Tuesday, September 24, 2013

ቅዱስ!ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያሕዌ!ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርሰቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመነፈስ ቅዱስ ሥም አንድ አምላክ አሜን!

ቅዱስ!ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያሕዌ!ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርሰቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመነፈስ ቅዱስ ሥም አንድ አምላክ
አሜን!
አቤቱ ቅዱስ አባት የዘላለም አምላክ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አእምሮዬን መልካም መልዕክትን እንዲያስተላልፍ እኛን
በሥጋ ተዛምደህን የክብርህ ወራሾች ልታደርገን ወደህ ከእኛ ወገን አናት ትሆንህ ዘንድ በመረጥካት በቅድስት እናትህ
ድንግል ማርያም ሥም እለምንሀለሁ! አሜን!
እኔ ማን ነኝ? እኛ ማን ነን? መንፈስስ ምንድነው? እውን ሰይጣን አለ? የሰዎች ውስብስብ ችግሮች
እንደሚባለው የሰይጣን ሥራ ናቸው? ሳይንስ በተለይ የስነሕይውት ሳይንስ ምን ያህል ሚስጢራትን
አውቋል? ሐይማኖትስ ምን ይላል? የሰዎችስ አምልኮት?
ሥለ መጨረሻ/ዳህራዊ እውነታ (Ultimate reality) ማወቅ መቼም ቢሆን የሚታሰብ ሊሆን አይችልም
ፈጣሪ ራሱ ይወቀው እንጂ ፡፡ በየትኛውም የዕውቀት ደረጃ ብንሆን የሰዎች ሁሉ ዕውቀት ተደምሮ
ከምላዐተ ዓለማት (The Universe) እውነታዎች (ሚስጢሮች) ኢምንት ወይም ምንም (ባዶ) ለማለት
በሚያስችል ሁኔታ ብቻ እናውቅ ይሆናል፡፡ ትንሽ ቆም ብለን ስለ ምልዐተ ዓለማት (ዩኒቨርስ) እናስብ፡፡
ሰማያትን፣ ምድርን፣ ፕላኔቶችን፣ ከዋክብትን፣ሳተላይቶችን ሌሎች ዓለማትንና በውስጣቸው ያሉትን
ሁሉ፡፡ ሳይንስ የቱንም ያህል አድጓል ብንልም የሌሎቹን ትተን ሰለምንኖርባት ዓለም (ምድር)ና በውስጧ
ስላሉት ነገሮች እንኳን የሚያውቀው በጣም ትንሽ እንደሆነ አይክደም፡፡ ከሳይንሶች ደግሞ ትንሽ የተሰናዘረ
(የተሻለ) እድገት ያሳየው የቁሳዊው (Physical) ሳይንስ ነው፡፡ ይህ ሳይንስም ቢሆን አሁን ባለን ግንዛቤ
እምርታ የምንለውን ያህል እድገት ያሳየ ቢመስለንም የብዙ መጨረሻ ዕውነታዎችን ስናስብ ግን ብዥታው
የበዛ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ ጭራሽ ክፍል ገብተን ስለተማርን ያወቅን ስለሚመስለንና
አእምሮአችንም አስተማሪ የተባሉትን ከመስማት በቀር ለምን ብሎ እንዲጠይቅ እድል ስላልፈጠርንለት
ጥልቅ ዕውቀት እንዳለው ድምዳሜ ስንሰጥ ሌላ ብዥታ በመፍጠር መሳሪያዎች ሆነናል፡፡ ለነገሩ ለምን
ብለን ብንጠይቅም ማን ሊመልስልን ይችላል? አብዛኞቹ አስተማሪዎቻችንም አይጠየቄ አይነት ነበሩ፡፡
ጥቂት ምሳሌዎች ብጠቅስ ብዙዎቻችን ተምረን ያለፍንውን አቶም (Atom)ን እንውሰድ፡፡ አሁን ባለው
ሳይንስ ምን እንደሚታወቅ አላውቅም፡፡ እኔ ስማር የተነገረን አቶም የቁሳዊ ነገር ትንሹ (መነሻ) አካል
ተብለን ነው፡፡ እሱም ኤሌክትሮን፣ፕሮቶንና፣ ኒውትሮን የተባሉ ዋና ዋና ነገሮች (Elements) እንዳሉት
ተነገረን፡፡ ጠለቅ ያሉት ፎቶንስና ሌሎች ጥቃቅን ነገሮችም እንዳሉት ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ለእኔ ግን ጥያቄ
ግርድፉ ይበቃኛል፡፡ አቶም ፕሮቶኖችንና ኒውተሮኖችን የያዘ ኒውክለስ የተባለና ኤሌክትሮኖች የሚዞሩበት
ምህዋር (ኦርቢት) እንዳለው ተነገረን፡፡ ፕሮቶኖች ፖሲቲቭ ቻረጅ ኤሌክትሮኖች ደግሞ ኔጋቲቨ ቻርጅ
እንዳላቸው ኒውትሮን ግን ቻርጅ አልባ እንደሆነ አስተማሩን፡፡ ቀጠሉና አስተማሪዎቻችን ተመሳሳይ
ቻርጆች (like charges) ይገፋፋሉ (repel each other) ተቃራኒ ቻርጆች ይሳሳባሉ (attract each
other) አሉን፡፡ ከዚህ በኋላ ጨቅላው/ወጣቱ አእምሮአችን ጥያቄ አነሳ! ኒውክለስ የተባለው
እንደመረብ/ከረጢት ያለ ፕሮቶኖችንና ኒውትሮኖችን አምቆ የሚይዝ ነገር ነው? አይ አደለም ምንም
አይነት ከረጢት ወይም መረብ የለም ብቻ ማህል ላይ ፕሮቶኖቹና ኒውትሮኖቹ ተቀቅፈው ያሉበት ቦታ
ነው ተባልን፡፡ እንዴ ፕሮቶኖቹ ተመሳሳይ ቻርጅ እያላቸው መገፋፋታቸውን (ሲሆን እንደመፈንዳት)
ትተው እንዴት አብረው ተቃቅፈው ይቀመጣሉ? በዚህ ላይ ከውጭ በኩል የፕሮቶኖች ተቃራኒ ቻርጅ
ያላቸው የኤሌክትሮኖቹ ስበት አለ፡፡? ኒውትሮኖቹም ቢሆን የሚያግዳቸው ነገር እስከሌለ ድረስ ዝም
ብለው መፈሰስ ሲገባቸው ምን እዛ አስተፋፈጋቸው? እነዚህንና የመሳሰሉትን ጠይቀን አስተማሪዎቻችን
ጥሩ ከሆኑ ወደፊት ታውቁታላችሁ ብለውናል ብዙ የምናውቃቸው አይነት ከሆኑ ደግሞ ጃስ ብለው
አስደንግጠውን ሁለተኛ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን እንዳናነሳ እንዳናስብም አድርገውናል፡፡ መልሱን ግን
ማንም አልመለሰልንም፡፡ አንዳንዶቻችን አእምሮአችን ፋታ ስላልሰጠን ወደፊት መባላችንን ስላልፈቀድን
ወደ ቤተ መጻሕፍት ሄደን በክብደት (ኪሎ) አኛን የሚበልጡንን መጻህፍት ማተራመስ ጀመርን፡፡ ትዝ
ይለኛል ሲርስ ዘመንስኪ (አንዳነዶች ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ዘመነ-ስቃይ የሚሉት) ኮሌጅ ፊሲክስ የሚል
ግብዳ መጽሀፍ ማገላበጡን ተያያዝንው፡፡ Nuclear Force የሚል ርዕስ ላይ ጥያቄያችን ለዓለምም
ሳይንቲስቶች ጥያቄ ሆኖ ቁጭ ብሏል!! ልክ አኛ የጠየቅንውን ጥያቄ አንስቶ በወቅቱ እስካሁንም ድረስ
የኒዩክለስ ኃይል አይታወቅም ይል ነበር፡፡ ለመሠረታዊው ጥያቄያችን መልስ ባናገኝም ጥያቄያችን ትክክል
እንደነበርና መጠየቅም እንደምንችል ማስተማመኛ ስላገኘን ተደሰትን፡፡ መልሱንም ለመመለስ የሚያስችል
ምርምር ለማድረግ የሚያስችል አቅም አእምሮአችን እንደነበረው አመላክቶን ነበር፡፡ ወደፊት ብለው
ተስፋ የሰጡንም እንደው ፊዚክስ የተባለውን የተማራችሁ ደርሳችሁበት ይሆናል፡፡ ብዙውቻችን ግን
አቅጣጫ ስለቀየርን እንዳንደርስበት ጉዞ ሄደናል፤ ርቀናል (ረስተንዋል) የተወጋ (ጃስ የተባለ) አይረሳ ሆኖ
ካስታወስን እንጂ፡፡ ምን አልባት የክብደት ስበታቸው (attraction between two masses) ከፍተኛ
ስለሆነ ይሆን? ከዚሁ ከፊዚክስ ሳንወጣ የብዝሀ (quantum) ፊዚክስ ጠበብቶች አንድ ቁስ በአንድ ጊዜ
ከአንድ ቦታ በላይ መገኘት ይችላል ይሉናል፡፡ ጉድ ፈላ! አንድ ሰው በአንድ ጊዜ (በተመሳሳይ ወቅትና
ሰዓት፣ ደቂቃ፣ሰኮንድ) ኢትዮጵያም ሌላም አገርም መኖር ይችላል ማለት ነው!! ደግነቱ እንደኛ የገዘፈው
አካል ያንን መስፈርት ለማሟላት ሌላ የማይሆን መስፈረት ተቀምጧል፡፡ በብርሃን ፍጥነት መጓዝ
(በሰኮንድ 300000 ኪ.ሜ)፡፡ ማን ያውቃል አንድ ቀን እንጓዝ ይሆናል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው
ኤሌክትሮኖች የተባሉትን ግን አሁንም እንዲህ ያለ ባህሪ (በአንድ ጊዜ ከአንድ ቦታ በላይ መገኘት መቻል)
እንዳላቸው ይነገርላቸዋል፡፡ እኛ የምናውቀው ግን መናፍስት ብቻ እንደዚህ ያለ ባህሪ እንዳላቸው ነው፡፡
ወይም ደግሞ በሁሉ ቦታ ያለ ተብሎ የተነገረን እግዚአብሔር ነው፡፡ ጠበብቶቹ ምንአልባት
የእግዚአብሔርን ባሕሪ በቀጥታ ላለመቀበል ያመጡት ማደናገሪያ ይሆን? እንጃ! ይህ ፍልስፍና የቆየ
በተለይም በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የነበሩት የነ ማክስ ፕላንክ ፅኑ እምነት ቢሆንም ዛሬም ግልፅ
ለመሆኑ እኔ አቅጣጫ የቀየርሁ ስለሆነ ምን እንደሚባል አላውቅም፡፡ የቁሳዊው ሳይንስ ግን ይሄው
እንደምናየው ዓለምን አንድ መንደር አስመስሏታል፡፡ ይህም ሆኖ ከዳህራው እውነታ (Ultimate reality)
አንጻር እድገቱ ምናአልባትም ኢምንት ያህል ነው ሊያሰኘው ቢችልም፡፡
ወደ ስነሕይወቱ ሳይንስ (Biology) ስንመጣ እናውቃለን ብለን ለራሳችን ከምናፍር አናውቅም ግን ማወቅ
እንፈልጋለን ማለቱ የብልህ መልስ ነው፡፡ ምክነያቱም የመጀመሪያዋ ሕይወት የምትለዋ ቃል ራሷ በትክክል
ትርጉም ያልተገኘላት እንቆቅልሽ እንደሆነች ነው ያለችው፡፡ ይህ ሳይንስ በታሪክ አንጻር የሰው ልጆች
ታሪክን የሚፎካከር እድሜ ቢኖረውም ዛሬም ጨቅላ (Infant) እየተባለ የሚጠራ ነው፡፡ እንደውም ከላይ
የተጠቀሰው የቁሳዊው አካል (ፊዚክስ ወይም ኬሚስትሪ የተባሉት) ሳይንስ እገዛ ባይኖር ፅንስ ብቻ ሆኖ
በቀረ ነበር፡፡ በሌላ መልኩ ሲታይ ከነጭርሱም አቅጣጫ የሳተ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ በሚያሰኝ
ሁኔታ የሚዳክር ይመስላል፡፡ ምናአልባትም የዚህ ሳይንስ መሰረት የነበሩት ጥንታውያኑ የዓለማችን
ክፍሎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ሕንድ፣ አረቦችና፣ የሩቅ ምስራቅ አገራት ጠለቅ ባለ ሁኔታ ገፍተውበት ቢሆን
የተሻለ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ በአካላዊ ጥረታቸው (Physical endeavor) እንጂ ከሕይወት ጋር በተያያዘ
ጥልቅ የሆኑ ሚስጢራትን ብዙም በማይደፍሩት በምዕራባውያን እጅ መውደቁ ለዚህ ሳይንስ ሳያድግ
ማርጀት እንደተባለውም መንገድ መሳት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
የአንድ የዳርዊን የዘገምተኛ ለውጥ ፍልስፍና ዛሬም ድረስ መቋጫ ያልተበጀለት ብዥታ ሆኖ ላለፉት 200
ዓመታት ቀጥሏል፡፡ይህ ፍልስፍና ዛሬ በስነሕይወቱ ሳይንስ ዘርፍ ጭላንጭል ያስገኘውን በተግባር ተሞክሮ
የተገኘውን የኦስትሪያውን መነኩሴ የሜንድልን ውጤት እንኳን ለዘመናት አፍኖት ኖሯል፡፡ እዚህ ጋር እኔ
የዳርዊን ፍልስፈናን ከሃይማኖት አንጻር ሳይሆን በትክክልም ከምገነዘበው እውነታ መሳት ጋር እያነሳሁት
ነኝ፡፡ ምዕራባውያኑ በተለይም የረጅም ጊዜ የሕይወት ታሪክ የሌላቸው (የዳርዊንን አገር እንግሊዝን
ጨምሮ) የአካል ጥረታቸው አጅግ የሚያስደንቅ ቢሆንም የሕይወት ሚስጥራዊ ለሆኑ ጥበቦች
አእምሮአቸው አቅም ያለው አይመስልም፡፡ ጭራሽ ዳርዊናውያን እኛው አገር መጥተው አጥንት
እየለቃቀሙ የሰው ልጆች አባት አዳም ሳይሆን ራሚደስ የተባለ ጦጣ ከሚመስሉ ዝርያዎች የተወለደ ነው
አሉን፡፡ በድፍረትና በእርግጠኝነት የሚናገሩት የአመታት ቁጥርም የሚገርም ነው፡፡ ከሚሊየን ከቢሊየን
ዓመት በፊት እንዲህ ነበር ይሉናል፡፡ ነገሩ "አንበሳ ምን ይበላል ተበድሮ ምን ይከፍላል ማንአባቱ ጠይቆት"
አይነት ነውና እኛም ያሉንን ሁሉ ከመቀበል ሌላ ልክ አይደላችሁም ልንል የምንችልበት አቅም የለንም፡፡
ይባስ እኛም በሙሉ ልብ አመናቸው! እንግዲህ እኛ ነን እግዚአብሔር አለ ብለን የምናምነው!? ወይ ራስን
መሸወድ! ረገጥ አድርገን እንቁምና አናስብ! ሰው ሲፈጠር ሰው ሳይሆን በዘገምተኛ ለውጥ ሂደት ነው ሰው
የሆነ ብሎ የሚያስብ በምን መስፈርት ነው እግዚአብሔርን የሚያምነው?! እግዚአብሔር አይሸወድም
ራሳችንን ግን ሸወድን!
በአንጻሩ የእኛን ጨምሮ ከላይ የጠቀስኳቸው አገር ሕዝቦች ለሕይወት ሚስጥራዊ ጥበቦች የተሻሉ
ቢሆኑም እነዚህን ጥበቦቻቸውን ገሃድ ለማውጣትና ለትውልድ ለማዳረስ ዘገምተኞች በመሆናቸው
እውቀቶቻቸው ከኋላ ቀርነት አስተሳሰብ እየተቆጠሩ እየኮሰመኑ በምዕራባውያኑ ተራ እውቀቶች ተፅእኖ
ስር ወድቀዋል፡፡ አልያም ስግብግቦችና ይልቁንም ዕውቀታቸውን ሚስጢራዊ (ለክፉ ሥራ ጭምር ሊሆን
ይችላል) መጠቀሚያ ስለሚፈልጉ ለራሳቸው ብቻ ሚስጢር አድርገው ይኖራሉ፡፡
ቀላል ምሳሌ ብናነሳ ብዙ የባሕል መድሐኒት አዋቂቆቻችን ኋላ ቀር እየተባሉ ሲወገዙ ቆይተው ድሮ እንሱ
ያድኗቸው የነበሩ በሽታዎች (ካንሰርን ጨምሮ) ዛሬ ከሞት በቀር ሌላ መፍትሔ የላቸውም ተብለን ተስፋ
የሚሆን ነገር እንኳን አጥተን ፈዘን ተቀምጠናል፡፡ ጠይቀን አንኳን እንዳንረዳ እነዚያ ጥቂት የነበሩ
ባለመድሐኒተኞች ሞተዋል፡፡ ዛሬ እናውቃለን የሚሉን የባሕል ሀኪሞቻችን ውስጥ እነዚያ የድሮዎቹ
ምርጦቹና የተለዩ የተባሉ በሽቶችን የሚያድኑት የሉም፡፡ ዛሬም ያሉትንም ቢሆን ትኩረት ሰጥተን ምን
አላችሁ ብለን ወደሳይንሱ ለመቀላቀል አልሞከርንም፡፡ እነሱም የዋዛ አይደሉም፡፡ ሚስጢር ናቸው፡፡
እርግጥ ነው በሌሎቹ የጥንት የስነሕይወት ጠቢባን (በሕንድ፣ ቻይናና በመሳሰሉት) አሁን አሁን ከፍተኛ
ትኩረት ተሰጥቷቸው ጥበቡ የሳይንሱን ጎራ እየተሳተፈ ነው፡፡ እኛ ጋር ዛሬም ኋላ ቀር ናቸው፡፡
ለብዙዎቻችን እናውቃለን ለምንለው ግን እውቀታችን ውሱን ለሆነው አፋችንን ሞልተን ለመናገር
ድፍረቱን በናገኝም በዘመናዊው ሳይንስ በጣም የጠለቁት ግለሰቦች ግን መሠረቱም መቋጫውም ግራ
ገብቷቸው ይገኛሉ፡፡ ለነገሩ ትንሽ ማወቅ ድፍረት ይሰጣል የሚጨነቀው ሚስጢሩን የደረሰበት ነው፡፡
የሰው ልጀ የዘረ መሎች አወቃቀር (Genome sequence) ሲታወቅ የሰው ልጆች የጤና ችግሮች ሁሉ
መፍትሔ ይኖራቸዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ በሞሆኑም በብዙ ወጭና ብዙ ላቦራቶሪዎች
ተሳትፈውበት ይህ አወቃቀር ታወቀ፡፡ የተባለውን መፍተሔ ግን አላመጣም፡፡ ለሕክምናው መርዳቱ
የማይካድ ቢሆንም፡፡ አሁን አሁን እንደውም ከመሳሪያዎች ምቾትና የመረጃ ሰጭነታቸው ብቃት ጋር
በተያያዝ የሳይንቲስቶቹና ሌሎች በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ተፈጥሮአዊ የአእምሮ የመመራመር አቅማቸውን
እያሰነፈ የመጣ ይመስላል፡፡ እንኳንስ የጥንቶቹን የስነ-ሕይወት ረቂቅ ሚስጢሮችን ለማወቅ ቀላል የተባሉ
ነገሮችንም ለማስተዋል አእምሮ እየደከመ መጥቷል፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግድየለሽነቱም፡፡ ሁሉንም
ባይወክልም ብዙ የሚባሉ የኛዎቹን ሐኪሞች እንውሰድ፡፡ መሳሪያ የነገራቸውን መረጃ ብቻ በመያዝ
በሕክምናው አእምሮን በማስጨነቅ ከብዙ መፍትሔ በኋላ መምጣት የነበረባቸውን የሕክምና እርምጃ
ወዲያውኑ ይተገብራሉ፡፡ ለምሳሌ ቀዶ ጥገና! በዚህ ምክንያት እንድናለን ብለው ተስፋ ያደረጉ ታካሚዎች
ጭራሽ ለባሸ ችግር ይጋለጣሉ፡፡ ሕይወት በእርግጥም ሚስጢር ናት! ከነዚህ በእጅ ከሚዳሰሱ በአእምሮ
ከሚታሰቡ እውቀቶቻችንም በላይ! ጥቂት የማንባል ሰውች ብዙ ለሰዎች አስደንጋጭ የሚባሉ ዓይነት
ጥያቄዎች ሳይቀር አሉን፡፡ ግን ለመመለስ አዳጋች ስለሆኑና ሰዎችንም ስለሚያስደነግጡ ጭምር ለሌሎች
ማካፈል ያስቸግራሉ፡፡ በጥልቀት መመራመር አያሰፈልግም እንዲሁ በግርድፉ መኖር ይሻላል እያልኩ
አይደለም! ግን መጀመሪያ ዋናውን በደንብ ሳናቅ ባህር ውስጥ ብንገባ አደጋም ሊኖረው ይችላል!
ከዚህ ሁሉ ሀተታ በኋላ ግን ላነሳው የፈለገሁት አሁንም ሕይወት (ነፍስ) አውን ምንድናት? እኛስ (ሰዎችን
ጨምሮ ሕወት ያለው ሁሉ) ማን ነን?! እኔ ራሴ ማን ነኝ?! በሐይማኖት በኩል የሚነገረውስ ነገር እውነት
ነው ወይ? ብዙዎቹ ሐይማኖቶች በአካል ስለማይታይ ሌላ አካል (መንፈስ የሚባል ነገር) እንዳለ
ይናገራሉ፡፡ እውን መንፈስ አለ? ካለስ ምንድነው? ምን ያህሎቻችንስ አለ ስለሚባለው ስለመንፈስ
እናውቃለን? እስኪ ሳንደባበቅ በዚህ ጉዳይ እንወያይ! ሰይጣን የሚባል ነገር አለ ወይ? አለ የምትሉ እንዴት
ልታዎቁ ቻላችሁ? ለመሆኑ ብዙ የጤና ችግሮች እውን እንደሚባለው ከሰይጣን ጋር ተያያዥነት አላቸው?
በጸበል በጸሎት ወይም ያለምንም ሕክምና ሐይማኖታዊ በሆነ ትእዛዝ የሚድኑ በሽታዎችስ አሉ?
ሐኪሞችስ ስለዚህ ነገር ምን ይላሉ? ሐኪሞች ሆይ ካለ አለ በሉ ኋላቀር የምተሏቸው ድርጊቶች የእናንተን
ኋላቀርነት ለማረጋገጥ በተግባር በማሳየት እንዳያሳፍሯችሁ! የምታዩትን ተናገሩ ምክነያትም ካገኛችሁለት
ለመስማት ዝግጁ ነን፡፡ ሌሎችም የካርቦን ዴቲንግና ሳይንቲስት ነን የምትሉና ዳርዊያውያንም እስኪ
ተጠየቁ! መተት፣ ዛር፣ ዉቃቤ ምናምን የሚባል ነገር አለ? ከድሮ ጀምሮ አሰማለሁ፣ አንዳንዴም ሲከሰቱ
አያለሁ ግን እውነት ለመሆናቸው እንዴት ማረጋገጥ ይቻለል፡፡ በአንዳነዶቻችን አትፍረዱብን
ባናውቃቸው፡፡ እኔ በግሌ ሲሉ እሰማለሁ እንጂ በጸበልም ሆነ በጸሎት በተረጋገጠ በሽታ ተይዘው የዳኑ
አላየሁም ነበር፡፡ ያስደነገጠኝንና ብዙ ጥያቄዎች ውስጥ የከተተኝ (እኔ ማነ ነኝ እስክል) ክስተት ለማየት
ከበቃሁ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፡፡ አሁንም እራሴን እንደጠየቅሁ ነው፡፡ እግዚአበሔር ይቅር ይበለኝ! ይህ
ለእኔ አስደንጋጭና ልዩ የሆነ ክስተት ግን በብዙዎች ዘንድ አዲስ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ የት ነበርኩ እስከምል
ድረስ ብዙዎች የሚያውቁት ግን በገሀድ የማያወሩት የሚያነሾካሽኩት ጉድ ነው!! አንዳንዶችም የሚኖሩት፡፡
የሚገርመው ሳይንቲስት ነኝ የሚለው ሳይቀር ለሌላው አላምንበትም እያለ ራሱ በየደብተራውና ጠንቋዩ
ሲልከሰከስና ሲያፈነድድ ነው የሚታየው፡፡ እኛ ጅሎቹ እንዳንነቃባቸው ግን እጅግ ተጠንቅቀው ነው
የሚኖሩት! እስካሁን ሐኪም የሆነ ሰው አልጠየቅሁም፡፡ ለጊዜው ሊክደኝ ይችላል ይሆናል ግን
በለመድኳቸው ጥያቄዎች ባጣድፈው ከነሱም ብዙዎቹ ሳይወዱም ቢሆን የሚያምኑትን መባረቃቸው
አይቀርም፡፡ ልብ በሉ ከላይ እንደነገርኳችሁ ሰምቼም ነበር አንዳንድም ሰዎች የሚያደርጓቸውን ድርጊቶች
አይቻለሁ ግን ከተራ ነገርነታቸው የዘለለ እምብዛም ትኩረት አልሰጠኋቸውም፡፡ ግን በሽታም ሲሆኑ
በሐይማኖታዊ ስርዓት ሲለቁም አላየሁም ነበር፡፡
ታዲያ አሁን እንዴት አወቅህ (ነቃህ) እንደምተሉኝ እጠብቃለሁ፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችሁ መምህር ግርማ
ስለተባሉ መንፈሳዊ ሰው የሰማችሁ ይመስለኛል፡፡ ደግሞ እዚህ ጋርም እንዳትዋሹኝ፡፡ ለእኔ ከአንድ
ጓደኛዬ በቀር የነገረኝ (ቢነግርኝ አላምነውም ነበር ቪሲዲ አምጥቶ ባያሳየኝ) በቀር (ሁለት ዓመት ዓመት
ከ3 ወር ይሆነዋል) ከዚያ በፊት ከአንድም ሰው ስለኝህ ሰው የሰማሁት ነገር የለም፡፡ ከዚያ በኋላ ስጠየቅ
ሁሉም ሰምቶ እኔ ብቻ ያልሰማሁት ጉዳይ ነው የመሰለኝ፡፡ ሁሉም የጠየቀኋቸው ቢያንስ ሰምተዋል፡፡
ብዙ ሰው ይባስብሎ ከሰባታ ከስምንት ዓመት በፊት እንደሚያውቃቸው ሁሉ ይነግረኛል፡፡ የሚገርመው
እኔን የስገረመኝና ብዙ ነገሮችን ያሳሰበኝ ጉዳይ ለብዙዎች አዲስ አይደለም፡፡ እንደሚነግሩኝ በፀበል ቦታ
በሌሎችም የእምነት ቦታዎች ይህ የተለመደ ነው፡፡ መምህሩ የሚሰሩት በአስማት ነው የሚሉኝም አሉ፡፡
ለእንደኔ ያለው በአስማት ሆነ በእግዚአበሔር ኃይል ለጊዜው ጉዳዬ አይደለም! ለእኔ ጉዳዬ የነበረው
በየትኛውስ ኃይል ቢሆን እንዲህ ያለ ነገር አለ ወይ? የሚለው ነበር!! ከእኔና አኔን መሰል የተወሰኑ የአገሪቱ
ጅሎች በስተቀር ስለመተትም፣ ሌሎች የመናፍስት ድርጊቶች ያውቁም ነበር ብዙዎችም የሚሞክሩትና የኑሮ
ስልት ያደረጉት ጭምር፡፡ የታዘብኩት እንደነዚህ ያሉ ነገሮች በገሀድ እንደማይወሩ ነው፡፡ ይባስ ብሎ ሰው
በአብዛኛው የሚያውቀዉ በሰይጣን በተባለው የሚሰራውን እንጂ በእግዚአበሔር ኃይል ሲባል
ይከብደዋል፡፡ ለእዛም ሳይሆን አይቀርም መምህር ግርማም የሚሰሩት በአስማት ነው የሚለው፡፡ እኔ ግን
የእግዚአብሔር ኃይል እንደሚሳራ በሥሙ ሰዎችን እጅግ አሳቃቂና ውስበስብ ከሆኑ ችግሮች መምህሩ
ሲፈውሱ አየሁ እንጂ ሌላ ያየሁት አለ ብል እግዚአበሔር እንደሚፈርድብኝ አምኛለሁ፡፡ የቀድሞው
እውቀቴና ፍልስፍናዬ እግዚአብሔርን ከመካድ አይተናነስምና፡፡ ሰይጣን የለም ብሎ ማመን በራሱ
እግዚአበሔርን መካድ ነው፡፡ ስለምንፈራ ብቻ እግዚአበሔርን በግልፅ አለመካድ እምነት አለን ለማለት
አያስደፍርም፡፡
አሁን ነገሮችን በጥንቃቄ እንዳይ ተገድጃለሁ! በአንድ ወቅት አንድ ጠንቋይ አዲስ አበባ ውስጥ ለጉድ ነግሶ
በኋላ ወንጀለኛ ነው ተብሎ በቴሌቪዥን ሳይቀር ሲቀርብ አኔ ሰውየውን በሰውኛው እሱ ጋር ሄደው
ከሚያነግሱት ሰዎች በላይ ወንጀለኛ ነው ብዬ ለመቀበል አልወደድኩም፡፡ እውነታውም ብዙዎች በመቶ
ሺዎች ሳይቀር እየገበሩት ይከተሉት ነበር፡፡ ትልልቅ ናቸው የሚባሉት ሳይቀር ጉዳያቸው በሚስጢር
ተያዘላቸው እንጂ የዚህ ሰው አምላኪ ነበሩ፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው እኛን ጅሎቹን ሳይንስ እንዲህ ይላል
እያሉ የሚያደናግሩን ሁሉ የዚህ ሰው መንፈስ አገልጋዎች ሆነው እንደታዩም ተሰምቷል፡፡ በወቅቱ ጎበዝ
አታላይ ነው ብዬ ነበር፡፡ ሰዎቹም የተታለሉ፡፡ አሁን ነገሮች ሲገቡኝ ግን እሱም ወዶ አይደለም ሰዎችም
የተከተሉት ወደው አይደለም፡፡ ሁሉም ግን ከመሠረቱ አጅግ ክፉዎች ስለነበሩ ለማይወዱት መንፈስ
ተገዥዎች ሆነዋል፡፡ የክፉ ዘሮች ነበሩና! በመቶ ሺዎች የሚገብረው የሌላ ወንድሙን ንብረት ለመቀማት
ሕይወት ለማጥፋት ነበርና፡፡ እኔ አሁንም ቢሆን የምታዘበውና የበለጠ ወንጀለኛም የማደርገው ገባሪዎቹን
ነው፡፡ ከዚህኛው ወንጀል አንጻር በትኛውም አሳቃቂ ሁኔታ በጉልበት ኃይል የሰው ነፍስ ያጠፋ ወንጀሉ
እጅግ የቀለለ ነው ለእኔ፡፡ እንደነዚህ ያሉት አንድን ነፍስ ብዙ ጊዜ አሳቃቂ በሆነ ሁኔታ ይገድላሉና፡፡
ሰውዬውም ቀይ መስመር ስለረገጠ ወንጀለኛ ተባለ እንጂ የስንት ደሀዎችን አምባ ሲያፈስ የመኖሪያ ቤት
ሳይቀር ከሰዎች በጉልበት ሲነጥቅ መች ወንጀለኛ ነበር፡፡ ኢቲቪም ሆነ መንግስት በወቅቱ ያጋለጡት
የራሳቸውን ገበና ነበር እንጂ የሰውየውን አልነበርም፡፡ ያ ሁሉ ሲደረግ የት ነበሩ፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት ግን ብዙ ሕዝባችን በእግዚአብሔር ኃይል ከሚደረጉት ክስተቶች ይልቅ የሚያምነው
በክፉ መናፍስት የሚደረገውን ነው፡፡ ብዙዎች አሁንም ሳይቀር ሊሸውዱን ይሞክራሉ፡፡ ለእኔ ቀድሞ ጅል
መሆኔ ጠቅሞኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ የሚያሳዝነው ሀይማኖተኛ የተባለው ሕዝባችን ሀይማኖተኝነቱ
ሰይጣንን በማመን አንዳንዱም ሳያውቀው በሀይማኖት ሽፋን የሰይጣን አገልጋይ በመሆን እንጂ
እግዚአብሔርን በማመን ለመሆኑ አጠያያቂ ሆኖብኛል፡፡ የሰሜኑ ክርስቲያን ነኝ ባዩ ዋናው የመታችና
አስመታች ዘር ነው፡፡ በየቀኑ ደብተራ ሳያይ የማይውል ቤተክርስቲያን ግን ለአመት በዓል ብቻ የሚታይ
አስደናቂ "ክርስቲያን"! በከተሞች ጠዋት ነጠላ ለባሽ ከሸዓት ጠንቋይና ደብተራ አሳሽ! በሌላው የአገሪቱ
ክፍል በባሕል የተሳበበ የክፉ መንፈስ አምልኮ፡፡ ከላይ የጠቀስኩት በአብዛኛው ኦርቶዶክስ ተከታይ ነኝ
የሚለው ሕዝብ ባሕርያት ሲሆን የሌላው አይነት ክርስትና ደግሞ በዘመናውያኑ ዛር አነጋሽ ልሳን ተናጋሪ
ነኝ እያለ የእግዚአብሔርን ቅዱሳን እየተሳደበ እግዚአብሔርን አመልካለሁ የሚል፡፡ እውነታው ከነዚህ
ሁሉ "ክርስቲያን" ነን ከሚሉት ይልቅ በእስልምና አማኞች ብዙም በስውር ባሉ የክፉ መናፍስት
አገልጋይነት የሚጠቃ የለም፡፡
አሁን እንደገባኝ በድብቅ የክፉ መናፍስት ሴራ ጠፍተናል፡፡ የክፉ መናፍስትን ሴራዎች ለማጋለጥ
ብዙዎቻችን(ሁላችንም ማለት ሳይሻል አይቀርም) ደፋሮች አይደለንም፡፡ ምንአለባት የራሳችን የውስጥ
ክፋት ይህንን አቅም እንድናጣ አድርጎናል፡፡ ሁሉም በሹክሹክታ ነው፡፡ እስካሁን ክፉ መናፍስትና
አገልጋዮቻቸው ጥቂት ሊነቁ የሚችሉ ሰዎች ስለቀሯቻ በድብቅ ነበር አሰራራቸው፡፡ ወደፊት ግን ሁሉም
የእነሱ ሲሆን እንደፈለጋቸው በገሀድ የሚፈነጥዙበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ በቀላሉ በብዙ አገራት
ተቀባይነት እንዲኖረው እየተደረገ የመጣውን የግብረሰዶማውያን አስተሳሰብን እናስተውል፡፡
ቤተክርስቲያናት የተባሉት ሳይቀሩ እየተቀበሉት እንደመጣ፡፡
የክፉ መናፍስተ ሴራዎች ለተከታዮቻችው የመረጃ ቅብብሉ በብዙ መልኩ የታገዘ ነው፡፡ ከጥንቆላ እስከ
ፍልስፍና የሚመስሉ የክፉ መንፈስ አሰራሮች ትክክል ናቸው እየተባለ ሳይንሳዊ ትንታኔ ሳይቀር
ሊሰጥባቸው ይሞከራል፡፡ ጀሌዎችም አዎ ልክ ነው እያሉ ከመረቡ ይገባሉ፡፡ የእግዚአብሔር ከተባለ ግን
ችግር አለ! እንዲያ ባይሆን 20 ዓመት ሙሉ እንዲህ የክፉ መናፍስትን ሲራ ሲያጋልጡ የኖሩትን መምህር
ግርማን በሚዲያ ምንድነው እየሆነ ያለው ብሎ ያናገራቸው አልነበረም፡፡ ግን ግን ይሄ ሁሉ ጉድ ሲደረግ
ሚዲያዎችስ ለምን ድፍረቱን አጡ፡፡ ከዚህ በላይ ሚዲያዎች ምን አዲስ ነገር ሊነግሩን ይፈልጋሉ?! ጉዳዩን
ሚዲያዎች መዘገብ ያለባቸው ከሐይማኖት አንጻር የግድ መሆን የለበትም፡፡ እውነታው ለሰዎች ጠቀሚ
መረጃ ነው ብዬ ስለማምን ሰዎችስ የየራሳቸውን ወሬ በማሰራጨት የተዛባ መረጃ ለማያውቁ ከሚደርስ
ሚዲያዎች በቀጥታ እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን በማነጋገር ጭምር ትክክለኛውን መረጃ ለሕዝብ ቢያደርሱ፡፡ ያኔ
ለእኔ እውነትም ባይመስል ኦፕራ ዊነፍሬ ጆን ኦፍ ጎድ የተባለ የአንድ ተመሳሳይ ብራዚላዊ ሰው ለሚዲያ
በማብቃቷ ሐኪሞች ሳይቀሩ በቦታው ተገኝተው አይተው ሥራቸውን እንዲያስተውሉ እድል ልትከፍት
በቅታለች፡፡ አቢሲኒያ ሬዲዮ የተባለ ከአሜሪካን አገር የመምህር ግርማን ጥልቅ የሆነ የሐይማኖት
ትመህርትና አንዳንዴም ገጠመኞቻቸውን በየሳንምንቱ እንደሚያስተላልፍ አውቃለሁ፡፡ አገሪኛዎቹ መገናኛ
ብዙሀን ግን ምንም ሲሉ አልሰማቸውም፡፡ የእኛስ ሐኪሞች ምን አልባት የሚጠቅማቸውን እውቀት ከዚህ
ቢያገኙ፡፡ እንደ መምህሩ ብዙ በሽታዎች ከመናፍስት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ከታወቁት ለመጥቀስ ያህል
ነርቭ፣ ዲስክ፣ አስም፣ ስኳር፣ ሌሎችም፡፡ በትክክልም እንዲሁ ሆነው ተገኝተው ሰዎች ሲድኑ ይታያል፡፡ ግን
ምን ይባላል!? ዋናው ጤና ብዬ የጤናውን ጉዳይ አነሳሁ እንጂ ነገሩማ ከዚህም በላይ አለ፡፡ መስለብ፣ ንብረት
ላይ የተለያዩ ችግሮችን መፍጠር በአጠቃላይ የኑሯችን ውስብስብ ችግሮች ከመናፍስት ጋር ሊያያዙ
እንደሚችሉ ነው አኚህ መምህር የሚናገሩት፡፡ መምህሩ (እኔ ፈላስፋው ብላቸው ነው
የሚመቸኝ)ንግግራቸውን በተግባር በማሳየት ነው እየሞገቱን ያሉት!! ንብረት ምናምን መስለብ እኔ
አልመንበት እንጂ ድሮም አሰማ ነበር አእምሮና እድል ይሰለባል ሲባል ግን የበለጠ አስገራሚ ነው እውነት
ከሆነ!? በአንዱ ብሩህ አእምሮ ሌላው ሊማር ሊኖር ይችላል! መንፈስ የተባለው (ሰይጣኑ) ከተሰለበው ሰው
ሲወጣ ግን ሰላቢው ሊያብድ ሁሉ ይችላል፡፡! ጉድ ነው መቼም!! ጅሎቹ አበሾች በዚህ ዓይነት አልቀናል!!!
ይህን ጥያቄ የሞላበት መልዕክት ለአንባቢዎች ሁሉ ሳቀርብ የበለጠ ሰዎች ምን ይላሉ የሚለውን ለማወቅ
ከመጓጓት ነው፡፡ በወሬ ጠግቤዋለሁ ምንአልባት ለየት ያለ ትንታኔ ሊሰጡበት የሚችሉ ሰዎችን ከማሰብም
አንጂ፡፡ እስኪ እውን በድፍረት እንነጋገር ምንድነው ሚስጢሩ?! እኛ (ሰዎች) ማን ነን? እንደመጽሐፍ ሰዎች
ከመላዕክትም እንደሚበልጡ ይነገራል፡፡ እውን ማን ነኝ? መንፈስስ ምንድነው? እስኪ ሁሉም ገጠመኙን
ሳይደብቅ ይንገረን? እነዚህነ ጥያቄዎች እያነሳሁ ያለሁት ዛሬ ለራሴ አይደለም፡፡ ከሞላ ጎደል እኔ
የማውቀውን አውቄአለሁ፡፡ ግን የሚያውቁ ለማያውቁት ገጠመኞቻቸውን እንዲያቀርቡ፣ ባለማወቅም
የተሸወዱ እንዲማሩ፡፡ ባይሸወዱም አስቀድመው እንዲያውቁ ከማሰብ እንጂ፡፡
አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልዩ ማስተዋል ይኖረን ዘንድ አእምሮአችንን ክፈት! አሜን!__

No comments:

Post a Comment