Wednesday, November 13, 2013

የጎሽ ስትራተጂ’!


አሁንም አንዳንድ ካድሬዎች የሳውዲ መንግስት በዜጎቻችን ላይ እየፈፀመው ያለ በደል ተቃውመን ስንፅፍ እየተቃወሙ ነው። መንግስትን ስንተች እነሱም እየተቹን ነው (መንግስትን ደግፈው)። የገዢው ፓርቲ አባል መሆን ሁሉም ተግባሩ በጭፍን መደገፍ ማለት አይደለም። የተቃዋሚ አባል መሆንም ሁሉም የገዢው ፓርቲ ተግባር መቃወም ማለት አይደለም።
መደገፍ ያለበት ተግባር መደገፍ፣ መቃወም ያለብን ተግባር ደግሞ መቃወም አለብን። በተቻለ መጠን የምንደግፍውን ፓርቲ በሐሳብ ለመደገፍ እንሞክር። የፓርቲው ተግባር ከህዝብና ሀገር ጥቅም ጋር የሚቃረን ከሆነ ግን ከፓርቲው ይልቅ የህዝብና ሀገር ጥቅም ማስቀደም ይኖርብናል። መቆም ያለብን ከህዝብ ጎን እንጂ ከፓርቲ ጋር አይደለም፤ የመጨረሻ ግባችን የህዝብ ደህንነት መጠበቅ ነውና።
መንግስት የህዝብ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ነፀብራቅ ነው። ህዝቡ ዓቅምና ግንዛቤ ከሌለው መንግስት የፈለገውን ማድረግ ይችላል። የመንግስትን ተግባር ለመቆጣጠር ህዝቡ ለመብቱ መነሳትና መተባበር አለበት። በሌሎች ላይ የሚፈፀመው ግፍ በኛ ላይ የተፈፀመውን ያህል ሊሰማን ይገባል። የሌሎች ችግር እንደራሳችን ችግር ማየት አለብን፤ ምክንያቱም ነገ በኛ ላይ ሊፈፀም ይችላል። በኛ ላይ በደል ስላልተፈፀመ ብቻ በሌሎች እየተፈፀመ እያየን ዝምታን ከመረጥን በደሉ በኛ ላይ ሲፈፀም ሌሎች ወገኖች ዝም ሲሉን በዝምታ ምክንያት በሌሎች ላይ ግፍ መፈፀማችን እንገነዘባለን።
ኢትዮዽያን የምንከተለው በደልን (ግፍ) የመከላከል መንገድ ‘የጎሽ ስትራተጂ’ (Buffalo Strategy) ነው። አንበሳ (lion) ጎሽን (buffalo) እያደነ ይበላል። ጎሽ (ጎሾች) ከአንበሳ መንጋ ለማምለጥ የሚከተሉት መንገድ መሮጥ ነው። ግን ሁሉም ጎሾች ሮጠው አያመልጡም። ሁሉም ጎሾች ደግሞ በአንዴ አይያዙም። ምክንያቱም አንበሶቹ ዒላማቸው አንድ ጎሽ ነው። ምክንያቱም ለግዜው አንድ ጎሽ ለአንበሶቹ ምግብ ይበቃል። አንበሶቹ ታድያ ወደ ኋላ የቀረውን ጎሽ ይይዙና ይቀራሉ። በዚሁ መንገድ ሌሎች ጎሾች ያመልጣሉ። ጎሾቹ ከጠላት የሚያመልጡበት መንገድ ለግዜው አንድ ጎሽ ለጠላት በመስጠት ነው። ይህ መፍትሔ ግዝያዊ ነው። ለግዜው አንድ እየሰጡ አንድ በአንድ ያልቃሉ። ስትራተጂያቸው ከጠላት ለማምለጥ የሚረዳ ሳይሆን እነሱ ነገ እንዲበሉ ዛሬ አንድ ወገናቸው መስዋእት ያደርጋሉ።
የኢትዮዽያውያን መንገድም የጎሽ መንገድ ነው። ችግሩ እኛ ላይ እስኪደርስ ከጠበቅን አንድ በአንድ ነው የምናልቀው። ችግሮቻችን ለመፍታት መተባበር አለብን።
ዛሬ በሳውዲ የሚኖሩ ዜጎቻችን ሲሰቃዩ የህወሓት መሪዎች ግን መቐለ ዉስጥ የሙዚቃ ባንድ ጠርተው ተማሪዎች ከየትምህርትቤታቸው በአስገዳች በህወሓት የድጋፍ ሰልፍ እንዲገኙ በማዘዝ የከተማው ፒያሳ ዳንስቤት አስመስለዉት አመሹ። በብዙ የትግራይ አከባቢዎች የህወሓት የድጋፍ ሰልፍ ጠርተው ስለ ፖለቲካቸው ይዘፍናሉ። ህዝብ ግን ይሰቃያል።
መንቃት አለብን። የሌሎች ችግር እንደራሳችን ችግር እንይ። የህዝብ ደህንነት ከፖለቲካ በላይ ነው።

 https://www.clickhabesh.com/~clickha1/?p=103640

No comments:

Post a Comment