Monday, August 5, 2013

ኢትዮጵያውያኑ ከአውስትራሊያና አሜሪካ ሽልማት አገኙ

ኢትዮጵያውያኑ ከአውስትራሊያና አሜሪካ ሽልማት አገኙ


ሶስት ኢትዮጵያውያን ከአውስትራሊያና አሜሪካ ሽልማት አገኙ።
ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በቤተ መንግስታቸው በሳይንስ ፣ በሂሳብ እና ምህንድስና ዘርፎች ለ6 ግለሰቦችና 8 ድርጅቶች ሽልማት በሰጡበት ሥነ ሥርዓት ላይ ኢትዮጵያዊው ሰለሞን ቢልልኝ ከተሸላሚዎቹ አንዱ በመሆን ከፕሬዝዳንቱ እጅ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡
የፊዚክስ ፕሮፌሰሩ ሰለሞን ቢልልኝ በአሜሪካ ሰሜን ካሮሊና ግዛት በሚገኝ የግብርናና ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ውጤታማ የምርምር ስራ እንዲያከናውኑ በማድረጋቸው ነው የፕሬዝዳንት ኦባማን የሂሳብ ፣የፊዚክስና የምህንድስና ልህቀት ሽልማትን ለመጋራት የበቁት፡፡
በቀጣይም ፕሮፌሰር ሰለሞን የሚያማክሯቸው የምርምር ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማድረግም ከአሜሪካ የሳይንስ ፋውንዴሽን 25 ሺህ ዶላር ያገኛሉ ተብሏል ፡፡
በተመሳሳይ ዜና ዶክተር ዮሃንስ ይህደጉ የተባሉ ኢትዮጵዊ የአውስትራሊያን የፓርላማ ሽልማት አግኝተዋል ፤ የአውስትራሊያ ፓርላማ ኢትዮጵያዊውን ዶክተር ዮሃንስ ይህደጉን ጨምሮ ለሌሎች 99 አፍሪካ-አውስትራሊያውያንም ብሔራዊ ሽልማት ሰጥቷል፡፡
ሽልማቱ የተሰጠው አፍሪካዊ ዝርያ ያላቸው አውስትራሊያውያን በህክምና ፣ በባሕል ፣ በስፖርት ፣ በፖለቲካ ፣ በትምህርት ፣ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የባህል ብዝሃነትን በተመለከተ በሰሩት ሥራ እና በአፍሪካ እና በአውስትራሊያ መካከል  መልካም ግንኙት እንዲፈጠር ላበረከቱት መልካም ሥራ ዕውቅና ለመስጠት በማሰብ ነው፡፡
በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቨን ሩድ እና ሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች  ተገኝተዋል፡፡
ዶክተር ዮሃንስ ይህደጉ ወልደዩሃንስ በዓለም አቀፍ የኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ውስጥ ፤ በምህንድስና ዘርፍ በአውስትራሊያ ፣ ኬንያ ፣ ታንዛኒያ፣ ኩዌት፣ ሳዑዲአረቢያ፣ ጆርዳን እና በሞንጎሊያ ውስጥ በውሃ ኃብት፣ በማእድን፣ በመሰረተ ልማት እና የኃይል አቅርቦት ዘርፍ በሰፊው የሚሰሩ ታዋቂ ምሁር ናቸው፡፡
በሌላ መስክም ኢትዮጵያዊው በኢትዮጵያ የእንስሳት ኃብት ምርምር ኢንስቲትዮት ውስጥ የሚሰሩት አዛገ ተገኘ ሲሆኑ ፥ ከአውስትራሊያው ጀምስ ኮክ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማት አግኝተዋል፡፡
ከጀምስ ኮክ ዩኒቨርሲቲ የአሉመኒን ሽልማት ከተቀበሉ 12 ግለሰቦች ውስጥ አንዱ በመሆን ነው ኢትዮጵያዊው አዛገ ተገኝ ሽልማታቸውን የተቀበሉት ፡፡
ይህንን ሽልማት የተለያዩ ምሁራን ከኢትዮጵያ፣ አፍጋኒስታን፣ ሰሜን አየርላንድ እና ፊሊፔንስ አግኝተዋል፡፡
ምንጭ፣ ፋና

No comments:

Post a Comment