Sunday, July 21, 2013

አባቱን አያውቅም አያቱን ይጠይቃል!! ለጆሀር

አባቱን አያውቅም አያቱን ይጠይቃል!! ለጆሀር

ስለ ጆሀር ብዙ ነገር ተጽፎ በማህበራዊ ድረ ገጾችና የጡመራ ደሮች ተጽፎ አንብቢያለው፡፡ አንድ ወዳጄ ፌስ ቡክ ላይ ‹‹ስለ ጆሀር ምን አስተያዬት አለህ!›› አለኝ፡፡ እኔም ቪዲዮውን እንዳላየሁትና አስተያየት መስጠት እንደሚከብደኝ ነገርኩት፡፡ ይህ ወዳጄ ቪዲዮውን ‹‹ሸር›› አድርጎልኝ ደጋግሜ አዳመጥኩት፡፡
እኔ በጆሀር ንግግርም ፌስ ቡክ ላይ አስተያዬት በሚሰጡ ሰዎችም እኩል አዝኛለሁ፡፡ ጆሀር ለክርስቲያኖችና ኦሮሞ ላልሆኑ ዘውጌ ማህበረሰባት ያለውን ጥላቻ እኩል ገልጧል፡፡ ‹‹እኔ ባደግኩበት አካባቢ 99 በመቶ ሙስሊም በመሆኑ ማንም ሰው ደፍሮ አይነናገርም! በፌንጫ አንገቱን ነው የምንለው›› ይላል ለሌላ እምነት ተከታዮች ያለውን የበቀል ስሜት ሲገልጽ፡፡ ጎንደር ላይ ያለው ሙስሊም እንደሱ ‹‹በፌንጫ›› አለማለቱ ሁሉ ያናደደው ይመስላል፡፡
ወጣቱ ፖለቲከኛ ጆሀር ‹‹ኦሮሞና እስልምና ሀይማኖት›› አንድ ነው፡፡ የኦሮምን ህዝብ ትግል መደገፍ የእስልምናን ትግል መደገፍ አንድ አይነት ነው ብሎም ለመደምደም ይሞክራል፡፡ እስልምና በአቢሲኒያ ‹‹እንደ መጤ›› ይቆጠር ነበር፡፡ የአቢሲኒያ ነገስታት ለኦሮሞም ለእስልምናም የነበራቸውን አመለካከት ጥሩ አለመሆኑን በስፋት ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡ በተለይ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በመጣው በፖርተቹጋል ወታደሮች እስልምናን ለማስወጣት በነበረው እንቅስቃሴ የኦሮሞ የመከላከያ ሀይል እንዳሰቀረው አስረግጦ አብራርቷል፡፡
የጆሀር ንግግር ብዙ ህጸጾች እንዳሉበት ማንም ሰው የሚያምን ይመስለኛል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ሀይማኖት ሙሉ በሙሉ እስልምና አለመሆኑን ጆሀር ይክደዋል ብዬ አላምንም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በክርስትና ፣ በእስልምና እና በአካባቢው ባለ የቆየ እምነት (ዋቃ) ያምናል፡፡ ምንም እንኳ በመቶኛ ስሌት መገለጽ አሁን ባልችልም ሁሉም የኦሮሞ ህዝብ አይደለም ሁለት ሶስተኛው እንኳ ሙስሊም ያልሆነን ማህበረሰብ የብሄርና የሀይማትን ትግል አንድ አድርጎ መመልከት ጤነኛ ነው ብየ አላምንም፡፡ አይደለም በኦሮሚያ በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች እንኳ ሀይማኖትንና የብሄር ጭቆናን አንድ አድርጎ ለማየት መሞከር ‹‹ኋላ ቀር›› አስተሳሰብ የሚለው የሚለው ሀረግ የሚገልጸው አይደለም፡፡
ኦቦ ጆሀርን ተቀብሎ መድረኩን የተቆጣጠረው ስሙን የማለውቀው ሰው ከሰማንያው ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ 50 ሚሊዮኑ ሙስሊም አድርገው ሲናገሩ ‹‹ዳታው›› ከየት እንደተገኘ ባለውቅም እኔ ስለማውቃት ኢትዮጵያ እየተናገሩ እንደሆኑ አልገባህ ብሎኝ ነበር፡፡
ያም ሆነ ይህ በዚያ ቤት ላይ የነበረው ስብሰባ በጥላቻ የተሞላ እንደነበር ቪዲዮውን ያዬ ሁሉ ለመገንዘብ ጊዜ አይወስድበትም፡፡
ካንድ ወር በፊት አንዳንድ ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት በካይሮ የኢትዮጵያን ግድብ ግንባታ ተቃውመው ሰልፍ ሲወጡ አቤ ቶክቾው ‹‹ጉድ በል ሰላሌ ኢትዮጵያዊ አይደለህም ተባልክ›› የሚል ጽሁፍ በድረ ገጹ አስነብቦ ነበር፡፡ እናም የነጆሀር ንግግር ሰላማዊ ሰልፍ ከወጡት ሰዎች አስተሳሰብ የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
እኔ ኦሮሞነትና እስልምና ይለያያሉ፣ አማርነትና ክርስትና ይለያያሉ፣ ትግሬነትና ክርስትና ይለያያሉ፣ አፋርነትና እስልምና ይለያያሉ፣ የትኛውንም ዘውግ ከየትኛው ከሀይማት ጋር ማመሳሰል አይቻልም፣ ይህ ማንም ምንም ቢል ሊያሳምነኝ የሚችል ሰው የለም፡፡
በተቃራኒው በግብጽ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰዎችን እና በጆሀርን ንግግር የሚቃወሙ አንዳንድ ጨዋት የጎደለው አስተያዬት የሚሰጡ ሰዎችንም ጽሁፍ ማንበብ ከኦቦው ንግግር እኩል ‹‹አፍራሽ›› አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሰዎች ቀላል አለመሆናቸውን ለማየት አስችሎኛል፡፡ ጆሀር አንድ ግለሰብ ነው፡፡ በምንም መልኩ የኢትዮጵያን የእስልምና እምነት ተከታዮችና የኦሮሞ ማህበረሰባትን ሊወክል ፈጽሞ አይችልም፡፡ አይደለም ጆሀር ሁሉም የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ‹‹ኦሮሞን››፣ በተቃራኒው ሁሉም የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት ‹‹እስልምናን›› መወከል አይችሉም፡፡
ስለዚህ በምን ስሌት እንደሆነ አላውቅም ከሌላ ዘውጌ ብሄረሰባት አካባቢ ያሉ ሰዎች በኦሮሞነትና በእስልምና ላይ ተገቢ ያልሆነ አስተያየት የሚሰጡት፡፡ በርግጥ በሳል አስተያዬት የሚሰጡ የሉም ለማለት አይደለም፡፡ ግን ብዙዎቹ ጽንፍ ይዘው የተጻፉ መሆናቸው አሳዛኝ ነው፡፡
ወደ ርዕሴ ስመለስ ኦቦ ጆሀርን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን አንኳር የታሪክ ፍሰት እንዲህ ላስታውሰው ፈለግኩ፡፡ ጆሀርን ብቻ አይደለም በጆሀር ፍልስፍና የተጠመቁ አጃቢዎቹን ጭምር እንጅ፡፡ በሀይማኖት እና በዘውግ የነበረውን የታሪክ ፍሰት ተጣጥሎ መመልከቱ አስፈላጊ መስሎ ስለታዬኝ ለየቅል እናየዋለን፡፡
1. ኢትዮጵያና ሀይማኖት
በኢትዮጵያ ታሪክ ከጥንት እስከ አለንት ዘመን ድረስ የነበሩ ገዢዎች ከጥቂቶች በቀር ክርስቲያኖች መሆናቸው እውነት ነው፡፡ ይህ ታሪክ በመሆኑ እንጆሀርን ለማስደሰት ሲባል ከፊሉቹ ‹‹የእስልምና እምነት ተከታዮች ነበሩ›› አሊያም ‹‹እኩል በእኩል የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት ነበሩ›› ብሎ ማስተካከል ከቶ የትኛው የታሪክ ምሁር ይቻለዋል!! የሚቻል ቢሆን ኖሮ ‹‹ለፍትሀዊነት›› ሲባል ማድረጉ ባልከፋ ነበር፡፡ በማይቻል ነገር ላይ ጊዜ ማጥፋቱ አስፈላጊ ባለመሆኑ ወደ ሌላው ጉዳይ ልለፍ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስትናን ካስተማራቸው ሰዎች አንዱ የኢትዮጵያዊቷን ንግስት ጃንደረባ ፊሊጶስ የተባለው ሀዋርያ አጠመቀና ወደ ሃገሩ ላከው (ሐዋ 8፡-)፡፡ ምንም እንኳ ይህ የሆነው በ34 ዓ.ም. እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ብሄራዊ ሀይማኖት የመሆን እድል አላገኘም ነበር፡፡
ኢትዮጵያ (የኢትዮጵያ ነገስታት) በ4ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ወይንም በ340 ዓ.ም. አካባቢ ክርስትናን ብሄራዊ ሀይማኖት አድርጋ ከተቀበለች በኋላ ብዙዎቹ ነገስታቶቿ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ነበሩ፡፡ አልፎ አልፎ ከኦርዶክስ ክርስትና እምነት ውጭ የነገሱ ወይም ወደ ሌላ ሀይማኖት የተቀየሩ ቢኖሩም በታሪክ በጥሩ መልኩ የሚወሱ አይደሉም (በጥሩ ላለመነሳታቸው ብዙ ምክንያት ሊኖር ይችላል፡፡ የታሪክ ጸሀፊዎቹ ክርስቲያን ስለሆኑ የሚያዩት ከራሳቸው ጥቅም አንጻር መሆኑ፣ በርግጥም ጥፋተኛ ስለሆኑ፣ … ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ችግር ማጥናት እና እውነተኛን ነገር ማሳወቅ/ ማወቅ የአንድ ጨዋ ሰው ግብሩ ነው)፡፡
በሰባተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ነጃሽ የሚባል የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ እንደነገሰ ቢወራም ይህን የሚያጠናክር ከወሬ የዘለለ የታሪክ ድርሳን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ እርግጥ ነው በ622 ዓ.ም. አካባቢ መሀመድ እስልምናን ለአካባቢው ቋሪሾች ሲሰብክ ‹‹አይንህን ላፈር›› ሲሉት በዘመኑ ለነበረው ኢትዮጵያዊ ንጉስ ቤተሰቦቹን አደራ ሰጠው፡፡ ንጉሱንም እንግዳዎቹን ተቀብሎ አስገድዶ አላስጠመቃቸውም፡፡ ነጻነት ሰጣቸው፡፡ ምንም እንኳ ለስርወ መንግስቱ መዳከምና ጨርሶ መፈራረስ ብሎም የግዘቶቹ ስፋት ማነስ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም፡፡ የአክሱም ስርዎ መንግስት ማክተሚያ ላይ በአስረኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በ980ቹ አካባቢ የነገሰችው የአይሁድ እምነት አራማጇ ዮዲት ስሟ በጥሩ ተነስቶ አያውቅም፡፡ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥላለች፣ የታሪክ መዛግብትን አውድማለች፣ የብዙ ሰው ህይዎት ቀጥፋለች፤…. ብዙ ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሰርታ ከማለፏ የተነሳ ‹‹ዮዲት ጉዲት›› ተባለች (በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ጽንፈኛ አይሁዳዊ እምነት አራማጅ ሊህቅ አለመኖሩ ነው እንጅ ‹የአይሁዳዊነትን› ትግል ደግፉ ብሎ የሚነሳ ሰው ባልጠፋ ነበር)፡፡
በ16ኛው ክፍለ ዘመን የመባቻ አካባቢ አንድ ሃያል ጡንቻማ ሰው ከወደ ምስራቅ በኩል ብቅ አለ፡፡ የአዳሉ ንጉስ ሙሉ ስሙ ግራኝ አህመድ እብን ኢብራሂም አልጋዚ በአጭሩ ደግሞ ግራኝ አህመድ ይባላል፡፡ ከ1522-1540 ዓ.ም. ድረስ አጼውን እያሳደደ ከቆየ በኋላ ገደለው፡፡ ንጉሱም ባለቤታቸውን ‹‹ቀዳማዊት እመቤት›› ሰብለወንጌልን ጋለሞታ፣ ልጃቸውን ገላውዲዮስን ደግሞ እጓለማውታ አድረገው ወደማይቀረው አለም ሄዱ፡፡ አንበሳየም ከዮዲት ጉዲት በላይ ከአገር አገር እየዞረ አብያተ ክርስቲያናትን፣ የታሪክ መጽሀፍትን፣ ቅርሶችን… ወዘተ ከሚገበው በላይ አወደመ፡፡ ብዙ ክርስቲያኖችን አሰለመ፤ አንሰልምም፣ ብለው የተቃወሙት ደግሞ ገድላቸው ያልተጻፉ ሰመዕታት ሆነው አለፉ፡፡ እልፍ አዕላፋት ነፍሳት አለቁ፡፡ (ከዚህ ላይ ጆሀር ከፖርቱጋል የመጡ ወታደሮች በእስልምና ላይ ከአገር ለማስዎጣት ያደረጉትን ጠቅሷል፡፡ ከኦቶማን ቱርክ የመጡትን ወታደሮች በተመሳሳይ ሁኔታ በክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጉዳት ግን መግለጽ አልፈለገም፡፡) በ1543 ዓ.ም. አካባቢ ባይሞት ኖሮ ከዚህም የከፋ እልቂት ሊኖር ይቸል ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ግራኝ አህመድ ቅንጣት ታክል በጎ ምግባር ነበረው ያለ የታሪክ ጸሀፊ የለም:: ወይም ተጽፎ ቢሆንም በክርስቲያኖቹ ነገስታት እንዲጠፋ ተደርጎ ሊሆን ይችላል (የግራኝ አህመድ አስገድዶ ማስለም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ብዙዎቹ ነገስታት አስገድደው ክርስቲያን ያደርጉ ነበርና፡፡ ስለሆነም እሱ ያደረገው ብዙዎቹ ስልጣን ላይ ፊጥ ሲሉ የሚያደርጉትን በመሆኑና በዘመኑ በነበረው አስተሳሰብ መኮነን አለበት አልልም)፡፡
ታሪክ መልኩን እየቀያየረ ይደጋገማል፡፡ በ17ኛ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከ1608 – 1632 ዓ.ም በኢትዮጵያ የነገሰው ንጉስ አጼ ሱስንዮስ ይባላል፡፡
የንጉሱ ዜና መዋልዕ እንደሚያስረዳው ንጉሱ ብዞ ጊዜያቸውን ያሳለፉት ከኦሮሞች ጋር በመሆኑ ከብሀረሰቡ በርካታ መልካም ሥብዕናንና ጦረኝነትን ተምረዋል፡፡ ንጉሱ በመጨረሻ የንግስና ዘመናቸው ካቶሊክን አምነው ተቀበሉ፡፡ ምን ይኸ ብቻ፤ ብሄራዊ ሀይማኖት እንዲሆን አወጁ፡፡ አይሆንም ያሉ መኳንንቶች ተቀሉ፤ ተሰየፉ፡፡ ህዝብ እርስ በእርሱ ተጨፋጨፈ፡፡ ኢትዮጵያችን እንደለመደችው በልጆቿ ደም ታጠበች፡፡ እማ ሙዝ/ ፍቅርተ ክርስቶስ የተባለች ጻድቅ ሰማዕት የሆነችው በዚህ ዘመን ነበር፡፡ /ገድለ ፍቅርተ ክርስቶስ መመልከት ይቻላል፡፡/ በመጨረሻ የንጉሱ ምላስ አርባ ክንድ ወደ ውጭ ተጎልጉሎ ወጣ፡፡ የንጉሱ ልጅ አቤቶ ፋሲል እንዲህ የሚል አዋጅ አወጀ፡፡
‹‹የሮም ሀይማት ይርከስ፣ የእስክንድር ሀይማኖት ትመለስ፣
ሱስንዮስ ይፍለስ፣ ፋሲል ይንገስ፡፡››
ይቀጥላል…፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ እምየ ምኒልክ ይታመማሉ፡፡ በ1908 ዓ.ም አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ የሚተካ ወንድ ልጅ አልነበራቸውም፡፡ የሸዋ መኳንንት ተጠበቡ፡፡ ከሞታቸው በኋላ የራስ ሚካኤልን ልጅ ወይም የቀድሞ የወሎውን ራስ አሊ ልጅ ልጅ ኢያሱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት፡፡ ልጅ ኢያሱ በአንድ በኩል ገና ሩጦ ያልጨረሰ ልጅ በመሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ በሀይማኖትና በብረሰባት ላይ ያለው አመለካከት ከሸዋ መኳንንት ፍላጎት ጋ ሊገጥም አልቻለም፡፡ ልጅ ኢያሱ ከክርስቲያኑም ከእስላሙም፣ ከአማራውም፣ ከኦሮሞውም፣ ከሶማሌውም ‹‹የሴት ወዳጅ›› እየያዘ በጋብቻ መልክ አንድነትን ለመፍጠር ያቀደው ሳይሳካ በነገሰ በሶስተኛ አመቱ በሌለበት ከዙፋኑ ተነሳ፡፡
2. ኢትዮጵያዊ ብሄረሰቦች
ኢትዮጵያችን ብዙ ቋንቋ ተናጋሪና ብዙ ባህል ያላቸውን ህዝቦች የያዘች አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ለልማቷም ለኋላ ቀርነቷም ሁሉም እኩል ሀላፊነት ይሸከማሉ ባይ ነኝ፡፡ አንዱ ሲያቀና ሌላው ሲያበላሽ፣ አሊያም ዝም ብሎ ሲመለከት፣ አንዱ አንዱን ሲያጠቃ የኖሩ ህዝቦችን የያዘች ሀገር ናት፡፡
አንዱ ብሄረሰብ ከየመን መጣ ሌላው ከደቡብ ምስራቅ አፍሪካ ጫፍ መጣ፣ አንዱ ቀድሞ ገባ ሌላው ዘግይቶ መጣ ለኢትዮጵያ ሁላችንም ልጆች ነን፡፡ ጆሀር እንደሚለው አንዱ ‹‹ማንነቱን›› በግዴታ የተቀበለው አሊያም ሌላው ደግሞ ‹‹ሰጪ እና ነሽ›› ሰዎች አይደለንም፡፡ መጋጨቱ፣ መፋቀሩ እና መናናቁ የታሪካችን አካል ሆኖ አልፏል፡፡ ግን አሁን ተማርን ያልን ሰዎች የበፊት ክፍተቶችን አርመን ወደ ፊት መጓዝ መቻል አለብን፡፡
ለምሳሌ በታሪክ የነበሩ እንዲህ አይነት ችግሮች አንኳር አንኳር የምንላቸውን ማየት እንችላለን፡፡ በሰለሞናዊውና በአገው ስርወ መንግስታት በነበረው ሽኩቻ ሰለሞናዊውን ስርዎ መንግስት አንኮታኩተው አገዎች የራሳቸውን መንግስት በ11/12ኛው ክፍለ ዘመን ዛግዌ ስርዎ መንግስት መሰረቱ እና ስልጣናቸውን በ1270 አካባቢ ፈጽመው እስኪያጡት ድረስ ተጠቀሙበት፡፡ በጣም ድንቅ የተባለው ‹‹የላሊበላ ኪነ ህንጻ ጥበብ›› የታየውም በዚሁ ዘመን ነበር፡፡ ምን አልባትም ንግስና ወደ አገዎች ባይመጣ ኖሮ ይህን የኪነ ህንጻ ጥበብ ላናውቅ እንችል ሁሉ ይሆን ነበር፡፡
በ15 /16ኛው ክፍለ ዘመን በነበረ የኦሮሞዎች የመስፋፍት እንቅስቃሴ ከሴሞቹ ጋር በነበረ ግጭት ብዙ ነገር እንደወደመ ግልጽ ነው፡፡ አማራዎቹ ይዘውት የነበረውን ለም መሬት በኦሮሞች በመነጠቅ ተራራ ላይ ብቻ እንዲወሰኑ ተገደዱ፡፡ በዚህ በኩል ከየትኛውም ብሄረሰብ የተሸለ ኦሮሞዎች ግዛታቸውን ከደቡብ ኢትዮጵያ እስከ ቀይ ባህር ድረስ ለመስፋፋት ቻሉ፡፡ ለዚህም ምስክር የሚሆኑ ብዙዎቹ ቦታዎች ቀድሞ የነበራቸውን ስያሜ በመተው ኦሮምኛ ስም ኖራቸው (ልክ አሁን ብዙዎቹ ከተሞች አማርኛ ስም አላቸው ተብሎ ወደ ኦሮምኛነት እንደተቀየሩት ሁሉ)፡፡ በተለይ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ሱስንዮስ ድረስ በነበረው ጊዜ በነበረው የግዛት መስፋፋት ኦሮሞዎች እደለኞች ነበሩ፡፡ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ትግራይ ድረስ ገብተው ጥቃት ይፈጽሙ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ምንም እንኳ ድል አንዴ ላንዱ ሌላ ጊዜ ለሌላው ቢሆንም የነበረው የእርስ በእርስ ትርምስ ቀላል አልነበረም፡፡
ከዘመነ መሳፍንት በኋላ በሰሜን በኩል ያሉ ነገስታት ቀድመው መንቃታቸው ምን አልባትም በሌላው ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ጠቅሟቸዋል፡፡ በአጼ ቴዎድሮስ የተጀመረው ሀገር የማቅናት ዘመቻ በአጼ ሚኒሊክ እስኪደመደም ድረስ የደረሰ ችግር አልነበረም ማለት አይቻልም፡፡ ግን ቀደም ብሎ ከነበረው ችግር የባሰ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች እርስ በእርስ ቢናቆሩም በአገር አንድነት ላይ ያላቸው አቋም ግን የሚያስደንቅ ሆኖ ለረጅም ዘመናት ዘልቋል፡፡ የውጭ ሀይል አገር በወረረ ጊዜ ሁሉም እኩል ይፋለማሉ፡፡ በቅርቭ ጊዜ ያነበብኩት ‹‹የሀበሻ ጀብዱ›› የሚል በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የታተመና ከአውሮፓዊ ጸሀፊ የተተረጎመ መጽሀፍ ‹‹ኦሮሞዎቹንና አማራዎቹን›› አገር ወዳድ አርበኞች አድርጎ ስሏቸዋል፡፡ በተለይ አንድ ‹‹አቢቹ›› የተባለን ብላቴና ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ወኔ በመደነቅ ነበር የገለጸው፡፡ ጆሀር የዚህን ልጅ ኢትዮጵያዊነት በምን መልኩ ሊያጣፋው እንደፈለገ አልገባኝም፡፡ አቤ ቶኪቻው ‹‹ጉድ በል ሰላሌ ኢትዮጵያዊ አይደለህም ተባልክ›› ያለው ወዶ አይደለም፡፡
ጆሀር ሞሀመድ እንበልና ሀሳቡ ቢሳካ እሱ አቢሲኒያ እያለ የሚጠራቸው ‹‹አማራዎች››ም ከሌላው ብሄረሰብ የበለጠ አይጎዱም፡፡ አብረው በመሆናቸውም የበለጠ አይጠቀሙም፡፡ ክርስቲያኖቹም በተመሳሳይ፡፡
እንደያው በመጨረሻ ግን ኦቦ ጆሀር በክርስቲያንና ኦርሞ ባልሆኑ ህዝቦች ላያ ያለው ጥላቻ ፈር የለቀቀ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ጥላቻቸው ከመጠን የዘለለ ሲሆን ወደ በቀል ይገባሉ፡፡ በቀሉ ደግሞ መደበቅ አይችልም፡፡ ኦቦ ጆሀር በ1984 ዓ.ም. በደኖ ላይ በነሌንጮ ለታ እና በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስተር የተገደሉ፣ በ1992/93 ወለጋ ጊዳ ኪላሞ ላይ ወደ እሳት የተጣሉትን ህጻናትን፣ በ1999 በጅማ በሻሻ የተሰ ክርስቲያኖችን፣ በቅርቡ ደግሞ በቢኒሻንጉል የተፈናቀሉ አማራዎችን አስብና አንድም የበቀል ስሜትህን አርከሰው አሊያም አንተ እንደፈለግከው፡፡
ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር፡፡
ሰላም


source.... freedom4ethiopian.wordpress.com

No comments:

Post a Comment