Friday, November 1, 2013

ሰበር ሰሚ ችሎት የነ አቶ በቀለ ገርባን ይግባኝን እንደማያይ አስታወቀ

-እነ አንዱዓለም አራጌም የፊታችን ሰኞ ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል
(ዘ-ሐበሻ)  የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የኦፌኮ-መድረክ ምክትል ሊቀመንበር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ላይ እና የኦፌኮ ሌላው አመመራር ወጣት ኦልባና ሌሊሳ የጠየቁትን ይግባኝ ዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የህግ ስህተት የለውም በሚል ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይግባኙን ውድቅ አድርጎታል፡፡ አቶ በቀለ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በፌደራሉ አቃቤ ህግ በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል 8 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን ፤ ይህን በመቃወም ፈደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀው ነበር፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነውን የ8 ዓመት እስራት ወደ 3 ዓመት ዝቅ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ አቶ ኦልባና ሌሊሳም በከፍተኛው ፍርድ ቤት 13 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸውን በይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ወደ 11 ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ እነ አቶ በቀለ ገርባ የተከሰስነው በሐሰት የፈጠራ ወንጀል እንጂ ምንም የፈፀምነው ወንጀል ስለሌለ፤ አቃቤ ህግም በከሰሰን ወንጀል ያቀረበው ማስረጃ እርስ በርሱ የሚጣረስ በመሆኑ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በነፃ ሊያሰናብተን ይገባል ሲሉ ይግባኝ ቢሉም ፤ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዛሬው ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ውሎው የይግባኝ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
በተያያዘ ዜና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ ፣ ሌላው የፓርቲው ምክር ቤት አባል አቶ ናትናኤል መኮንን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ እና ሌሎች የአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወሰነባቸውን የጥፋተኝነት ውሳኔ በመቃወም ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብለዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8 ሰዓት 6 ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀነ ቀጠሮ መሰጠቱን ጠበቃው አቶ አበበ ጉታ አስታውቀዋል፡፡
ይህም ለነ አቶ አንዱዓለም ቀጠሮ የመጀመሪያው የሰበር ሰሚ ችሎት ቀነ ቀጠሮ መሆኑ ታውቋል፡፡ አቶ አንዱዓለም አራጌ በከፍተኛው እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕድሜ ልከል ፅኑ እስራት ሲፈረድበት ጋዜጠና እስክንድ ነጋ ደግሞ 18 ፅኑ እስራት ፍርድ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መፅናቱ ሲታወቅ የሌሎችም እንዲሁ መሆኑም አይዘነጋም፡፡

No comments:

Post a Comment