Wednesday, November 6, 2013

የሚኒሶታው ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ


“በተለያዩ ውዥንብሮች የተነሣ ግራ ለተጋቡት ምእመናን መልስ ለመስጠት የሁለት ቀናት ጉባኤ አዘጋጅተናል”

- በቤዛ-ኵሉ ሰንበት ትምህርት ቤት

“የቤተክርስቲያናችንን ሰላምና አንድነት መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው!!”

- ለሰላምና ለአንድነት ከቆሙ ምእመናን

(ዘ-ሐበሻ) የሚኒሶታው ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ በረድ ብሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ደግሞ እንደአዲስ ጥያቄዎች በመነሳት ጉዳዩ እንደገና እየተቀጣጠለ ይገኛል። ደብሩ “በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ስር መጠቃለል አለበት” በሚሉ እንዲሁም “እርቀ ሰላም እስኪወርድ ድረስ በገለልተኛነት መቆየት አለብን” በሚሉ ወገኖች ሁለት ሃሳቦች ተነስተው ከፍተኛ ክርክር ሲደረግባቸው ቆይቷል። ክርክሩ ለምርጫ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ይህ የሃሳብ ልዩነት ቤተክርስቲያኒቷን ሊበታትናት ይችላል በሚል በሽማግሌዎች ይህ ጥያቄ ለጊዜው እንዳይነሳ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። ሆኖም ግን አሁን እንደአዲስ በሁለቱም ወገኖች የቆሙ ምእመናን የየራሳቸውን ሃሳብ ለሕዝብ ለማሳወቅ የተለያዩ ስብሰባዎችን በመጥራት፣ ወረቀት በመበተን፣ ኢሜይል በመላላክ ሃሳባቸው ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ዘ-ሐበሻ እንደነፃ ሚድያነቷ የሁለቱንም ወገኖች ሃሳብ ስታስተናግድ ቆይታለች። እነሆ አሁንም ከቤዛ ኩሉ የሰንበት ተማሪዎች “በተለያዩ ውዥንብሮች የተነሣ ግራ ለተጋቡት ምእመናን መልስ ለመስጠት የሁለት ቀናት ጉባኤ አዘጋጅተናል” በሚል የደረሰንን መግለጫ እና “ደብራችን እንደ ለንደኗ ጽዮን ማርያም ቤ/ክ እንድትሆንብን አንፈልግም” ከሚሉት ለሰላምና ለአንድነት ከቆሙ ምእመናን የደረሱንን ሁለት መልዕክቶች በየተራ አስተናግደናል። ወደፊትም የትኛውንም ሃሳብ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ቃል ዝግጁ ነን።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ክብርት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” (ጸሎተ ሃይማኖት)

በቤዛ-ኵሉ ሰንበት ትምህርት ቤት የተዘጋጀ የሁለት ቀናት መንፈሳዊ ጉባኤ።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየቦታው በፈተና ላይ በመገኘትዋ ከፈተናው ለማምለጥ፣ ችግሩን ለመቅረፍ፣ አንድነትዋን ለመጠበቅ፣ ሃይማኖቷን አስከብራ እንድትኖር ለማድረግ እና ሌሎችም የጎደሉ ነገሮችን አሟልታ ለመራመድ እንዲቻላት የልጆቿ አብሮ መሥራት እና ለመነጋገር መዘጋጀት ከሁሉ በላይ ስፍራ ሊሰጠው የሚገባበት ጊዜ ነው። አሁንም ሰንበት ትምህርት ቤታችን “ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ክብርት ቤተክርስቲያን እናምናለን” (ጸሎተ ሃይማኖት) በሚል ርዕስ ቅዳሜ ጥቅምት ፴ እና እሁድ ኅዳር ፩/ ፳፻፮ ዓ.ም. (November 9th and 10th) መንፈሳዊ ጉባኤ አዘጋጅቷል። በዚህ ጉባዔም ሦስት አበይት ጉዳዮች በተጋባዥ መምህር እና በደብራችን ካህናት በሰፊው ትምህርት ይሰጥባቸዋል። church minneapolis
፩ኛ- የቤተ ክርስቲያን አንድነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ፤
በሃይማኖትና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንፃር አንድነት እንዴት መታየት እንዳለበትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆችም በዚህ ፈታኝ ሰዓት በአንድነት መቆማቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይነገርበታል።
፪ኛ- በተለያዩ ውዥንብሮች የተነሣ ግራ ለተጋቡት ምእመናን መልስ ለመስጠት፤
ምእመናኑ በማወቅም ባለማወቅም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በሚሰሟቸው የተለያዩ ጉዳዮች የተነሣ ስለተደናገሩና እና ውዥንብር ውስጥም ስለገቡ የአንድነቱን አስፈላጊነት እና የሰንበት ትምህርት ቤቱ አካሄድም ፍጹም ሃይማኖታዊ እና ሥርዓቱን የጠበቀ መሆኑን ለመግለጽ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችም በውስጣቸው ያላቸውን ፍርሃት ማስወገድ እንዲችሉ ያለውን እውነታ በመናገር ለጥያቄአቸው መልስ ለመስጠት ነው።
፫ኛ- ስለ ቀደመችውና ስለ አንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ትምህርት እንዲሰጥ፤
ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል ትምህርት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የወንጌል አደራ ያለምንም ቅድመ ዝግጅት እንዲያስተምሩ እና ምእመናን የተለያዩበትን ጉዳይም በትምህርት ማቀራረብ ስለሚቻል እና የተወሳሰበ መስሎ የሚታየውን ነገር ሁሉ ቃለ እግዚአብሔር ስለሚያስተካክለው አዘውትሮ በአንድነቱ ዙሪያ ትምህርቱ እንዲሰጥ ነው። በተጨማሪም በሐሳብ ልዩነት መካከል የቤተ ክርስቲያን አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር ሁላችን እጅ ለእጅ ተያይዘን የጋራ መፍትሔ የምናገኝበትን መንገድ ለማመላከት ነው።
ተጋባዥ እንግዶች: መምህር ቀሲስ ሱራፌል ወንድሙ
ዘማሪት ፋንቱ ወልዴ
እንዲሁም የደብሩ መምህራንና ካህናት
Date: Saturday November 9th 5:00 PM- 9:00 PM
Sunday November 10th 5:00 PM-9:00 PM
Address: Betel Evangelical Church
4120 17th Ave S Minneapolis MN 55407
—————————————————————————————————————

ሚኒሶታ ደ/ሰ/መ/ኢ/ኦ/ተ/ቤ የሰላምና የአንድነት ደብር

በስመ ሥላሴ አሐዱ አምላክ። አሜን !

” የቤተክርስቲያናችንን ሰላምና አንድነት መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው !!” ለሰላምና ለአንድነት ከቆሙ ምእመናን

deb
እንደሚታወቀው ይህች ሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤ ላለፉት 20 አመታት በስደት ለምንገኘው ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች። ቤተክርስቲያናችን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተመሰረተችና የምትመራ፣ ሐዋሪያዊ አገልግሎት የምታበረክት የእኛን የልጆቿን የምእመናንን መንፈሳዊ ረሃባችንን የምታረካልን፣ልጆቻችንን የምናስጠምቅባት፣ጋብቻ የምንመሰርትባት፣በእግዚአብሔር ፈቃድም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምንቀበልባት ልዩና የጋራ ቤታችን ናት። በተጨማሪም በችግራችን ጊዜ የምንጽናናባት፣ በደስታችንም ፈጣሪን የምናመሰግንባት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅስድት ሃገራችን ኢትዮጵያን የምናስታውስባትና ከወዳጅ ዘመድ ጋርም የምንገናኝባት ልዩ መንፈሳዊ ማዕከል ናት ። ይህች ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ እምነት የሚፈጸምባት ቅድስት መካን ያለማጋነን በውጪው አለም ከሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያናት መካከል እጅግ የሚያስደስትና ኦርቶዶክሳዊ እምነትንና ቀኖናን የጠበቀ ሰፊ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥባት ታላቅ ደብር ናት። ይሁን እንጂ ለመልካም ሥራ ጠላት የሆነ ዲያቢሎስ የዚህችን ታላቅ ቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ለመበጥበት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ የቆየ መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው።ነገር ግን ከሁሉም በላይና ከሁሉም የሚበልጠው የቤተክርስቲያችን ሰላምና አንድነት መጠበቅ ነው በሚለው ምእመን ያለግብሯ ስም እየሰጡ ከሚወነጅሏትና ሰላሟን ለማደፍረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲያሴሩ ከነበሩ አካላት ተከላክሎ እዚህ አሁን ያለችበት ታላቅ ደረጃ ላይ እንድትደርስ አስችሏታል።
ፈተና ለክርስቲያኖች ዘወትር የሚቀርብ አንድም የሰይጣን አንድም የምኞት ወይም የቀቢጸ ተስፋ ውጤት ነው። እንደ ክርስቲያን ይህ ሊሆን ግድ እንደሆነ ካወቅን ዋናው ቁም ነገር የሚደርስብንን ፈተና እንደ አመጣጡ በጋራ መመለስና በአሸናፊነት መውጣት ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው በአባቶቻችን ጳጳሳት መካከል በመንግስት ጣልቃገብነት በተፈጠረው መለያየትና ይህንንም ተከትሎ በተከሰተው የሁለት ፓተርያረኮች በአንድ ወቅት በቤተክርስቲያኗ መኖር ምክንያት በውጪው ዓለም የሚገኙ አብያተክርስቲያናት ይህኛውን ወይም ያኛውን ፓትርያርክ ወግኖ በቅዳሴ ጊዜ ስም ለመጥራት አስቸጋሪ መሆኑን በማመን የቤተክርስቲያኗን እምነትና ቀኖና ሳያጎድሉ አገልግሎት እየሰጡ የስም መጥራቱን ጉዳይ ግን ከላይ ያሉት አባቶች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሰላምና አንድነትን እስኪያመጡ ድረስ ወይንም እንደቤተክርስቲያኗ ህግ በአንድ ዘመን አንድ ፓትርያርክ ብቻ እስኪሆን ድረስ ስም ከመጥራት ተቆጥበው ምእመናንን እያገለገሉ እስካሁን ድረስ ይገኛሉ። ይህም እንደክርስትና ትምህርት፣ እንደቤተክርስቲያኗ ህግና ታሪክ ትክክለኛ አቋም ነው። አንዳንዶች ግን እነርሱ የደገፉትን የፖለቲካ ኃይል ለዛውም በኢትዮጵያ እና በታላቋ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ መጠነ ሠፊ ጥፋት ያደረሰን ቡድንና ከእርሱ ጋር የሚሞዳሞዱ ‘ጳጳሳትን’ ባለመደገፋችን ከእምነት ሥርዓት የወጣን አድርገው በመክሰስ ሰላማችንን ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ ሳይቃጠል በቅጠል ልንላቸው ይገባል። ፍትህ መንፈሳዊ(ፍትሐ-ነገሥት)ስለ ጳጳሳት ሹመት በተናገረበት አንቀጽ እንዲህ ይላል።
feteh negest
የቤተክርስቲያኗ ህግ ይህ ሆኖ ሳለና ለችግሩ መፍትሔ ሰጥቶ አንድነትንና ሰላምን ለማምጣት ከመትጋት ይልቅ በጥፋት ላይ ጥፋት በመፈጸም ትልቋን ቤተክርስቲያናችንን በታሪክ ካጋጠማት ፈተና ሁሉ የከፋ አደጋ ላይ እንድትወድቅ አድርገዋታል። ይህንን ችግር ለመፍታትም ችግሩ ያሳሰባቸው አባቶች ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ችግሩን አስቀድሞ የፈጠረው አካል እርቁ ከፍጻሜ እንዳይደርስ እጅግ አሳዛኝ እርምጃ በመውሰድ የእርቅና የሰላም ሒደቱን በማኮላሸት የሚሊዮኖችን ተስፋ ያጨለመ ታሪክ የማይረሰው በደል በቤተክርስቲያናችንና በአማኞቿ ላይ መፈጸሙ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም የራሳቸው ክፋት ሳይበቃቸው በሰላምና በአንድነት የሚኖሩትን በውጪው አለም የሚገኙ ታላላቅ አብያተክርስቲያናትን የዚህ አፍራሽ ሥራቸው ተባባሪ ለማድረግ፣ ለመከፋፈልና ለማወክ ያላሰለሰ ስራዎች በተለያየ መንገድ ሲፈጸሙ ይስተዋላል። በዚህም በርካተ አብያተክርስቲያናት በዚህ ጉዳይ እዲከፋፈሉና ሰላማቸው እንዲታወክ ተደርጓል።
በቅርቡ የዚህ አፍራሽ እንቅስቃሴ ሰለባ የሆነቸው የለንደን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስ አይነተኛ አብነት ነች። አሁን ደግሞ ይህችን ታላቅ የሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያናችንን ለመከፋፈልና ለማፍረስ ከውስጥ ባሉ አንዳንድ ጥቅመኞችና ጥቂት የዋሃን ምእመናን አማካይነት አፍራሽና ሰላም ነሺ አሳዛኝ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። እኛ ግንሐዋሪያወ እንዳስተማረን ከእንደነዚህ ያሉ ሰዎች ፈቀቅ ልንል ይገባናል። ‘‘ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ።ይህን አፍራሽ ተልእኮ ለማስቆምና የቤተክርስቲያናችንን አንድነትና ሰላም ጠብቆ ለመጓዝ ይቻል ዘንድ አንድነትንና ሰላም ከሚሹ ወገኖች ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም ሴት የላከው…. እንዲሉ የዚይህች ቤተክርስቲያን አንድነቷ ተናግቶና ሰላሟ ፈርሶ ካላዩ እረፍት የማያገኙ አካላት አንድነታችንንና ሰላማችንን ለመንሳት ቆርጠው የተነሱ ስለሆነ በዚህች ቤተክርስቲያን የምንገለገል ምእመናን ሁሉ ቤተክርስቲያኔ ሆይ ከጎንሽ አለንልሽ የምንልበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ተገንዝበን ይህን አፍራሽ ሴራ ለማስቆም በአንድነት መነሳት ይኖርብናል። እኛ የአፕሎስ ወይንም የጳውሎስ ወይንም የኬፋ ሳንሆን የሁሉ አለቃ የሆነው የሊቀ ካህናት የኢየሱስ ክርስቶስ ነን።
እንደቤተክርስቲያናችን ባህል/ልምድ የአባቶችን ስም በጸሎት ጊዜ ለመጥራት መጀመሪያ እነሱ ሰላምና እርቅ ማድረግ ይገባቸዋል። ያን አድርገው እስከምናይ ድረስ ግን እንደክርስቲያን አንደኛውን ወገን ብቻ ለይተን ልንደግፍና (ለዛውም ሰላምና አንድነት እዳይመጣ ያደረገውን) ሌላኛውን ደግሞ ልናወግዝ አይገባንም።ኃይማኖታችንን መጠበቅና አንድንነታችን እንዳይናጋ ዘብ መቆም ግን የሁላችንም ድርሻ ነው። “…. እንግዲህ በሰማያት ያለ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ።’’ ዕብ.4፥13-14 የሚለውን ምክር ማስተዋል ይገባል። አንድነትንና ሰላምን ስለሚያናጉ ሰዎችም መጽሐፍ እንዲህ ይለናል፦ ‘‘ እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል። እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤ እነርሱ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና። እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው። እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። ’’ ይሁዳ መልዕ. ፩፥፲፮-፳፪
ወሰወብሐት ለእግዚአብሔር ! መድኃኔዓለም የቤቱን ሰላምና የእኛንም አንድነት ይጠብቅ ። አሜን!

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/8955

No comments:

Post a Comment