Friday, November 1, 2013

አሳዛኝ ዜና -በጀርመን ህክምና እየተከታተለ የሚገኘው ኮሜዲያን አብርሐም አስመላሽ አረፈ።

የዲስክ መንሸራተት አጋጥሞት በጀርመን ህክምና እየተከታተለ የሚገኘው ኮሜዲያን አብርሐም አስመላሽ አረፈ።
ነፍስ ይማር
ርቲስት አብርሃም አስመላሽ ባደረበት ህመም ምክንያት ላለፊት ጥቂት ወራት በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ አካባቢ የእክምና እርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ ባለፈው አርብ ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
በአብዛኛው በገጠርኛ ዘይቤ አቀራረቡና በኮሜዲ ስራዎቹ የሚታወቀው አርቲስት አብርሃም አስመላሽ በዲስክ መንሸራተት ህመም ምክንያት ለረጅም ጊዜያት ሲሰቃይ ቆይቷል።
አርቲስት አብርሃም ከዲስክ መንሸራተት በተጨማሪ በጉበትና በኩላሊት እንዲሁም በሳምባ ምች በሽታዎች ሲታመም የነበረ ቢሆንም ከወዳጆቹና ከጥቂት የስራ ባልደረቦቹ ባገኘው የገንዘብ እርዳታ ህክምና አግኝቶ ከተወሰኑት በሽታዎች ሊድን ችሎ ነበር።
ይሁንና የዲስክ መንሸራተት መሙን በግሉ ከፍሎ መታከም ባለመቻሉ ህብረተሰቡን ለህክምና የሚሆን የገንዘብ እርዳታ በመጠየቅ ላይ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህ የዲስክ መንሸራተት ህመም ምክንያት አርቲስት አብርሃም እንደልቡ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ለረጅም ጊዜያት በህዝብ ከሚታወቅባቸው የመነባንብና የኮሜዲ ስራዎቹ ሊርቅ ተገዶ ነበር።
በተለይ ”እረኛውና” ፣ ”ጠበል ቅመስ” በሚል ስራዎቹ የሚታወቀው አርቲስት አብርሃም አስመላሽ ከሃያ ያላነሱ ዓመታትን በኢትዮጵያ ራዲዮ ቅዳሜ መዝናኛ የተለያዩ ማህበረሰብ ነክ በመነባንቦችንና የኮሜዲ ስራዎችን ሲያቀርብ እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸው ቃለመጠይቆች ላይ ገልፃል።
አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ተወልዶ ያደገው አርቲስት አብርሃም አስመላሽ የገጠርኛ ዘይቤ አቀራረቡን ለበግ ንግድ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢው ወደሚገኘው ”ደንሴ ተራራ” ይመጡ ከነበሩ የመንዝና የወሎ አካባቢ ነጋዴዎች ቀስሞ እንዳደገ ይገልፃል።
አርቲስት አብርሃም ከተለያዩ አካባቢዎ ወደ ”ደንሴ ተራራ” ይመጡ ከነበሩ የገጠር የሀገሪቱ አካባቢ ነዋሪዎች ለየት ያለ የአማርኛ አነጋገር በመመሰጡ የተነሳ ”ሌሎች ሰዎች በገበያዎች በጎችን ሲሰርቁ እኔ ግን የአማርኛ አነጋገር ዘይቤያቸውን ነበር ስሰርቅ ያደግኩት ”ሲል ገልፆ ነበር።
አርቲስቱን ከሞት ለመታደግ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የድረሱለት ጥሪ ቢያሰሙም ከጥቂት ግለሰቦች በስተቀር ማንም ምላሽ የሰጠው አልተገኘም።
አርቲስት አብርሃም አስመላሽ ወደ ቀድሞው ጤንነቱ ቢመለስ ኖሮ ለህትመት ያልበቁ በርካታ ስራዎችን የማሳተም እቅድ እንደነበረው ገልፆ ነበር።
አርቲስት አብርሃም ትዳር እንዳልመሰረተና ያፈራው ልጅም እንደሌለው ገልፆ የነበረ ሲሆን በህመም ተይዞ ለህክምና እርዳታ እጁን እስከዘረጋበት ጊዜ ድረስ መነኩሴ እናቱን በመርዳት ብቻ ይኖር እንደነበር ገልፃል።
ለአርቲስቱ ቤተሰቦችና አድናቂዎች መፅናናትን እንመኛለን!
zehabesha.com
source: freedom4ethiopian

No comments:

Post a Comment