by Fisseha Tegegn •
የፊታችን ቅዳሜ ኮንጎ ብራዛቪል ውስጥ የኢትዮጵያ
ብሄራዊ ቡድን ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ለሚያደርገው ጨዋታ ተጨዋቾቻቸው በሙሉ
ጤንነት ላይ እንደሚገኙ እና ውጤት ይዘው እንደሚመጡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ተናገሩ።
ብሄራዊ ቡድኑ ረቡዕ (ነሀሴ 29 ቀን 2005) እለት
በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል የአሸኛኘት ስነ-ስርአት ሲደረግለት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ
ቡድናቸው ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ላለበት ዋሳኝ ጨዋታ ጥሩ ዝግጅት እንዳደረገና ለዚህ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን
ለቀጣይ ግጥሚዎችም ቡድናቸው ዝግጁ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሳህሉ ገብረወልድ
በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች በማሰለፉ በፊፋ የሶስት ነጥቦች ቅነሳ ቅጣት የተጣለበትን
ሁኔታ በማስታወስ “ታሪካዊውን ስህተት በመካስ ታሪካዊ ስራ እንደምትሰሩ እተማመናለሁ” በማለት በአሸኛኘቱ ዝግጅቱ
ላይ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገሮች ሻምፒዮና (ቻን)
ሩዋንዳን አሸንፎ ደቡብ አፍሪካ ላይ በመጪው አመት በሚካሄደው ውድድር ማለፉን በማረጋገጡ እና ከመካከለኛው አፍሪካ
ሪፐብሊክ ጋር በሚኖረው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ማበረታቻ እንዲሆነው በሚል ለተጨዋቾቹ እና ለቡድኑ አባላት ሽልማት
የተሰጠ ሲሆን፣ ከሩዋንዳ ጋር በነበረው የቻን ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ ለተጫወቱ የቡድኑ አባላት እያንዳንዳቸው 30
ሺህ ብር፣ ተቀይረው በመግባት ለተጫወቱት የ 20 ሺህ ብር እና ለቀሪዎች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የ15 ሺህ ብር
ሽልማት ተሰጥቷል።
በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል በተካሄደው የአሸኛኘት ዝግጅት ላይ የነበረውን ሁኔታ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ (@tesfalemw) በፎቶ ካሜራው እንደሚከተለው ይዞታል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመሸኛ ዝግጅት የፎቶ ዘገባ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአለም ዋንጫው ማጣሪያ ዝግጅት በሚል
ከሁለት ሳምንት በላይ ለሆነ ጊዜ ያህል አዳማ ከተማ ውስጥ ልምምዱን ሲሰራ የቆየ ሲሆን የአቋም መለኪያ ጨዋታ
አለማድረጉ ግን በበርካቶች ቅሬታን ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል።
ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ የተመረጡት 23 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች
በረኞች
ሲሳይ ባንጫ፣ ሳምሶን አሰፋ እና ደረጀ አለማየሁ።
ተከላካዮች
ሞገስ ታደሰ፣ ደጉ ደበበ፣ ቢያድግልኝ ኤሊያስ፣ ሳላዲን በርጌቾ፣ ስዩም ተስፋዬ፣ አበባው ቡታቆ፣ ብርሀኑ ቦጋለ እና ቶክ ጀምስ።
አማካዮች
ምንያህል ተሾመ፣ በሀይሉ አሰፋ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አስራት መገርሳ፣ ፋሲካ አስፋው።
አጥቂዎች
አዳነ ግርማ፣ ጌታነህ ከበደ፣ መድሀኔ ታደሰ፣ ዳዊት ፈቃዱ፣ ሳልሀዲን ሰኢድ፣ ኦመድ ኡክሪ እና ገብረሚካኤል ያቆብ ናቸው።
No comments:
Post a Comment