ዛሬም (እንደወትሮው) አንድ ቀሽም አስተያየት ልስጥ!
በህወሓት ዉስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ እያየን ነው። ስብሃት ነጋ የሚዘውረው ቡድን አንሰራርቶ የፖለቲካ
የበላይነቱ የሚቆጣጠርበት ዕድል ሊኖር ይችላል (መላምት ነው፣ ከውዲሁ በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም)።
የስብሃት ነጋ ኔትዎርክ ህወሓት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ የትግራይ ህዝብ ጠፍሮ ሲገዛና ሲያሰቃይ የነበረ ነው።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በሆነ ዉስጣዊ አለመግባብት ምክንያት የስብሃት ኔትዎርክ እየተመናመነ መጣ። አቶ አባይ
ወልዱ የትግራይ ክልል ፕረዚደንት ከሆነ በኋላ ኔትዎርኩ በሌሎች ተተካ። ይባስ ብሎ ደግሞ ከመለስ ዜናዊ ህልፈት
በኋላ አቶ አባይ ወልዱ የህወሓት ሊቀመንበር ሆነ። ከዚህ ግዜ ወዲህ ስለ አባይ ወልዱ ባህሪ መጥፎነትና የፖለቲካ
ብቃት ማነስ በሰፊው ይወራ ጀመር።
እኔ የሌሎች የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ያህል የአባይ ወልዱ የተሟላ መረጃ የለኝም። እንደሌሎቹም በሓሳብ
ክርክር ፊት ለፊት ተገናኝተን አናውቅም። (መለስ፣ ስብሃት፣ ስዩም፣ አባይ ጸሃየ፣ አርከበ፣ ቴድሮስ ሓጎስ፣ ፀጋይ
በርሀ … ብዙዎቹ በደንብ አቃቸዋለሁ)። አባይ ወልዱ ግን በደንብ አላውቀውም። አንድ ግዜ ብቻ በሆነ አጋጣሚ
ተገናኝተን ብዙ አውርተን ነበር (አብርሃ ደስታ መሆኔን ሳያውቅ ማለት ነው)። ያኔ እንዳየሁት ትህተኛ (humble)
ይመስላል (በአንድ ግዜ የሰው ባህሪ ለመገምገም ቢከብድም)።
ስለዚህ ስለ የአባይ ወልዱ ፖለቲካዊ ብቃትና የግል ባህሪ ጥሩነት ወይ መጥፎነት መመስከር አልችልም። ቁልፍ
የሚባል የህወሓት ስልጣን ለባለቤቱ መስጠቱ ግን እንደማንኛውም ሰው ገርሞኛል። ይህ እንዳለ ሁኖ ስለ አባይ ወልዱ
አንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ። አባይ በህወሓት ካድሬዎች አይወደድም። አባይ የአምባገነንነት ባህሪ እንዳለውና የፖለቲካ
ብቃት እንደሚያንሰው ለህዝቡ እንዲደርስ ተደርጓል። ማነው ስለ አባይ መጥፎነት የሚያወራ ቢባል መልሱ የህወሓት
ካድሬዎች መሆናቸው ግልፅ ነው።
ለምን? አባይ የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ከመሆኑ በፊት ቁልፍ የህወሓት ኔትዎርክ ተቆጣጥረው የነበሩ
ካድሬዎች የስብሃት ነጋ ታማኞችና ዘመዶች ነበሩ። ትግራይ ሙሉ ተቆጣጥረውት ነበር። አባይ ወልዱ የነሱ ዘመድ
አይደለም። አባይ ስልጣኑ ከጨበጠ በኋላ የስብሃት ታማኝ ኔትዎርከኞች ስጋት አደረባቸው። ስጋታቸውም የህወሓት
ኔትዎርከኞች ቀስ በቀስ ይቀየራሉ፤ ቁልፍ የሆኑ የስልጣን እርከኞችም ከስብሃት ታማኞች ወደ አክሱም ተወላጆች
ይሸጋገራሉ የሚል ነበር።
የስብሃት ህወሓቶች አንድ ሰው ከስልጣን ለማውረድ ወይም ስልጣን ለመስጠት ሲፈልጉ ስለሰውየው የፈጠራ ወሬ
(የሚያዋርድ ወይ የሚያስወድስ) ለህዝብ ይነዛሉ። በቂ ኔትዎርክ ስላላቸው እነሱ የፈለጉትን ወሬ ከህዝብ ለማድረስ
አይቸገሩም። እነሱ የፈልጉትን ሰው ወደ ስልጣን ለማውጣት ስለሰውየው ጥሩ ነገር ያወራሉ፤ ካልፈለጉት ደግሞ ስሙን
ያጠፉታል። በዚህ መንገድ ስልጣን ወደ አክሱም ተወላጆች እንዳይሸጋገር በመስጋት የአባይን ስም ከማጥፋት አልቦዘኑም።
አባይ ብቃት አለው ወይ የለውም ለሚለው ሰው ትክክለኛ ግንዛቤ የለውም።
በትክክልም አባይ የቀድሞው የኔትዎርከኞቹ ማንነት በተቻለ መጠን ቀይሮታል። እንደፈሩት አልቀረም። ነገር ግን
የአባይ ኔትዎርክ እግር ሳይተክል ፈተና ገጥሞታል። የስብሃት ኔትዎርክ እንደገና የሚያንሰራራበት ዕድል እያገኘ
ይመስላል። ለትግራይ ህዝብ (በኔ እምነት) ከስብሃት ኔትዎርክ የአባይ ኔትዎርክ በብዙ እጥፍ ይሻላል። ምክንያቱም
የአባይ ኔትዎርክ ከሞላ ጎደል ለዘብተኛ ነው። የስብሃት ግን መርዘኛ ነው። ትግራይ በተወሰኑ የቤተሰብ አባላት ስር
የወደቀችበት ምክንያት በስብሃት ኔትዎርክ ነው። (አሁን አባይም ተመሳሳይ ነገር የጀመረ ይመስላል)።
ምናልባት ስብሃት ከተሳካለትና ትግራይን መልሶ ከተቆጣጠረ አደገኛ ስለሚሆን የሽግግሩ ግዜና አጋጣሚ ተጠቅሞ
ዓረና ፓርቲ የህወሓት አመራር አባላት በማሳመን በህወሓት ዉስጥ ህቡእ የዓረና አባላት የሚፈሩበት መንገድ መመቻቸት
አለበት። ህወሓትን ማሸነፍ የምንችለው ወደ ህወሓት ዘልቆ በመግባት ነው። ህወሓት ዉስጡ ስለበሰበሰ ፓርቲው ዉስጥ
ገብቶ ኔትዎርኩን መቆጣጠር ያን ያህል የሚከብድ አይሆንም።
It is so!!!
ለተቃዋሚዎች
ህወሓቶች በዉስጣዊ ቀውስ እየታመሱ ነው። ከታሪካቸው እንደምንረዳው ዉስጣቸው ሲበሰብስና የመውደቅ አደጋ
ሲደቀንባቸው የዉጭ ‘ጠላት’ ያፈላልጋሉ። ጠላት ከዉጭ መጣ ሲባል የርስበርስ ንትርኩ ለግዜው ይተውታል፤ ምክንያቱም
ሁላቸውም የሰሩት የጋራ ጥፋት አለ። ለውድቀት ከተዳረጉ ጉዳቸው ይወጣል። ስለዚ የውጭ ጠላት ሲመጣ ለጋራ ህልውናቸው
ሲሉ ይተባበራሉ። ስለዚህ ህወሓቶች የዉጭ ጠላት ይፈልጋሉ፤ ከሌለም ራሳቸው ይፈጥራሉ። በነሱ እምነት የዉጭ ጠላቱ
ህልዉናቸው የሚፈታተን ግን መሆን የለበትም።
በኢህአዴግ ደረጃ ጠላታቸው ለይተዋል። አንድነቶች፣ ሰመያዊዎችና ሙስሊም ጠያቂዎች ለኢህአዴግ ህልውና አስጊ
የሆኑ የውጭ ‘ጠላቶች’ ናቸው። ግን በኢህአዴግ የሚፈለጉ ዓይነት ጠላቶች አይደሉም፤ ምክንያቱም ለፓርቲው በትክክል
አስጊ በመሆናቸው ለኢህአዴግ ዉስጣዊ ትብብር የሚረዱ ሳይሆን ክፍፍሉ የሚያባብሱ ናቸው።
በህወሓት ደረጃም ጠላት ተለይተዋል። የህወሓት ጠላት ተደርጎ የተወሰደው ዓረና ፓርቲ ነው። ዓረና እንደ ዋነኛ
አስጊ ጠላት ተይዞ እርምጃ እንዲወሰድበት ተመካክረውበታል። እንደዉጤቱም የዓረና ፓርቲ አባላት ማሰርና ማንገላታት
ጀምረዋል። ለምሳሌ በተምቤን ቀሲስ ሃይላይ አረጋይ፣ በራያ ደግሞ ወጣት አድሃና ንጉሰ ያለምንም ጥፋት በህወሓት
ታስረዋል። በመቐለም ይርጋ ገብሩ የተባለ የኮሌጅ መምህር ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ከስራው እንዲባረር ተደርጓል።
ስለዚህ ህወሓቶች/ኢህአዴጎች ዉስጣዊ ችግራቸው ለመሸፈን በተቃዋሚዎች ላይ አላስፈላጊ እርምጃዎች ሊወስዱ ስለሚችሉ ከወዲሁ መጠንቀቅ ጥሩ ነው።
የህወሓት የሃይል ሚዛን
የህወሓት ሁለቱ ቡድኖች (የመቐለና አዲስ አበባ) ዉዝግብ እንደቀጠለ ነው። በፖለቲካ ዘርፍ የአዲስ አበባው
ቡድን ጥሩ እየተጫወተ ነው። አብዛኞቹ የመቐለ ቡድን አቀንቃኞች (ግን አዲስ አበባ አከባቢ የሚኖሩ) በሙስና ሰበብ
እየታሰሩ (ሌሎችም እየደነገጡ) ከጨዋታ ውጭ እየሆኑ ሲሆን ለአዲስ አበባው ቡድን ደግሞ ዓቅም እያስገኙ ነው።
ግን የአዲስ አበባ ቡድን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ ይችላል የሚል ግምት የለኝም። ምክንያቱም የመቐለው ቡድን የትግራይ
ክልል መንግስታዊ መዋቅር ለግል ፍላጎቱ በማዋል አብዛኞቹ የህወሓት አባላት በቁጥጥር ስር ለማድረግ እየመከረ ነው።
በትግራይ ክልል ቢሮ የሚሰራ የህወሓት አባል ለአዲስ አበባው ቡድን ለመደገፍ ይቸገራል። ምክንያቱም ለአዲስ አበባው
ቡድን የደገፈ የትግራይ ባለስልጣን ከሓላፊነቱ ይባረራል። ስለዚህ አይሸናነፉም።
ይህ በንዲህ እንዳለ የህወሓት ሊቀመንብርና የትግራይ ክልል ፕረዚደንት የሆኑ አቶ አባይ ወልዱ ባለቤታቸው
የሆኑት (ወይ የነበሩ) ወይዘሮ ትርፉ ኪዳነማርያም የህወሓት ፅሕፈትቤት ሓላፊና የፖለቲካ አማካሪ አድርገው
ሽሟቸዋል። ይህ ስልጣን ከፓርቲው ሊቀመንበርነት ቀጥሎ በህወሓት ቁልፍ የሚባል ስልጣን ሲሆን የአቶ ቴድሮስ ሓጎስ
የነበረ ነው።
እንዲህ ነው መተካካት። ባልና ሚስት ሁለቱም ቁልፍ ስልጣኖች ሲቆጣጠሩ። ‘ራእይን ማስቀጠል’ ካልቀረ እንዲህ ነው፤ የራስ ሚስት በቁልፍ ቦታ መሾም።
ህወሓት የፖለቲካ አማካሪዋን ይዛ ወደፊት። ጥሩ ነው፤ ትርፉ
ኪዳነማርያም የህወሓት የፖለቲካ አማካሪ የምትሆንበት ዘመን። ህወሓቶች እንኳን ደስ አላቹ።
zehabesha
No comments:
Post a Comment