ኢትዮጵያ የሀይል አጠቃቀም ፖሊሲዋን እየከለሰች ነው
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 23 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የሀይል አጠቃቀም ፖሊሲ አስራ ዘጠኝ አመታትን አስቆጥሯል ።
ይህ ፖሊሲው እስካሁን ያገልግል እንጂ አሁን ካለው የአገሪቱ ነባራዊና አለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር የሚጣጣም አይደለም።
በሀገራችን በየዓመቱ በፍጥነት እያደገ ያለውን የሀይል ፍላጎት መናርን ከግምት ውስጥ አለማስገባቱም ሌላው እጥረቱ ነው ።
ከዚህም ባሻገር ለሀይል አቅርቦት ሲባል በርካታ የውጭ ምንዛሬ እያወጣች የምታስገባቸውን ምርቶች እዚሁ ልታመርት ስትችል ይህን እምቅ ሀይል እንድትጠቀም ብዙም የሚያበረታታ አይደለም ይላሉ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ጥናትና ልማት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ጎሳዬ መንግስቴ ።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ፥ በስራ ላይ ያለው የሀይል ፖሊሲ አገሪቱ ታዳሽ ሀይል እንድትጠቀም ቢያበረታታም ፥ ኢትዮጵያ ካስቀመጠችው መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የመሰለፍ ግብ ጋር የሚናበብም አይደለም ።
ለአብነትም ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳላት ጥናቶች ቢያሳዩም አሁን ሁሉንም የነዳጅ ፍላጎቷን በውጭ ምንዛሬ እያስገባች ነው ።
የጋዝ ክምችት
በዘርፉ በተካሄደው ጥናት መሰረት በምስራቅ ኢትዮጵያ ብቻ ሌሎች አይነት የሀይል ምንጮች ሳይካተቱ አንድ መቶ አስራ ሁለት ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አላት።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2000 እስከ 2009 ድረስ ብቻ የኢትዮጵያ የፔትሮሊየም ፍላጎት በ87 በመቶ አድጓል።
በተመሳሳይ በ2009 ብቻ ሀገራችን ነዳጅ ለማስገባት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች።
ይህ ማለት ሀገሪቱ በወቅቱ ከውጭ ንግድ ከምታገኘው ብር አብላጫውን ይወስዳል እንደማለት ነው ።
ክለሳው የሚወልደው አዲስ ፖሊስ ተግባር ላይ ሲውል ታዲያ ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ፔትሮሊየም ባዮ ፊውል በመሰሉት የታዳሽ ሀይሎች ዓይነት መተካት የሚያስችላት ነው ።
በተጨማሪም ፖሊሲው ሀገራችን የራሷን የተፈጥሮ ጋዝ እንድታለማ በእጅጉ እድል ይሰጣል።
የሀይል ብክነት
ፖሊሲው የሀይል ብቃትና የቁጠባን አሰራር በጥብቅ የሚያዝ ሲሆን ፥ በተለይም የኤሌክትሪክ ሀይል ብክነትን ከመከላከል አንጻር የጎላ ሚናን ያበረክታል ተብሎም ነው የታመነበት ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽንን በመሰሉ የሀይል አቅራቢና በተጠቃሚው መካከል መሟላት ያለባቸው የሀይል አጠቃቀም መስፈርቶች ላይም ልዩ ትኩረት ይሰጣል ።
በ6 ሺህ የሀይል ተጠቃሚ ድርጅቶች ላይ የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ፥ ድርጅቶቹ ሙሉ ለሙሉ የሀይል አጠቃቀማቸው በብክነት የተሞላ ነው።
ድርጅቶች ከሚያገኙት የኤሌክትሪክ ሀይል ቢያንስ ዘጠና በመቶውን መጠቀም እንዲኖርባቸው ይጠበቃል።
ሆኖም እጅግ ጥቂት የሚባሉት ድርጅቶች ከሚደርሳቸው የኤሌክትሪክ ሀይል ሰማንያ በመቶውን እንደሚጠቀሙና ብዙዎቹ ከሚያገኙት ሀይል ከግማሽ በላይ የሚሆነውን እንደሚያባክኑ ነው ጥናቱ የሚያመለክተው ።
አዲሱ ፖሊሲ ድርጅቶች የሚበቃቸውን ሀይል ብቻ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ አሰራሮችን ያበረታታል።
የአቶም ሀይል ለኢትዮጵያ
አዲሱ ፖሊሲ የአቶሚክ ሀይልን በረጅም ጊዜ ከጥንቃቄ ጋር መጠቀምን አካቷል።
በሀገሪቱ በህክምና ተቋማትና በግብርናው ላይ የአቶም ሀይል ጥቅም ላይ ቢውልም ፥ ከሀይል አንጻር ያለው አቅርቦት ግን ምንም ነው ማለት ይቻላል።
አቶ ጎሳዬ መንግስቴ እንዳሉት ለአቶም ሀይል ማበልፀጊያ ከሚያስፈልጉት ሀብቶች መካከል ዩራንየም በአገሪቱ እንደሚገኝ ለማወቅ ጥናቶች እየተደረጉ ነው ።
በተጓዳኝ ግን አገሪቱ የአቶም ሀይልን መጠቀም የሚያስችላትን የአቅም ግንባታ ስራ የሚከናወን ይሆናል ነው የሚሉት ።
ፖሊሲው የግሉ ዘርፍ በሀይል ዘርፍ እንዲሳተፍ እድልን ይከፍታል።
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የታዳሽ ሀይል ማዕከል ሆና እንድትወጣ ያለመም ሲሆን ፥ ይህም የሚፈጥረው የሀይል ንግድ ትስስር ሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ያደርጋታል ተብሎ ታምኗል።
በካሳዬ ወልዴ
source...fanabc.com
No comments:
Post a Comment