<<ጄኔራል አማን ብቸኛ ነበሩ:: ቤታቸውን የሚጠብቁትና አትክልት የሚኮተኩቱ አንድ ሽማግሌ ዘበኛ
ናቸው ቤታቸው ያሉት:: ከብቸኝነታቸውም የተነሳ ሊሆን ይችላል ማታ ማታ ቤት ሲገቡ መጠጥ በሀይል ይጠጡ እንደነበር
በኋላ ተረዳን:: ምግብ ከእህታቸው ቤት እየመጣላቸው ነው የሚመገቡት:: ቤተሰብ የላቸው ምን የላቸው::
እንደተነገረኝ መትረየሳቸውን ቤታቸው መስኮት ላይ ጠምደው ቁጭ ብለው ሊይዟቸው የሄዱትን ወታደሮች አላስጠጋ
አሉ:: አስቀድመው በደንብ ተዘጋጅተዋል:: ጥይት ሞልቷቸዋል:: ወደቤታቸው መግቢያ ያለ አንድ መንገድ ነው:: ያንን
መቃረቢያውን ይዘው መሳሪያቸውን ጠምደዋል:: ግራና ቀኙ በሙሉ መኖሪያ ሠፈር ነው:: ይሄን መትረየስ ይዘው ሲለቁት
በየጎረቤቶቻቸው ቤት በየመስኮቱ በየበሩ ጥይት ይገባል::
በትዕዛዙ መሠረት በድምጽ ማጉያ እጃቸውን እንዲሰጡ ተጠየቀ:: መልስ የሚሰጡት ተኩስ በመክፈት ነው:: ጐረቤቱ
<ኡ ኡ> ይላል:: ሠፈርተኛው ተሸብሯል:: እነ ተስፋዬ ተቸገሩ:: አሁን እንግዲህ ለአመጸኛና በዚህ
አይነት የሠላማዊውን ነዋሪ ሕዝብ ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ሰው ምንድነው መደረግ ያለበት? ያለው አማራጭ ታንከኛ
መጥራት ነው:: ምክኒያቱም ከሳቸው ጋር ተኩስ በመለዋወጥ ማንም ሰው መሞት የለበትም:: ወታደሮችስ አስፈላጊ ያልሆነ
መስዋዓትነት ለምን አንድ ሰው ለመያዝ ብለው ይክፈሉ? ታንክ መጣ:: በዚያ ቤታቸውን ደርምሰው ገቡ:: በእንዲህ
አይነት ሁኔታ የአማን ፍጻሜ ሆነ:: በኋላ እንደተወራው ራሳቸውን አልገደሉም:: በታንክ ነው ያጨማለቋቸው::
መንግሥቱ ነው ይገደሉ ያለው የሚለው ነገር ትክክል አይደለም:: እንኳን እኔ ደርጉም ቢሆን ይገደሉ አላለም::
እንዲታሰሩ በደርጉ ተወሰነ:: ያንን ማስፈጸም ኃላፊነቱ የኔ ነው:: የደርጉን ውሳኔ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለተስፋዬ
ገብረኪዳንና ለዳኔል ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ:: እነሱ በሥፍራው ላይ ተገኝተው ያጋጠማቸው ነገር ሠላማዊ ሰዎችንም
ወታደሮችንም አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ አስፈላጊውን እርምጃ ወስደዋል::
ይሄ በማንኛውም የሚሊታሪ ግዳጅ ላይ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው:: ለአንድ ግዳጅ አንድ ሠራዊት ሲላክ በቦታው
ላይ ተለዋዋጭ ነገር ሊያጋጥመው ይችላል:: ያንን እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ሁኔታው ይከላከላል:: ይመክታል::
ይደመስሳል:: ይሄም ከዚያ አይለይም:: አንድ አመጸኛ ሊይዝ የሄደ ወታደራዊ ቡድን በሥፍራው ላይ ደርሶ በገጠመው
አስገዳጅ ሁኔታ የተወሰደ ወታደራዊ እርምጃ ነው:: መስኮታቸው ላይ መትረየስ በመደቀን ቤታቸውን የጦር አውድማ
ለማድረግ የመረጡት ጄኔራል አማን ራሳቸው ናቸው::>>
source: facebook
https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/11/04/91/
No comments:
Post a Comment