መሬት የማን ነው? አንድ
አገር ማለት በአባቶች፣ በአያቶችና በቅድማያቶች አጥንትና ደም ተገንብቶ የታጠረ መሬት ነው፤ የዶር. በድሉ ዋቅጅራን ዋይታ እየኮረኮረ የሚያወጣውና የሚያስተጋባው የፍቅር ስሜት ምንጭ ነው።
የተከሰከሰውና
ተፈረካክሶ አፈር የሆነው አጥንትና የወረደው የአያቶችና የቅድማያቶች ደም እየፈሰሰ መሬቱ ላይ በሚገኙ ወንዞች
ውስጥ ሁሉ ገብቶአል፤ እንዲያውም እነዚህ ወንዞች ወስደው በቀይ ባሕር፣ በሜዲቴራንያን ባሕርና በሕንድ ውቅያኖስ
ጨምረውታል፤
ይህ በአጥንትና በደም የታጠረ መሬት የማን ነው? በመሬቱ ላይ የባለቤትነት መብትን ለማስከበር ከውጭ ኃይሎች
ጋር የተጋደሉት ጥንታውያን ነፍጠኞች ቅድሚያን የሚያገኙ ይመስለኛል፤ እነዚህ ጥንታውያን ነፍጠኞች ብቻቸውን
አልነበሩም፤ ለምግብ የሚሆናቸውን ሁሉ የሚያመርቱ ገበሬዎች ነበሩ፤ ለልብስ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ የሚፈትሉና
የሚሸምኑ ባለሙያዎች ነበሩ፤ ልጆቻቸውን የሚንከባከቡና የሚያሳድጉም ለዘማቹ ምግብ የሚያቀብሉ እናቶች ነበሩ፤
በአጠቃላይ የሕዝቡን መንፈሳዊ ጤንነት ለመጠበቅ በቤተ ክርስቲያኖችና በመስጊዶች የሚጸልዩ ሰዎች ነበሩ፤ ሰላምን
የሚያስከብሩና የሚያስተዳድሩ ሰዎች ነበሩ፤ … አንድ ማኅበረሰብ ለተለያዩ የመደጋገፍ ሥራዎች የሚያስፈልጉት የሰዎች
ዓይነት ሁሉ ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ አጥሩን ለመገንባት አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ስለዚህ መሬቱ
የእነዚህ ሰዎች ሁሉ ነው።
ታሪካችንን በተግባር በኩል ስንመረምረው ግን መሬቱን እኩል እንዳልተካፈሉት እናያለን፤ ዛሬ ነፍጠኛ የሚባሉት
መሣሪያ የታጠቁት ሰዎች ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንደሚባለው ሰፋፊ መሬት የመያዝ ዝንባሌ ነበራቸው፤ ነገር ግን
ለማረስ የነበራቸው የሰው ጉልበትና የጥንድ በሬ ቁጥር የተወሰነ በመሆኑ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ብቻ
ለሚፈልገው ገበሬ በቂ መሬት ይደርሰው ነበር፤ ሰፋፊ መሬት የያዙት ጉልበት አጥሮአቸው ሲቸገሩና ትናንሽ ማሳ ያለው
ገበሬ ሰብሉ ቀንሶበት ሲቸገር በመጋዞ በማረስ ይረዳዱ ነበር (ገበሬዎችና ከብት አርቢዎችም ላሚቱ ስትወልድ ሴት
ከሆነች ለከብት አርቢው፣ የከብት አርቢው ላም ወንድ ስትወልድ ለገበሬው እየተሰጣጡ ይረዳዱ ነበር፤) ሰፋፊ መሬት
ያዙትም በጉልበት እጥረት ምክንያት፣ ትናንሽ ማሳ የያዙትም በትንሽነታቸው ምክንያት ከአስፈላጊው በላይ ስለማያመርቱ
ትርፍ ምርት ቢኖርም በጣም ትንሽ ነበር፤ ከላይ እሰከታች ያለው ሰው ሁሉ የሚተዳደረው በመሬት ስለነበረ በጣም ጥቂት
ለሆኑ ሰዎች (ቀጥቃጮች፣ አንጣሪዎች፣ ሸክላ ሠሪዎች፣ ሸማኔዎች … ወዘተ.) ለጉልበት ዋጋ ከሚከፈለውና
ለአስተዳዳሪዎች ከሚከፈለው ግብር በቀር አብዛኛው ምርት ለቤት ፍጆታ ነበር።
እዚህ ላይ በመሬት ጉዳይ ላይ ለመታረም ያስቸገሩ ሁለት ስሕተቶችን ሳላመለክት ለማለፍ አልፈልግም፤ ብዙ ጊዜ
እንዲታረሙ ብጥርም ፈረንጆች በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ በሙጫ አጣብቀውት ሊፋቅ አልቻለም፤ አንደኛ ገባር ማለት ባለመሬት ማለት ነው እንጂ ጪሰኛ ወይም መሬት የሌለው ሰው ማለት አይደለም፤ መሬት የሌለው ገባር አይባልም፤
መገበር ማለት የባለመሬት ግዳጅ ነው፤ ገባር ማለት ግብር ወይም ታክስ የሚከፍል ባለመሬት ነው፤ ጉዳዩን አጣርተው
ያልተገነዘቡት ፈረንጆች በራሳቸው አገር የመሬት ስሪት ዓይነት እንደተረጎሙት ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች አስተማሩ፤
እነዚያም ያንኑ እንደገደል ማሚቶ እያስተጋቡ ስሕተቱን አራቡት፤ ‹‹ፊውዳሊዝም›› የሚለው ቃልም ከዚህ ስሕተት ጋር
የተያያዘ ነው፤ አውሮፓ የነበረው ፊውዳሊዝም የሚባል ነገር በኢትዮጵያ ኖሮም አያውቅ።
ሁለተኛው ከመሬት ጋር የተያያዘ ቃል ጉልት ነው፤ ጉልት በመሬት ላይ ያለ መብት ሳይሆን በመሬቱ ከፊል ምርት
ላይ የተሰጠ መብት ነው፤ ዱሮ ገንዘብ አልነበረምና በጥሬ ገንዘብ የሚከፈል ዋጋ አልነበረም፤ ለወታደሮችም ቢሆን
በደመወዝ ፈንታ የሚሰጣቸው ገባሮች ነበሩ፤ ዛሬ ባለመሬቶች በጥሬ ገንዘብ ለመንግሥት ይከፍሉና ገንዘቡ ተሰብስቦ
ለወታደሮችም ሆነ ለሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ይከፈላል፤ ጥንት ግን ግብር ከፋዩን (ማለት ገባሩን) በቀጥታ
ከመንግሥት አገልጋዩ ጋር ያገኛኙትና በእህል እንዲቀልበውና በጉልበት እንዲረዳው ይደረግ ነበር፤ ይህ ሥርዓት
አልተበላሸም ለማለት አይቻልም፤ ሆኖም የመንግሥት አገልጋዮች በገባሩ መሬት ላይ ምንም መብት አልነበራቸውም፤ እንዲሁም ጉልት የተሰጣቸው
የመንግሥት ባለውለታ የሆኑ መሳፍንትና መኳንንት፣ ሴት ወይዘሮዎችም በመሬቱ ላይ ሳይሆን ለመሬቱ በሚከፈለው ግብር
ላይ ነበር፤ የጉልት ሥርዓት እያሉ የሚጽፉ ወይም የሚናገሩ ሰዎች አለማወቃቸውን እያራቡ ነው።
የኢትዮጵያን የመሬት ስሪት ውስብስብነት በትንሹም ቢሆን ለመረዳት ሌላ ቢቀር የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴን
ዝክረ ነገር ይመልከቱት፤ የጥንቱን እንተወውና በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያ ከሶማልያ ጋር ቢያንስ ሁለት ጊዜ
ተዋግታለች፤ ከኤርትራ ጋር የተደረገውን ጦርነት ደግሞ ብዙ ወጣቶችም የሚያውቁት ነው፤ እነዚህ ጦርነቶች የተደረጉት
በመሬት ምክንያት ነበር፤ ምናልባትም ከሶማልያ ጋር ሁለት ጊዜ ከተደረጉት ጦርነቶች ይልቅ ከኤርትራ ጋር በተደረገው
ጦርነት የተገደሉት የኢትዮጵያውያን ቁጥር በጣም የላቀ ሳይሆን አይቀርም፤ ከዚያም በላይ ከኤርትራ ጋር ጦርነት
የተደረገበት ምክንያት ከሶማልያ ጋር ከተደረጉት ጦርነቶች ምክንያት በጣም ያነሰ ነው፤ በአጠቃላይ አገሪቱን በሙሉ
ለመውረር የመጣውንም ሆነ አንዲት ትንሽ መንደር የወረረውን እኩል በመዋጋት ሀብትንና የሰው ሕይወትን ማቃጠል የማሰብ
ችግር ውጤት ነው፤ ለጊዜው ዋናው ነጥባችን በነዚህ ጦርነቶች የሞቱት ሰዎች መሬቱ የኛ ነው፤ አንሰጥም፤ በማለት ነው፤ በሌላ አነጋገር የመሬቱ ባለቤት፣ የመሬቱ ባለመብት እኛ በመሆናችን ያለፈቃዳችን ሌላ አይወስደውም በማለት ነው።
ባለቤትና ባለመብት ሆኖ የሞተውና በየሜዳው ላይ ሬሳው ወድቆ ሳይቀበር ለጅብና ለአሞራ ምግብ የሆነው ኢትዮጵያዊ
መሬትን እንኳን ለኑሮ ለመቃብርም አላገኘም፤ በሆነው ባልሆነው መጫወቻ የሆነው መስዋእት የሚባል ቃል ትክክለኛ
ትርጉሙ ይህ ነው፤ እንግዲህ ይህ ሰው መስዋእት የሆነው ለምን ዓላማ? ለማን ዓላማ ነው? የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ
ነው፤ ማንም ሰው ለመሞት በቆረጠበት ጊዜ ‹‹የምሞተው ለምን ዓላማ ነው?›› ብሎ መጠየቅ አለበት።
የምርትና የሕዝብ እድገት እሽቅድምድም ፤ ሁለት
እአአ በ1798 (ከሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት በፊት) መምሬ ቶማስ ሮበርት ማልቱስ የሚባል የ32 ዓመት
የብሪታንያ ቄስ የዘመኑን የነገረ ንዋይ አስተሳሰብ የለወጠ አዲስ ሀሳብን የያዘ መጽሐፍ አሳተመ፤ ሀሳቡ በጣም
ግልጽ ነበረ፤ የሰው ልጆች ቁጥር እድገት መጠኑ እያጠፈ የሚሄድ ነው፤ የሕዝብ ቁጥር 1፣ 2፣ 4፣ 8፣ 16፣
32፣ 64፣ 128፣ እያለ የሚጨምር ነው፤ ከእርሻ የሚገኘው ምርት ደግሞ የእድገቱ መጠን አያጥፍም፤ 1፣ 2፣ 3፣
4፣ 5፣ 6፣ 7፣ 8፣ 9፣ 10፣ እያለ የሚሄድ ነው፤ የመምሬ ማልቱስን ሀሳብ በሌላ መንገድ ካየነው የበላተኞች
ቁጥር እያጠፈ ሲያድግ የምግቡ አቅርቦት የሚያድገው ግን በጣም በዝግተኛ ፍጥነት ነው፤ የሚል ነው፤ እንግዲህ
የሕዝብ ቁጥርና የምርት አቅርቦት እኩል መጓዝ ሲገባቸው የሕዝቡ ቁጥር እየቀደመ ስለሚገኝ፣ መምሬ ማልቱስ የደረሰበት
መደምደሚያ የሕዝቡን ቁጥር ለመቀነስ በሰው ልጆች መሀከል በሽታ፣ ችጋርና ጦርነት የማይቀሩ ይሆናሉ፤ ችጋር፣
ጦርነትና ሌሎችም አደጋዎች በሕዝቦች ላይ እየደረሱ የሕዝብ ቁጥርና የምርት እድገት በሚያደርጉት መሽቀዳደም መሀከል
ሚዛንን ይጠብቃሉ።
መምሬ ማልቱስ በነበረበት ዘመን ላይ ሆኖ ከሃምሳና መቶ ዓመታት በኋላ እውቀትና (ሳይንስ) የእውቀት ጥበብ
የሚያስከትሉትን መሠረታዊ የአስተሳሰብ፣ የአሠራርና የኑሮ ለውጥ ለመገንዘብ አልቻለም፤ እንዴት ብሎ? በመምሬ ማልቱስ
ዘመን በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘው ምርት አምስት ኩንታል ብቻ ቢሆን በኋላ ግን በአንድ ሄክታር ላይ
በእውቀትና በእውቀት ጥበብ ኃይል ምርቱን ከእጥፍም በላይ ማምረት የሚቻልበት ዘመን መጣ፤ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣
የተለያዩ የእርሻ ዘዴዎች የእርሻውን ሥራ ቀልጣፋና ምርታማ አደረጉት፤ በዚህም ምክንያት የመምሬ ማልቱስን ሀሳብ ብዙ
ሰዎች ይነቅፉት ጀመር፤ ሆኖም የመምሬ ማልቱስን ሀሳብ ዛሬም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ጊዜ አልሻረውም፡፡
ከመሠረት ለመጀመር — አንድ አገር መሬት አለው፤ ሕዝብ አለው፤ መሬትም ሆነ ሕዝብ በጥሬአቸው ከቆሙ የመምሬ
ማልቱስ ትንተና መደምደሚያ መሬቱ ከሚችለው በላይ የሆነውን ሕዝብ ችጋር፣ በሽታና ጦርነት ያነሣዋል፤ መሬትና ሕዝብ
ብቻ አገርን አያቆሙም፤ በሕዝብ መሀከል ያለውን ግንኙነት፣ እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ጋር ያለውን አብሮ የመኖር
ትስስር ሕግና ሥርዓት እንዲኖረው ያስፈልጋል፤ የመሬትም ሀብት አጠቃቀም በእኩልነትና በፍትሐዊነት ዘዴ ለመደልደል
ሕግና ሥርዓት ያስፈልጋል፤ እንግዲህ ሕዝቡ ኑሮውን በሕግና በሥርዓት ለመምራት አንድ መንግሥት የሚባል እንደእድር
ያለ ድርጅትን ይፈጥራል፤ እያንዳንዱ ሰው በግሉ የኑሮ ጣጣ ተወጥሮ በሚራወጥበት ጊዜ መንግሥት የሚባለው ድርጅት
ለጠቅላላው ማኅበረሰብ የሚበጀውን ይሠራል።
በእያንዳንዱ ሰው የኑሮ ግዴታ መሬቱ ያለማቋረጥ በጥቅም ላይ እየዋለ በግጦሽና በእርሻ፣ በሌሎችም ምክንያቶች
እየተጎዳ ይሄዳል፤ በዚህም የተነሣ መሬቱ የሚሰጠው ጥቅም በያመቱ ይቀንሳል፤ የመሬቱ መደህየት ከሕዝብ መደህየት
ቀድሞ ይመጣል ማለት ነው፤ እንግዲህ መንግሥቶች የሚቋቋሙት እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳይፈጠር፣ ከተፈጠረም ብዙ ጉዳት
እንዳያደርስ አስፈላጊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ነው፤ በኢትዮጵያ ስለኢትዮጵያ የሚፈበረከው የአሐዝ መረጃ
ወይም ስታቲስቲክስ አስተማማኝ ነው ባይባልም አማራጭ ባለመኖሩ ልንጠቀምበት እንገደዳለን፤ ለምሳሌ በ2004 ዓ.ም.
የስታቲስቲክስ ጽ/ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት የታረሰው መሬት 13 690 119 ሄክታር ነበር ይባላል፤ የስታቲስቲክስ
መሥሪያ ቤት ገበሬዎች ሳይሆን ባለይዞታ የሚላቸው 14 747 439 ይሆናሉ፤ ይህንን ቁጥር በአምስት ስናባዛው
(በአንድ የገጠር ቤተሰብ በአማካይ አባሎች) 73 737 195 ይሆናል፤ ይህንን ቁጥር ከ2007 የሕዝብ ቆጠራ ውጤት
ጋር ማስተያየቱ ያስተምራል፤ ከዚያም በላይ አንዳንዶቹ ቁጥሮች በሌላ ቦታ አይደገሙም፤ ወይም መልካቸውን ለውጠው
ይቀርባሉ።
ለጊዜው ግን ለያዝነው ርእስ የሚከተሉትን አሐዞች እንመልከት፤ በመጀመሪያው ሰንጠረጅ ባለይዞታ የተባሉት
ገበሬዎችና የታረሰው መሬት (በሄክታር) በሦስት ዓመት ውስጥ ያሳዩትን ለውጥ ለማሳየት ይሞክራል፤ ሠንጠረጅ ሁለት
ደግሞ የእርሻ ምርት (እህል፣ ጥራጥሬና የቅባት ዘር) ከገበሬው ቁጥር ጋር ለማነጻጸር ይሞክራል፤ ኢትዮጵያ የተአምር
አገር መሆንዋን ተንተርሶ የስታቲስቲክስ ጽ/ቤት የእርሻ መሬቱንም በ2004 ዓ.ም. ትንሽ አሳድጎታል፤ አይቻልም
ማለት አይደለም፤ በመስኖና በእርከን የእርሻውን መሬት መጨመር ይቻላል።
ሠንጠረጅ አንድ
የታረሰ መሬትና (በሄክታር) የገበሬዎች ቁጥር 2002-2004 ዓ.ም
ዓ.ም. | ባለይዞታ | እድገት ከመቶ | መሬት (ሄክታር) | ካለፈው ዓመት እድገትከመቶ | አማካይ ድርሻ መሬት ለባለይዞታ(ሄክ) | |
2002
|
13439174
|
100.0 |
12953636
|
100.0 |
0.96
|
|
2003
|
14789071
|
110.0
|
13358883
|
103.13 |
0.90
|
|
2004
|
14747439
|
109.7
|
13690119
|
105.69 |
0.93
|
ምንጭ የስታቲስቲክስ ጽ/ቤት ድረ-ገጽ
ዋናው ነጥብ ግን የስታቲስቲክስ ጽ/ቤት የፈለገውን ያሀል ቢጠማዘዝም እውነቱን እምብዛም ሊለውጠው አልቻለም፤
የቁጥር ነገር ወዲያ ቢሉት አራት፣ ወዲህ ቢሉት አራት ሆነና በአማካይ የአንድ ገበሬ እርሻ አንድ ሄክታር
እንደማይሞላ መሸሸግ አልተቻለም፤ በእርሻ መሬቱ ላይ ያለው ጭነት በጣም ከፍተኛ ነው፤ እውነተኛውን የሕዝብ ቁጥር
ብናውቅ ደግሞ ጭነቱ ምን ያህል የበለጠ እንደሆነ እንረዳ ነበር፤ የዓለም ባንክና የአሜሪካው ዓለም-አቀፍ የስለላ
ድርጅት (ሲአይኤ) የኢትዮጵያን ሕዝብ ቀጥር በአሁኑ ጊዜ ከዘጠና ሚልዮን በላይ ያደርሱታል፤ በአገር ውስጥ
የሚነገረው ቁጥር ግን በሰባና በሰማንያ መሀከል ነው፤ የዛሬ ሠላሳ አምስትና አርባ ዓመት ግድም በደቡብ (በተለይ
በከምባታና ሀድያ፣ በወላይታና በሲዳሞ፣ በደራሳ) የሕዝብ ቁጥር የሚፈነዳ እንደሆነ ተናግሬ ነበር፤ በትግራይና
በወሎም፣ በሰሜን ሸዋም በመሬቱ ላይ ያለው ጭነት ከባድ ነው።
ሠንጠረጅ ሁለት
የእርሻ ምርትና (አህል፣ጥራጥሬና የቅባት) የገበሬዎች ድርሻ
ዓ.ም. | ምርት ኩንታል | ካለፈው ዓመት እድገት ከመቶ | የባለይዞታ ቁጥር | የባለይዞታ/የዓመት ድርሻ ኩንታል | የአንድ ሰው የወር ድርሻ ኪሎ |
2002
|
180758897
|
100.0
|
13439174
|
13.45
|
22.25
|
2003
|
203485288
|
112.57
|
14789071
|
13.76
|
22.92
|
2004
|
218569429
|
120.92
|
14747439
|
14.82
|
24.67
|
ባለይዞታ ምናልባት በአማካይ አምስት ሰዎችን ያካትታል፤ ነፍስወከፍ እያንዳንዱን ሰው
ይመለከታል።
በእነዚህ ሁለት ሠንጠረጆች ላይ በግርድፍ (መረጃው ነው ግርድፍ!) የሚታየውን እውነት መሸሽግ አይቻልም፤ በወር
25 ኪሎ እህል ከችጋር አለመውጣትን ያሳያል፤ መሬት ተትረፍርፎ ሠራተኛ ሕዝብ የጠፋበት አገር አንዳልሆነም
ይታያል፤ ታዲያ ለህንድና ለቻይና፣ ለሌሎችም መሬት በችሮታም ሆነ በሽያጭ የምንሸጥበት ምክንያት ዕብሪት ከወለደው
እብደት ሌላ ምን ሊኖር ይችላል?
zehabesha
No comments:
Post a Comment