ከትራንስፎርመሮች ግዥ ጋር በተያያዘ መንግስትን ከፍተኛ ገንዘብ ያሳጡ 9 የኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ተከሰሱ
አዲስ አበባ ፣ሀምሌ 26 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) ከትራንስፎርመሮች ግዥ ጋር በተያያዘ መንግስት 25 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንዲያጣ አድርገዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ 9 የኢትዮጵያ ኤለሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ዛሬ ክስ ተመሰረተባቸው።
ሁለት ስራ አስፈጻሚዎች በሚገኙባቸው በእነዚህ መዝቦች ላይ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት 2ኛ የወንጅል ችሎት ለሁለተኛ ጊዜ የጊዜ ቀጠሮ ከፈቀደ በኋላ ነው፤ የፈደራሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ዛሬ የምርመራ ቡድኑ ስራውን በማጠናቀቁ ክስ ለመመሰረት የበቃው።
አቃቤ ህግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ብርሃኔ ፣ የሲስተምና የደንበኞች አገልግሎት ድጋፍ ክፍል ሃላፊ አቶ ሞገስ በላቸው ፣ የቴክኒክ ክፍል ቡድን መሪው አቶ መኮንን ብርሃኔ ፣ ሚስተር ጂሰስ ባራሶይን የኮብራ ኢንስታሌሽን ዋይ ሰርቪሽየስ ኢንዲያ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዳይሬክተር እና የጉድ ላክ እስቲል ቲዩብስ ሊሚትድ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ናሬሽ ቻንድራን በአንደኛው መዝገብ ሲከሰሱ ፤
በሁለተኛው መዝገብ ደግሞ በአትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የሃገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ስራ እሰፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ፣ የኢንጂነሪንግ ክፍል ሃላፊው አቶ ሚሊዮን ማቱሳላ ፣ የሰፕላይ ቼን ሃላፊ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት አቶ ዳንኤል ገብረስላሴ ፣ የኢንጂነሪንግ ፕሮሰስ የስራ ሂደት ተወካዩ አቶ ሰመረ አሳቤ እና የጨረታ ገምጋሚዎቹ አቶ አሸናፊ ዮሃንስ ፣ አቶ ፋሪስ አደም ፣ ብሩክ ተገኝ ፣ ጌታቸው አዳነ እና ሁለቱ የውጭ ሃገር ኩባንያ ስራ አስኪያጆች ናቸው።
የኮብራና ጉድላክ ኩባንያዎች ሁለቱንም መዝገቦች የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ በሁለት መዝገቦች የተጠቀሱ ተጠርጣሪዎችን በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት 1ኛ እና 15ኛ የወንጀል ችሎቶች ነው ክስ የመሰረተባቸው።
እነ አቶ መስፍን በተጠቀሱበት የክስ መዝገብ አቶ መስፍንን ጨምሮ አቶ ሞገስ በላቸው እና አቶ መኮንን ብርሃኔ ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው ራሳቸውን እንዲሁም በመዝገቡ የተጠቀሱ ሁለቱን የውጭ ሃገር ኩባንያዎችን በመጥቀም መንግስትን ጎድተዋል በሚል ወንጀል ነው የተጠረጠሩት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮችን በሰፕላየርስ ክሬዲት ለመግዛት ከዛሬ አራት አመት በፊት ባወጣው ጨረታ ፥ ጉድላክ ቲዩብስ የተሰኘው የህንድ ኩባንያ ጨረታውን በማሸነፍ 3520 ትራንስፎርመሮችን ከ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሆነ ዋጋ ለማቅረብ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ይስማማል።
ኮርፖሬሽኑ ጉድላከ ስቲል ቲዩብስ የትንስፎርመር አቅራቢ ፣ ኮብራ ኢንስታሌሽንስ ግዥውን በገንዘብ እንዲደግፍ እና ኮርፖሬሽኑ ደግሞ የትራንስፎርመሮቹ ገዥ በመሆን ወደ ስራ ለመግባት የውል ስምምነቱ ተጠናቋል።
ጉድላክ ከወራት በኋላ እኔ አቅሙ ስለሌለኝ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ውለታ የገባው ኮብራ ኩባንያ ደርቦ ሁለቱንም ስራ ያከናውን በማለት ያመለከተ ሲሆን ፥ ኮርፖሬሽኑ በወቅቱ ጉድላክ ከስምምነቱ እንዳይወጣ በማለት ደብዳቤ መጻፉም በክሰ መዝገቡ ተመልክቷል።
አቶ መስፍን ግን ያለኮርፖሬሽኑ እውቅና የሶስትዮሹን ስምምነት ወደ ሁለትዮሽ ዝቅ በማድረግ ፥ ሁለቱ የውጭ ሃገር ኩባንያዎች ያዘጋጁትን ውል ያለምንም ማገናዘቢያ በመቀበል ማጽደቃቸው በክስ መዝገቡ ተመልክቷል።
ከዚያም ተከሳሹ የገንዘብ ምንጭ ለሆነው ለሪዘርቭ ባንክ ኦፍ ኢንዲያ በጻፈው ደብዳቤ ለውሉ ተቀባይነት ማረጋገጫ ሰጥቷል ይላል ክሱ።
ከአቶ መስፍን ጋር በመዝገቡ የተጠቀሱ ሁለቱ የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ትብብር በማድረጋቸው ከእነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ህገ ወጥ ስምምነት በመደረጉ መንግስት ከ17 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካን ላር በላይ ማጣቱም በመዝገቡ ተጠቅሷል።
አዳዲስ ትራንስፎርመሮች ወደ ሃገር ቤት መጥተው ከትራንስፎርመር ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው የሃይል አቅርቦት ችግር ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ ያገለገሉ እና የቅርብ ስሪት ሆነው ተገኝተዋል።
በክሱ 4ኛ እና 5ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱ የውጭ ሃገር ኩባንያዎች ከአቶ መስፍን ጋር በመመሳጠር ችግሩ እንዲከሰት ማድረጋቸውንም ክሱ ያስረዳል።
እነ አቶ ሽፈራው ተሊላ የሚገኙበት የክስ መዝገብም በተመሳሳይ መልኩ ባደረጉት የውል ስምምነት ያገለገሉ 1950 ትራንስፎርመሮች ወደ ሃገር ቤት ገብተዋል።
አስሩም ተከሳሾች ፈፅመውታል በተባለው የሙስና ወንጀል ዛሬ የተከሰሱ ሲሆን ፥ ተከሳሾቹ የፊታችን ሰኞ በሁለቱም ፍርድ ቤቶች የክስ መቃወሚያ ያቀርባሉ ተብሎ ትጠበቃል።
በጥላሁን ካሳ
No comments:
Post a Comment