Wednesday, October 9, 2013

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ግምገማ ላይ ናቸው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ግምገማዊ ሥልጠና ላይ ናቸው፡፡ የከተማው አስተዳደር ካቢኔ ሰሞኑን ከተማው የሚመራበትን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ካፀደቀ በኋላ ነው አመራሮቹ ግምገማዊ ሥልጠና የገቡት ተብሏል፡፡
በዚህ ግምገማዊ ሥልጠና ያልተገቡ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ የተባሉ አመራሮች ሂስና ግለ ሂስ የሚያደርጉ ከመሆኑም ባሻገር፣ ጠንከር ያሉ ችግሮችን ፈጥረዋል የሚባሉ አመራሮች ክስ እንዲመሠረትባቸው ለፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተላልፈው እንደሚሰጡ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አመራሮች በዚሁ መነሻነት ባለፈው እሑድ መስከረም 26 ቀን 2006 ዓ.ም. አዳማ ከትመው ግምገማና ሥልጠናቸውን ተያይዘውታል፡፡ 
በዋናነት ሥልጠናው የተዘጋጀው የከተማው ካቢኔ በ2006 እና 2007 ዓ.ም. ተግባራዊ ስለሚደረጉ ሥራዎች ያወጣው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ተግባራዊ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ አመራሮቹ ወጥ አቋም እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሒደት ዕቅዱ እንዳይሳካ እንቀፋት ሊሆኑ በሚችሉ አመራሮች ሊፈጽሙ በሚችሉዋቸው ያልተገቡ ድርጊቶች፣ ከዚህ በፊት የፈጸሟቸው ሕገወጥ ተግባራት የዕቅዱን ተፈጻሚነት ጥያቄ ውስጥ ሊጥሉ ይችላሉ በሚባሉ አመራሮች ላይ ግምገማ ይካሄዳል ተብሏል፡፡ 
በግምገማ ሒደቱ የሚስተካከል ጥፋት ያጠፉ አመራሮች ሂስና ግለ ሂስ የሚያካሂዱ ሲሆን፣ ጠንከር ያሉ ጥፋቶች ያሉባቸው አመራሮች ከማስረጃ ጋር ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ተለልፈው እንደሚሰጡ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከብቃት ጋር የተያያዙ ችግሮች ያሉባቸው አመራሮች ካሉበት ቦታ እንደሚነሱና የኃላፊነት ሽግሽግ እንደሚካሄድ ምነጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በከፍተኛና በመካከለኛ አመራሮች ዙርያ ግምገማ አካሂዶ ትንታኔ የሰጠበት ሰነድ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ 
በዚህ ትንታኔ ከፍተኛ አመራሮች ሥራዎችን ጠበቅ አድርገው ከመሥራት ይልቅ ያዝ ለቀቅ እንደሚያደርጉ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በሥራ የሚሰላቹና በተወሰኑ ሥራዎች የሚረኩ፣ የጠባቂነት ዝንባሌ የሚታይባቸው መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩልም የፀረ ሙስና [ኪራይ ሰብሳቢ] እና ሕገወጥነት ትግል በማካሄድ በኩል ዳተኝነት ይታያል፡፡ አልፎ አልፎም አንዳንድ አመራሮች በአመለካከትም ሆነ በተግባር የችግሩ ሰለባ ሆነው መገኘታቸውን ሰነዱ ያብራራል፡፡ ሰነዱ በመቀጠል አንዳንድ አመራሮች እነዚህን ችግሮች ታግለው ከማስተካከልና ሥርዓት ከማስያዝ ይልቅ አይቶ እንዳላየ ያልፋሉ፡፡ ‹‹በአጠቃላይ አመራራችን የሚካሄደው የእርስ በእርስ ትግል ከአድርባይነት ያልፀዳ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፤›› ይላል ሰነዱ፡፡ 
በመካከለኛ አመራሩም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ ሰነዱ ትንታኔውን ያቀርባል፡፡ መካከለኛ አመራሮች የመሬት ወረራ፣ ሕገወጥ ግንባታና ሕገወጥ ንግድ በየአካባቢያቸው ሲስፋፉ አይተው እንዳላዩ የሚሆኑ አሉ፡፡ አልፎ አልፎም በእነዚህ ጉዳዮች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ድርድር ያካሂዳሉ፣ ለሕገወጦች ሽፋን ይሰጣሉ፡፡ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ይደለላሉ የሚለው ሰነዱ፣ ትንታኔውን በጥልቀት በማካሄድ በተግባር ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ መኖራቸውን ይዘረዝራል፡፡ 
አልፎ አልፎም በመርህ ላይ ተመሥርቶ ከመታገል ይልቅ በኔትወርክና በቡድንተኝነት መጠቃቃት በመካከለኛ አመራሮች አካባቢ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ሰነዱ ትንታኔ አቅርቦ አመራሮቹን ወቅሷል፡፡ 
ሰሞኑን በየደረጃው በሚካሄደው ግምገማና ሥልጠና እነዚህ ጉዳዮች በስፋት እየተነሱ አመራሮቹ ከመገምገማቸውም በላይ፣ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች እንደሚኖሩ ምንጮች አመልክተዋል፡፡ 
ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment