Monday, September 23, 2013

ኅብረተሰቡ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት መሸከም ከብዶታል፡፡ መጨመር እንጂ መቀነስ የማያውቀው የኑሮ ውድነት የኅብረተሰቡን ጫንቃ እያዛለው ይገኛል፡፡


September 23, 2013 at 9:21am
ለሰው ልጅ መሠረታዊ የሆኑና አስፈላጊ የምንላቸው ነገሮች ለበርካቶች የሕልም እንጀራ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በኑሮ ውድነት ናላው የዞረ ማኅበረሰብም በሚሠራው ሥራ ውጤታማ ይሆናል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ የኑሮ ውድነቱ አጠቃላይ ጫናውን አገሪቱ ላይ ስለሚያሳርፍ አሁንም ቢሆን አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡ 
አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር በርካቶች የሚያገኙት ገቢና የሚያወጡት ወጪ ልዩነት እየሰፋ መጥቷል፡፡ ልጓም የታጣለት የኑሮ ውድነት ወዴት እንደሚያመራ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ከነገ ዛሬ ይሻላል በሚል ተስፋ በርካቶች የኑሮ ውድነቱ ይቀንሳል ብለው ቢጠባበቁም፣ አሁንም ማሻቀቡን እየቀጠለ ይገኛል፡፡ ለኑሮ ውድነት መናር በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በዋናነት ግን ነጋዴው የሚጫወተው ሚና ተጠቃሽ ነው፡፡ 
የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ሦስት አማራጮች አቅርበው ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የዋጋ ግሽበት ያሳሰባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ በአገሪቱ የሚገኙትን ከፍተኛ ነጋዴዎች ሰብስበው ማስጠንቀቂያ እስከመስጠት ደርሰው ነበር፡፡ በመሆኑም በጊዜው የቀረበውና የመጀመሪያ አማራጭ የነበረው የዋጋ ተመን ብዙም ሊያስኬድ አልቻለም ነበር፡፡ እንዲያውም በግብይት ሥርዓቱ ላይ ባስከተለው ቀውስ ሸማቾች ተንገላትተው ነበር፡፡ 
በዚያን ወቅት በሁለተኛነት የቀረበው አማራጭ ሸቀጦችን መንግሥት እንዲያቀርብ ማድረግ ሲሆን፣ በሦስተኛነት የቀረበው ሐሳብ ደግሞ በዓለም አቀፍ የጅምላ ንግድ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ነበር፡፡ ከሰሞኑ እንደሰማነው መንግሥት በሁለተኛና በሦስተኛ ደረጃ ያቀረባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች በማዳቀል ለመተግበር እየሞከረ ያለ ይመስላል፡፡ በመሆኑም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተቋቋመውንና በመላ አገሪቱ የተደራጀ የሸቀጦች ንግድ አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ ንግድ ኢንተርፕራይዝ ለማስተዳደር በዓለም ታዋቂ የሆነው ግዙፉ የሸቀጦች አቅራቢ ዎልማርት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ ይህ በተለይ ለአገራችን የንግዱ ማኅበረሰብ የማንቂያ ደውል ሊሆን ይገባዋል፡፡
እንደሚታወቀው የአገራችን የንግድ ሥርዓት በዘልማድ የሚከናወንና እጅግ ኋላ ቀር ነው፡፡ ስለሆነም በገበያ ሥርዓቱ ላይ በሚፈጠረው ስንክ ሳር ምክንያት ሁሌም ሸማቾች እየተጐዱ ይገኛሉ፡፡ በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ሥር ያለው የአገሪቱ የንግድ ሥርዓት በየጊዜው ከሚፈጠሩ ችግሮች ሊያመልጥ አልቻለም፡፡ በዚህም ሳቢያ በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ተፈላጊው ጤናማ ውድድር ስለሌለ፣ እነዚህ ጥቂት ነጋዴዎች የንግድ ሥርዓቱን እንደፈለጉ ያሽከረክሩታል፡፡ በመሆኑም ሸማቾች የንግድ ሥርዓቱ ችግር ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ በመሆን እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡
በአገሪቱ የጅምላ ሸቀጦች ላይ የተሰማሩት እነዚህ ነጋዴዎች የጅምላ ንግድ ሥርዓትን ባፋለሰ መንገድ ሸማቾችን እያማረሩ ይገኛሉ፡፡ በርካታ የጅምላ ነጋዴዎች በብዛት በመሸጥ ከፍተኛን ትርፍ ከማትረፍ ይልቅ፣ ከትንሽ ዕቃዎች ሳይቀር ስንጥቅ ትርፍ የለመዱ ናቸው፡፡ በዚህ ተራ ስግብግብነት ሳቢያም የአገሪቱን የንግድ ሥርዓት ወዳልተገባ መንገድ እየወሰዱት ይገኛል፡፡ ነገር ግን በዓለማችን የሸቀጦች ንግድ ላይ ከተሰማሩት እንደነዎልማርት፣ ቴስኮ፣ ኬርፎርና የመሳሰሉት ብዙ ሊማሩ ይገባል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በከፍተኛ መጠን ሸቀጦችን በማቅረብ ዳጐስ ያለ ትርፍ ያስገባሉ፡፡ በዚህም ሸማቾች የሚፈልጓቸውን ሸቀጦች ኪስ በማይጐዳ ሒሳብ እያቀረቡ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሸማቾችን ቁጥር እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም አሁን የኢትዮጵያ ንግድ ኢንተርፕራይዝን ለማስተዳደር እንቅስቃሴ እያደረገው የሚገኘው ዎልማርት ተሳክቶለት ወደዚህ ከገባ፣ የአገሪቱ ነጋዴዎች ሊማሩ የሚገባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ነጋዴዎች ዎልማርትን ከመሳሰሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ራሳቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም የጅምላ ንግድ ማለት በብዛት በመሸጥ ትርፍ ማግኘት በመሆኑ፣ በአገራችን የተለመደው የ200 እና የ300 በመቶ ትርፍ ሊቆም ይገባል፡፡ በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ ቢሆን ከ20 በመቶ በላይ ትርፍ ከተራ ስግብግብነት የመነጨ መሆኑን የዓለም አቀፍ የንግድ ተሞክሮዎች ያመላክታሉ፡፡ የአገራችን ነጋዴዎችም የጅምላ ንግድ ሥርዓትን ሊያስቀጥሉ የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ከተጓዙ መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል፡፡
ከዚህም ባሻገር የአገሪቱ ነጋዴዎች አቅማቸውን በማሳደግ ሸማቾችን ማዕከል ያደረገ ኢኮኖሚ መፍጠር አለባቸው፡፡ ይህንንም ሊያደርጉ የሚችሉት በመካከላቸው ጤናማ የውድድር መንፈስ በመፍጠርና ተገቢ የንግድ ሥነ ምግባርን መከተል ሲችሉ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ነጋዴዎች የወደፊቱን አሻግረው ማየት ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከአፋፍ ላይ ያለች ሲሆን፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የድርጅቱ አባል ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹አሁን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፣ ኋላ ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ፤›› እንደሚባለው፣ የአገሪቷ ነጋዴዎች ከፊታቸው ያለውን ከባድ ውድድር ከአሁኑ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሸማቾችን ማዕከል ያደረገ ኢኮኖሚ መፍጠር ከቻሉ፣ አገሪቱ ወደፊት የምትከተለውን የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ 
ከአገሪቱ ነጋዴዎች በተጨማሪ ግን መንግሥትም የማንቂያ ደውሉን ሊሰማ ይገባል፡፡ ምንም እንኳን የዋጋ ግሽበት የአገሪቷን ኢኮኖሚና ሸማቾችን እየተፈታተነ ቢገኝም፣ መንግሥት እንደዎልማርት ያሉ ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ሲከላከል ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን ዎልማርት አሁን በጥቂቱም ቢሆን ወደ አገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ አንገቱን የሚያስገባ ይመስላል፡፡ ቢሆንም ግን ዎልማርት ጉዞውን በዚሁ ያበቃል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ መንግሥት ጥፋትን በጥፋት ማረም ስለሌለበት፣ አሁንም ቢሆን የግል ዘርፉን መደገፍና ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡ የአገሪቱን ነጋዴዎች ማስተማርና መለወጥ እንጂ ከናካቴው ማጥፋት ማንንም አይጠቅምምና፡፡ 
ሸማቾችም ቢሆኑ የማንቂያ ደውሉን ሊሰሙ ይገባል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴው ዋነኛ ተዋናዮች እንደመሆናቸው መጠን፣ ራሳቸውን በማደራጀት ድምፃቸውን ማሰማት ይገባቸዋል፡፡ በአንድነት ተደራጅተው ጡንቻቸውን በማፈርጠምም፣ የመደራደር አቅማቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ሸማቾች፣ መንግሥትም ሆነ ነጋዴዎች የማንቂያ ደወሉን ሊሰሙ ይገባል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ኃይሎች የሚባሉት እነዚህ ሦስት አካላት መናበብ ይገባቸዋል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com


No comments:

Post a Comment