Monday, September 2, 2013

ከመንግስት የቤቶች ግንባታ ጀርባ ያለው ትክክለኛ ዓለማ ሲገለጥ (ግርማ ሠይፉ ማሩ )


ሰሞኑን ከፀረ አሸባሪነት ህግ በማስቀጠል የአዲስ አበባን ከተማ ነዋሪን ሲያምስ ከርሞ አሁንም በማመስ ላይ ያለው የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው፡፡ በእዲስ አባባ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳለ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ይህ ችግር እዚህ እንዲደርስ ደግሞ ዋናው ተዋናይ መንግሰት እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ ምክንያቱም ለቤት መስሪያ የሚሆነውን ቦታ በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ለዜጎች እንዳይደርስ በማድረጉ ነው፡፡ አንደኛው በቁጥ-ቁጥ ቦታ በሊዝ ጨረታ እያወጣ በውድ ዋጋ እየሸጠ የመሬትን ዋጋ በማስወዳድ እና የመኖሪያ ቤት ውድ እንዲሆን በማድረግ ነው፡ ፡ ሌላው ደግሞ ለመኖሪያ ቤት ግንባት የሚውል የብድር አገልግሎት የተለየ አቅርቦት ባለማዘጋጀቱ ሲሆን፣ የመንግሰት ሹሞች ደግሞ በተለየ ሁኔታ የተመረጠ ቦታ እያገኙ በሽያጭ እንዲከብሩ በተቃራኒው ዜጎች ከከተማ ወጣ ባሉ ቦታዎች በህገወጥ መንገድ እንዲሰፍሩ በማድረግ ነው፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ልዩ ወዳጅነት የመሰረቱ ይመስላል፡፡ ባንኩ በተለይ መመሪያ የሚቀበለው በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ መሆኑ ቀርቶ ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እስኪመስል ድረስ ግራ አጋቢ ሆኖብናል፡፡ በእኔ አምነት በቅርቡ መንግሰት ዜጎች ቤት እንዲኖራቸው ለቤቶች ግንባታ በሚል 10/90፣ 20/80፣ 40/60፣ አና ሌለችም በቁጠባ ላይ መሰረት ያደረገ ዜጎችን የማመስ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን ጉዳይ ዛሬ ላይ ሆኜ የምፅፈው ከዓመት እና ሁለት ዓመት በኋላ ለውይይት ይጠቅማል በሚል ነው፡፡ አቋሜን ግልፅ ለማድረግ የኢህአዴግ መንግሰት በምንም ዓይነት መለኪያ ለኢትዮጵያ ህዝብ የመኖሪያ ቤት ሰርቶ የመስጠት አቅምም ሆነ ፍላጎት የለውም፡፡ ስለዚህ የፕሮግራሙ ዓላማ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ማየት ተገቢ ነው፡፡
የኢህአዴግ መንግሰት በዓለም ላይ ካሉ መንግሰታት በተለየ ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤቶችን አንደኮንትራከትር ለመገንባት ሙከራ እያደረገ ያለ መንግሰት ነው፡፡ መንግስት እንደ መንግስት ሊሰራቸው የሚችለው ብዙ ተግባራት ወደ ጎን በመተው ዜጎች እንደፍላጎታቸው እና አቅማቸው ቤታቸውን መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሲገባው መንግስት በፈለገው እና በተወሰኑ የቤት ዓይነቶች ውስጥ ታጥሮ እንዲኖር ለማድረግ እየሞከረ ነው፡፡ ወደ መጨረሻ ላይ ይህን መንግሰት ለምን እንደሚያደርግ የግል ምልከታዬን አሰቀምጣለሁ፡፡ የመንግሰት ቤቶች ግንባታ ዋና ዓላማ መንግሰት በ2006 በጀት መግለጫ ላይ እንዳስቀመጠው የሀገር ውስጥ ቁጠባን ለማሳደግ ከተያዙት ዕቅዶች አንዱ ነው፡፡ ይህ የሀገር ውስጥ ቁጠባን ማሳደግ የተቀደሰ ሃሳብ ነው፡፡ ይህን ቁጠባን በፈቃደኝነት ማሳደግ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስለም፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያት ስለአለው ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡ መንግሰት ግን ለዚህ እንደመፍትሔ አድርጎ ያስቀመጠው ዜጎች ቤት ይስራልናል በሚል በተስፋ ላይ መሰረት ያደረገ ገንዘብ ተቀማጭ እንዲያደርጉ ማድረግ ነው፡፡ እግረ መንገዱንም መንግሰት ለተለያየ ሰራ የሚፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት እንዲችል ዕድል መፍጠር ነው፡፡ ይህ በቁጠባ የተሰበሰበ ገንዘብ በግል ባንኮች ቢቀመጥ፣ የግል ባንኮች ለግል ባለሀብቶች በብድር መልክ ሊሰጡት ስለሚችሉ መንግሰት የሚፈልገውን ገንዘብ ላያገኝ ስለሚችል ይህ ገንዘብ ተጠቃሎ ወደ ንግድ ባንክ እንዲገባ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኖ ተገኝቶዋል፡፡ በዚህ ፖሊሲው መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ተቋማትን እና ዜጎችን በአንድ ዓይን እንደማይመለከት ግልፅ ማሳያ ነው፡፡
ብዙ ሰዎች የመንግሰት ዋና ዓላማ የገባው አይመስልም፡፡ ይልቁንም መንግሰት ቤት መስራት ለማይችሉ ሰዎች ቤት ቢሰራ ምን ችግር አለው? የሚሉ አሉ፡፡ መንግሰት እንደሚያወራው ቤት መስራት ያልቻሉ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ቤት ለመስራት እንዳልሆነ የሚያሳብቀው ግን በተነፃፃሪ የተሻለ አቅም ያላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ቢሆኑ በዚሁ ፕሮግራም እንዲሳተፉ ዕድሉ ክፍት ነው ይባላል፡፡ ይህ ዕድል ግን ክፍት የተደረገው በውጭ ምንዛሪ መቆጠብ ሲችሉ ነው፡፡ ገባችሁ አይደለም የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ የተያዘ ዕቅድ ነው- ትክክለኛውም ዕቅድ ይህ ነው፡፡ ተሰፋን እየመገቡ ዶላር መሰብሰብ፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገራችን ላለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት መፍትሔ መስጠት መቻል ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ዜጎች ለጋራ ልማታችን የሚያውሉት እንጂ መንግስት ብቻ ለሚያቅደው ዕቅድ መዋል አለበት የሚል እና የግል ባለሀብት ከጫወታ የሚያስወጣ ዕቅድ ለመተግበር መሆን የለበትም፡፡ ሌላው የመንግሰት እቅድን ፊት ለፊት ከሚያወራው በተቃራኒው መሆኑን የሚያሳብቀው በአርባ ስልሣ ሙሉ ክፍያ የከፈለ ቅድሚያ ያገኛል የሚለው መመሪያ ነው፡፡ ቅድሚያ መክፈል የሚችል ማለት አርባ ስልሳ (አርባ ቆጥቦ ስልሳ በብድር የነበረ ፕሮግራም) ሳይሆን መቶ ዜሮ (መቶ ቆጥቦ ዜሮ ብድር ሆኖዋል) ፕሮግራሙ መባል ያለበት፡፡ በእርግጥ መንግሰት ቤት በተመጣጣኝ የመስራት እቅድ አለው ብለን እንድናምን የሚያደርግ ነገር አለወይ? ነው የእኔ ጥያቄ፡፡ መልሱ በፍፁም መንግስት ይህ እቅድ የለውም፡፡ ዕቅዱ በጭፍን አለው ብለን ብንወሰድም አቅሙ የለውም፡፡
የመንግሰት አቅም እንዴት እንለካው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ኢህአዴግ በ1997 የአዲስ አበባ ህዝብ ያለበትን ችግር ለመቅረፍ ቅድሚያ የሚሰጠው የመኖሪያ ቤት ነው በሚል ከአራት መቶ ሃምሳ ሺ በላይ ቤቶችን በአምስት ዓመት ለመገንባት ብሎ ምዝገባ አድርጎ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን ውጤቱን ስንመለከተው በስምንት ዓመት ውስጥ በጅምር ላይ ያሉትን ጨምሮ አንድ መቶ ሺ ቤቶችን ነው መገንባት የተቻለው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት መቶ ሺ ቤቶች የገነባ ሌላ መንግሰት የለም፡፡ ምክንያቱም የሌላ ሀገር መንግሰታት በማያገባቸው አይገቡም፡፡ ስለዚህ ይህን ያህል ቤት አይገነቡም፡፡ እስራኤል አወዛጋቢ በሆኑ ቦታዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ስትገነባ እንኳን ለግል ኮንትራክተሮች ነው የምትሰጠው፡፡ መንግሰታት የተሰጣቸውን ኃለፊነት ያውቃሉ እርሱን በቅጡ ይተገብራሉ፡፡ የእኛ መንግሰት ለአምስት ዓመት ከያዘው ዕቅድ ውስጥ በስምንት ዓመት ውስጥ ከሃያ በመቶ በታች ብቻ ግርማ ሰይፉ ማሩበማከናወን ሌላ ሶስት ዕጥፍ የሚሆን ሌላ ዕቅድ ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ይህ ዕቅድ ዝርክርክ እንደ ሆነ ለማወቅ በምዝገባ ወቅት ብቻ የሚለዋወጠውን መመሪያ ማየት በቂ ነው፡፡ ለድሃ ነው የምንሰራው ብለው፣ መሉ በሙሉ ለከፈለ ቅድሚያ ይስጣል ይሉናል፡፡ በዚህም ተባለ በዚህ መንግሰት የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት የሚያሰችል መላው ዜጋውን እና በተለይም የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታ ዕቅድ ማውጣት ግድ ይለዋል፡፡
ሌላው በጥቂቱም ቢሆን የተሰሩት ቤቶች ዓላማ ምንድነው ካላችሁ በልማት ስም የተነሱ የቀበሌ ቤቶችን በመተካት ዜጎችን ለቁጥጥር በሚመች መልኩ ማስፈር ነው፡፡ ለዚህ ዋነኛው ማሳያ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በህጋዊ መንገድ በሽያጭ ማዛወር አይቻለም፡፡ ዜጎች ይህን የመንግሰት ቁጥጥር መስመር ለማለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀም ሲሆን ይህን ለማድረግም የተለያዩ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ይፈፅማሉ፡፡ ይህ ብቻም አይለም የመንግሰት የቁጥጥሩ አባዜ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም የሚቀር አይደለም፣ ገንዘባቸውን ገቢ ካደረጉ በኋላ መንግሰትን በሚቃወም ተግባር ቢሳተፉ በቁጠባ ያስቀመጡት ገንዘብ አደጋ ላይ ስለሚወድቅ ጭጭ ማለት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነፃነታችንን ከፍለን ሽጠናል የምለው ለዚህ ነው፡፡ በሀገራችን ቤት እናገኛለን ብለው ነፃነታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡ ሁሉም እንደሚታዘበው ኢትዮጵያዊያን ለሁለት ተከፍለናል ግማሹ ለነፃነት፣ ቀሪው ለኮንዶሚኒየም እየተሰለፍ ነው፡፡
ኢህአዴግ የቀበሌ ቤቶችን በመንግሰት ቁጥጥር ስር እንዲቆይ ያደረገው በምንም ዓይነት በቀበሌ ቤት ለሚኖሩት ሰዎች አዝኖ አይደለም፡፡ ዋና ዓላማው በገጠር ገበሬውን በመሬት ጭሰኝነት እንደያዘው ሁሉ በከተማ ደግሞ በቀበሌ ወይም በኪራይ ቤት እንድንኖር ታቅዶ እየተተገበረ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የቀበሌ ቤቶች በዕድሜ ምክንያት ከጫወታ ሲወጡ ይህ ተግባር በኮንዶሚኒየም በኩል ነብስ እንዲዘራ ዕቅድ አለ፡፡ ይህ ዕቅድ የለም የሚሉ ከሆነ ለዜጎች በነፃነት ቤታቸውን ሽጠው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡

No comments:

Post a Comment