እነመላኩ ፈንታ እና በእነ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መዝገቦች ላይ ለ5ኛ ጊዜ የምርመራ ቀጠሮ ተፈቀደ
በአሸናፊ ደምሴ
በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የፌዴራሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምርመራ እያካሄደባቸው በሚገኙት
በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቀድሞ አመራሮችና ነጋዴዎች ተቀዳሚ ሁለት መዝገቦች ስር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ
የመርማሪ ቡድኑ ስራዬን አላጠናቀኩም በማለቱ ለ5ኛ ጊዜ የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜን ፍ/ቤት ፈቀደ።በትናንትናው
ዕለት በእነመላኩ ፈንታ መዝገብ ላይ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የስራ ክንውናቸውን
ለችሎቱ ሪፖርት ያደረጉት የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን አባላት እንደገለፁት፤ 1ኛ፣ 2ኛ፣3ኛ እና 4ኛ ተጠርጣሪዎችን
ጠቅሶ ወደሀገር ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለን ስሚንቶ በህገ ወጥ መንገድ እንዲገባ በማድረጋቸው ክስ
የተመሰረተባቸውን ግለሰቦች የክስ ሂደት ማቋረጥን በተመለከተ ሰነዶች መሰብሰባቸውን ከሶስት ሰዎችም የምስክርነት ቃል
መቀበላቸውን አስረድተዋል። በተለያዩ የጉምሩክ ህጎች ጥሰት ሳቢያ የተመሰረተ የጅምላ ክሶች ማቋረጥን በተመለከተ
በ1ኛ፣ በ2ኛ፣ በ3ኛ፣ በ4ኛ እና በ7ኛ ተጠርጣሪዎች ላይ 20 የሚደርሱ መዝገቦች መሰብሰባቸውና የምስክሮችን ቃል
ስለመቀበላቸው አትቷል። የመርማሪ ቡድኑ አክሎም ከተገቢ በላይ ሀብት ማካበትን አስመልክቶ ከተለያዩ ባንኮችና
ግንኙነት ካላቸው ተቋማት ማስረጃዎችን ስለመሰብሰቡ ጠቁሟል። አክሎም በተጠርጣሪዎች ላይ የምስክሮችን ቃል መቀበልና
ሰነድ ማሰባሰብን እንዲሁም የኦዲት ሪፖርቶችንና የባለሙያ አስተያየቶችን እየሰበሰበ መሆኑን በመጥቀስ የምርመራ
መዝገቡን በማደራጀት ስራ ላይ እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል። ክንውኑን በዝርዝር ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ይቀረኛል ያላቸውን ስራዎችም ዘርዝሯል። በዚህም መሰረት ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕቃዎች
ለታለመላቸው አላማ ስለማዋል ወይም አለመዋላቸው ማጣራት እያደረኩ ነው፤ በህገ-ወጥ መንገድ ወደሀገር ውስጥ የገባ
ስሚንቶዎችን በተመለከተ የስድስት ምስክሮችን ቃል መቀበል፤ በናዝሬት በሚሌና በድሬዳዋ ያሉ ሰነዶችንና የሰው
ምስክሮችን ቃል መቀበል ቀጣይ የቡድኑ ስራ ስለመሆኑ ተቀምጧል። በሌላም በኩል በቦሌ ኤርፖርት አድርገው ወደሀገር
ውስጥ የገቡ ዕቃዎችን በተመለከተ የተቋረጡ ክሶች ላይ የሶስት ምስክሮችን ቃል መቀበል እና ምንጩ ያልታወቀ የሀብት
ክምችትን በተመለከተ የምስክሮችን ቃል እና የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እንደሚቀረው ጠቁሟል። በዚህም ፍ/ቤቱ
ተጨማሪ የ14 ቀናት ተጨማሪ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።ከዚህም ባሻገር መርማሪ ቡድኑ በእነመላኩ ፈንታ መዝገብ
ሶስተኛኛ ተጠርጣሪ ሆነው የቀረቡት የገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ አቃቤ ህግ ምክትል ዳይሬክተር የአቶ መርክነህ
አለማየሁ እህት እንደሆኑ የተነገረላቸውን ወ/ሮ ትዕግስት አለማየሁ በመዝገቡ 10ኛ ተጠርጣሪ አድርጎ አቅርቧል።
ግለሰቧ ከወንድማቸው ጋር በመመሳጠር በሀዋሳ የተንጣለለ ቪላ ቤት ከመገንባታቸውም በተጨማሪ በባንክ ምንጩ ያልታወቀ
ገንዘብ አኑረዋል ሲል ያትታል። በዚህም ሳቢያ ወንድማቸው በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ
ከባንክ አውጥተው ለማሸሽ ሲሞክሩ ደርሼባቸዋለሁ ሲል ያትታል። በተያያዘም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው
በመታየት ላይ በሚገኘው በእነአቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መዝገብ ስር የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ያከናወናቸውን እና
የሚቀሩትን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን የጠየቀ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ ግን
የ10 ቀናት ቀጠሮን ሰጥቷል። በዚህም መዝገብ ውስጥ ሁለት አዳዲስ ተጠርጣሪዎች ተካተው ቀርበዋል። በዚህም መሰረት
የአዳማ ቅርንጫፍ ሰራተኛ የሆኑት አቶ ያለው ዋቆ እና እንጀራ እናቱ ናቸው የተባሉት ወ/ሮ ሽቱ ነጋሽ ተካተውበታል።
ይህም አጠቃላይ የተጠርጣሪዎቹን ቁጥር 63 ያደርሰዋል።በመሆኑም በእነገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መዝገብ ስር ቀሪ
የምስክሮቹን ቃል ለመቀበል እና መዝገቦችን ለማሰባስብ እንዲሁም በአዳማና በሚሌ ፣ በድሬዳዋ የሚደረጉ ምርመራዎችን
ለማጠናቀቅ የ14ቀን ተጨማሪ ጊዜን ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ግን 10 ቀናትን በመፍቀድ ለሐምሌ 12 ቀን 2005 ዓ.ም
ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።በአንፃሩ ደግሞ በእነመላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ስር ለተዘረዘሩት ስምንት ተጠርጣሪዎች የ10
ቀናት ተለዋጭ የምርምራ ጊዜን በመፍቀድ ለሐምሌ 14 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሯል።
source........sendek
No comments:
Post a Comment