በሔሊኮፕተር አደጋ የተጐዱ አራት ሩሲያውያን በባልቻ ሆስፒታል እየታከሙ ነው Four Russians who were injured in Helicopter crash in Ethiopia are being treated at Balcha Hospital
የጨፌ ዶንሳ አርሶ አደሮችና አየር ኃይል በነፍስ አድን ጥረት ተደንቀዋል
ባለፈው ረቡዕ ከአዲስ አበባ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከየረር ተራራ
በስተጀርባ ጨፌ ዶንሳ በተባለ አካባቢ በደረሰው የሔሊኮፕተር አደጋ የተጐዱ አራት ሩሲያዊያን ፓይለቶች፣ በአዲስ
አበባ ባልቻ ሆስፒታል ከፍተኛ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡
አራቱ ሩሲያዊያን አብራሪዎች አደጋው በደረሰ ዕለት ከሰዓት በኋላ ወደ
ባልቻ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ በደረታቸውና በእግራቸው ላይ ስብራት እንደደረሰባቸው፣ ማምሻውን ቀዶ ጥገና
እንደተደረገላቸው ከባልቻ ሆስፒታል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ አራቱም አብራሪዎች ክፉኛ የተጎዱ ሲሆን፣ በተለይ
ዋና አብራሪው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
አብራሪዎቹ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ድረስ በማገገሚያ ክፍል ውስጥ
ከፍተኛ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ተገኝተን ተጎጂዎችን
ለመጎብኘት ብንሞክርም የሆስፒታሉ አስተዳደር ተጎጂዎቹ ባሉበት ሁኔታ ጋዜጠኛ ሊያናግሩ አይችሉም በማለት መልሶናል፡፡
ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በደቡብ ሱዳን ለሚያካሂደው የዕርዳታ ተግባር፣ ተቀማጭነቱ
ክራስኖዳር ሩሲያ ከሆነ ፐንች ጆይንት ስቶክ ከተባለ ኩባንያ የተከራያቸው ሁለት ሩሲያ ሠራሽ የትራንስፖርት ሚ8
ሔሊኮፕተሮች ረቡዕ ማለዳ ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ነበሩ፡፡
ሔሊኮፕተሮቹ ከሩሲያ በመነሳት በየአገሩ በማረፍ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ተነስተው ጂቡቲ ደርሰው ነዳጅ ከሞሉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጄነራል ኮሎኔል
ወሰንየለህ ሁነኛው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሔሊኮፕተሮቹ የኢትዮጵያን አየር ክልል አቋርጠው ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና
ከተማ ጁባ ለመብረርና አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አርፈው ነዳጅ ለመቅዳት ባለሥልጣኑን ፈቃድ
ጠይቀው ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሁለቱም ሔሊኮፕተሮች አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ
ከሚገኘው የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ ጋር የሬዲዮ ግንኙነት ሲያደርጉ እንደነበር የገለጹት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣
አንደኛው ሔሊኮፕተር ከጠዋቱ 4፡20 ጀምሮ የሬዲዮ ግንኙነት አቋርጧል፡፡
‹‹አርኤ 25 497›› በሚል የምዝገባ ቁጥር የሚለየው ሔሊኮፕተር
ምሥራቅ ሸዋ ውስጥ ከየረር ተራራ በስተጀርባ ልዩ ስሙ ጨፌ ዶንሳ በተባለ አካባቢ ተከስክሶ ሊገኝ ችሏል፡፡
በአካባቢው የነበሩ አርሶ አደሮች በሔሊኮፕተሩ ውስጥ የነበሩ አራት አብራሪዎችን ለማዳን ያደረጉትን ጥረት ኮሎኔል
ወሰንየለህ በአድናቆት ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ወደወደቀው ሔሊኮፕተር በፍጥነት በመሄድ ተጎጂዎቹን
ለማውጣት ቢሞክሩም በሮቹ አልከፈት ስላሉዋቸው በመጥረቢያ ቆርጠው ተጎጂዎቹን በማውጣት በእንጨት በሰሩት ቃሬዛ
በአካባቢው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ወስደዋል፡፡ የተቀሩት አርሶ አደሮች በሩጫ በመሄድ በቅርብ ርቀት ላይ ለሚገኙ
የመከላከያ ሠራዊት አባላት ስለደረሰው አደጋ ተናግረዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባላት በበኩላቸው አደጋውን ለደብረ ዘይት አየር
ኃይል ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ አየር ኃይል የነፍስ አድን ቡድን በሔሊኮፕተር በመላክ የአደጋ ተጎጂዎችን ወደ ቦሌ
ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አምጥቷል፡፡
የአየር ኃይል አባላት አደጋውን ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን
ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ አዲስ አበባ ለሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲና ባልቻ ሆስፒታል አሳውቋል፡፡ በመሆኑም
ባልቻ ሆስፒታል የሕክምና ቡድንና አምቡላንሶች ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ልኮ ተጎጂዎቹን ወደ
ሆስፒታል አጓጉዞ አስቸኳይ የሕክምና ዕርዳታ አድርጓል፡፡ በነፍስ አድኑ ጥረት ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት
እንደተሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓይን ምስክሮች አደጋው በደረሰበት ወቅት
አካባቢው በጉም ተሸፍኖ እንደነበር ገልጸው፣ ሔሊኮፕተሩ ከመከስከሱ በፊት በአካባቢው ማንዣበቡን ገልጸዋል፡፡ እንደ
ዓይን ምስክሮቹ ገለጻ፣ ሔሊኮፕተሩ ለማረፍ በመሞከር ላይ እንዳለ በግምት ከ200 ሜትር ርቀት ላይ ወደ መሬት
ወድቋል፡፡ አብራሪዎቹን ያነጋገሩ አንድ ግለሰብ በበኩላቸው፣ ሔሊኮፕተሩ ጉም ውስጥ መግባቱንና የመገናኛ ሬዲዮኑም
በድንገት መበላሸቱን ገልጸውልኛል ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ሚ8 ሔሊኮፕተር አብራሪዎች ስለደረሰው አደጋ ሳይረዱ 4፡45
ላይ ቦሌ በሰላም አርፈዋል፡፡
ኮሎኔል ወሰንየለህ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በፍጥነት ያካሄደው የነፍስ
አድን ሥራ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ በሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአውሮፕላን አደጋ መከላከልና ምርመራ ክፍል
ኃላፊ በሻምበል ግርማ ገብሬ የሚመራ ቡድን ሐሙስ ጠዋት አደጋው በደረሰበት ሥፍራ ተገኝቶ የምርመራ ሥራ ጀምሯል፡፡
የአደጋውን መንስዔ አሁን መናገር አይቻልም ያሉት ሻምበል ግርማ፣ የአደጋ ምርመራ አራት ደረጃዎች (መረጃ ስብሰባ፣
ምርመራ፣ ትንተናና የውሳኔ ሐሳብ መስጠት) እንዳሉት ገልጸው፣ ቡድናቸው ገና መረጃ በመሰብሰብ ላይ እንደሆነ
ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአገሪቱን የፈልጎ ማዳን ብሔራዊ ኮሚቴ ለማጠናከር ባለሥልጣኑ ባለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ ጥረት ሲያካሂድ መቆየቱን ኮሎኔል ወሰንየለህ ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ ኮሚቴው ከአየር ኃይል፣ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከፌደራል ፖሊስና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተውጣጡ 20 አባላት ሲኖሩት፣ የአውሮፕላን
ወይም ሔሊኮፕተሮች አደጋ በሚደርስበት ወቅት በቅንጅት አፋጣኝ የፈልጎ ማዳን ሥራ እንዴት መሥራት እንዳለበት
በየጊዜው እየተገናኙ እንደሚነጋገሩ ኮሎኔል ወሰንየለህ አስረድተዋል፡፡
ሚ8 የተሰኙት የትራንስፖርት ሔሊኮፕተሮች በኢትዮጵያና በሌሎች በርካታ
የአፍሪካ አገሮች በብዛት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሔሊኮፕተሮቹ መንገደኛና ዕቃ
የሚያጓጉዙ በመሆኑ ለወታደራዊና ለሲቪል አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡ ከሩሲያ ኤምባሲ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት
ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
sodre.....
No comments:
Post a Comment