By Abisinia Alexander Zegreat
ናይጀሪያን ለማሸነፍ ምናባታችን እናድርግ? • እኔ አስር ምርጥ ዘዴዎች አሉኝ (መልካምሰው አባተ) ይሄ
እግር ኳስ ያለመቻላችን ነገር የአባቶቻችን ልጆች አለመሆናችን ማሳያ ነው፡፡ ምክንያቱም የእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ
ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት የእግር ኳስ ጨዋታ 70 ፐርሰንት የሚፈልገው ነገር ወኔ ወይም አልሸነፍ ባይነት ነው፡፡
ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ከማንኛውም ጥንታዊ አፍሪቃውያን በበለጠ ባልሸነፍ ባይነት የላቁ ስለመሆናቸው የሞቱ አያት
ቅድመ አያቶቻችን ከሞት ቀስቅሰን ማረጋገጥ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ የዘመኑ አንዳንድ የአፍሪካ ልጆች ግን
ከዘመኑ የኛ ልጆች በወኔ የላቁ ስለመሆናቸው የእግር ኳስ ደረጃችን ማሳያ ነው፡፡ በርግጥ የዘንድሮ ቡድናችን
በችሎታም ሆነ በወኔ የሚታማ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በሚመጣው ጨዋታ ናይጀሪያ አሸንፋን ወደ ብራዚል የሚያበር
ቲኬት ከቆረጠችብን፤ በበኩሌ እኛ ያባቶቻችን ልጆች አለመሆናችን በማረጋገጥ ተስፋ ቆርጨ ከስታዲዮም ወደ ስታዲዮም
እመለሳለሁ፤ ከአዲሳባ ስታዲዮም ወደ ለንደን ስታዲዮም ማለቴ ነው፡፡ ጌታዬ ግን ይህን አያድርገው፡፡ ኢትዮጵያ
እንደምንም ብላ ለአለም ዋንጫ እንድታልፍ አድርጎ የምንጎርርበት ጉዳይ አያሳጣን ዘንድ ቤተክርስቲያን እና መስጊድ
እናጨናንቅማ፡፡ ......ግን ደግሞ እጃችን አጣጥፈን ተቀምጠን እግዜርን ብቻ ማስቸገር ተገቢ አይመስለኝም፡፡
ጀግናው ብሔራዊ ቡድናችን ይቺን ጉረኛ ናይጀሪያ ድባቅ እንዲመታልን የየራሳችን የዜግነት አስተዋፅኦ ማበርከት
ይጠበቅብናል፡፡ ዝም ብሎ የተጫዋቾቻን እግር ብቻ ማዬት ዋጋ የለውም የሚል እምነት እና ሃይማኖት ነው ያለኝ፡፡ ብዙ
ጊዜ ኳስ ጨዋታ ሲኖር እና ቴሌቪዝን ላይ ሳፈጥ ጓደኞቼ ቀንደኛ ኳስ ተመልካች እመስላቸዋለሁ፡፡ ተሳስተዋል፡፡ እኔ
ቀልደኛ የኳስ ተመልካቾች ተመልካች ነኝ፡፡ ቼልሲና አርሰናል እየተጫወቱ ነጭ ስክሪን ላይ አፍጥጨ ካያችሁኝ ከነጩ
ስክሪን ባሻገር አረንጓዴ ሜዳ ላይ የሚፈነጩ ተጫዋቾችን እያዬሁ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከአሰልጣኝ ሞሪንሆ ጀርባ
አይስክሬም የምትልስ ሴትዮ ወይም ከአሰልጣኝ ቬንገር ጀርባ በርገር የሚገምጥ የፈረንጅ ጎረምሳ እያዬሁ ነው ማለት
ነው፡፡ ምክንያቱም እግር ኳስ ለኔ ምግብ ነው፡፡ ባለፈው እናት አገር ከደቡብ አፍሪካ ስትጫዎት የኛ ልጅ ጌታነህ
ጎል ሲያገባ ጥላ ፎቅ ያለ አንድ ወጣት በጭፈራ አስታኮ የአንዲት ኮረዳ ከንፈር አስገድዶ ሲስም አየሁ፡፡ እግር ኳስ
ለኔ ጅንጀና ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እዚሁ ጨዋታ ላይ የደቡብ አፍሪካው ተጫዋች ጎል ሲያገባበብን ጥላ ፎቅ
የተቀመጠ ሸገር ከሚባለው የቤተሰብ ኤፍ. ኤም. ጣቢያ የመጣ አንድ አጠር ብሎ ረዘም ያለ፤ ወፈር ብሎ ቀጠን ያለ፤
ቀላ ብሎ ጠቆር ያለ፤ ጋዜጠኛ ወገቡን ሲያክ ተመለከትኩ፡፡ እግር ኳስ ለኔ የወገብ ቅማል ነው፡፡ ታስታውሱ ከሆነ
በአፍሪካ ዋንጫ ጊዜ ሳላዲን የአርቲስቶች ቡድን አጥቂ የሆነው እንቶኔ እንኳን የማይስተውን ጎል ሳተ፡፡ አጠገቤ
ጨዋታውን የሚከታተል አንድ ቲፎዞ የሳላዲንን መሳት በሞቱት ጠቅላይ ሚኒስቴር አሳበበ፡፡ እግር ኳስ ለኔ የጎሳ
ፖለቲካ ነው፡፡ አንበሳው ምንያህል ተሾመ በሴንትራል አፍሪካው ጨዋታ ምን የመሰለች ጣፋጭ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ጎሏን
ለውድ ፍቅረኛው (ስሟን ኤፍ.ኤሞች ነግረውኝ ነበር ረሳሁት) መታሰቢያነት አደረገ፡፡ እግር ኳስ ለኔ ፎንቃ ፊርፊር
ነው፡፡ ከሴንትራል አፍሪካ ጋር የሚደረገው ጨዋታ ሊጀመር ሁለት ደቂቃ ሲቀረው አንዲት የደቡብ አፍሪካ ምላጭ
በምላጭ አጥቂያችን ጫማ ውስጥ ተወሽቃ ጉድ ሰራችን፡፡ ለኔ እግር ኳስ ቲያትር ነው፡፡ ወደ ጥሎ ማለፉ ማለፋችን
እውነት ሲሆን አንድ ዝነኛ የኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም፤ ፕሬዚዳንት ግርማ እና የዘጠኙ
ክልሎች መሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋችኋል አለን፡፡ እግር ኳስ ለኔ ነጭ ውሸት ነው፡፡ ይገርማችኋል በወቅቱ
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንኳን ኳስ አይተው የደስታ መግለጫ ሊያስተላልፉ ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን እንዳላት
እንደማያውቁ ያወኩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከኮንጎ
ብራዛቪል ጨዋታ ድል በኋላ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ‹‹እችላለሁ! ሁልጊዜ በዕድል ማሸነፍ የለም!›› በማለት ሰይፉና
እና ታደለ በተባሉ አገር ውስጥ በተመረቱ ቱቦዎች አማካኝነት ለገነነ መኩሪያ መልዕክት አስተላለፉ፡፡ እግር ኳስ
ለኔ የቤት ጣጣ ነው፡፡ ገና ከናይጀሪያ ጋር ሳንጫዎት ኢትዮፒካ ሊንክ የተሰኘ የሬዲዮ ብግራም ‹ኢትዮጵያ ለአለም
ዋንጫ አለፈች› ብሎ አወራ፡፡ እግር ኳስ ለኔ የጫት ማጣፈጫ ኮረሪማ ነው፡፡ ዛሚ ዘጠና የሚሉት ሬዲዮ ሰውነት ቢሻው
ያሸነፉትን ጨዋታ የ‹መለስ ራዕይ› ነው ያሸነፈው አለ፡፡ እግር ኳስ ለኔ ‹አታሰማን የለ!› የሚሉት ተረት ነው፡፡
ባለፈው ይሄ የተባረከ ምንያህል የሚባል ልጅ ሴንትራል አፍሪካ ላይ ጎል ባስቆጠረበት ቅፅበት እህቴ ወንድ ልጅ
ከነቃጭሉ ዱብ አደረገች፡፡ እግር ኳስ ለኔ ህይወት ነው፡፡ ያኔ ደግሞ ደቡብ አፍሪካን ያሸነፍን ለታ ከሶስት በላይ
ዜጎቻችን በደስታ ብዛት መሞታቸው ተሰማ፡፡ እግር ኳስ ለኔ ሞት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ እግር ኳስ ለኔ በቃ እግር
ኳስ ነው፡፡ ***** ይህን
ያህል ሳላስበው ብዙ ካወራሁ፤ አስቤ ለማውራት ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ደግሞ ልምጣና ናይጀሪያን ውሃ ውሃ
የምናሰኝበትን የማጥቃት፤ የመከላከል፤ የማንከልከል እና የመበከል ዘዴ ያልኩትን እንደሚከተለው ልዘርዝር፡፡ መቼም
የዘንድሮ ሰው በደንብ አይሰማ፤ እስቲ የዛሬን ልብ ብላችሁ ስሙኝ፡፡ (እኔ’ምለው የኢትዮጵያ ህዝብ በደንብ
እንዲሰማኝ፤ እንዲያደምጠኝ እንዲሁም እንደከታተለኝ ............ቆይ.........አስናቀን ልሁን እንዴ!?
ወይስ ራሱን ድራማውን ሰው ለሰው ልሁን? ወይስ ምናባቴ ልሁን? የመደመጥ ሱስ እንደሚገድል እያወክ አይተህ
አትለፈኝማ ወገኔ (ትምህርተ ስላቅ!)) 1. ኢትዮጵያ
ናይጀሪያን በቀላሉ እንድትገረስስ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከማጨብጨብ አንስቶ ‹‹ቦኮ ሃራም›› እስከመሆን መድረስ
መቻል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ (‹ቦኮ ሃራም› የናይጀሪያ ተጫዋቾች እጅግ የሚፈሩት ተንከሲስ እስላማዊ አሸባሪ
ነው፡፡ በናይጀሪያ ተጫዋቾች ፊት የቦኮ ሃራም ስም ተጠራ ማለት እግራቸው ቄጠማ ሆነ ማለት ነው፡፡ ‹ቦኮ ሃራም›
በቀን ስድስት ቦምብ ካላፈነዳ፤ ቀኑን ሙሉ ምግብ ሳይበላ ዋለ እንደማለት ያለ ነገር ነው፡፡ ናይጀሪያውያን በጣም
ነው የሚፈሩት፡፡ እናም ቲፎዞዎቻችን ‹‹እኔ ቦኮ ሃራም›› እያሉ በመጮህ የናይጀሪያ ተጫዋቾችን ማስበርገግ ተገቢ
ነው፡፡ የመንግስት ተቃዋሚ ወጣቶች ‹‹እኔ እስክንድር ነጋ ነኝ፤ እኔ አቡበክር ነኝ›› የሚለውን ፉከራ ለጊዜው
‹‹እኔ ቦኮ ሃራም ነኝ›› በሚል ለውጣችሁ ናይጀሪያን አስፈራሩልንማ፡፡ ለጊዜው ነው የምናስቸግራችሁ፤ ቆታችሁ ‹እኔ
እንትና ነኝ› ወደሚለው ዋናው ስቱዲዮዋችሁ መመለስ ትችላላችሁ፡፡ እኔም በእናት አገሬ በኩል የናንተ ነኝ፤ ባባት
አገር ግን ሳንለያይ አንቀርም፡፡ ይሁን፤ ዋናው የእናት ልጅ መሆን ነው፡፡) 2.
የሴቶች አስተዋፅኦ ለኤኮኖሚያችን ብቻ ሳይሆን ለእግር ሳችንም መሆን አለበት፡፡ እንደሚታወቀው የአፍሪካ
ወንድሞቻችን ትልቁ ደካማ ጎን የሴቶቻችን ደም ግባት ነው፡፡ ታዲያ በሴቶቻችን ዳሌ እያማለልን ጎል
ብንስከፍታቸውሳ!? ይሄማ እንዴት ይሆናል ብሎ የሞራል ጥያቄ የሚያነሳ ፌሚኒስት ሁላ ይንጫጫ ይሆን ይሆናል፡፡ ግንኮ
የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሰሞን የአፍሪካ ህብረት አጥር ዙሪያ ግልገል ሱሪ ባጠለቁ ፈጣጣ ሴቶቻችን ተከቦ ሳለ
የተንጫጫ ማንም አልነበረም፡፡ እንግዲህ መዋረዳችን ካልቀረ የሴቶቻችን ውርደት ለናይጀሪያ ተጫዋቾች ውድቀት
ብንጠቀምበት አይከፋም፡፡ አፍዝ አደንግዝ ቀይ፤ ጠይም፤ ሰማያዊ፤ ቢጫ፤ ወፍራም፤ ቀጭን.......ምናምን ሴታቻችን
በናይጀሪያ ተጫዋቾች መሃል እንዲርመሰመሱ በማድረግ የእግርኳሱን የመለስ ራዕይ እንዲሁም የፌደሬሽኑን ትራንስፎረሜሽን
ዕቅድ ማሳካት አለብን ነው የምለው፡፡ (እኔምለው አሁን አቶ መለስ ለኳሳችን ራዕይ ነበራቸው? አረ ተው፤ ተው፤
ተው፤ ተው፤ተው፤ ተው፤.......አንተዛዘብ!) ልማታዊ
መንግስታችንም ይህን በሚገባ ይደግፋል፡፡ ምክንያቱም ቻይና ራሷ ኤኮኖሚዋ እንደ መንገዳገድ ሲቃጣው የአንዳንድ
ሴቶቿን ዳሌ ጠረብ ጠረብ አድርጋ foreign currency ምናምን ትሰራለች ተብለን የተማርንበት ሁኔታ ነው
ያለው፡፡ ልማታዊት ቻይና እንዲያ ካደረገች ልማታዊት ኢትዮጵያ ምን ቆርጧት ትግደረደራለች? እንዳው ግን መንግስታቸን
የመለስ ራዕይ ውግዝ ከመዐሪዮስ ብሎት ይሄማ አይደረግም ቢል እንኳ፤ ሴቶቻችን የናይጀሪያ ተጫዋቾችን ለመጥለፍ
በስታዲዮም ዙሪያ መኮልኮላቸው ባይቀር ምን አለ በሉኝ፤ እኔ ራሴ ዳሌ ቢኖረኝ....ኖሮ፤ ተው ጎበዝ ክፉ
አታስወሩኝ፤ የጆን ኦቢ ሚኬል ደመወዝ እኮ በሳምንት 100 ሺ ዶላር ነው፡፡ የኔ ቤተሰብ እና ዘር ማንዝር የዘላለም
ደመወዝ ማለት ነው፡፡ 3. እስኪ ሰሞኑን የሰማሁትን
ቀልድ ነገር ላጫውታችሁ፡፡ ቀልዱን ያጫወቱኝ ቀልደኞች ቀልድ አሉት እንጂ እኔስ እውነት ነው ባይ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያ
ከሴንትራል አፍሪካ ጋር ስትጫወት ምን ያህል ተሾመ በግራ እግሩ (እግሩን መሳም ነበር፤ ፍቅረኛው ትቆጣ ይሆን?)
ጎል አግብቶ አገር ቀውጢ ሲሆን ቀውጢነት ያልበቃቸው አንዳንድ ያዲሳባ ጋዜጠኞች ወዲያውኑ ወደ ሰውነት ቢሻው ደውለው
ነበር አሉ፤ ጨዋታው ገና ሳያልቅ እኮ ነው?! የወሬ ህመም ሲጠና እንዲህ እንደሚያረግ መች አውቄ እናቴ፤ መና
የሆንኩ ልጅ?! ‹‹ሄሎ?›› አለ ጋዜጠኛው፡፡ ‹‹ሄሎ ሰውነት፤ ሰይፉ ነኝ… እባክህ ምንያህልን አገኛኘኝ!?›› ‹‹እንዴ! ገና ጨዋታው ሳያልቅ ምነካህ?›› ‹‹አይለቃ! ታዲያ እኔ ልሙት እንዴ!?›› ‹‹ለወሬ ልሙት በልና ላገናኝህ!?›› ‹‹ለወሬ ልሙት!›› ‹‹ድብን
ትላታለህ እንጂ አታገኘውም!›› አሉና ስልኩን ጥርቅም፤ አቶ ሰውነት፡፡ እኔም እሰይ ማለት፡፡ አሁን እኔ የአዲስ
አበባ ፖሊስን አደራ የምለው የናይጀሪያው ጨዋታው እስከሚያልቅ ድረስ በተለይ ሰይፉ ፋንታሁን እና አበበ ግዳይ
የተባሉ ግለሰቦችን ማረሚያ ቤት እንዲያቆይልን ወይም ጋዜጠኝነት እንደ ጉድ የሚነኮርበትን እንጦጦ ጋራ ስር ዝቅ ብሎ
የሚገኝ አንድ የዘመድ አዝማድ መሰባሰቢያ ኤፍ.ኤም. ጣቢያ ለአንድ ቀን እንዲዘጋልን ነው፡፡ ይህን የምለው ወድጄ
እንዳይመስላችሁ፤ እስኪ አስቡት በጨዋታው መሃል ሰይፉ ለወሬ ቸኩሎ ጀማል ጣሰውን ኢንተርቪው ካላደረኩህ ቢልብንሳ!?
ጀማል ደግሞ ጥሎበት ቃለመጠይቅ ይወዳል፤ ለቃለ መጠይቅ ብሎ ጎሉን ትቶ አይሄድም ብትሉ ጀማል ራሱ ይቀየማችኋል፡፡
እንዳውም አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በአማርኛ ክፍለ ጊዜ መምህሩ ‹ክሊንስማን ካለ ጎል አለ›
የሚለውን አባባል ተመሳሳይ አረፍተ ነገር ሰራለት ቢሉት ‹ኢንተርቪው ካለ ጀማል አለ› ብሎ አረፈ አሉ፡፡ አደገኛ
ትውልድ እየተከተለን ነው! 4. ብዙ ጊዜ ሰዎች የሰውነት
ቢሻውን ስኬት ከችሎታ ጋር ብቻ ያያዙታል፡፡ እኔ ግን የሰውነት ቢሻው ችሎታ ምንጭ ገነነ መኩሪያ የተባለ
‹‹ጠላታቸው›› ይመስለኛል፡፡ ልብ ብላችሁ ካያችሁልኝ ሰውነት ቢሻው በሚሰጡት አስተያዬት ውስጥ ገነነ መኩሪያ ገኖ
ይታያል፡፡ ምንም እንኳን የገነነ መኩሪያ የስልጠና ፍልስፍና ከራሱ ከገነነ በስተቀር ለሌላው እንግዳ ቢሆንም ገነነ
(አሰልጣኝ ነው ጋዜጠኛ?) ሰውነት ቢሻው ላይ የፈጠረው ዕልህ ለቡድናችን ውጤት አስተዋፅኦ አበርክቷል ማለት
ይቻላል፡፡ ገነነ ሰውነት ቢሻውን ማብሸቅ ይቀጥል ዘንድ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ 5.
ለናይጀሪያ ተጫዋቾች የእንቅልፍ መድሃኒት መስጠታችን እንዳንረሳ፡፡ ከዚህ ቀደም ናይጀሪያውያን ደጋፊዎች በሜዳቸው
ስንጫወት ተጫዋቾቻችን ላይ ዳቦ በመወርወር ረሃብተኛ ብለው ሰድበውናል፡፡ ባለጌ የባለጌ ልጅ ሁላ፡፡ ታዲያ ብድሩን
የማይመልስ ወንድ ልጅ አይወለድ አላሉም እንዴ አባቶቻችን? እናም ጨዋታው ሞቅ ባለበት ሰዓት ላይ ድንገት የሚያስተኛ
ከዳቦ ጋር የተጋገረ የእንቅልፍ መድሃኒት ለምን አንሰጣቸውም ?የሚል ከአገር ፍቅር ስሜት የመነጨ አስተያዬት
አለኝ፡፡ ለዚህ ያልሆኑ ሃኪሞቻችን ለምን ሊሆኑ ኖሯል ታዲያ? ለነገሩ ሃኪሙ ሁሉ አማሪካን ገብቷል ለካ!ዶክትሬት
ተምሮ መኪና መጠበቅ? ባይበላ ቢቀርሳ! ሆድ ምናባቱ አንድ ቀን ልረፍ ብሎ አያውቅ መቼም፡፡ እናም ሃኪም እስከሌለ
ድረስ እኔው ራሴው የእንቅልፍ መድሃኒት ማዘዜ ነው፤ ለናይጀሪያ ወንድሞቻችን፡፡ ፓራሲታሞል፤
ዲክሎፌናክ………..በብዛት ሲወሰዱ ለሽ ያሰኛሉ፡፡ ግን የናይጀሪያ ተጫዋቾች የሚያርፉበት ሆቴል ይህን ሃላፊነት
የመወጣት የዜግነት ግዴታ አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡ የግል አስተያዬት ነው፡፡ የመናገር ነፃነት ማለት እንደዚህ
ነውና በአነጋገሬ ከተቆጣችሁ ህግ እንደጣሳችሁ ይቆጠራል፡፡ 6.
በርበሬ፡፡ ናይጀሪያውያን በርበሬ እንደማይወዱ የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም እንግሊዞች በርበሬ አይወዱም፡፡ ታዲያ
ምግባቸው ላይ እንደምንም በርበሬ በማብዛት በማስነጠስ ሃይል እንዲያወጡ ማስገደድ ነው፡፡ ወይም በርበሬ የኢትዮጵያ
ባህላዊ ምግብ ነው እያሉ በጥብጦ መጋት፡፡..... 7.
ጉብኝት፡፡ የናይጀሪያ ተጫዋቾች ፋታ እንዲያጡ በጉብኝት ማዋከብ ጥሩ ነው፡፡ በራሳችን ወጭ አክሱም፤ ላሊበላ፤ ሃረር
እየወሰድን ቀልብ ብናሳጣቸው መልካም ነው፡፡ ለዚህ ያልሆነ ቱሪዝም ምናምን ለምን ሊሆን ነው ታዲያ? 8.
ቁማር፡፡ የናይጀሪያ ተጫዋቾች እና ቁማር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ በተለይ የቼልሲው ጆን ኦቢ
ሜኬል እናቱ ቁማር እየተጫወቱ የወለዱት ነው የሚመስለው፡፡ ጆሴ ሞሪኖ በፊት ቼልሲን ሲያሰለጥኑ ጨብራራ ጠጉሩን
በመቀስ ይቆርጡት ነበር፤ የቁማር ዛር የሰፈረብህ ፀጉርህ ላይ ነው በሚል፡፡ ያም ሆኖ ጆን ኦቢ ከቁማርተኝነቱ
አልተፈወሰም፡፡ ስለዚህ ይህን አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አንድ ያገራችን ሃብታም ኢትዮጵያ ላይ ‹ጎል
ታስቆጥራለህ› ብሎ ከጆን ኦቢ ሚኬል ጋር ቢወራረድ ናይጀሪያ ያልቅላት ነበር፡፡ 9.
የመከላከያና ፖሊስ ሰራዊት ቦምብ፤ መትረጊስ፤ ክላሽ፤ ከተቻለም ታንክ የታጠቁ ወታደሮችን ጨዋታ አስከባሪ አስመስሎ
በሜዳው ዙሪያ ማሰለፍ ያስፈልጋል፡፡ ኳስ ሊያቀብል ድንገት የሚወጣ የናይጀሪያ ተጫዋችን ‹ጎል ይገባና ወዮልህ›
እያሉ ማስፈራራት ነው፡፡ ታንክ የታጠቀ የመንግስት ሰራዊት ከአንድነት ሰልፈኞች ላይ ከሚበረታ ናይጀሪያ ተጫዋቾች
ላይ ቢበረታ ጉዳዩ እንደ ሃገር strategic importance ይኖረዋል፤ አቤት አቤት...እንግሊዝኛ ከቀደዱ
አይቀር እንደዚህ ነው፡፡ 10. ኢንተርቪው፡፡ የናይጀሪያ
ተጫዋቾችን በኢንተርቪው ማጣደፍ፡፡ ይሄ የጋዜጠኞቻቸን ስራ ነው፡፡ ተጫዋቾቹን በቃለ መጠይቅ ዕረፍት ማሳጣት ላይ
በርቱ በናታችሁ፤ በተለይ ጠዋት ጠዋት በስፖርት ወሬ ድርቅ የምታረጉን ጋዜጠኞች፡፡ ኦ ማይ ጎድ!….ለካንስ
ናይጀሪያውያኑ አማርኛ አይችሉም፡፡
በመጨረሻም ድል ለብሄራዊ ብድናችን ብዬ አልፎክርም! ሙያ በልብ ነው፡፡ ድል ለብሄራዊ ቡድናችን!!!
http://sodere.com/forum/topics/10-ways-to-defeat-nigeria?groupUrl=sodere-news-in-amharic
No comments:
Post a Comment