በአንድነትና በ33ቱ ፓርቲዎች በጋራ የተሠጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለሶስት ወራት የሚቆይ ህዝባዊ ንቅናቄ በስትራቴጅው መሰረት በመጀመር፤
በመላው አገሪቱ የሚገኙ አባላቶቹንና ደጋፊዎቹን በማንቀሳቀስ ሕዝቡን ያሳተፈ ትግል በመላ ኢትዮጵያ በማካሄድ
የተቃውሞ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ በብቃት ማከናወን ችሏል፡፡
የመጀመሪያ ዙር የሆነውን ሕዝባዊ ንቅናቄ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል ሰኔ 12 ቀን 2005
ዓ.ም ይፋ ስናደርግ በሰጠነው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳረጋገጥነው የዕቅዳችን ዋና አላማ ከጊዜ ወደ ጊዜ
አምባገነንነትን እያስፋፋ፤ ዴሞክራሲዊና ሰብዓዊ መብትን እየገፈፈ፣ ዜጎችን በፍርሃት ተዘፍቀው በምንደኛነት
እንዲኖሩ ያደረገውን ስርዓት ላይ ሕዝቡ ጫና ፈጥሮ መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ስልጣን የህዝብ እንዲሆን፣
ግለሰቦች በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ በዕምነታቸውና ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው የማይታሰሩባት ሃገር በመፍጠርና
ፍትሃዊነትን ማስፈን ነው ብለን ነበር፡፡
ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የሚሊዮኖችን ድምፅ በመሰብሰብ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚጋጨውንና ገዥው ፓርቲ
ተቀናቃኞችን ለማሸማቀቅ የሚጠቀምበትን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ እንዲሰረዝ ማድረግ፤ ሚሊዮኖች የፀረ ሽብር አዋጁን
በመቃወም የሚፈርሙበት ሰነድም በማዘጋጀት ድጋፍ ማሰባበሰብና በአጠቃላይም ህዝቡ ከሚሊዮኖች አንዱ የሚሆንበትንና
የሀገሬ ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው የሚል ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስም በአመራር ደረጃ፣ አባላትና
ደጋፊዎች ዋጋ ለመክፈል ካሳዩት ቁርጠኝነት በተጨማሪ የመታሰር፣ የንብረት ማጣትና የሞራል መጎዳት ዋጋ የተከፈለበት
ነው፡፡
አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ገዥ ሀይል ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑና ዴሚክራሲያዊ ባህሪ ስለሌለው በሰላማዊ
ህዝባዊ ንቅናቄዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠትና በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር በርን ከመክፈት
ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ ለጥያቄዎቹ አስተጋቢዎች የተለየ መልክ ለመፍጠር የሚያደርገው ሩጫ እንደተጠበቀ ሆኖ
በህገ መንግስቱ በግልጽ የተቀመጡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትን በአደባባይ
እየጨፈለቀና እነዚህ መብቶች ይከበሩ ዘንድ የሚጠይቁ አባላቶቻችንን ከህግ አግባብ ውጪ በገፍ እያሰረም ቢሆን
ህዝባችን ጋር ለመድረስና ተቃውሞ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለማሰማት ችለናል፡፡ ትግላችንንም የኢትዮጵያ ሕዝብ
ለበርካታ ዓመታት ዋጋ የከፈለለት የነፃነቱ ባለቤት እስከሚሆንና የህግ የበላይነት እስከሚረጋገጥ ከዴሞክራሲያዊ
ኃይሎች ጋር በመሆን የሚቀጥል እንደሆነ ለማረጋገጥ እንወዳለን
በሦስት ወር ህዝባዊ ንቅናቄያችን በጎንደር፣ በደሴ፣ በባህርዳር፣ በአርባምንጭ፣ በጅንካ፣ በአዳማ፣ በፍቼ
አባሎቻችን ታስረውና ተደብድበውም ቢሆን በተሳካ ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን በመቀሌና ባሌ ሮቤ በከፍተኛ
ጫናና ህገ-ወጥነት ሳይካሄዱ ቀርተዋል፡፡ በወላይታ ሶዶና አዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባዎች ተከናውነዋል፡፡ በአፋናና
በጫና ያላካሄድንባቸው ቦታዎች ላይ ሕዝቡን የሚያስተዳድሩትን የስርዓቱ ሰዎችና ስርዓቱን ያጋለጥንበት፣ ሕዝቡም
በቁጭት ከጎናችን እንዲቆም ያደረግንበትና ለቀጣይ የተደራጀ ትግል እንድንዘጋጅ ያነሳሳ ሁነት ነበር፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ ከላይ በጠቀስናቸው ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎቹን ለማሰናከል ሃላፊዎቹ የየአካባቢዎቹን
ሚሊሻዎች፣ የደንነት ሰዎች፣ ታጣቂዎችና ፖሊሶች በመጠቀም አባላቶቻችንን አስረዋል፣ አስፈራርተዋል፣ ደብድበዋል፣
አዋክበዋል፣ ሜጋ ፎኖች ተነጥቀዋል፡፡ በአዲስ አበባም ከአንድ የመንግስት አካል በማይጠበቅ መልኩም አመራሮቻችንን
አግተዋል፣ የቅስቀሳ መኪኖቻችንን እስከነ ሞንታርቦና ጀነሬተሮች ጠኋት አስሮ ማታ በመፍታት የተሳካ ቅስቀሳ
እንዳናደርግ ተደርጓል፡፡ በራሪ ወረቀቶችን እንዳናሰራጭና ፖስተሮችን እንዳንለጥፍ በፖሊስ ተከልክለናል፣ ታስረናል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጭ ደግሞ የተለጠፉ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ወረቀቶችን እንዲቀደዱ በማድረግና ህዝቡ በሰልፎቹ
እንዳይገኝ በካድሬዎች አማካኝነት የቤት ለቤት ቅስቀሳ ከማካሄዳቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር
በማድረግ ከየከተሞቹ አቅራቢያ ከሚገኙ ወረዳዎች ዜጎች ድምጻቸውን ለማሰማት እንዳይመጡ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡
በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ገዢው ፓርቲ 99.6 ፐርሰንት እንዳሸነፈ ቢነግረንም በተግባር ያረጋገጥነው
ከህዝብ የተነጠለ መሆኑንና ህዝቡን እየመራሁ ነው የሚለው ህዝብን በማሸማቀቅ እንደሆነ ነው፡፡
የመጀመሪው ዙር የሶስት ወር ሕዝባዊ ንቅናቄችን ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ለማጠናቀቅ የአዲስ
አበባ ከተማ መስተዳድር የከንቲባው ጽ/ቤት መስከረም 3 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ሠላማዊ ሠልፉን በመስከረም 19 ቀን
ማድረግ እንደምንችል የሚገልፅ የዕውቅና ደብባቤ ቢሰጠንም በእጅ አዙር ሠልፉን በመስቀል አደባባይ እንዳናደርግ
ከመከልከሉም በላይ ከሕግ ውጨ በመከላከያ በፀጥታ ተቋማት አካባቢ እንድንሰለፍ ለማስገደድ በመሞከርና ቅስቀሳ
እንዳናደርግ በመከልከል ነው፡፡ ፖሊስም ህገ መንግስቱንና ህዝቡን መጠበቅ ሲገባው ለመቀስቀስ፣ ፖስተር ለመለጠፍ፣
በራሪ ወረቀቶችን ለማሰራጨት ፈቃድ ያስፈልጋል ትዕዘዝ አልደረሰንም በሚል ተልካሻ ምክንያት ህገ-መንግስታዊ
መብታችንን በመጣስ የፓርቲያችንን ሊቀመንበር ጨምሮ በአጠቃላይ 101 (አንድ መቶ አንድ) አባላትን ከማክሰኞ እስከ
እሁድ አስሮብናል፡፡ ፖሊስ ለህግ የበላይነት መቆም ሲገባው በድብቅ ለተሰጠው ትዕዛዝ ተገዥ በመሆኑ ከማዘናችንም
በተጨማሪ ወደ ህግ በመሄድ የደረሰብንን ህገ-ወጥ የእስር መንገላታት፣ ካላግባብ ስለደረሰብን የንብረትና የገንዘብ
ጉዳት እንዲሁም የሞራል ካሳ የአዲስ አበባ ፖሊስን፣ የአዲስ አበባ መስተዳድርን በሕግ የምንጠይቅ መሆኑን
እንገልፃለን፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ!!!
የአንድነት ፓርቲና የ33ቱ ፓርቲዎች
መስከረም 23 ቀን 2006
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment