ኢትዮዽያውያን ዘረኞች አይደለንም፤ በዘር አልተለያየንም። ኢትዮዽያ ዉስጥ የተለያየ ዘር የለም። ዘራችን አንድ
ነው፤ የሚለያየው ቋንቋችን ነው። የተለያየ ቋንቋ (ና እምነት) አለን። የተለያየ ቋንቋ መኖር ደግሞ ባህሪያዊ ነው።
የተለያየ ቋንቋ መኖር በራሱ ችግር አይደለም።
የኢትዮዽያውያን ችግር ብሄር (ቋንቋ) ሳይሆን ፖለቲካ ነው። የሚያጣላን ቋንቋችን ሳይሆን ለስልጣንና ሃብት
ያለን ስስት ነው። የችግሩ መንስኤ የስልጣን ፍላጎታችን ብቻ አይደለም፤ የህዝባችን ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና ማነስ
ጭምር እንጂ። ስልጣን ፈላጊዎች (ፖለቲከኞች) የፈለጉትን ለማግኘት ህዝብን መቀሰቀስ አለባቸው። በተወሰነ መልኩ
ህዝብን ለመቀስቀስ ስሜቱን መንካት አለብህ። ስሜቱ ለመንካት ከሌላው የሚለይበት ነገር እያነሳህ “እኛና እነሱ”
የሚል ክፍፍል መፍጠር ግድ ይላል (በምክንያታዊነት ለማያምን ህዝብ)።
ኢትዮዽያውን የምንጣላ የተለያየ ቋንቋ (ና እምነት) ስላለን አይደለም። አንድ ዓይነት ቋንቋ (ብሄር) ቢኖረን
ኑሮ አከባቢ መሰረት ያደረገ ልዩነት ይኖረን ነበር። ኢትዮዽያ ብትከፋፈልና ትግራይ ለብቻው፣ ኦሮምያ ለብቻው፣ አማራ
ለብቻው ምናምን … ቢሆኑ ክፍፍሉ በባሰ መልኩ ይቀጥል ነበር። ለምሳሌ ትግራይ ዉስጥ አንድ ቋንቋ ስለተናገርን
አንድ ዓይነት ፖለቲካዊ አቋም ይኖረን ነበር ማለት አይቻልም። በርግጠኝነት በዞን እንከፋፈል ነበር። ቀጥሎም በወረዳ
ደረጃ፣ በቅጥሎም በጣብያ፣ ቀጥሎም በቁሸት፣ ቀጥሎም በመንደር፣ ቀጥሎም በቤተሰብ (ከጎረቤቶቻን እንጣላ ነበር)፣
ቀጥሎም በግለሰብ ደረጃ (ከወንድሞቻችን ጋር መለያየቱ ይቀጥላል)። በመጨረሻም ከራሳችን ጋር መጣላታችን አይቀሬ
ነው።
አንድ ሰው በብሄር (በቋንቋ) ካሰበ ወደ ራሱ (በግለሰብ ደረጃ) እንደማይወርድ እርግጠኞች መሆን አንችልም።
ኦሮምያ ቢገነጠል በክልሉ ያሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና … ሌሎች በአንድነት መኖር ይችላሉ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም
ችግሩ ያለው ቋንቋው ላይ አይደለም። ፖለቲካው ላይ ነው። በኢትዮዽያ ስር ሁነን የትግራይ ስሜት፣ የኦሮሞ ስሜት
ወዘተ ሊኖረን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ስሜት ያለው ሰው የራሱ ክልል ሲገነጥል ቀጥሎ የራሱ ወረዳ መገንጠሉ
አይቀርም።
በአንድ ሀገር ፖለቲካ እስካለ ድረስ የብሄር ጭቆና (National Oppression) ሊኖር ይችላል። በአንድ
ብሄር (ወይ ብዙ ብሄሮች) ላይ ያነጣጠረ ጭቆና ሲኖር ሁላችን ተባብረን መዋጋት አለብን። ብሄራዊ ጭቆናን የማስወገድ
ትግሉ ለአንድ ብሄር (ወይ ግለሰብ) የሚተው የግል ስራ አይደለም። ብሄር (ወይ ቋንቋ) መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ
ቅስቀሳ (Ethnic Politicization) ግን ስህተት ነው። ሀገርን የባሰ ይከፋፍላል፣ ያዳክማል።
ብሄር (ወይ ቋንቋ) መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ በማድረግ የብሄር ጭቆና ማስወገድ አይቻልም። ምናልባት
ተሳካ ከተባለ ጨቋኞቹና ተጨቋኞቹ ይቀያየራሉ። ተጨቋኞች የነበሩ ጨቋኞች፣ ጨቋኞች የነበሩ ደግሞ ተጨቋኞች ይሆናሉ።
በዚህ መንገድ የብሄር ጭቆናን ማስወገድ አንችልም። ምክንያቱም ያው ጨቋኞችና ተጨቋኞች ቢቀያየሩም ጭቆናው ግን
አለ።
መገንዘብ ያለብን ነገር አለ። የብሄር ጭቆና ስንል አንድ ብሄር ለሌላው ብሄር ሲጨቁን ማለታችን አይደለም።
ምክንያቱም አንድ ብሄር ጨቋኝ ሊሆን አይችልም (ተጨቋኝ ግን ሊሆን ይችላል)። ምክንያቱም ጨቋኝ ለመሆን የፖለቲካ
ስልጣን መያዝ ያስፈልጋል። ብሄር ደግሞ ስልጣን ሊይዝ አይችልም። ምክንያቱም ብሄር ማሕበረሰብ የሚወክል ነው (የራሱ
ቋንቋ እስካለው ድረስ)። የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው ግን በግለሰቦች ነው። ግለሰብና ማሕበረሰብ ይለያያሉ።
ፖለቲከኞች (ግለሰቦች) ግን በስልጣን የመቆየት ሕልማቸው ለማሳካት ሲሉ (ከተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ወይ
ብሄር ድጋፍ ለማግኘት) ራሳቸው ከአንድ ብሄር ወይ ብሄሮች ሊያስተሳስሩ ይችላሉ። ፖለቲከኞች በተወሰነ የሕብረተሰብ
ክፍል (እስካልተነቃባቸው ድረስ) በአንድ ብሄር ስም ሊነግዱ ይችላሉ።
አሁን በሕብረት ታግለን የሁሉም ሰው (ወይ ብሄሮች) እኩልነት ማረጋገጥ አለብን። ሁሉም ሰው (ብሄር) እኩል
ከሆነ አንድ ብሄር ገዢ ሌላው ተገዢ የሚመስልበት ግዜ ይቀራል። እንዲህ ከሆነ ግለሰቦችም (ፖለቲከኞች) በብሄር
የሚነግዱበት ግዜ ያበቃል። ሁሉም ሰው እኩል ከሆነ ማንም ለማንም አይገዛም። ታድያ ማን ያስተዳድራል? ሁላችን
(ሁሉም ዜጋ ያስተዳድራል)። ሁሉም ዜጋ እንዴት ማስተዳደር ይችላል? ሁሉም ዜጋ በእኩል የሚያስተዳድርበት መንገድ
ስምምነቱ ነው።
ዜጎች ተስማምተው አብረው ለመኖርና ለመተዳደር ይዋዋላሉ (ዉል ይፈርማሉ)። ሁሉም ዜጎች የተፈራረሙበት ዉል
‘ሕገ መንግስት’ ይሆናል። ሕገመንግስቱ ለሁሉም ዜጎች በእኩል ያስተዳድራል። ሕገመንግስቱ የሚተገብሩ ግለሰቦች
በየደረጃቸውና ዓቅማቸው ይመረጣሉ። የተመረጡ ግለሰቦች በሕገመንግስቱ መሰረት ይሰራሉ። ሕጉ ከጣሱ ይወርዳሉ።
ግለሰቦቹ የሚመረጡት እንዲገዙ (ጌቶች እንዲሆኑ) ሳይሆን ሕገመንግስቱን ለማስተዳደር ፈርመው ተቀጥረው ነው።
የሚቀጠሩበት መንገድ በህዝባዊ ምርጫ ሊሆን ይችላል።
የሚመረጡት ግለሰቦች ብሄር ወይ ሌላ አካል የሚወክሉ አይደሉም። መወከል ያለባቸው ሕገመንግስቱ ነው።
ሕገመንግስቱ ደግሞ አጠቃላይ ህዝቡን ይወክላል። በዚህ መንገድ የሰውን አገዛዝ አስወግደን የሕግ ስርዓት መገንባት
እንችላለን። የሕግ የበላይነት ከተረጋገጠ የብሄር ጭቆናም አይኖርም። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው የሚዳኘው በቋንቋው
ሳይሆን በሕገመንግስቱ መሰረት ነው። ሰው ሁሉ ደግሞ በሕግ ፊት እኩል ነው። ፍትህ ለማግኘት ሰው መሆኑ በቂ ነው።
ስለዚህ መጀመርያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ መገንባት አለብን፤ ሁሉም የፖለቲካ ችግሮቻችን ለመፍታት።
አዎ! ብሄር በራሱ ችግር አይደለም።
It is so!!!
https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/11/03/89888/
No comments:
Post a Comment