Thursday, September 12, 2013

የወህኒ ቤቱ ሁለት ገጾች (ሃይማኖትና ርዕዮት) የስርዓቱ ማሳያ አይሆኑም?

 ቃሊቲ እስር ቤት በከተማ ውስጥ ያለ አነስተኛ የማይሰኝ ከተማ ከሆነ ከራረመ፡፡የታሰረ ሰው ለመጠየቅ ጎራ ካሉ በዚያ ለአመታት ከእይታዎ የራቀን ሰው ታስሮ ወይም የታሰረ ሊጠይቅ መጥቶ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡ወህኒ ቤቱ ስንት ሺህ ካሬ ላይ እንዳረፈ መረጃ ባላጠናክርም ‹‹የከተማ ውስጥ ከተማ››የሚለው ስያሜ ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡
የእስር ቤቱ ስፋት ሁሉን ውጦ ጸጥ ለማለት አስችሎታል፡፡የሃይማኖት መምህራን፣የህክምና ባለሞያዎች፣የቀድሞ መንግስት ሃላፊዎች፣የጦር ጀነራሎች፣ካድሬዎች፣አክቲቪስቶች፣ጋዜጠኞች፣ደረቅ ወንጀለኞች፣የውጪ ዜጎች፣ቀይ ፣ጥቁር፣ወፍራም፣አጭር፣ፈሪ፣ደፋር ፣ባንክ የዘረፈ፣አንድ ብር የሰረቀ ብቻ ምን አለፋችሁ በቃሊቲ የሌለ የሰው አይነት የለም፡፡
ከሁሉ ተለይቶ ግን በዚህ ሳምንት ርዕዮት አለሙና የአቶ ገብረዋህድ ባለቤት ኮሎኔል ሃይማኖት የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ርዕዮት ወደ ቃሊቲ ሴቶች ዞን የመጣችው መንግስት በሽብርተኝነት ከስሶ ያስፈረደባት በመሆኑ ነው፡፡ከእስር ጊዜዋም ላይ  ሁለት አስቀያሚ አመታት ተገባዶለታል፡፡ኮለኔሏ ቃሊቲ የደረሱት ባለቤታቸው በህገ ወጥ መንገድ የሰበሰቡትን የመሬት ካርታ፣ገንዘብና ሌሎች ማስረጃዎችን ደብቀው ለማሸሽ ሲሞክሩ ተደርሶባቸው ነው፡፡የቀድሞዋ ታጋይና የአዜብ መስፍን የቅርብ ጓደኛ ገና ፍርዳቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሁለቱ እስረኞች ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተላልፈው የተሰጡት በህግ ነው፡፡ነገር ግን ርዕዮትና ሃይማኖት የሚደረግላቸው እንክብካቤ፣ጥበቃ፣በቤተሰብ የሚጠየቁበት ሁኔታ፣የሚተኙበት አጠቃላይ ነገር የሰማይና ምድር ያህል የተራራቀ ነው፡፡
ሃይማኖት በማረሚያ ቤቱ በአሁኑ ሰዓት በሴቶች ዞን ሃላፊ የሆነች የቅርብ ዘመድ አለቻቸው፡፡ስለዚህ ታሳሪዋን ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎች በተዘዋዋሪ የሃላፊዋ ዘመድ በመሆናቸው የሚደረግላቸው አቀባበል የተለየ ነው፡፡ጠያቂዎቹ ወደ ተዘጋጀላቸው ቤት ይገባሉ፣ፖሊሶች ቡና ያፈላሉ ሃይማኖት ወደ ቤቱ ይገቡና ሰርግና ምላሽ ይሆናል፡፡ሰዓት ደረሰ ንግራችሁን አቋርጡ የሚል ትዕዛዝ እነርሱን አይመለከትም፡፡ንግግራቸውን የሚያደምጡና እንዲህ ብላለች በማለት የሚከሷቸው ፖሊሶች አይኖሩም፡፡የሃይማኖት ጠያቂዎች ገደብ ባልጠጣለባቸው ሁኔታ ርዕዮትን መጠየቅ የሚችሉ እናቷ፣አባቷና የንስሃ አባት ብቻ ናቸው ማለት ምርጥ እስረኛና ያልተመረጠ ለመኖሩ ማረጋገጫ ነው፡፡
ርዕዮት የምትጠየቀው 6፡00 ብቻ ነው፡፡ወደ ግቢው የሚገባ ሰው ርዕዮትን ነው የምጠይቀው ካለ ምኗ እንደሆነ ይጠየቃል፤ስልኩ ይመዘገባል፣ጫማውን አውልቆ ይፈተሻል፤ይህንን አልፎ ጋዜጠኛዋ ጋር እንደደረሰ ርዕዮትን ሰላም ለማለት እጆቹን በሽቦ(በእንጨት)መሃል ማሾለክ ይጠበቅበታል፡፡ወሬ ለማውራት ከፈለገም ከሶስት የማያንሱ ፖሊሶች ጋዜጠኛዋን ከብበዋት ይመለከታል፡፡በዚህ መሃል ምን ሊያወራ ይችላል፡፡ሰዓቱ 6፡10 እንዳለ ፖሊሶቹ ፍርጥም ብለው ‹‹ሰዓት አልቋል››ይላሉ፡፡
አሁን ርዕዮትና ሃይማኖት አጠገብ ለአጠገብ እንዲተኙ ተደርገዋል፡፡የቀድሞዋ ታጋይ ርዕዮትን ‹‹አንቺን ብሎ ጋዜጠኛ፣አሁን አንቺ ነሽ መንግስትን የምትተቺ››እያሉ በተለይ ሌሊት ላይ ይሰድቧት ጀምረዋል፡፡
ጋዜጠኛዋ በሃይማኖትና በሴቶች ዞን ሃላፊዋ እየደረሰባት ያለውን በደል በመቃወም የርሃብ አድማ መጀመሯ ታውቋል፡፡ ኢህአዴግ ልጆችና የእንጀራ ልጆች እንዳሉት ሲያሳየን 22 ዓመታት ተቆጥረዋል ፡፡ልዩነቱ በእስር ቤትም ልጆችና የእንጀራ ልጆች መኖራቸው መረጋገጡ ነው፡፡
ከቃሊቲ ውጪም ልዮነቱ ፈጦ ይታያል፡፡በተደራጀና ባልተደራጀ፣በነጋዴ ፎረም አባልና በተራ ነጋዴ፣ፎርም በሞላ ሰራተኛና ባልሞላ፣በጥቃቅን አነስተኛና በጉዳና ላይ ነጋዴ መካከል ልዮነቱ የት የሌለ ነው፡፡በእኔ እምነት ርዕዮትና ሃይማኖት የስርዓቱ ሁነኛ ማሳያ ናቸው፡፡


Dawit Solomon Yemesgan
 https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/09/12/68-2/

No comments:

Post a Comment