Tuesday, December 3, 2013

ሞት፣ ወያኔና “እኛ”


(ፊልጶስ)
ethsaud1i
የግፍ ጽዋው ሞልቶ፣ ……
ሞልቶ፣….. ሞልቶ ፈሶ
ሰው መባል በሰው፣ ስዕብናችን አሶ
ከ’ጥናፍ- እስከ-አጥናፍ፣ ደማችን  “’ረክሶ’’፤
ውቅያኖስ፣ ባህሩን፣ ወንዙን አደፍርሶ
እዩት ይ’ጣለላል፣ አስፋልቱን አልብሶ።
ግን እኮ፣ …….. እንኳ’ ደም
ውኃ ፈሶ፣ አይቀርም
ይዘገያል እንጂ፣ በሰፈሩት ቁና፣ መሰፈር አይቀርም::
ዓለም የምጠፋው፣ ሰይጣናዊ  ምግባር  በሚፈጽሙ  ሳይሆን፤ ምንም ሳያደርጉ ቀጭ ብለው በሚመለከቷቸው ሰዎች ነው።/አልበርት አነስታየን/
እናም  የምድርን የሰቆቃና የሞት አይነት ሁሉ እያስከፈሉን፣ ኢትዮጵያንና  ኢትዮጵያዊያንን እያጠፉ ያሉት፣ ወያኔ/ሻአቢያ፣ ሳውዲ አረቢያ/ አረቦች፣ ምእራቡ ዓለም፣ ወይም ሌላ ሳይሆን፣ እኛ እራሳችን ቁጭ ብለን የምንመለከተው ወይም ለታይታ የምንታይው፣ ኢትዮጵያዊያኖች ነን። እኛ ነን….. በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ ተቀምጠን፤ ለወገኖቻችን መሆን ያልቻልነው። እኛ ነን…..  ለጠባብ መንደርተኞች ሀገራችን አሳልፈን የሰጠን። ትላ’ትናም ይሁን ዛሬ እውነቱ ይኸው ነው። ይኸን እውነታ ተቀብለን፣ በተለይም በዚች ወቅት ለህልውናችን ስንል የሚጠይቀውን መሰዋእትነት እስከ አልከፈልን ድረስ፣ ስቃይና ሰቆቃ፤ እንደትላ’ቱና እንደዛሬው ሁሉ፣ ነገም ተባብሶ ይደገማል። አሁን በያዝነው ከቀጠልን፤ ትውልድ ‘እየመከነ’፣ እኛም ‘ርስ-በርስ ስንጠላለፍ፣ የሚያለፍው ወያኔ፣ የማታልፈውን  ኢትዮጵያን ”ለህልፈት” ያበቃታል። ይህ እንዲሆን ደግሞ እንዴት እንፈቅዳለን? ቅደመ-ህዝበ ኢትዮጵያዊያን አልዳረጉትም። እኛም  አናደርገውም!
ለመሆኑ ከዚህ የበለጠ አሰቃቂና ዘግናኝ ሞት የበለጠ ምን ይሆን የም’ጠብቀው? ወይስ ገዥውቻችንም ከዚህ የባሰ በገዛ ሀገራችን  ስለሚፈጽሙብን?  ወይስ የሚሞቱትና የምድርን ፍዳ የሚከፍሉት ስደተኞች ስለሆኑ? የሞቱትስ  ምን አንጅት ቢቆርጥና እንደግር እሳት ቢያንገበግብ፤ ወደ ‘ማይቀሩበት ሄዱ። እኛ ግን ቀሪዎቹ፣ ሀገራችን በወያኔ መዳፍ ወስጥ እስከ አለች ድረስ ወርቅ ብንጫመት፣ እንቁ ብንላበስ፣ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ብንገነባና ሜዳ ሙሉ የእምነበረድ ቤት  ሰርተን ብንኖር በየደቂቃው፣ በየሰአቱና በየቀኑ እንሞታለን! እንቀበራለን!
ከሀገር ቤት ጀምሮ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ በ’ስር ቤት የሚማቅቁት፣  የአቅመ-ደካሞች እምባ፣ የወላጆች ዋይታ፣ በየአውራ ጎዳናው ያሉት ምንዱባኖች፣ በየአስፍልቱ የሚፈሰው ደም፣ በጉዴፈቻ ስም የተሸጡት የህጻናት ለቅሶ፣ በየባህሩና በየውቅያኖሱ የዓሳ ነባሪ ቀለብ  የሆኑትና  የሚሆኑት ወገኖቻችን፣ በየበርሀው አሸዋ ለብሶ የቀረው አጽማቸው፣ እትብቱ ሳይቆረጥ፣ ጣሊያን ጠረፍ ላይ የተገኘው የህጻን ልጅ ሬሳ፣  ይጮሀል! ይጣራል! “ማራ ናታ!” ይላል:: ይህ ጩህትና ጥሪ ደግሞ እየበላን ያስርበናል፣ እየጠጣን ያስጠማናል፣ እየለበስን ያሳርዘናል፣ እየትኛን ያቃዥናል፣ ሳንሞት ይገለናል። ከዚህ የከፋ ደግሞ ለሰው ልጅ ምንም ነገር የለም። ‘ርግጥ ነው፤
ኑሮማ ይኖራል ኑሮ ከትባለ
ኅሊና ተሽጦ ለስጋ እየዋለ።
ለወያኔ አሳልፈን የሰጠነውን መብታችንና ነጻነታችንን፤ በዚህም ሳቢያ የሚደርስብንን ድህነት፣ እስራት፣ ውርደትና ንቀት በመሸሽ ፤ በባእድ ሀገር እናገኘዋለን ማለት የህልም እንጀራ ነው። ሁሉንም የሰቆቅቅ እይነት አልፈን፣ ከሞት ብ’ተርፍና ቁሳዊው ነገር ቢሳካ እንኳ’፣ የመንፈስ ድህነቱና የህሊና ህመሙ እሰከ መቅብራችን ይከተለናል። ታዲያ እጅግ የሚያሳዝነውና  የሚዘገንነው ግፉና ሞቱ የሚደርስባቸው ፣ታግሎ የሚያታግላቸው ያጡና  ከሀዲወችና ስግብግቦች በስማቸው የሚነግዱባቸው፣ የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ነው። ትውልድ የማጥፋቱም አንደኛው ዘዴም ይኸው ነው።
በዚች ሰዓት እንኳ’ አረቦችና ሌሎቹም በሀገራችን ምድር ደርታቸውን ነፈተው ሲራመዱና በመኪናቸው ገፍተውን ሲያልፍ፤ በፍርሀት አንገታችን ደፍተን ወይም እየትልጎመጎምን እንጂ የምናልፈው፤ ቀና ብለንም አናያቸውም። ‘የጥቂቶች” በሆነችው፣ ነገር ግን እትብታችን በተቀበረባት ምድራችን ”ባ’ዳነት” ይሰማናል።
ሀገሬ ላይ ሁኘ፣ እጅግ አ’ርጎ ከፋኝ፣ ሀገሬ ናፈቀኝ
በሰው ሀገር ሁኘም፣ እጅግ አ’ርጎ ከፋኝ፣ ሀገሬ ናፈቀኝ
እሬ በይ ሀገሬ!  እሬ በይ ኢትዮጵያ! ሀገሬን ንገሪኝ።
ወያኔም ሆኑ የሌሎቹ፣ የሌት-ተቀን ምግባራቸውና ምኞታቸው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ከምድረ ገጽ ጠፍተው ማየት ነው። ይህ ደግሞ በተለይም ወያኔ/ሻአቢያ ገና ሲፈጠሩ ጀምሮ፣ በተግባርም  አሳይተውናል። አረቦች አይደሉምን ከምዕራቡ ዓለም ጋር በመተባበር ፤ ወያኔ/ሻአቢያዎችን ”ጡጦ እያጠቡ”  ከዚህ ያደረሷቸው ? ወይስ መጽሐፍ እንደሚለው፤
” ….. አይናችን እያየ፣ አናስታውልም፤ ጆሮ’ችን እየሰማ፣ እናዳምጥም?………”
ወይስ “….. ህሊናችን በጋለ ብረት እንደተተኮሰ ሆኖ ደንዝዞ?…….’’ ወይስ
ፍርሀት?  ማን ነበር  “ፈራን ለማለት እንኳ ፈራን” ያለው::
በተለመደው ‘ቱልቱላቸው’ ”በሳአውዲ አረቢያ የሚገኙ ሕገ-ወጥ ስደተኞች ….” እኮ ነው ያሉን። እነሱ በኢትዮጵያ ምድር ”ሕጋዊ” ሆነው፣ ከርታታ ወገኖቻችንን  ግን ” ሕገ-ወጥ ስደተኞች…” እያሉ በሚፈሰው ደማቸው ተሳለቁ፤ በሚዘምበው እ’ምባቸው ላይ ገለፈጡ ። ግን እነሱ ምን ያደርጉ?  እኛ እንጂ! እነሱማ ትግላቸውን ታግለው፣ አላማቸውን እየተገበሩ ነው።
ለመሆኑ በየትኛው መመዘኛና ሀገራዊ ፍቅራቸው ነው፣ ለኢትዮጵያዊያን  እንዲቆሙና  እንዲቆረቆሩ የምንጠይቃቸው? የኢትዮጵያ መንግስት ነን ስላሉ?  ታዲያ ማን ብለው ኢትዮጵያን ያፍርሱ? ማን ብለው ኢትዮጵያዊያንን እንደ አውሬ ያሳድኑ፣ ያድኑ? ማን ብለው ኢትዮጵያዊያንን ያዋርዱ?…
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ ከኤርትራ ወገኖቻችን የለያዩን?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ ያለ ወደብ ያስቀሩን?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ ሱዳንን ለምነው ሀገራችን ቆርሰው ያስረከቡልን?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠረውን ወገናችን በባድሜ ስም ይስረሸኑልን?
  • ኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ ወገኖቻችንን ከገደል የወረወሩልን?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ እኛ ቁራሽ መሬት የጎጆ መቀለሻና ጥማድ በሬ የምናውልበት ነፍገው፣ ለአረቡና እግር ላደረሰው ሁሉ የማእድን ሀብታችንን ሳይቀር የሚቸበችቡት?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ የሚገሉን፣ የሚያስገድሉን?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ እነሱ የሚዘርፉን አልበቃቸው ብሎ፣ እኛ ጠኔ  እየጣለንና  እያተሳደዱን፣ ለጥላቶቻችን አሳልፈው የሚሰጡንና ያሚያዘርፉን?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ በእስር ቤት ኢትዮጵያዊያንን የሚያማቅቁትና የሚገርፉት?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ በቋንቋና በሀይምኖት ከፋፍለው፣ስ’ብናችን ገፈው የሚጫወቱብን?
  • የኢትዮጵያ መንግስት ነን እያሉ አይደለም እንዴ፣ በጣሊያን ሀገር የግራዚያን ሀውልት መሰራቱን ለመቃወም የወጡትን ያሰሩ? አሁንስ የሳአውዲን ግፍ ለመቃወም የወጡትን ምን እያደረጉ ነው? እነዚህን ሰላምዊ ሰልፎች እንኳ’ ቢፈቅዱ፤ ከሞኞቹ ላይ የለመዱትን ቦለቲካ ይቸረችርላቸው ነበር። ነገር ግን  ባንዳነታቸውና  ቅጥረኛነታቸው ስለማይፈቅድላቸውና ምንነታቸው ስለሆነ አላደረጉትም።
  • ኧረ ስንቱ…….ኧረ ለመሆኑ  ያለተነገር እንጅ ያልሆነው ነገር አለን?
ግን የትላ’ትናውንም ሆነ የየቀኑን ግፋቸውንና የሀገር ክህደታቸውን እየረሳን፣ አሁንም እንደ ሞት ሁሉ እነ’ሱም አዲስ  ይሆኑብናል። ግን ለምን? ወይስ  ከታሪክና  ከትላንቱ ያለመማርና  የመርሳት አባዜ?
ሞት ሁሌም አዲስ ይመስለናል ወይም ይሆንብናል፤ ይህ ‘ራሱን የቻለ ለሰው ልጅ ያለተፈታ ምስጢርና እንቆቅልሽ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ተቀኝተውለታል፤
“እግዚ’ር በአንድ ነገር፣ አይጠረጠርም
የከፋው ሰው ሞቶ፣ ደስ ያለው አይቀርም” / የህዝብ /
ሌላው ቢቀር ወያኔ ግን ምስጢር ፣ አዲስና  እንደ ሞት እንቆቅልሽ  ሊሆንብን ፈጽሞ ባልተገባ ነበር:: አንድ ትውልድ ሙሉ የማንነቱንና የእኩይ ምግባሩን መከር እየሰበሰብን ነውና ያለነው።
ጥረታችን፣ ድካማችን፣ ጌዚያችን፣ ተግባራችንና ሁለንተናችን፤ ህዝቦችን ከውድቀት አትርፎ፤ ኢትዮጵያ የዜጎች ሀገር ማድረግ መሆኑ ቀርቶ፤ እኛ ግን እንደ ሞት ሁሉ የወያኔን ምግባሩንና ማንነቱን ትላንትናም ሆነ ዛሬ እንደ አዲስ እናወራለታለ፣ እናስወራለታለን፣ እናራግብለታለን፣ እንገረምለታለን፣ እናስገርምለታለን። እነሱ  እንደሚሉን ”ውሻወቹ ይንጫጫሉ፤ ግመሎቹ ግን………  ትውልድንና ሀገርን የማጥፋቱን አላማችን እንተገብራለን፤ የ’ናንተም ስቃይና ሞት ከሀገር አልፎ በዓለምና በየደርሳችሁበት ሁሉ ይሆናል።”አንድ አዛውንት፤ ” ‘ርሀቡንና ንቀታቸውን ችለነው ነበር፤ እነ’ሱ ግን ጥጋቡን አልችለው አሉ።” የሚል ፈስቡክ ላይ አይቻለሁ። ግን እነ’ሱ  እንዲያስርቡናን እንዲንቁን ማን ፈቀደላቸው?
መሞቱ የማይቀረው ወያኔ፣ እስከዚች ሰዓት ድረስ  በሆድ – አደር ሎሌዎቹና በሀገሪቱ ጥላቶች እታገዘ፤ አላማውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይፈጽማል፣ ያስፈጽማል። ወያኔ ትላንት ሆነ ዛሬ፤
ወያኔ + ወያኔ – ወያኔ x ወያኔ ÷ ወያኔ = ወያኔ ነው።
ወያኔ ይህን አደረገብን፣ ለምን ይህን አደረገ ፣ ሀገር ሸጠ፣ ለዜጎቹ አይቆረቆርም፣ ትውልድን አጠፋ፣ ወዘተ እያልን ዓመታት ሙሉ ማላዘናችንና በጠላቶቻችን በር ድጅ  መጥናቱ፣ የበለጠ ለግዥወቻችን የልብ- ልብ በመስጠት፣”ከእሳት ወደ ‘ረመጡ፣ ቁስሉ ወደ ማይሽር ውርደት ከተትን እንጂ ያስገኘው ተጨባጭ ውጤት የለም። አስገኘም ከተባለ አንድ እስረኛ አስፈትቶ፣ አምስት ማሳሰር ነው::
ከዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን፤ የግዥዎቻችንን ማንነትና እሥስታዊነት ማጋለጥና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሰላማዊ ሰልፍም ተቃውሞው ተጠናክሮ  መቀጠል አለበት። ይህ ግን የትግሉ አንድ መቶኛ  እንደ ማለት ነው። ስለዚህም ያለትቋረጠ ህዝባዊ አመጽና እምቢተኝነት የግድ ይላል።  ተደጋግሞ እንደተነገረው ይህ ደግሞ ሊሆንና ሊፈጸም የሚገባው ከባህር ማዶ በሚበራ ሻማ ወይም በሚውለበለብ ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆን በሀገር ቤት ወስጥ  ብቻ ነው።
በተለይም በአሁኑ ሰዓት፣ ወያኔ ገፊ ኀይል አ’ቶ እንጂ፤ ‘ራሱ በቆፈረው ጉድጓድ እየተሸራተተ ነው።  ተቃዋሚ ነን ባዮች በዚህ የመከራችን ዘመን ወደ ተባበረ ኃይል መምጣት የማያስችላችሁ ነገር ካለ ወያኔያዊነት ወይም ሆድ-አደር ሎሌነት ወጭ ሌላ ምክንያት ሊኖር  አይችልም። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተለመደው ምርጥ ብዕሩ ባለፈው ሳምንት፤ ”አደባብዩ ምን ያህል ይርቃል?” በሚል ርዕስ አንድ ጦማር አስነብቦናል።
እኔ ግን እላለሁ፤
አደባብዩ ምንም ያህል አይርቅም፤ ለ’ኛማ እንዲያውም እጅግ በጣም ቅርብ ነው። አደባብዩ ያለው ልባችን ውስጥ ነውና! እናም የአደባብይ ሰው ያድርገን!
አስተያየት ለመስጠት ለምትፈልጉ:  philiposmw@gmail.com


goolgule

No comments:

Post a Comment