ከምኒልክ ሳልሳዊ
ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የግለሰቦች ጥርቅም እስከሆኑ ድረስ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ጽንፈኛ፣ አሸባሪ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ተላላኪ፣ ኒዮ ሌንራል፣…….የሚባሉት መለጠፊያዎች እየተሰጧቸው አሳራቸውን የሚበሉት ‹‹ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች›› ናቸው፡፡
ምንም ያህል ልዩነት ቢኖረው የአንድን አገር ህዝብ የማይለወጠው የጋራ ማንነቱ ዜግነቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ህዝቦች ይልቅ የሚያመሳስሉን፣ የምንጋራቸው በርካታ እሴቶች አሉን፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውይነታችን (ዜግነታች) የጋራችን ነው፡፡ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ ተብሎ በጅምላ ዜግነት ሊሰጠው አይችልም፡፡ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ለመሆን መደራጀት አይጠበቅበትም፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግለሰብ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን ‹‹ኦሮሞ››፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ግለሰብ አማርኛ ተናጋሪዎች ‹‹አማራ››፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግለሰብ ሶማልኛ ተናጋሪዎን ‹‹ሶማሊ››…….እያሉ ነው ኢትዮጵያውያንን ‹‹ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች›› በሚል አዲስ ማምነት የሚደረድሩን፡፡ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ የሚባለው ከግለሰቦች እንጅ ከምንም የመጣ አይደለም፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር ካለበት መጀመሪያ መቅደም የሚገባው የስሪታቸው የግለሰቡ መብት ነው፡፡
‹‹ኦሮሞ፣ አማራ፣ትግሬ….› እየተባሉ የተቦደኑት ህዝቦች አንድ አይነት አይደሉም፡፡ እንዲያውም ኦሮምኛ ተናጋሪው ‹‹ኦሮሞ›› ከሚባለው ውጭ ከአማርኛ ተናጋሪው ጋር የሚጋራው በርካታ ማንነቶች ይኖሩታል፡፡ አማርኛ ተናጋሪው ‹‹አማራ›› ከተባለው ይልቅ ከኦሮምኛ ተናጋሪው ጋር የሚያመሳስሉት በርካታ ማንነቶች ይኖሩታል፡፡ ለአብነት ያህል ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ፣ ….ተናጋሪው ህዝብ ከቋንቋውም በላይ አንዱ የሌላውን ድንበር ተሸግሮ ከሌላኛው ቋንቋ ተናጋሪ ጋር በእምነት፣ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ገመዶች ይገናኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የአንድ ብሄር ሰዎች አይደሉም፡፡ የሙስሊሙ እንቅስቃሴ እንዲህ እስካሁን በጥንካሬ የዘለቀው በድንበር ተሸጋሪው ማንነቱ እንጅ በጠባብ ‹‹የብሄር›› ማንነት ታጥሮ አይደለም፡፡ ኦርቶዶክሶቹ፣ ፕሮቴስታንቶቹ፣ ካቶሊኮቹ በ‹‹ብሄር›› የታጠሩ አይደሉም፡፡
የአንድ ‹‹ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ…›› የእምነት፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ…መብቱ በግለሰብ ደረጃ ካልተጠበቀለት በስተቀር የ‹‹ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ…›› መብት ሊጠበቅ አይችልም፡፡ ችግሩ የ‹‹ብሄርና›› ሌሎች ማንነቶችን የሚጠቀሙ የፖለቲካ ቡድኖች ከግለሰብ ማንነት ይልቅ ጥቅል ማንነትን የሚያስቀድሙት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መሆኑ ነው፡፡ በ‹‹ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ሶማሊ…….›› ስም በጅምላ ከመነገድ ያለፈ ስለ እያንዳንዱ ህዝብ አያስጨንቀቃቸውም፡፡ 30 ወይንም 40 ሚሊዮን የአንድ ‹‹ብሄር›› ህዝብ በአንድ ጉዳይ ሊከፋ አይችልም፡፡ ቢያንስ ከገዥዎች ጋር ሆኖ የሚጠቀም አይጠፋም፡፡
ከፊሉን በእምነቱ፣ ከፊሉን በኢኮኖሚው፣ ከፊሉን እናከብርልሃለን በሚሉት ቋንቋው፣ ከፊሉን በነጻነቱ…. እያሉ ግን ሁሉንም ይጨቁኑታል፡፡ ሁሉንም ይጎዱታል፡፡ መስፈርቱ በብሄር ሳይሆን በግለሰብ ቢሆን ግን የሚድበሰበስ ነገር አይኖርም፡፡ ሁሉም የግለሰብ መብቶች እስከተከበሩ ድረስ የአገሪቱ ህዝብ መብት ይከበራል፡፡ የግለሰብ መብት ካልተከበረ ግን የማንም መብት ሊከበር አይችልም፡፡ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የግለሰቦች ጥርቅም እስከሆኑ ድረስ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ጽንፈኛ፣ አሸባሪ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ተላላኪ፣ ኒዮ ሌንራል፣…….የሚባሉት መለጠፊያዎች እየተሰጧቸው አሳራቸውን የሚበሉት ‹‹ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች›› ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment