Tuesday, July 30, 2013

ፍርድ ቤቱ በእነ መላኩ ፈንታና ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ መዝገቦች በተጠረጠሩ 19 ግለሰቦች ላይ ለ8ኛ ጊዜ የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 22 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት በእነ መላኩ ፈንታ እና ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ መዝገቦች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉ 19 ግለሰቦች ላይ ለ8ኛ ጊዜ የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ።
የፈዴራሉ ስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮምሽን የምርመራ ቡድን በመዝገቦቹ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉ 19 ግለሰቦች ላይ የካሄደውን የምርመራ ሂደት ለፍርድ ቤቱ ዛሬ አቅርቧል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች የፌደራሉ ስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በየጊዜው የሚያቀርበው የምርመራ ሂደት ተመሳሳይነት ያለው ነው ሲሉ ፥ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ መዝገቡን በመመርመር ሂደቱ በየጊዜው መሻሻል እያሳየ ነው ብሏል።

ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡ ተጠርጣሪዎች በሁለት መዝገብ የተካተቱ 19 ግለሰቦች ሲሆኑ ፥ የቀድሞው የኢትዮዽያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ በእርሳቸው በተሰየመው መዝገብ የተጠቀሱት አቶ እሸቱ ወልደሰማያት ፣ አቶ ማርክነህ አለማየሁ ፣ አቶ አስመላሽ ወልደማርያም ፣ አቶ ከተማ ከበደ ፣ አቶ ስማቸው ከበደ ፣ ዶክተር ፍቅሩ መሃሩ እና የአቶ ማርክነህ እህት ወይዘሮ ትእግስት አለማየሁ ናቸው ።

አቶ መላኩ በሚሌ ፍተሻ ጣቢያ ህገ ወጥ በሆነ ትእዛዝ ሳይፈተሹ ያለፉና ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ እቃዎችን አስመልክቶ እጃቸው ነበረበት በሚል በተጠረጠሩበት ወንጀል ፥ እየተካሄደ ባለው ምርመራ ሂደቱ ወደፊት እየተጓዘ መሆኑን የምርመራ ቡድኑ ገልጿል ።

ቡድኑ ያከናወናቸው ተግባራት

በመዝገቡ ከተካተቱ ስምንት ተጠርጣሪዎች መካከል ከአቶ ከተማ ከበደ ፣ አቶ ስማቸው ከበደ እና ወይዘሮ ትእግስት አለማየሁ ውጪ ፥ የተቀሩት በህገ ወጥ መንገድ በጅምላ የተቋረጡ መዝገቦች እና ያአግባብ የታክስ ኦዲት በመከለስ ተግባር የመንግስት ገቢ ዝቅ እንዲል ማድረግ የሚለው ሌላው የምርመራ ቡደኑ እድገት ያሳየ ምርመራ ካካሄደባቸው ወንጀሎች ተጠቃሽ ነው።

መላኩ ፈንታን ጨምሮ በመዝገቡ ተካተው የነበሩ የመንግስት ሰራተኞች ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አካብተዋል በሚል በየተረጠሩበት ወንጀል ፥ የምርመራ ቡድኑ በተሰጠው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የሃብት ጥናት መረጃ ማሰባሰቡንም አስታውቋል።

ቡድኑ ተያያዥነት ያላቸው የምርመራ ስራዎችን ማከናወኑን እና ለቀሪ ምርመራ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ በማለት የጠየቀ ሲሆን ፥ የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላችው የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄው በዝቷል፤ ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢለቀቁ የነበራቸው ሃላፊነት አሁን ከእነርሱ ጋር ስለሌለ እንደተባለው ምስክሮችን አያስፈራሩም፣ ማስረጃም አያጠፉም፤ የሚሉና ሌሎችንም አቅርበዋል።

ከተጠርጣሪዎች አቶ ማርክነህ ጠበቃቸው ሳይመጡ በመቅረታቸው በግላቸው በጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ ምንም የማቀርበው የመከራከሪያ ነጥብ የለኝም ፍርድቤቱ ራሱ የመሰለውን ትእዛዝ ይስጥ ፤ ነገር ግን የዋስትና መብቴ ይከበርልኝ ሲሉ አመልከተዋል።

የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን በበኩሉ ከተጠርጣሪዎች እና ከጠበቆቻቸው ዘንድ በዋስትና ጥያቄው ላይና የተነሳው የተቃውሞ ሃሳብ ፥ የወንጀሉ ውስብስብነት እና ከባድነት ካልሆነ በስተቀር፤ ቡድኑ በየጊዜው በልዩ ትኩረት በትጋት እየሰራ መሆኑንና ተጓተተ ለተባለው  የሁለት ኩባንያዎች የኦዲት ስራም እንዲሁም መስክ የሄደው የምርመራ ቡድን ለሁለተኛ ጊዜ የምርመራ ስራ ማካሄዱን በምሳሌነት አንስቷል።

ግራ ቀኙን የመረመረው ችሎቱ ቡድኑ ቀሪ የምርመራ ስራዎች እንዳሉት በመገንዘብ የተጨማሪ 10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ የምርመራ ውጤቱን ለመጠባበቀ ለነሃሴ 2, 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በሌላኛው እና በአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ስም በሚጠራው መዝገብ ደግሞ የምርመራ ቡድኑ በኢትዮዽያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በነበሩት አቶ ገብረዋህድ አቶ በላቸው በየነ እና አቶ ጥሩነህ በርታ ፥ በህገ ወጥ መንገድ በጅምላ አቋርጠውታል በሚል በተጠረጠሩበት ወንጀል ላይ በተፈቀደው 10 የምርመራ ቀን ውስጥ የሁለት ምስክሮችን ቃል መቀበል እና የሰነድ ማስረጃ የማሰባሰብ ስራዎችን አከናውኛለሁ ብሏል ።

ሁሉም ተጠርጣሪዎች በመመሳጠር የመንግስት ቀረጥና ታከስ እንዳይሰበሰብ በማድረግ ያለአግባብ ተጠቅመዋል በተባለው የሙስና ወንጀል ላይ ፥ በተመሳሳይ የሰውና የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡን አስረድቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንግስት ሲሚንቶ ያለቀረጥ በአስመጪዎቸ መጥቶ ለታለመለት ስራ እንዲውል ፍቃድ የሚሰጥ ሲሆን ፥ አቶ ነጋ ያለቀረጥ እንዲገባ የተደረገውን ሲሚንቶ ከአስመጪው ኮንትራት በመውሰድ አሁን ኮሚሽኑ እየደረስኩበት ነው ባለው የምርመራ ሂደት አቶ ነጋ ከባለሰልጣኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ሲሚንቶውን እያጓጓዙ በተለያዩ ሱቆች አራግፈዋል ብሏል።

ቡድኑ ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ወደ አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት በማምራት ስሚንቶው ለታለመለት አላማ መዋል አለመዋሉን የተመለከተ መረጃ ኮፒ አድርጎ መውሰዱን ያመለከተ ሲሆን ፥ ለቤቶች ልማት ይገባል ተብሎ በየሱቆች ለገባው ሲሚንቶ ከቀረጥ ጋር በተያያዘ ከባለስልጣኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተወልደ ብስራት እና አሞኘ ታገለ ተጠያቂ ተደርገዋል።

ቡድኑ በዚህ መዝገብ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ እና አቶ ጥሩነህ በርታ ላይ የመንግስት ግብር የሚሰውሩ ግብር ከፋዮችን ማጋለጥ ይቻል ዘንድ በተዘረጋው ስርአት መሰረት ፥ ለጠቋሚዎች የሚከፈል አበል ጠቋሚ ሳይኖር ጠቋሚ እንዳለ ተደርጎ ለግል ጥቅማቸው አውለውታል በተባለው ከፍተኛ ገንዘብ ምዝበራ ዙሪያ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡን አስታውቋል።

በአጠቀላይ በዚህ መዝገብ የምርመራ ቡድኑ ከ27 የሚልቁ የምስክሮችን ቃል ሲቀበል ፥ 26 የሚሆኑ ምስክሮች ይቀሩኛል ብሏል።

ቀሪ ተግባራትን ለማከናወንም ቡድኑ ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ያስፈልገኛል በማለት ሲጠይቅ ፥ የግራ ቀኙን የመረመረው ችሎቱ ቀሪ የምርመራ ስራዎች እንዳሉ ተገነዘቢያለው በማለት  የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ለ8ኛ ግዜ በመፍቀድ ፥ የምርመራ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለነሃሴ 2 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።



በጥላሁን ካሳ



source...http://www.fanabc.com/index.php?option=com_content&view=article&id=4776%3A---------19---8----&catid=102%3Aslide


No comments:

Post a Comment