ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ
በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን ዘንድ በመረጥካትና ስለብዙዎች ልቧ
(አእምሮዋ) ሐዘንን (ነብዩ እንደተናገራት ፍላጻዎችን) ሁሉ ያስተግድ ዘንድ ባጸናሀት፣ ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል በሆነች
እናትህ ማሪያም ሥም ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
የባለፈው ማይክሮ ችፕስ 3፡ ውጤታማ አስተዳደር ማሳጣት፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል
ክፍል 7 መሆን ሲገባው ክፍል 6 ተብሎ የቀረበው ስህተት ስለነበር የታላቋ ቀን ልጅ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ይሄኛው ክፍል
8 ይሆናል፡፡ አስቀድሜ ለአንባብያን እንደገለጽኩት የታላቋ ቀን ልጅ አንዴ ይጽፋል እንጂ ተመልሶ ለማስተካከል አያነብም በዚህ ላይ
የአማርኛ ሶፍት ዌር የኪቦርድ አጠቃቀም ችግር አለበት፡፡ በመሆኑም በጽሑፎቹ ላይ ብዙ ግድፈቶች ይታዩበታል ለዚህም ይቅርታ ይጠይቃል፡፡
ሆኖም መሠረታዊ ሀሳቡን አንባብያን በሚረዱት ሁኔታ አስቀምጬዋለሁ ብሎ ያምናል፡፡
የአገር አስተዳደር ዝቅጠታችን ቢዘረዘር ማለቂያ የሌለው ትንተና ይሆናልና በመጠኑ አሁን ስላለው አስተዳደር አንስቼ
ወደሌላ ወደ ማይክሮ ችብስ 4 እገባለሁ፡፡ በክፍል 7 (በስክተት ክፍል 6 በተባለው) እንዳነሳሁት ብዙዎች በፓርቲነትም ይሁን በሌላ
ቡድን የሚንቀሳቀሱት አገርን ለማስተዳደር በቂ ዝግጅት አድርገው አይደለም፡፡ ይህ እውነታ የደርግንም አስተዳደረር ይጨምራል፡፡ የንጉሱ
አስተዳደር በግርግርና በአብዛኛው በተማሪዎችና ባልበሰሉ ወጣቶች ጫጫታ ሲፈርስ አገሪቷን በበቂ ዝግጅትና መረጋጋት ሊመራት የሚችል
አካል በመታጣቱ ከብዙ ግርግር በኋላ ደርግ እጅ ላይ ወደቀች፡፡ ሊያውም ስንት የበሰለ ልምድና ብቃት ያለቸው ጀነራሎች እያሉ በአንድ
ሻለቃ (ኋላ ኮሎኔል በሆኑት) መዳፍ ገባች፡፡ ደርግ 17 ዓመታት
አባክኖ የአሁኑ አስተዳደር ሲተካም ነገሮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ 17 ዓመት በዱር ተዋግቶ የመጣ ኃይል ቢሆንም እስከመጨረሻው ድረስ
ኧረ እንደውም ስልጣኑንም ከያዘ በኋላ አገርን ለመምራት ግልጽ አላማ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ ሕወሐት የተባለው አላማው ትግራይን
ከኤርትራ ጋር ለመገንጠል እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በወቅቱ አብሮ የገባው ኦነግ ግልጽ የሆነ የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያ መገንጠል
የሚል አቋሙ አሁንም ያለ ነው፡፡ ሌላው የኦሮሞን ሕዝብ እወክላለሁ የሚለው ኦሕዲድ አሁንም የገዥው አንድ አካል የሆነው በደርግ
ውድቀት ጊዜ ገና ሁለት ዓመት እንኳን ያልሆነው አምቦቀቅላ ነበር፡፡ ነገሩ አሁንም ከ20 ምናምን ዓመት በኋላም ያው ነው፡፡ ኢሕዲን
(አሁን በአዴን) አገር የመገንጠል አላማ ባይኖረውም ሰው የለውም አሁንም ድረስ ይህ ፓርቲ ሰው አልባ ነው፡፡ ደሕዴግን ተውት ማንስ
ከቁጥር ያስገባዋል? ያው ግን ኢሕአዴግን ለመመሥረት ከአራቱ አንዱ ሆኗል፡፡ በእንዲህ ያለ ውዥንብር እነዚህ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመታየት
ራሳቸውን ኢሕአዴግ ብለው ሰይመውና ሌሎችንም ትንንሾችን ከየቦታቸው ለስብሰባ ጠርተው በድፍረት አገርን መምራት ጀመሩ፡፡ ልክ ነበሩ
ደርግም በድፍረት እንጂ አገርን ለመምራት በሚያስችል ብቃትና ዝግጅቱ አልመራትም፡፡ ልብ በሉ ኢሕአዴግ አገርን አንደ አገር ለመምራትና
የሀገር መምራት ኃላፊነት ሊመጣለት እስከሚችል ድረስ ቢያንስ 10 ዓመት ፈጅቶበታል፡፡ በዚህ መካከል ብዙ ውድመቶች ተከስተዋል፡፡
የኢሕዴግ ባለስልጣናትም ስኳሩን መላስ ለምደው ኋላ ሱስ ሆኖባቸው ዛሬ ሀገርን መዝረፍ ሕጋዊ ያደረጉትን ልምምድድና ሥልጠና ያደረጉት
በእነዚያ ዓመታቶች ነው፡፡ የ1990ው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጥቶ እስከሚገላግለን ድረስ እናቲቱ ኢትዮጵያ በጡት በምትጠባው ኤርትራ
ሞግዚትነት ትተዳደር ነበርም፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ኢትዮጵያውያን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የተቆጠሩበት ኤርትራውያኑ በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ነግሰው የታዩበት
ወቅት በመሆኑ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አንድጦርነቱ ለብዙ ኢትዮጵያውያን አስደንጋጭ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በብዙዎች ዘንድ የጦርነቱ
መቀስቀስ ወሬ እንደ ታላቅ የምስራች ነበር፡፡ በእርግጥም ሰዎች ይችን አገር ሊያጠፉ በተነሱበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ በልዩ
ጥበቡ ተዓምሩን ያሳየን ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱ ተሰብስበው በአንድ
ሆቴል ውስጥ የጦርነቱን መነሳት ድንገት ከሰሙት ጓደኛሞች አንዱ በደስታ እየዘለለ "ዛሬ እግዚአብሔር እየፈረደ ያለው በላይ
በሰማይ ርቆ ሳይሆን እዚህ ያለንበት ጣሪያ ኮርኒስ ውስጥ ሆኖ ነው!" በማለት ነበር ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ፍትህ ለኢትዮጵያውያን
እንደወረደ የተናገረው፡፡ እውነት ነው! አምላክ ሕዝቡን መዳኘት ነበረበት ምድራዊ ዳኞች ሁሉ አልቀዋልና፡፡ ያኔ የአገር ፍቅር ወኔውም
አልነጠፈም ነበርና የኤርትራውያንን ሳያስተውሉ በቆፈሩት ጉድጓድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀበራቸው፡፡ ይህ በአቶ መለስ ይመራ የነበረውን
የኢሕአዴግን አስተዳደር ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ነው እንደ አገር መሪነት መንፈራገጥ የተጀመረው፡፡
ኢሕአዴግ ብዙ ጥፋቶችን ቢያጠፋም ካለማወቅ ወይም ከአቅም ማነስ ሊሆን ስለሚችል ይቅር ሊባል ይችላል፡፡ እንደኔ ግን
ሁለት ጥፋቶቹ መቼውንም ቢሆን ይቅር ሊባሉ የማይችሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ማድረጉና የብሔር (የጎሳ) ክፍፍል፡፡ እነዚህ ደግሞ ጥፋቶች ሆን ተብለው የተደረጉ ክፋቶች እንደሆኑ
ሳስብ ይበልጥ አዝናለሁ፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የባሕር በርን ዳግም ለመመለስ ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ ግን ነገሩ "እባብ
ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው" እንደተባለው ሆነ፡፡ አንዴ ሳያየው ነደፈው አሉ ሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ያ ባለፈው የነደፈኝ ነገር
ይሄውልህ ብሎ በጣቱ ነክቶ ለጓደኛው ሲያሳይ ነደፈው አሉ፡፡ በቃ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲሁ ነው የሆነው በወደብ ጉዳይ፡፡ አቶ
መለስ ከኢሳያስ ጋር አላቸው የተባለው የሥጋ ዝምድና የሁን ወይም የሚመሯትን ኢትዮጵያ ጥላቻ ወይም ሌላ አዚም ብቻ አጥብቀው ኢትዮጵያ
የባህር በር አልባ እንድትሆን የታገሉ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው፡፡
የኢሕዴግ አስተዳደር በወቅቱ እንደ አገር መሪነት ራሱን ባወቀበትና ትንሽ ትንሽም ቢሆን ልማትም እየተንቀሳቀሰ ባለበት
ወቅትም ቢሆን በአስተዳደር በደል የተከፋው የኢትዮጵያ ሕዝብ በ1997ቱ ምርጫ አይደለም ኢሕአዴግን የትኛውንም ሀይል እድሉን ካገኘ
ሊጥል እንደሚችል ምልክት ሰጠው (በጉልበትም በሰላማዊ መንግድም)፡፡ ከዚያ በፊት በ1994 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች
ላይ በተፈጸመው ድብደባ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቤተመንግስት ሳይቀር ሰብሮ ሊገባ እንደሚችል ስለተረዳ ፌደራል የተባለ ያገኘውን ከመደብደብና
ከመግደል ሌላ ለምን ብሎ የማይጠይቅ ኃይል አደራጀ፡፡ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ግን ፌደራል ተብዬውም ሊቋመው የሚችል ስላልነበር
የአገሪቱን የመከላከያ ኃይል በተለይም በሕዝብ ላይ አዘመቶ ራሱን
ከጊዜያዊ ውርጅብኝ አስጣለ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከሕዝብ ውጭ የትኛውም ኃይል አቅም እንደሌለው ስለገመተ ይመስላል ሕዝብን በተለያየ
ነገር መደለልና መለማመጥ ጀመረ፡፡ ሒደቱም እውነት ለመናገር ጥሩ ነበር፡፡ ራሱንም ከየተኛውም ፓርቲ በላይ ለሕዝብ አሳቢ አድርጎታል፡፡
ሕዝብንም ለማረጋጋት ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አቶ መለስ ታች እየወረዱ ማነጋገር ጀመሩ፡፡ በእርግጥም ጠ/ሚኒሰቴሩ በዚህ ወቅት
ታላቅ የሕዝብንም ፍቅር አግኝተዋል፡፡ አሳቸውም የሕዝብነታቸውን እያረጋገጡ መጡ፡፡ ያቺ ድሮ በብሔር መከፋፈሉ ትክክል ነው ብለው
ያመኑባት ነገርም ትንሽ ሕሊናቸውን ነክታቸው ነው መሰለኝ "ልዩነታችን ውበታችን አንድነታችን ኃይላችን ምናምን"
ማለትን አበዙ በተግባርም ይህንን አንድነት ለመፍጠርም የብሔር ብሔረሰብ ቀን በሚል በዓል ማክበር ተጀመረ፡፡ ጥሩ ነው ቢያንስ አንድነት
የምትለው ቃል አዋጭነቷ ተረጋገጠላት!
ጉዱ ግን ለመለማመጥ በተደረገ እንቅስቃሴ ውስጥ አደገኛ የሆኑ ዜጎችን አፈራ፡፡ ለመደልል እያለ ባለስልጣናትንና በተለያየቦታ
ያሉ ወሳኝ ግለሰቦችን ያቀማመሳቸው ዳረጎት በኋላ መቆጣጠር ወደማይችለው ግልጽ የሀገር ዝርፊያ ተሸጋግሮ ይሄው አሁን የምናያትን
የምጣኔ ሀብትና የግብይት ሥርዓት ያጣች አገር ፈጠረ፡፡ ነገሩ እንዲህ ታች ድረስ አልደረሰም እንጂ የኢሕአዴግ ትልልቅ ባለስልጣናት
ዝርፊያውን ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ እያጧጧፉት ነበር፡፡ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ግን በቃ -----! ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከጥቂት የአገሪቱ
ባለስልጣናት በቀር በየትኛውም ደረጃ ያሉ መዝረፍን የመጀመሪያ ተቀዳሚ ስራቸው አደረጉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ግን አቶ መለስ በግላቸው
የሚታሙ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ችግሩን ከእንጭጩ ማስቀረት ባለመቻለቸው ምክነያት ኋላ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ራስ ምታት እነድሆነባቸው
እንገምታለን፡፡ እዚህ ላይ በአንዳንድ ድረ-ገጾች በአቶ መለስ ሥም በውጭ አገር የሚገኝ ገንዘብ መጠን በሚል የሚሰራጨው ምንም ማረጋገጫ
የለውም፡፡ አቶ መለስ ድሮ ጫካ እያሉ ገንዘብ ለድርጅቱ በሥማቸው እነደሚቀመጥ ይነገራል፡፡ ያም ገንዘብ እስካሁንም በእሳቸውና በሌላ
አንድ ሰው ሥም በውጭ አገር ባለ ሒሳብ እንዳለ ይነገራል፡፡ እንደውም ሌላው ሰው በአሜሪካ ይኖሩ ነበርና በአንድ ወቅት ሚስታቸው
ይህንን ገንዘብ በባለቤቴ ሒሳብ የሚገኝ የጋራችን ነው በማለት ተካፍለዋል ይባላል፡፡ በአቶ መለስ ግን ከኢትዮጵያ የተዘረፈ ገንዘብ
በውጭ አገር ባንክ አለ የሚለው ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን አቶ መለስ በግላቸው እንጂ ለእርሳቸው ቅርብ የተባሉትን ሰዎችንም
ነጻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው አቶ መለስ ከ1997 በኋላ በሕዝብ ዘንድ ከፈተኛ የሚባል ተወዳጅነትን አትርፈዋል፡፡ በእርግጥም
የአገርና የሕዝብ አሰቢነታቸውም በግልጽ በሚታይ ሆኔታ ጨምሯል፡፡ አቶ መለስ በግላቸው ባላቸው ችሎታ የሚታሙ ባይሆንም ለዘመናት
በአብዛኞቹ የአስተዳደር ዘመናቸው በሕዝብ ዘንድ ተዋዳጅ አልነበሩም፡፡ ወደመጨረሻው የአስተዳደር ዘመናቸው በሕዝብ ዘንድ ያለቸው
ተወዳጅነት ተደምሮ ምርጥ የአገር መሪ የሚያሰኛቸውን ብቃት ደርሰው ነበር፡፡ ሆኖም ግን አቶ መለስ በግላቸው ምርጥ ይሁኑ እንጂ
አገሪቱን በቀጣይነትና በብቃት ሊመራ የሚችል መዋቅር አላዘጋጁም፡፡ ይልቁንም በአስተዳደር ብቃታቸውና በሕዝብ ዘንድ ተዋዳጅ የሆኑ
ባለስልጣናትን ከሕዝብ እያገለሉ ራሳቸው ብቻ ጎልተው ታይተው ነበር፡፡ ለዚህ ደግም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት በሕዝብ ዘንድ ጥሩ እይታ
የነበራቸው አንደ አቶ አረከበን የመሰሉ ኃላፊዎችን ወደ ጓዳ ማድረጋቸው ነው፡፡ በግላቸው ከአደረጉት ጥረት ሌላ መዋቅራዊ የሆነ
የአስተዳደር ሥርዓትን ባለማስፈናቸውም አሁን ለተፈጠረው ሌላ ውዥምብር አገሪቷን ጥለዋት አልፈዋል፡፡ በድምሩ ግን የአቶ መለስ የመጨረሻ
ዓመታቶቻቸው ጥሩ የሚባል ነበር፡፡
አሁን ያለው አስተዳደር እንደገና እንደ አዲስ የሆነ ይመስላል፡፡ በዚህ ላይ ድሮውንም በዝርፊያ የተዘፈቀ ሥርዓት
ታክሎ፡፡ አሁን ያሉት ጠ/ሚኒስቴር ከግል ብቃታቸው ባሻገር የነበረውን ውስብስብ የአገሪቱን የአስተዳደር ሥርዓት ለመቆጣጠር ቀደመው በበላይነት ቁልፍ ቦታዎችን የያዙ ባለስልጣናትን ለመቆጣጠር እንኳን
እንደሚቸገሩ ይገባኛል፡፡ ሲጀምር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብሮ የመጣ የመሪነት ኃይል ያለው መንፈስ ይላቸውም፡፡ ብዙዎች የማይረዱት
ነገር ሰው ስለተማረ ወይም የተለያየ ኃላፊነት ላይ ስላለ አገር ለመምራት ያበቃዋል ተብሎ እንደሚተሰበው አይደለም፡፡ በራስ የመተማመንና
የመሪነት ኃይል ያለው መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ የመሪነት ኃይል መንፈስ ደግሞ የሚመጣው ጥልቅ ከሆነ ራስን በትልልቅ ቦታዎች ላይ የማየት
አቅም ሲኖር ነው፡፡ መሪ ለመሆን ሕዝብን አገርን አኔ ብሎ ማሰብ መቻልን ይጠይቃል፡፡ የአቶ መለስ የመጨረሻ አስተዳደር ዘመን አቅም
እዚህ ደረጃ በመድረሱ ነበር በትክክልም ለሕዝብም ለአገርም ኩራት እስከመባል የደረሱት፡፡ አቶ መለስ ይህን አቅም ለመገንባት ግን
አመታት አባክነዋል ሊያውም ሁሉንም ነገር መዘወር የሚያስችል ሥልጣን ይዘው፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ግን ጠ/ሚኒስቴር ተባሉ እንጂ ምን
ያህል ሥልጣን እንዳላቸው አጠያያቂ ነው፡፡ ያልተለመደ ሶስት ምክትል
ጠ/ሚኒስቴሮች ተመድበውላቸዋል፡፡ እንዚህ ምክትሎች ግን የተመደቡት በአጋዥነት ሳይሆን የጠ/ሚኒስቴሩን ሥልጣን ለመጋራት ነው፡፡
ሊያውም ቁልፍ የተባሉትን ሳይቀር፡፡ ከዚህ ውጭ ባሉ ክፍተቶች ደግሞ በየፓርቲው ያሉ ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነቱ አይቀሬ ይመስላል፡፡
በእኔ እይታ ኢትዮጵያ አሁን እየተመራች ያለችው በአቶ ኃ/ማርያም ሳይሆን በደቦ ይመስላል፡፡ ነገሮችም ቻይናውያን እየሰሩልን ካሉት
ግንባታዎቻችን ውጭ ዝም ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ አቶ ኃ/ማርያም ጠ/ሚኒስቴር የሆኑበት ሂደት የቱንም ያህል ሕገ-መንግስታዊ ነው ቢባልም
ስህተት ነው ብዬ እንዳምን ተገድጃለሁ፡፡ ሌላ በኢሕአዴግ ውስጥ ነባር ተሳትፎ የነበረው ሰው ቢሆን በተሸለ ነበር፡፡
ሌላው የኢሕአዴግ መሥራች የተባሉት ፓርቲዎችን ስናይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የተሻለ የሚባል ሰው እንደሌላቸው እናስተውላለን፡፡
በሁሉም ፓርቲዎች ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኙት ባለስልጣኖቻቸው እንኳንስ ለጠ/ሚኒስቴርነት ለሌላውም ይሁን እየተባለ እንጂ ከብቃት
አንጻር የሉበትም፡፡ በሚኒሰቴርነት ደረጃ ያሉትን በናስተውል ከአቶ መለስም ጊዜ ጀምሮ የወረደ ብቃት ያላቸው ይበዛሉ፡፡ አሁን ደግሞ
ብሷል፡፡ ከመስራች ፓርቲዎቹ ደግሞ ትልልቅ ሕዝብ አለን የሚሉት የባሰ
የወረደ ብቃት ባላቸው መሪዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ ከኦሕዴድ ብንጀምር ማን ጥሩ ሊባል እንደሚችል ይከብዳል፡፡ በአዴንም እንደዚያው
ነው፡፡ ደሕዴግን አንኳን ማን ያስታውሰዋል ደግነቱ በዋናው ተወከለ እንጂ፡፡ ዞሮ ዞሮ ያው ሕወሐት አነስተኛ ሕዝብና የፓርላማ ውክልና
እየተባለ በወገዝም በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ሰዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ
አቶ ቴዎድሮስ አድሀኖም በፊትም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርነታቸው ብቸኛው (ሌሎቹ ሁሉም በራሳቸው አቅደው የሚሰሩ ሳይሆኑ የአቶ መለስን
አፍ የሚጠብቁ ነበሩ) የሚኒሰቴር ሥልጣን የነበራቸው ነበሩ አሁንም የሚያሳፍሩ አይደሉም፡፡ ልብ በሉ እኝህ ሰው የሕዝብና የአገር
አኔነት የሚታይባቸው ናቸው፡፡ በሥልጣናቸው ያላቸው ስኬታማነትና ሞገስ ሚስጢርም ይሄው ይመስላል፡፡ ከላይ ያነሳሁትን አገረርን ለመምራት የአገርና ሕዝብ እኔ ብሎ ማመን ቁልፍ እንደሆነ አስታውሱ፡፡ አርከበም በዚህ የሚታሙ አይደሉም፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮንም ደህና እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
ከሌሎቹ ግን እንደዚህ በምሳሌነት እነኳን ሊጠቀስ የሚችል ለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ ስለሌለም ይመስላል አሁን ምክትል የሆኑት የብአዴንና
የኦሕዴድ ተወካዮች የተመረጡት የቱንም ያህል የምክትሉን ቦታ ባይመጥኑም፡፡
ይህ ችግር ምነአልባት የሕዋሐት የኖረ የበላይነት ወደሌሎቹ ፓርቲዎች ደህና ሰው እንዳይመጣ ውስጣዊ ሴራ ተደርጎ ሊሆን
ይችላል፡፡ ያም ሆኖ የፓርቲዎቹ የየራሳቸው ራዕይ ማጣት ግን በየፓርቲዎቹ ብቃት ያለው መሪ መታጣት ዋነኛ ምክነያት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
መጀመሪያ ሀሳቡ ከአቶ ተፈራ ዋልዋ ሲነሳ በደናገጥ ፈጥሮ በኋላ በታመነበት
የመተካካት መርሆ መተካካቱ ተተገበረ ቢባልም አተገባበሩ ብቃትን ለማምጣት ሳይሆን ሥልጣን ለወዳጅ ግለሰቦች ማውረስ አይነት ነበር፡፡
ይባስ እሱም ቀርቶ ተተኩ የተባሉትም የአቶ መለስንም ሞት እንደ ጥሩ አጋጣሚ አግኝተውት ነው መሰለኝ ተመልሰው አሁንም ዘዋሪ ሆነዋል፡፡
የታላቋ ቀን ልጅ እንኳንስ ብሔረሰብን መሠረት ያደረጉ ጎጠኛ ፓርቲዎች ውክልናን ይቅርና በአጠቃላይ በኮታ የሚባሉ ውክልናዎች አይመቹትም፡፡ ምርጥ ያአገር ልጆችን ወደመሪነት ማምጣትን አንጂ የአኛ ቀበሌ አልተወከለምና አንድ ሰው ከእኛ የሚባል ነገር በአገር ጉዳይ ቀልድ አይገባውም፡፡ የእኛው አገር እውነታ ግን ኮታ እንጂ ብቃት አይደለም፡፡ ክልሎቹ ሁሉ የአገር ሸክም በሆኑ ባለስልጣኖች ተወክለው በብዙዎቹ ክልሎች ያሉ ልማቶች ከፌደራሉ መንግስት ካልተሰሩ በቀር ንቅንቅ የሚሉ አይደሉም፡፡ በዚህ ላይ በሕዝብ ላይ የሚያደርሱት በደልና ዝርፊያው የተሰራውን ሁሉ የሚያወድም ነው፡፡ ቢሆን ቢሆን በአንዱ ክልል ምርጥ መሪ ከተገኘ በዚያው ክልል ባያስተዳደር የተሻለ በሌላ ክልል ቢሰራ፡፡ አሁን ያለንበት አይነት አስተዳደር ግን ጥሩ ውዥምብር ስለሆነ ምዕራባውያኑንም ይሁን ሌሎችን እንደልባቸው ለመዘወር እድል ስለሚሰጣቸው እንዲሁ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ ሕዝብ የእኔ የሚለውን ብዙም አይወዱትም፡፡
ማይክሮ ችፕስ 4 መሀይም ምሁራንን ማፍራት ምሁር ምሁራንን መንጠቅ
ቀደም ብዬ ከአነሳሁት የትምህርት ሂደቱን የማምከን ሴራ ጋር ይያያዛል ግን ይሄ በከፍተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርቶችን
ስለሚመለከት ልለየው አሰብኩ፡፡ ዛሬ የአገሪቱን ቁልፍ ኃላፊነት የያዙ ብዙ ሰዎች እራሳቸውን የ60ዎቹ እያሉ ከሚኮፍሱት የመከነ
አእምሮ ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹም የትምህርት እድል አግኝተው ወደተለያየ አገራት ሄደው የመጡ ቢሆኑም ስለተማሩት ነገር ቢጠየቁ
መልስ የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ በውጭ አገር ሄደው ከተማሩት በብዙ እጥፍ አገር ውስጥ የተማሩት የተሻሉ ለመሆናቸው አያጠያይቅም፡፡
በቀድሞው ዘመን የውጭ ትምህርት ይሰጡ የነበሩት በብዛት ወዳጅ አገር እየተባሉ የሚጠሩት የሶሻሊዝም ሥርዓት የሚከተሉ በመሆናቸው
ብዙዎች ወደእነዚህ አገራት ሄደው ተምረዋል፡፡ ዛሬ ሥልጣኑን ከያዙትም እነዚህ ይበዛሉ፡፡ በወዳጅ አገራት ተምረው የመጡት ምሁሮቻችን
ግን ብቃታቸውን ላየ አንዴ የት ነበር ሄደው የነበሩት ሻኪሶ ወርቅ ቁፋሮ ነው ወይስ ለትምህርት ወደ ውጭ አገር ያሰኛል፡፡ እንደውም
አንድ ከቡልጋሪያ የሁለተኛ ዲጊሪውን ይዞ የመጣ ሰው ያንተ ዲግሪ ከቡልጋሪያ ነው ወይስ ከዚችው ከእኛው ቡልጋ ነው እያሉ ሲፎግሩት
ሰምቼ ትክክለኛ አገላለጽ ነው ብያለሁ፡፡ በቃ እንደውም ድሮ አገር ውስጥ የተማሩትም ካል ተሰርዞባቸው የመጡ ነው የሚመስለው፡፡
እርግጥ በዚያን ወቅት የትምህርት እድሉ ይሰጣቸው የነበሩት ከጅምሩም የተወዳዳሪነት ብቃት ያላቸው አልነበሩም፡፡ የሚያሳዝነው ግን
በጣም በሰለጠኑና የሳይንስ መሠረት ናቸው በተባሉት አገር የተማሩት ደግሞ ይብሳሉ፡፡
ቀደም ባሉት ዘመናት አብዛኛው የሄድ የነበረው በሳይንስ ቀዳሚ ወደነበረችው ወደራሽያ ነበር፡፡ ግን የራሽያን ዲግሪ
ሁላችንም የምናውቀው አይነት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አብዛኛው የትምህርት እድል በምዕራባውያኑ አውሮፓ አገራት በተለይም ጀርመን፣ ኒዘርላንድ፣
ቤልጅየምና የመሳሰሉት የሚሰጥ ነው፡፡ በተለይ የጀርመን የትምህርት ዕድል ከሁሉም ይበዛል፡፡ በተመሳሳይ ጀርመን በምዕራባውያኑ አውሮፓ
በሳይንስ ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡ እንደ ራሽያው ሁሉ በጀርመን ተምሮ የመጣ ዜጋ ግን ዲግሪው አጠያያቂ እየሆነ ነው፡፡ እውንም ጀርመን
ክፍል ውስጥ ባይገቡ እንኳን ሁለ ነገሯ ለማስተማር የሚችል አገር ናት ብዬ አምናለሁ፡፡ ብዙዎችም እንደሚያማርሩት ለውጭ ዜጎች የሚሰጠው ትምህርት ብቃትን
ለማሳደግ ሳይሆን ጭራሽ ለማፍዘዝ ነው ይባላል፡፡ በእርግጥም ማንም አገራት ወሳኝ የሆነ ጥበባቸውን ለእኛ አስበው ላያስተምሩን ይችላሉ፡፡
በዚህ ሁሉ ግን የእኛው ችግር ዋነኛውን ቦት የሚይዝ ይመስለኛል፡፡ የጥበባቸውን ሚስጢር እንደማይነግሩን ካሰብን ሚስጢሩን መጎርጎር
ነበረብን፡፡ ግን እኛ የሄድንባትነ አገር ከረገጥን ጀምሮ እነሱ የሚሰጡትን እነኳን ትምህርት አንከታተልም፡፡ ከዚህ የዘንው የሄድንወ
ድህነታችን ያስገበግበንና ወራዳ ወደሆኑ ሥራዎች ሳንቲም ለመልቀም እንሰማራለን፡፡ ቀኑን ቆጥረን ግን ዲጊሪውን ይሰጡናል፡፡ በቃ
የሚፈለገው እሱ ነው የነጠፈ ጭንቅላት የከበደ ዲግሪ ይዘን ወደአገራችን፡፡ ያለ ደረጃችን ወርደን ወረዳ ሥራ የሠራንባቸው ዘመኖቻችንም
በዛው ልክ ጭንቅላታችንን ስለሚያወርዱት ትልቅን ነገር መመኘት፣ ክብርን፣ ሞገስን እንረሳለን፡፡
ልብ በሉ ሥራ አይሰራ እያልኩ አይደለም፡፡ የቱንም የወረደ ሥራ ብንሰራ ግን ማንነታችንን ረስተን መሆን የለበትም፡፡
ተቸግረን ታች ወርደን እንሰራለን፡፡ ግን አእምሮአችንና ምኞታችንን እላይ ማማው ላይ በክብር አስቀምጠን ሊሆን ይገባል፡፡ እዛድረስ
ያወረደንን ችግርም ነገ እንዴት እንደምነበቀለው በማሰብ፡፡ ልብ በሉ የሄ ሀሳብ ኩራትና ጉረኝነት ከሚሏቸው ሀሳቦች ተቃራኒ ነው፡፡
ታች ወርደን መስራታችንን ፈጽሞ መርሳት የለብንም፡፡ ይህ እንዴትና ከየት የት እንደደረስን የምንማርበት ሌሎችንም የምናስተምርበት
ነው፡፡ ክፋቱ የሚመጣው ከሁለት ጽንፍ ላይ ከሚገኙ የአስተሳሰብ ዝቅጠቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ጉረኝነት ሲሆን ታች ወርደን እንዳልሰራን
ድንገት ዛሬ ሲያልፍልን ሌሎችን የመናቅ በሽታ፡፡ አደገኛው ምንግዜም የማይታመን ሕሊና እነዳለን የሚያረጋግጥ ዝቅጠት ነው፡፡ ሁለተኛው
ደግሞ ሌላውም በተመሳሳይ ወርዶ መስራት አለበት ብሎ ማመን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጉረኝነቱ በተቃራኒ ወራዳን ሥራ ለሌሎችም መናፈቅና፣
ትልልቅ ራዕይ የማጣት ችግር ነው፡፡ እኔ ስለተቸገርኩ ታች ወረጄ የሠራሁትን ሌሎች ከእኔ በኋላ ያሉት እነደኔ ወርደው እነዳይሰሩት
ሌላ የተሻለ እድል መፍጠር ሲገባኝ ያው እኔ ያለፍኩበትን የችግር ሕይወት ብቻ የሕይወት ስኬት መስመር አድርጎ ማሰብ ትንሽነት ነው፡፡
ችግርን ልንበቀለው እንጂ ልናወርሰው መሆን የለበትም፡፡ እንዲህ ባለ አስተሳሰብ ታዲያ ገንዘብ ብቻ እንጂ ክብር የተባለ ነገር ሳይገባቸው
በሀላፊነትም ሲመጡ ያንኑ የወረደ አስተሳሰባቸውን ብቻ ሊያስተገብሩ ይሞክራሉ፡፡
በብዙ አገራት ከሚሰጡ የትምህርት እድሎች በተሻለ አሜሪካ ዕውቀትና ጥበብ የሚገበይባት ናት፡፡ ከሳይንሱም መዳበር
በተጨማሪ ሁሉም አይነት ቀለም ሕዝብ የሚኖርባት ስለሆነ ባይተዋርነቱ ስለማይኖር ለተማሪዎች ጥሩ ድጋፍ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡
እርግጥ የአሜሪካ የትምህርት ተቋማትም ከሌሎች በተሻለ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓታቸው በሚገባ አይነት ነው፡፡ በዚህ ላይ የእኛውም
አገር የትምህርት ሥርዓት በብዙ መልኩ ከአሜሪካ የትምህርት ሥርዓት ጋር ስለሚመሳሰል በጎ አስተዋጽዖ አለው የሚል ግምት አለኝ፡፡
በአሜሪካ አንዱን ከአንዱ መለየቱም ብዙ አይደለም፡፡ በተለይ አሁን አሁን፡፡ በአውሮፓና በሌሎች አገራት ግን እስካሁንም የዘር ልዩነቱ
አለ፡፡ በብዙ አገራት ደግሞ ለታዳጊ አገራት እየተባሉ የሚዘጋጁ ሥልጠናዎች በእርግጥም ዜጎችን ለማደንቆር ሆን ተብለው የተወጠኑ
ይመስላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሥማቸው ኢንተርናሽናል የሚል ቅጽል ያለባቸው የሥልጠና ፕሮግራሞች በጣም አደገኛና ምንም ይሄ ነው የሚባል
ዕውቀት የማይገበይባቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም እኛን ከመናቅ የተነሳ ይሁን ከሌላ አንጻር አይታወቅም ዝም ብለው ዲግሪ የሚሰጡ አሉ፡፡
በዚህ የትምህርት ተቋሞቿ አለም ዓቀፍ ዝናን ያተረፉት ኢንግሊዝ ትታወቃለች፡፡ ይህ ደግሞ የዚያች አገር መርዛማ የሆነ ሴራ ነው፡፡
ዲግሪውን በሥራ ላይ አንቀበልም ቢባል እኛ የሰጠንውን የማትቀበሉት እነማን ናችሁ ይሉናል፡፡
እንግዲህ እንደነዚህ ያሉ መክነን ሁሌም ከችግር እንዳንወጣ የሚደረጉ ተዘዋዋሪ ሴራዎች እንዳሉ ለግንዛቤ እንዲረዳ
ጠቆምኳቸው እንጂ የማክሮ ችፕሶቹ ነገር ግን ከዚህም በላይ ሊሆን እነደሚችል እገምታለሁ፡፡ ጉዳዩ ቀጥታ አእምሮን በሚያመክን የቴክኖሎጂ
ውጤትም ሊሆን ይችላልና፡፡ ጨረር ወይም ሌላ ቴክኖሎጂ ማለቴ ነው፡፡ ሌላው በክፉ መናፍስት እገዛ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ዛሬ የአለም
ፍትጊያው እዛላይ እንደሆነ ብዙዎቻችን አልነቀንም፡፡ የሚስጢራዊ ማሕበረሰብ ዋናኛ ሥራው እንዲህ ያሉ ሴራዎችን መተግበር እንደሆነ
እናስተውል፡፡ እኛ ለመለወጥ አንጥራለን በዙሪያችን ግን ብዙ ወጥመዶች እነዳሉ ብዙ አናስተውልም፡፡ አንች ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል!
በተከታታይ 8 ክፍሎች የቀረበው አንች ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል እዚህ ላይ ይብቃን፡፡ በሌላ ርዕስ እስከምንገናኝ
ቸር እንሰንብት፡፡
ልዑል አባት ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ የምናስተውልበትን አእምሮ ስጠን! አሜን!
የታላቋ ቀን ልጅ ሕዳር 19ኛው ቀን 2006 ዓ.ም (Son of the great day 28th of
November 2013)
No comments:
Post a Comment