Thursday, September 5, 2013

ኢትዮ-ቤተ እሥራኤላውያንና ኑሯቿዉ


ኢትዮ-ቤተ እሥራኤላውያንና ኑሯቿዉ

በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላዉያን ባለፉት ሠላሣ ዓመታት እስራኤል ገብተዋል። ይሁንና ቤተ እሥራኤላውያኑን ከሀገሪቱ ኅብረተሰብ ጋ የማዋሀዱ ተግባር ዛሬም ትልቅ እክል ይታይበታል።
ባለፈው ሳምንት የእሥራኤል መንግሥት የመጨረሻ ያላቸው አራት መቶ ሀምሣ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላዉያን ቴልአቪቭ ገብተዋል። ዘገባዎች እንደሚሉት ከሆነም ወደ አንድ መቶ ሃያ ሺህ የኢትዮጵያ ቤተ እሥራኤላውያን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት እሥራኤል ገብተዋል። እነዚህ ወገኖችም አሁንም በዝቅተኛው የኑሮ ደረጃ እንደሚገኙ፣ ለከፋ አድልዎ እና ዘረኝነትም እንደተጋለጡ እነሱም ሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይናገራሉ። ጀርመን ጎቲንገን ከተማ የሚገኘው ለተጨቆኑ ሕዝቦች የሚሟገተው ድርጅት (Gesellschaft für bedrohte Völker) ሰሞኑን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በርካታ የኢትዮጵያ አይሁዳውያን እስራኤል ውስጥ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ እንደሚታዩ አመልክቷል። ድርጅቱ ለምን እንዲህ ሊል እንደቻለ የድርጅቱ ተጠሪ ኡርሊሽ ዴሊዮስ ያስረዳሉ፤ «እስራኤል ዉስጥ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና እንደ ተባበሩት መንግስታት ባሉ አለም አቀፍ ድርጅቶች የተከናወኑ ብዙ ምርመራዎች አሉ። እጅግ የሚያሳዝን ነዉ። እንደዘገባዎቹ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ። ብዙዎች እጅግ ዝቅተኛ ገንዘብ በሚከፈልባቸዉ የሥራ መስኮች ነው የተሰማሩት። ጨርሶ ሥራ የሌላቸውም ብዙ ናቸው። ህይወታቸውን የሚያጠፉትም ቁጥር ከፍተኛ ነው። እነዚህ ሁሉ ባለፉት 30 ዓመታት እስራኤል የገቡትን ስደተኞች ተዋህዶ የመኖሩን ሂደት አዳጋች እንዳደረገው ያመላክታሉ።»
ኡርሊሽ ዴሊዮስ
የችግሩ መነሻ ምን ይሆን፤ ኢትዮጵያዉኑ ቤተ እስራኤላዉያን በአይሁዳዊነታቸው ተቀባይነት አለማግኘታቸው ወይንስ ከአገሬዉ ተዋህዶ ለመኖር መቸገራቸዉ? «አብዛኛዉ መንስኤ ከአገሬዉ ተዋህዶ የመኖሩ ሁኔታ ላይ ያለ ነው። ትንሽ ቆየት ብሏል በ 2005 « የሩሳሌም ፖስት» ላይ የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ወጥቶ ነበር። እዛ ላይ 43 ከመቶ የሚሆኑ እስራኤላውያን ወላጆች ልጆቻቸው ቢቻል ከፈላሻዎች ጋ ግንኙነት ባይኖራቸው እንደሚመርጡ ተናግረዋል። ይህ በግልፅ የሚያመላክተው አብዛኛው ማህበረሰብ ፈላሻዎችን ወይም ፈላሻ ሙራን በእኩል ዜጋነት ለመቀበል እንደሚከብዳቸው ነው።»
ባለፈዉ ሳምንት 450 የሚሆኑት የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላዉያን ቴልአቪቭ ሲገቡ ከዚህ በኋላ እንዲያ ያለ የጅምላ ጉዞ እንደማይኖር ተገልጿል። ቤተ እስራኤላዊነታቸዉ የሚረጋገጥ ወገኖችም በተናጠል ሊሄዱ እንደሚችሉ ነዉ አጽንኦት ተስጥቶ የተገለጸዉ። በወቅቱ እዚያ የሚኖሩ በርካቶች አምስት ሺህ የሚሆኑ ቤተሰቦቻቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደቀሩ በማመልከት ቀሪዎቹም እንዲመጡላቸዉ የእስራኤልን መንግስት ጠይቀዋል። ለተጨቆኑ ህዝቦች የሚሟገተው ድርጅት እስራኤል ዉስጥ ለሚገኙት አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላዉያን እዚያ ከገጠማቸዉ ያልጠበቁት የዘረኝነት ሁኔታ አንጻር ሀገሪቱ ተወዳጅነቷ ቀንሷል።
ቤተ እስራኤላዉያን ለዓመታት ሲያልሟት በነበረችዉ ሀገር በእኩልነት እንዲኖሩ እና ይህ አሉታዊ አመለካከት እንዲቆም ያለውን ትልቅ ችግር ችላ ማለት እንደማይገባ ዴሊዮስ ያሳስባሉ።
«ምንም እንዳልተፈጠረና ሁሉም ነበር ጥሩ እንደሆነ ማስመሰል አያስፈልግም። ብዙዎች በአንድ በኩል ተመልሰው ሃገራቸው ገብተው እምነታቸውን እንደሚፈልጉት መከተል በመቻላቸው ይደሰታሉ። ነገር ግን ሀገሪቷ እነሱ በጣም እንደጠበቋት ጥሩ እንግዳ ተቀባይ አይደለችም በማለት ብዙዎቹ ስደተኞች ደስተኞች አይደሉም። ከዛ መሸሽ ነው የሚፈልጉት። ስለዚህ በግልፅ ስላለው ማውራት አስፈላጊ ይመስለኛል። የሀገሪቱ መንግስት ሕዝቦች ተዋህደዉ የመኖራቸዉ ሙከራ ስኬታማ እንዲሆን የበለጠ ማድረግ ይኖርበታል። ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ መፍቀድ ብቻ በቂ አይደለም። ዘረኛነትን ከማጥፋት ጀምሮ በሁሉም ረገድ ብዙ መሰራት አለበት»
ምክንያቱም ይላሉ ዴሊዮስ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላዉያን ወደ እስራኤል የገቡ ብቸኛ ስደተኞች አይደሉም። ከሌሎች ከተለያዩ ሃገራት መጥተዉ በእስራኤል ከሚገኙ ቤተ እስራኤላዉያን ጋ ሲነፃፀሩ አቀባበል ረገድ ያለዉ ልዩነት እጅግ ትልቅ ነው።
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሰ

dw.de

No comments:

Post a Comment