማመን መብቴ ነው፡፡ ግን እኮ ያን ሁሉ መዳከር የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ከባሕር ወጣ፣ ከማዳጋስካር መጣና ሌሎች መሰል ተረቶች ማፍረሻ እየሰጡን ከሆነ ከጅምሩ አኛ ተረቶች እንደሆኑ እንጅ ታሪክ እንደሆኑ ስላለተቀበልናቸው ይህንን ያህል ሌላ ግራ የሚያጋብ ውስብስብ የታሪክ ማጣቀሻ አያስፈልግም፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው አስተያየቴ በቀጥታ ለደ/ር ፍቅሬ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያዊ ምሁራን ይሆናል፡፡ ዶ/ር ፍቅሬም ራሳቸውን እንደ አንዱ ማየት ይችላሉ፡፡ የብዙ ኢትዩጵያውያን ምሁር ነን ባዮች ችግር ከክፍል ትምህርት (መምህራችን ከነገረን) ውጭ ይህ ለምን ይሆናል በሚል የራስን ጥያቄ ተመረኩዞ አዲስ ምርምር በማካሄድ አዲስ ግኝትን ከማቅረብ ይልቅ ድሮ በደብተር የተማርናትን ትንሽ ደግሞ አንዴ ምሁር ተብለናልና ሌሎች ሲሉ የሰማናትን በማቅረብ ገዝፈን እንታይባታለን፡፡ ከዚያ በቃ እኛ ምሁሮቹ ተናግረናል ቀጣዩም ከእኛው ተቀብሎ ምሁር እየሆነ ለዘመናት በአዲስ እውቀት ሳንታነጽ ብዙ ጥያቄዎችን ለሚያነሱየተጠራቀሙ ጉዳዮችም መልስ ሳንጥ በአለህበት እርገጥ አይነት እንኖራለን፡፡  ምን አልባት ከጥያቄ አንሺው አንዱ የራሱን ምርምር ለማካሄድ ቢሞክር እንኳን ግዙፎቹ ምሁር ተብዬዎች ጨፍልቀውት ይቀራል፡፡ ይህ በታሪካችንም ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዘርፍ ያለ ችግራችን ነው፡፡ እነ አባ ባሕሬን የትኛውንም ያህል አወዛጋቢ (ተረት-ተረት) ቃላቶች ቢጽፉም የአንድም ይሁን የሌላ ክስተትን ታሪክ መዝግበው በማቆየታቸው እንደኔ አሁን በዘመናዊው አለም ካሉት ብዙ ምሁራኖች በተሻለ አበርክተዋል፡፡ ጥሬውን ከገለባ መለየት የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ዛሬ ስንት የታሪክ ምሁራን ነን የሚሉ ባሉባት አገር የብዙ ሕዝባዊ ታሪኮቻችን እውነታ ምን እንደሆነ ባለመታወቃቸው ሁሉም የመሰለውን በመተርጎም ለጭቅጭቃችንና አልፎም ተርፎም ግጭታችን መንስኤ ሆነው እርስ በእርሳችን የጎሪጥ እየተያየን እንኖራለን፡፡ ሁሉም እውነታን ፍለጋ ምርምር ቢያደርግ ግን አንዱ ያላካተተውን በሌላው ስኬታማ ምርምር ውጤት እያሟላን እስካሁን ግልጽና የምንስማማበት ታሪክ በኖረን ነበር፡፡ ግረሃመ ሐንኩክ በሰሜን አስመሮም በደቡብ (ቦረና) ያደረጉት እንኳን የምርምር ጥረት ቢያንስ ለሌላ አማራጭ ምርምር ሂደቶች ፈር ሊቀዱ እንደሚችሉ አማላካች ናቸው፡፡ የሆነው ግን የግርሃምም፣ የአሰመሮምም ጥረት ለሌሎች ለራሳቸው አጋጣሚ ለሚፈጥሩ ሰዎች መጠቀሚያ ከመሆን በቀር ለቀጣይ ጥናቶች የእነሱን ጠቋሚ ግኝቶች/ሐሳቦች የተጠቀመባቸው ምሁር አለመኖሩ ነው፡፡ በየገዳማቱ፣ ደብራቱ፣ መስኪዶች ያሉ መዛግብቶችንስ ሌሎች በጥተው ከአጠኑ በኋላ አይደል እንዴ ከነመኖራቸውም ትዝ የሚለን፡፡ እኛ የደብተር ምሁራን ነና! ይህ አልበቃ ብሎን ደግሞ አሁን አሁን (ለነገሩ ቆየ 20ና ከዚያ በላይ ዓመት) ታሪክ ጸሐፊዎቻችን በብዛት ከከፋ ጎሰኝነታቸው የተነሳ እያስነበቡን ያሉት የነበሩ እውነታዊ ክስተቶችን ሳይሆን የየራሳቸውን ምናባዊ ልቦለዶችን ሆኗል፡፡ ታሪክም ሆነ ሌላ ምርምር ነጻና ገለልተኛ የሆነ አስተሳሰብን የሚጠይቅ ነው፡፡ በየቋንቋዎቻችን መናገራችን መልካም ነበር ግን በየቋንቋዎቻችን ማሰባችን ከፋ እንጂ፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪው በኦሮምኛ፣ አማርኛ ተናጋሪው በአማርኛ፣ ትግሪኛውም እንደዚያው ሆነና፣ ሁሉም የየራሱን እያገዘፈ የሌላውን አያሳነሰና እያጥላላ የሚጽፈውን ሁሉ ታሪክ ነው ብሎ ሊያስነብበን ይሞክራል፡፡ እንደምሁርነት ግን ያለውንም ሳያጎድል የሌለውንም ሳይጨምር ነኝ የሚለውንም ሕዝብ የሌላውንም በእኩል እይታ ማቅረብ ቢቻል እንዴት ባማረ፡፡ ለዚህ ባለመታደላችን በጣም አዝናለሁ፡፡ በእኔ ግንዛቤ የኢትዮጵያ የዘር ግንድ ጥያቄና የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ እንደነገረኳችሁ እኔ በዘር ማንንም አልወክልም፡፡ ግን ኢትዮጵያዊ መሆንን የሚከለክለኝ የለም፡፡ የግድ የእንትና በሔር ነኝ ብዬ ማሰብም የለብኝም፡፡ እኔና መሰሎቼ በቅርበት የምናወቀው የተወሳሰበ የዘር ሐረግ ሰላለን ተገላገልን! ለቀሪዎቹ የእንትና ብሔር ነኝ ለምትሉት ግን የዘር ማንነታችሁን በምን ልታረጋግጡት ትችላላችሁ፡፡ በዘር ግንድ (በደም) አንድ አይነት በሔር ነን ከሚሉት ይልቅ በድንበር በሚዋሰኑ ብዙ የተለያዩ ብሔሮች መሀከል ያለው ቅርርቦሽ የበለጠ ነው፡፡ የሸዋ ኦሮሞ ከባሌ ወይም ቦረና ወይም ሐረር ኦሮሞ ሕዝብ ጋር ካለው የደም ትስስር ይልቅ በአቅራቢያው ካሉት አማራና ጉራጌ ነን ከሚሉ ሕዝቦች የበለጠ ትስስር እንዳለው መገመት እንችላለን፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሁሉ አንድ አይነት የደም ዘር አለው ተብሎ ሁሉንም ወደ መዳወላቡ ማቆር ምሁራዊ አይመስለኝም፡፡ አንድ ምሳሌ ላንሳ ዛሬ በግንደ በረት አካባቢ የሚኖር ብዛት ያለው ኦሮምኛ ተናጋሪ አማራ ናቸው ተብለው ከሚታመኑት የሸዋ ነገስታት ዘር እንደሆኑ በግልጽ የተመዘገበ ታሪክ አለ፡፡ ታሪኩ ከነ አጼ ንብለድንግል አካባቢ ብዙም ራቀ የማይባል ነው፡፡ እንግዲህ ዶ/ር ፍቅሬ እንዳሉት አጼ ንብለድንግል ከመጀመሪያውም ኦሮሞ ከሆኑ እሰየው ግን ለምን ይህ ከሆነ ይህን ታሪክ ግልጽ በሆነ የምርምር ውጤት መደገፍ አልተቻለም፡፡ አማራ ነኝ የሚለው ጎጃሜና ኦሮሞ ነኝ የሚለው ወለጋም ከጎጃሜና አማራ ነኝ ከሚለው የሸዋ ሕዝብ የተሻለ የዘር ትስስር እንደሚኖራቸው ቢታሰብ መሠረተ ቢስ አያሰኝም፡፡ አንድ ሌላ ማስተዋል፤ በኦሮሞ ሕዝብ ፍልሰት በሉት እንቀስቃሴ ጊዜ የኦሮሞው ሕዝብ ወሮ ወደገባባቸው ቦታዎች ሰዎች ነበሩ ይመስለኛል፡፡ እና የኦሮሞው ሕዝብ እነዚሕን ሕዝቦች አዋሃዳቸው (assimilate) ተብሎ ሲነገር በስፋት ይሰማል፡፡ ቢያንስ እነዚህ ሕዝቦች ዛሬ ቋንቋቸው ወደ ኦሮምኛ ተቀይሮ በደማቸው ግን ሌላ ሕዝብ ሆነው እየኖሩ እንዳሉ እንዴት ማሰብ ያዳግታል፡፡ በተለይ ምዕራብ ሸዋ፣ ጥቁር እንጭኒ፣ ወንጪ፣ የተጠቀሰው ግንደ በረት፣ ጋፋት ሌሎችም እስካሁንም በአይን በማየት እንኳን መለየት የሚቻልበት ነው፡፡ ብዙብዙ ሊባል ይቻላል፡፡ ጉዳዩ የተነሳው ከኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ጋር ስለሆነ እንጂ እንዲህ ያለ ውስብሰብነት በአማራ ነኝ ትግሬ ነኝ የሚለውም ተመሳሳይ ነው፡፡ ዛሬ ለምናየው ብሔረተኝነት ቋንቋ እንጂ የደምም ሆነ የባህል አንድነት መሠረት ላለመሆነቸው ለሚያስተውል ግልጽ ይመስለኛል፡፡ የታሪክ ምሁራን ነን የሚሉት ነገሩንም አልነገሩንም፡፡ የመጀመሪያው የኦሮሞ ሕዝብ ባሕል (ዛሬም ድረስ በቦረና ያለ ነው) አንድን ሰው ከወደዱት ፍጹም የሆነ ቤተሰባዊ ውህደትን በመስጠት ስሙ በቀጥታ ከዘር (Biological)አባቱ ተለውጦ በወደደው የቦረና አባት ከዚያ በኋላ ባለው የዚሁ አዲሱ የመውደድ አባት ቢባል ይሻላል ዘር ሥም ይጠራል፡፡

 

 በኦሮሞ ሕዝብ ያሉ የሥም ሐረጎች ትክክለኛውን የዘር ግንድ ላይጠቁሙ የሚችሉበትም እንዲህ ያለ አጋጣሚ እንዳለስ ስንቶቻችን እናውቃለን፡፡ እንዲህ ባለ ውስብስብ ቤተሰባዊነት እኔ እንደዚህ ነኝ ተብሎ ሊያስደፍር የሚያስችል የዘር ሀረግ እውን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ አደንቃለሁ፡፡ አንዳንዶች በተለይም ደግሞ ኦሮሞ ነን የሚሉት ቢጠሉትም ሐበሽ (ድብልቅ) የሚለው የአረብኛ ሥያሜ ያለምክነያት አለተሰጠንም፡፡ መጀመሪያ ሴሜቲኮችንና ኩሽቲኮችን ማደባለቅ ቢሆንም አሁንም ድረስ የሚገባን ስማችን ነው፡፡ በመልክስ አንዱን ከአንዱ መለየት ይቻላል? የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክን በተመለከተ ኦሮሞ ነኝ የሚለውም ደብተራ የተባሉትም የጻፉትን ጽፈዋል፡፡ ታሪክ በቲፎዞ እውነት ሊሆን ባይችልም ለየራሳቸው ደጋፊዎቻቸው የሚሉትን ይበሉ፡፡ እኔን ግን የሳበኝ ኦሮሞ ከደቡብ (ባሌ-መደዳወላቡ) ሳይሆን ከሰሜን (ቀይ ባሕር) ነው የተንቀሳቀሰው የሚለው የኤርትራዊው አስመሮም ሀሳብ ነው፡፡ ለእኔ ይህ አዲስ አቅጣጫ ጠቋሚ ግኝት ሊነበቡ የሚችሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚያሳይ ነው፡፡ ከመዳወላቡ ተነስቶ ትግራይ ደረስ ከማለት ዛሬ ትግራይ ምናአልባትም ወሎ ውስጥም ያሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ጨምሮ ከመጀመሪያው ከሰሜኑ (ቀይባህር) ወደ ደቡብ ሲንቀሳቀሱ እዛው ሊቀሩ ከቻሉት ሊሆን እንደሚችል ማሰብ የታሪክ አማራጭ ይሆነኛል፡፡ ወደ ደቡብ በዛው ታነዛኒያ፣ ማዳጋስካር የሄዱ አሉ አያጣላም ቢያንስ ማሳዮች ይመስሉናልና፡፡ ፊደላት ፊደላትን በተመለከተ ይመቻኛል እሰካለ ድረስ የፈለገ የቻይናም ፊደል መጠቀም ይችላል፡፡ በድመፅ ብዛት ግን ከላቲን አይደለም ከየትኛውም የአለም ፊደላት የግዕዝ ፊደላት የበለጸጉ እንደሆነ ይነገርላቸዋል፡፡ ካስፈለገም ተጨማሪ ደምጽ ሊሆኑ የሚችሉ ፊደላትን መጨመር ነው፡፡ በአማርኛም ይሁን በሌላ ግዕዝ ተጠቃሚ ቋንቋዎች እኮ እንደነ ፐ ቨ የመሳሰሉት ድምጾች ከነጭርሱም የሉም፡፡ አዲስ ድምጾችን ለማስተናገድ የገቡ ናቸው፡፡ በኦሮምኛ በሁለት የላቲን አልፋቤት የሚጻፈው dh በግዕዝ ፊደል ተቀርጾለት ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉ ድመጾች በግዕዝ ፊደላት የማይወከሉ ካሉ ተናጋሪዎቹ በነግሩን፡፡ ግን እስከዛሬም የግዕዝ ፊደላት ሶፈት ዌር ባለሙያዎች የdh ፈደልና ዘሮቹን በግዕዝ ሶፈት ዌር ባለማካተታቸው በጣም አዝናለሁ፡፡ በመሆኑም የሰዎችን ሥም እንኳን በአግባቡ ለመጻፍ ተቸግረናል፡፡

 ምንአልባት ኦሮምኛ በላቲን እየተጻፈ ስለሚገኝ ለኦሮምኛ ድመጾች ፊደል አናስገባም ባይባል ጥሩ ነው፡፡ ቢያንስ በነዚህ የፊደል ዘሮች የሚጻፉ ሥሞች አሉንና፡፡ ላቲን ለሚመቻቸው ከተመቻቸው ይቀጥሉ፡፡ ነገሮች ግን ከስሜታዊነት ይልቅ በትክክልም ስለሚያስፈልጉና ስለሚቀሉ መሆናቸውን በማስተዋል ቢሆን ይመረጣል፡፡ አነሳሱ ከግዕዝ ፊደላት ችግር ሳይሆን እራስን ከግዕዝ ተጠቃሚዎች (እነሱ አቢሲኒያን የሚሏቸው) ለማራቅ የተደረገ ጥረትን ይመስላልና፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሌሎችም በተለይ ከሴሜቲክ ቋንቋ ቤተሰብ ያሉ ላቲን ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በግርግር የሴሜቲክ ቋንቋ ቤተሰብ የነበራቸውም ሞክረውት ነበር ኋላ ሳይሳካ ሲቀር ቀየሩት እንጂ፡፡ ለምሳሌ፡ ሐረሪ፡፡ ከተመቸ እሺ፣ ግን ለእነእንትና ብሔረሰብ ካለን ጥላቻ እነሱ የሚጠቀሙትን አንጠቀምም ከሆነ እነጂ ችግሩ፡፡ አሁንም ደግሞ ካፈርኩ አይመልሰኝ አይነት ከሆነ፡፡ ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች በአንድም ይሁን በተዘዋዋሪ ዶ/ር ፍቅሬ የተባሉት ሰው በአነሷቸው ጉዳዮች ላይ ነበር፡፡ ወደ ዶ/ር በያን ስመጣ ዶ/ር ፍቅሬ ያሳዩትን ድክመት ዶ/ር በያን ሊያጸድቁት ባይሞክሩ ጥሩ ነበር፡፡ ግብግቡ ሁሉ ሥም ላይ ነበርና፡፡ እርግጥ በተሻለ አግባብ እንደሆነ አያለሁ፡፡ ዶ/ር ፍቅሬ ዶ/ር በያንንና ድረጅታቸውን እንደተለማመጡት የሚመስል ንባብ በዶ/ር በያን ደብዳቤም ላይ የሌሎችን ሕዝብ ብሔሮችን በመጥቀስ እባካችሁ ኢትዮጵያዊ ባለመሆን ከጎናችን ቁሙ የሚል ጥሪን አስተላልፈዋል፡፡ ይህ በትክክልም ከአቅም ማነስና በራስ መተማመን ማጣት፣ አላማንም ጭምር በትክክል ካለመረዳት የሚመጣ ድምጽ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ነኝ ካሉ እዛው ቢገደቡ ጥሩ ነበር፡፡ የሌሎችን እገዛ ባላስፈለጋቸው፡፡ ቢያንስ ወላይታ፣ ከምባታ፣ ሐዲያ በኢትዮጵያዊነታቸው ያምናሉ፡፡ የቱንም ያህል ቀደም ባሉ ገዥዎች ተጨቁነዋል ቢባልም ጥያቄያቸው የማንነት አይደለም፡፡ አስተዳደራዊ በደል ካልሆን በቀር፡፡ እውነታው ደግሞ በየተኛውም መሥፈርት ዶ/ር በያንና ድርጅታቸው የሚያነሷቸው አይነት ታሪካዊ ጥያቄ የላቸውም፡፡

 በእኔ ግንዛቤ ዶ/ር በያን ውስጥ ጥላቻ አለ ይህ ጥላቻ ደግሞ መሠረታዊ ነገሮችን በደንብ ከማስተዋል አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር ፍቅሬ በልምምጥም ቢሆን ለዶ/ር በያን ሊነግሯቸው የሞከሩት ይህን እንድሆነና ማስወገድም እንዳለባቸው እየመከሩ ይመስላል፡፡ እውነታው የኦሮሞ ሕዝብ ያለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻውን ቢለቀቅ አመት ሳይቆይ ዘጠኝ ትንንሽ ሊሆን የሚችል ባሕላዊና ሌሎች ሰፊ የተባሉ ልዩነት ያሉት ሕዝብ ነው፡፡ ወለጋ ከሀረር፣ ቦረና ከሸዋ በጣም ይራራቃል፡፡ ቋንቋ አይደለም የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተሳስሮት ያለው! እውነታው ያ ነው! ድርጅቱ ውስጥ ኦሮሚያ ብቻ የሚል ኦነግ የተባለውን አይነት ደብቅ ድምፅ ይሰማል፡፡ አላማን ለማሳካት እውነትንና ለሕዝብ ታማኝነትን መሠረት ማድረግ እንጂ ሌላውን መጥላት፣ ወይም ከሌላው ጋር እውነት ባልሆኑ የእኔነት መቼም አይሳካም፡፡ ይሄንን የሚያሕል ግዙፍ ሕዝብ አጋር አለኝ እያሉ የእነኦነግ አይነቱ ድርጅት ውድቀት ከምን እንደሆነ ማሰብ መልካም ነው፡፡ በአጠቃላይ የዶ/ር ፍቅሬ ደብዳቤ ታሪክን ተረት ተረት በሚመስል ሌሎችን ለመለማመጥ በሚመስል አቀራረቡ ልክ ባለመሆኑ በጥርጣሬ እንድናያው አድርጎናል ወይም ተልፈስፍሶብናል፡፡ ታሪክ ተናጋሪው ነው አይደለም እንዲል እንጂ አንተና እኔ ብሎ ዝምድና ሊፈጥር አይገባም፡፡ የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ደብደቤ ግን መልዕክት አለው፡፡ ዶ/ር በያን ከዶ/ር ፍቅሬ የተጻፈላቸውን ደብዳቤ ልምምጫውን (እሳቸው እንዳሉት ማስመሰሉን) ትተውት ምን እውነታዎች አሉት ብለው ቢያነቡት ባዶ አይደለም፡፡ የተወሰነ ነገር እንደሚያገኙበት ይሰማኛል፡፡ ሰፋ ባለ አእምሮ ጠንካራም ነገር ሊገበይበት ይችላል፡፡ ሌሎች የሰጡት ትችት በአብዛኛው ከዶ/ር በያን ተመሳሳይነት ያለው ኢትዮጵያ የሚለውን አሁንም መስማት እንደማይፈልጉ የሚናገሩ ድምጾች ናቸው፡፡ ይሄንን አመለካከታቸውን ወደ ራሳቸው ተመልሰው ቢያዩት ጥሩ ነው፡፡ በጥላቻና በመፈራራት ሳይሆን ከሌላውም ጋር አብሮ በሚያስኖር በልበሙሉነት ሊናገሩት በሚያስችል ማስተዋል ቢሆን ምሁራዊነትን ያሳያል፡፡ 

በመጨረሻ የእኛን የማንም ብሔሮችን የማንወክለው ውስብስብ ኢትዮጵያውያንን ከሚገጥሙን ክስተቶች አንዱን ልንገራችሁና ላብቃ፡፡ አንዷ ኢትዮጵያዊ (ከእነ አያቷ መጥራት ማንነቷን ስለሚያሳወቅ የመጀመሪያ ስሟን ቀይሬዎለሁ የአባትና የአያቷ እንዳለ ነው) ሥሟ ሠላማዊት (ተቀይሯል) ደበላ ኪሮስ ነው፡፡ አንድ መስሪያቤት ልትቀጠር ትሄድና ብሔረሰብ ተብላ ትጠየቃለች፡፡ እኔ ብሔረሰብ የለኝም ብላ ትናገራለች፡፡ ጠያቂው የግድ ያስፈልጋል ይላታል፡፡ የእንጀራ ነገር ሆኖባት አማራ ትለዋለች፡፡ ጠያቂው ደግሞ መስማት ያልፈለገው ነበርና በንዴት ደበላ ብሎ አማራ አለ? ይላታል፡፡ አሷም ነገሩ አናዷት ነበርና ሰውዬው እንድትልለት የፈለገውን ስላወቀች ኪሮስ ብሎ ኦሮሞ አለ? ብላው በንዴት ቢሮውን ለቃለት ወጥታለች፡፡ ብዙ ሌሎች የሚገጥሙን ነገሮች አሉ፡፡ ብዙዎች የእዚህ ብሔረሰብ ነን ብለን መናገር የማንችል ዜጎች እንዳለን ለመረዳት እንኳን ፍቃደኞች አይደሉም የቱንም ያህል ብናስረዳቸውም፡፡ ለእኛም የዘረኝነት (ብሔረተኝነት) ነገር ባይገባን ለምን ይገርማል፡፡ ደግሞ የሰው ሞገሳዊ (Royal) ባሕሪ የእኛ ነው! ዘረኝነት አሳፋሪ ነው፡፡ አገሪቷን ለመመራትም አኛ በተፈጥሮ ብቁ አንመስላችሁም! አንዴ ውጥንቅጥ የሚል ፓርቲም ከእኛዎቹ የሞከሩ ነበሩ፡፡

አመሰግናለሁ!

ዘረ-ብዙው ኢትዮጵያዊ__

 D.Sertse Desta

No comments:

Post a Comment