ወ/ት ቃልኪዳን ብርሃኑ፣ በኢትዮጵያ የሳይኮሎጂስቶች ማኅበር የፕሮግራምና አስተዳደር ረዳት
ወ/ት ቃልኪዳን ብርሃኑ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ ሠርታለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሳይኮሎጂስቶች ማኅበር (ኢፒኤ)
የፕሮግራምና አስተዳደር ረዳት (ፕሮግራም ኤንድ አድሚን አሲስታንት) በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ የማኅበሩን
አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከምሕረት አስቻለው ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ኢፒኤ ምንን ዓላማ አድርጐ ተቋቋመ?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- ማኅበሩ የተቋቋመው በ1984 ዓ.ም.
በጥቂት የሳይኮሎጂ ባለሙያዎች ሲሆን በወቅቱ ስለሙያው የተሳሳተ አመለካከት ስለነበር ያን አመለካከት በሒደት
መለወጥን ዓላማ በማድረግ ነበር፡፡ በነበረው የግንዛቤ ችግር ባለሙያዎቹ በመንግሥት ይመደቡ የነበረበት የሥራ
ዓይነትም ከሙያቸው ጋር በቀጥታ የሚገናኝ አልነበረም፡፡ ስለሙያው የነበረውን የግንዛቤ ችግር መፍታት ብቻም ሳይሆን
ሙያውን ማስተዋወቅ፣ ሙያው የማኅበረሰቡን ችግር በመፍታት ምን ዓይነት ፋይዳ እንደሚኖረው ማሳየትም ማኅበሩ
የተቋቋመላቸው ሌሎች ዓላማዎች ነበሩ፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ረዥም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ አሁን ምን ያህል አባላት አሉት?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- 650 የሚሆኑ አባላት ሲኖሩት አብዛኞቹ
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሳይኮሎጂ የሠሩ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሳይኮሎጂ የሠሩ ናቸው፡፡ የሥነ
ልቦና ባለሙያዎች ሆነው ሙሉ አባል የሆኑ፣ ሙያቸው ከሳይኮሎጂ ጋር የሚገናኝና ተባባሪ አባል የሆኑ፣ እንዲሁም
ሳይኮሎጂ በማጥናት ላይ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆኑ አባሎችም አሉን፡፡ ኢፒኤ በዋነኝነት ትኩረት አድርጐ የሚሠራው
የአባላት አቅምን መገንባት ላይ ነው፡፡ ሌላው ትኩረቱ ደግሞ ኅብረተሰቡን ሊያግዙ የሚችሉ ጥናቶች ላይ በተለይም
ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ አንድምታቸው ከፍተኛ የሆነ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥናቶች ላይ መሳተፍ ነው፡፡ እስካሁን ሰባት
የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ችለናል፡፡ በቅርብ ጊዜ ያዘጋጀነው የውይይት መድረክ የማኅበረሰቡ ራስ ምታት የሆነው
የኢትዮጵያውያት የዓረብ አገር ስደት ላይ የሚያተኩር ነበር፡፡ ውይይቱን ያዘጋጀነው ከዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት
አይኦኤም ጋር በመተባበር ነበር፡፡ የሕፃናት መብትና ወላጅ አልባ ሕፃናትን የሚመለከቱ የውይይት መድረኮችንም
አዘጋጅተን ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ግብረ ሰዶማዊነት ማኅበረሰቡን ጭንቅ ውስጥ እየከተተ ያለ ጉዳይ በመሆኑ፣
የተደፈሩ ሕፃናት ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ ስለሚገቡ እዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት
እንፈልጋለን፡፡ በዚህ ረገድ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ድጋፍ መስጠትም ስለምንፈልግ ከሌሎች ተቋማት ጋርም
እየተነጋገርን ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ጥቃት የደረሰባቸው ሕፃናት ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል ይቸገራሉ፡፡ ይልቁንም
በደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት ራሳቸውን ማግለልን ይመርጣሉ፡፡ ስለዚህ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለእነዚህ
ሕፃናት ድጋፍ መስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ድርጅቶችን እያነጋገርን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ ረዥም ጊዜ የማስቆጠሩን ያህል ተራምዷል ብለሽ ታምኛለሽ?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- ሁላችንም አናምንም፡፡ የዕድሜውን ያህል
ብዙ መሥራት አልቻለም፡፡ አሁን ግን አብረን ልንሠራ የምንችላቸውን ተቋማት በመፈለግ በጋራ የተሻለ ሥራ ለመሥራት
እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በእርግጥ ለማኅበሩ የዕድሜውን ያህል አለመራመድ በተወሰነ መልኩ ከሥነ ልቦና ጋር በተያያዘ
የሚሠሩ ሥራዎች ላይ ተቋማት ገንዘብ ማውጣት (ፈንድ ማድረግ) አለመፈለግ የራሱ ድርሻ አለው፡፡ በብዙ ማኅበራት
የሚታየው በአባላት በኩል ማኅበሩን በሚመለከት የባለቤትነት ስሜት አለመኖር የእኛም ሌላው ችግር ነው፡፡ ምንም እንኳ
ብዙ አባላት ቢኖሩም በአባላቱ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት ከሌለ የአባላት ብዛት በራሱ የሚያመጣው ውጤት የለም፡፡
ይልቁንም ማኅበሩን እንዲህ አደረጉት እንደዚያ የሚለው ሌላውን ተጠያቂ የማድረግ ነገር ሊያይል ይችላል፡፡ ሌላው
ምንም እንኳ የአባላት ቁጥር 650 ቢባልም ተሳትፎ የሚያደርገው 167 ያህሉ ብቻ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የማኅበሩ መዋቅር ምን ይመስላል?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- ቦርድና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አለ፡፡ የቦርድ አባላቱ በየጊዜው ይገናኛሉ፡፡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውም በተቀመጠው መሠረት በየጊዜው ይነጋገራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የቅርብ ጊዜ ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- ግብረሰዶማዊነት ላይ በተለይም ሕፃናት
ላይ ትኩረት አድርገን የመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ እዚህ ላይ ለመሥራት ከኔዘርላንድስ ኤምባሲ ጋር ተነጋግረን
ለኤምባሲው ሁለት ፕሮፖዛሎችን አስገብተናል፡፡ የመጀመሪያው ሴክሽዋል ኦረንቴሽንን (ጾታዊ ገጽታ) የሚመለከት ሲሆን፣
ሌላው ወንዶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ላይ ያተኩራል፡፡ ኤምባሲው ውስጥ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በሌላ እየተተኩ
ያሉበት የሽግግር ጊዜ በመሆኑ እንጂ በመጪው ሁለት ወር ውስጥ ነገሮች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ የምንገባበት እንደሚሆን
ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የረዥም ጊዜ ዕቅዳችን ደግሞ በአካል ጉዳተኞች ላይ መሥራት ነው፡፡ አጫጭር ሥልጠናዎችን
መስጠት፣ ነፃ የምክር አገልግሎት መስጠት እናስባለን፡፡ በእርግጥ አሁንም ነፃ የምክር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡
የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን በሚያቀርቧቸው ሥነ ልቦና ላይ የሚያተኩሩ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍ ሙያዊ ግዴታችንን
እንወጣለን፡፡ የራሳችን የአየር ሰዓት ቢኖረን ደግሞ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡ በተደጋጋሚ ፕሮፖዛል አዘጋጅተን ይህን
እውን ለማድረግ የተንቀሳቀስንበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አሁንም የራሳችን የአየር ሰዓት እንዲኖረን የተለያዩ ጥረቶችን
እያደረግን ነው፡፡ እስከዚያው ግን በተለያዩ መጽሔቶች ላይ በማኅበሩ ስም ጽሑፎች እንዲወጡ እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- የማኅበሩ የፋይናንስ ምንጭ ምንድን ነው?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- በዋነኛነት የገንዘብ ምንጮቻችን
ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት በውድድር አሸንፈን የምናገኛቸው ፈንዶች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የአባላት ዓመታዊ መዋጮ
ነው፡፡ ነገር ግን ይህ መዋጮ እንዲህ ነው ተብሎ የሚወራም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳ አባላት ብዙ ቢሆኑም
የነቃ ተሳትፎ ያላቸው በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ መዋጮ የማይከፍሉም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ የሳይኮሎጂ ሙያ ምን ያህል ሚና ይኖረዋል ብለሽ ታምኛለሽ?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- ሙያው በሰው ልጅ ሁለንተናዊ ሕይወት
ውስጥ የሚኖረው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡ ባደጉት አገሮች ካለው እውነታ ጋር ሲነፃፀር በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ግን
የሙያው ጠቀሜታ እምብዛም አይደለም፡፡ ሳይኮሎጂ ያጠኑ ሰዎች የማይገቡበት ተቋም የማይገቡበት የሥራ ዘርፍ የለም፡፡
ሰዎች በተለያዩ ነገሮች ሲቸገሩ ወደ ሥነ ልቦና ባለሙያ የመሔዳቸው ዕድልም በጣም ሰፊ ነው፡፡ በተቃራኒው እኛ አገር
ሙያው በደንብ ካለመታወቁ የተነሳ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት አልቻለም፡፡ ሰዎች ወደ ሥነ ልቦና ባለሙያ ጋር መሔድ
የአእምሮ ችግር አለበት/ባት ያስብላልና ብሎ ያስባል፡፡
ነገር ግን የዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ መደበኛ ሕይወትን የበለጠ
ያሻሽላል፡፡ ስለሙያው የተሳሳተ አመለካከት ተምረዋል፣ አውቀዋል በሚባሉ ሰዎችም ጭምር የሚንፀባረቅ ነው፡፡ ለምሳሌ
የሕክምና ዶክተሮች ምንም ዓይነት አካላዊ የጤና ችግር የሌለበት በሽተኛ ሲያጋጥማቸው ወደ ሥነ ልቦና ባለሙያ
ለመምራት አይፈልጉም፡፡ ቢሆንም ግን በአሁኑ ወቅት የሥነ ልቦና ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡
በየመንገዱ የምናየው የአእምሮ ሕመምተኛ ቁጥር ቀን በቀን እየጨመረ ነው፡፡ ይህ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ከሥነ
ልቦና ጋር የተያያዘ ክፍተት ያሳያል፡፡ ስለዚህ ሳይኮሎጂ ንፁህ ሳይንስ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ነገር
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሥነ ልቦና ጋር የተያያዘ ነገር ላይ ልሥራ ሲባሉ ፈንድ አያደርጉም፡፡ የሚፈልጉት
ለውጡ በአጭር ጊዜ በሚታይ በሚጨበጥ ነገር ላይ መሳተፍ ነው፡፡ ይህም ሌላው ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ሴተኛ አዳሪዎች
ላይ ይሠራ ቢባል ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎችን ማንቃት ላይ ይሠራ
ቢባሉ ያፈገፍጋሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ወደተለያዩ ዓረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት ሔደው ለአእምሮ ሕመም ተጋልጠው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያትን በሚመለከት የምትሠሩት ሥራ አለ?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- አዎ እነዚህ ሴቶች ከደረሰባቸው የአእምሮ ችግር፣ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ወጥተው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሥነ ልቦና ድጋፍ የመስጠት ሐሳብ አለን፡፡
ሪፖርተር፡- አጋሮቻችሁ እነማን ናቸው?
ወ/ት ቃልኪዳን፡- አይኦኤም፣ ሴቭ ዘ ችልድረን፣ ጉድ ሳማሪታን፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ወርከሮች፣ ሶሺዮሎጂስቶችና አንትሮፖሎጂስቶች ማኅበር አጋሮቻችን ናቸው፡፡ ከእነሱ ጋር ብዙ የመሥራት ሐሳብ አለን፡፡
http://shaybuna.com/amharic/711/-
No comments:
Post a Comment