Monday, August 5, 2013

ኦሊምፒያ አካባቢ የሚገኘውን የቀበሌ መዝናኛ እሳት በላው

ኦሊምፒያ አካባቢ የሚገኘውን የቀበሌ መዝናኛ እሳት በላው Fire destroyed Kebele Recreation Center behind Denbel City Center

ተጻፈ በ ውድነህ ዘነበ, EthiopianReporter.com
ባለፈው ዓርብ ረፋድ ላይ በአፍሪካ ጎዳና (ቦሌ መንገድ) ከደምበል ሲቲ ሴንተር ሕንፃ ጀርባ የሚገኘው ቀበሌ 20/21 መዝናኛ (17 መዝናኛ) በተከሰተ ድንገተኛ እሳት አደጋ ጉዳት ደረሰበት፡፡
መዝናኛ ማዕከሉ ለምሳ ምግቦች እየተዘጋጁ ባሉበት ከረፋዱ 4፡30 ላይ ከሥጋ መጥበሻ ቤት ተነሳ በተባለ እሳት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ የመዝናኛ ማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ አልቤ ለሪፖርተር እንደተናገሩትና ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ መመልከት እንደቻለው የመዝናኛ ማዕከሉ የምግብ ማብሰያ፣ የሠራተኞች ልብስ መቀየርያ፣ ማብሰያዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች፣ ጄኔሬተር፣ የምግብ ግብዓቶችና በዕለቱ ሜኑ መሠረት ለምሣ የተዘጋጁ የተለያዩ ምግቦች ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡
‹‹ለምሳ የተዘጋጁ ምግቦች እስከ ሰባት ሺሕ ብር ድረስ ሽያጭ ነበራቸው፤›› ሲሉ አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ቅፅበታዊው የእሳት አደጋ ከ35 እስከ 40 ደቂቃዎች ውስጥ መዝናኛ ማዕከሉ 300 ሺሕ ብር የገመተውን፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ኤጀንሲ 150 ሺሕ ብር የገመተውን ንብረት አውድሟል፡፡
ብዙዎችን ያስገረመው መዝናኛ ማዕከሉ የወደመበት ንብረት 300 ሺሕ ብር ሲገመት ሊጠፋ ይችል የነበረ ሁለት ሚሊዮን ብር መትረፉን መግለጹ ሲሆን፣ የእሳና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ኤጀንሲ በበኩሉ የወደመውን ንብረት በግማሽ ቀንሶ 150 ሺሕ ብር ሲያደርግ ሊወድም የነበረውን ንብረት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ አድርጎታል፡፡ ይህ የግምት መፋለስ በወቅቱ መከሰቱ ጉዳዩን ለተረዱ ሰዎች አስገራሚ ሆኗል፡፡ የዕለቱን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር በአቶ ቁምላቸው ንጉሴ የሚመሩ 22 የኤጀንሲው አባላት ተሰማርተዋል፡፡
አቶ ቁምላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እሳቱን ለማጥፋት 13,500 ሊትር ውኃ ተጠቅመዋል፡፡ የእሳት አጥፊው ኤጀንሲ ወትሮ ከሚደርስበት ወቀሳ ነፃ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የመዝናኛ ማዕከሉ ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡
ኤጀንሲው በአምስት ደቂቃ ውስጥ በቦታው መድረሱ ሲነገር፣ አቶ ቁምላቸው በዚህ ጊዜ ውስጥ ለመድረስ ከፍተኛ የተሽከርካሪ መጨናነቅ እንደነበር ጠቅሰው፣ የግድ እሳቱን መቆጣጠር ስለነበረባቸው ሕገወጥ ጉዞ አድርገው በስፍራው መገኘታቸውን አልሸሸጉም፡፡
በየጊዜው እየተከሰተ የሚገኘው የትራፊክ መጨናነቅ እሳት የማጥፋት ሒደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው አቶ ቁምላቸው አስረድተዋል፡፡ የቀበሌ 20/21 መዝናኛ ማዕከል 50 ሠራተኞች አሉት፡፡ ማዕከሉ መሿለኪያ አካባቢ የሚገኘው ቀበሌ 15 መዝናኛ ማዕከል በሥሩ ይገኛል፡፡
መዝናኛ ማዕከሉ በአሁኑ ጊዜ በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ሥር የሚገኝ ሲሆን፣ በሥራ አመራር ቦርድ ይተዳደራል፡፡ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ላልተወሰነ ጊዜ ከአገልግሎት ውጭ የሚሆን በመሆኑ በማዕከሉ ሥር የሚተዳደሩ ሠራተኞች በዕጣ ፈንታቸውና በቀጣዩ የማዕከሉ አደረጃጀት ላይ የሥራ ኃላፊዎቹን በማነጋገር ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

sodere............

No comments:

Post a Comment