በወር ከ42 ሺሕ በላይ ሴቶች ፅንስ ለማቋረጥ የሚሄዱበት ሜሪስቶፕስ
ሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ክሊኒኮችን ከፍቶ የሥነ ተዋልዶና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን መስጠት ከጀመረ 21 ዓመታት ሆኖታል፡፡
ተቋሙ በኢትዮጵያ 31 ክሊኒኮች ሲኖሩት ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ አዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡ ተቋሙ ከ570
ክሊኒኮች ጋርም በመጣመር የሥነ ተዋልዶና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሜሪስቶፕስ የማዋለድ አገልግሎት
የሚሰጥ አንድ ክሊኒክ ሲኖረው በወር 210 እናቶችን ያዋልዳል፡፡ ተቋሙ ሁለት ተጨማሪ ሆስፒታሎችን በባሕር ዳርና
በአዳማ ገንብቶ ለአገልግሎት አዘጋጅቷል፡፡
የሜሪስቶፕስን ዝናና ስም ያናኘው ዋና ጉዳይ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎትን በስፋት በመስጠቱ ነው፡፡ ቢሆንም ግን
ተቋሙ በየዓመቱ 476,323 ለሚሆኑ እናቶች ዘመናዊ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የረጅም ጊዜ የፅንስ
መከላከያ ዘዴን ለ170 ሺሕ ሴቶች የሰጠ ሲሆን፣ 700 ሺሕ ለሚሆኑ እናቶች ደግሞ የሥነ ተዋልዶ አገልግሎትና
የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ሰጥቷል፡፡
ሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል 43 አገሮች ውስጥ የሚሠራ ተቋም ሲሆን ዋና መሥሪያ ቤቱም በለንደን ይገኛል፡፡ 580
ሠራተኞች ያሉት የኢትዮጵያው ሜሪስቶፕስ እየሰጠ ስላለው አገልግሎት የተቋሙን የፕሮግራሞች ዳይሬክተር አቶ አበበ
ሽብሩን ምዕራፍ ብርሃኔ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ሜሪስቶፕስ በአሁኑ ወቅት ምን ላይ ይገኛል?
አቶ አበበ፡- በአሁኑ ወቅት የሥነ ተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ ዕቅድ
አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ሜሪስቶፕስ ነው፡፡ ከአራት ዓመታት ወዲህ የተቋሙ ፕሮግራም እንደ አዲስ
ተቃኝቶ፣ ከመንግሥት ዕቅድ ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ የእናቶችን
ሞት ቁጥር ለመቀነስ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሚና ከፍተኛ ስለሆነ የአገልግሎቱ ተደራሽነት ላይ በስፋት እየሠራን
ነው፡፡
ሌላው ገጠር ውስጥ ያሉ እናቶች የቤተሰብ ዕቅድና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት የዘረጋቸውን የጤና
ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን በማጠናከርና አሥር ተንቀሳቃሽ በሆኑ የሕክምና ቡድኖች አማካይነት ወደ 200 የሚሆኑ
ወረዳዎች ላይ (በአማራ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በኦሮሚያና ትግራይ) የረዥም ጊዜና የዘላቂ ፅንስ መከለያ ዘዴ
ላይ እንዲሠራ እያደረግን ነው፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ 123 ከተሞች ላይ የኤችአይቪ ኤድስና የአባለዘር በሽታዎች
ክትትልና ቁጥጥር ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየሠራን ነው፡፡ በተጨማሪም 8044 የተሰኘ የሥነ ተዋልዶ ምክር
አገልግሎት የሚሰጥ የጥሪ ማዕከል አለን፡፡ የጥሪ ማዕከሉ በወር እስከ 14 ሺሕ የሚደርስ ጥሪዎችን ያስተናግዳል፡፡
70 በመቶ የሚሆኑት ደዋዮች ዕድሜያቸው ከ19-24 ዓመት ድረስ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በተለያዩ አካባቢዎች
የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ክልል ላይ የት የት ትሠራላችሁ?
አቶ አበበ፡- ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ በስተቀር ሁሉም ክልል ላይ እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የማትሠሩበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ አበበ፡- እዚያ መሥራት ጀምረን የነበረ ቢሆንም ሊሳካልን ግን
አልቻለም፡፡ አብረን ልንሠራ ያሰብነው ያላቸውን የግል ጤና ተቋማትን አጐልብተን የነበረ ቢሆንም ልናጎ ለብተው
የምንችለው ዓይነት ደረጃ ያላቸው የግል ተቋሞችን ስላላገኘን መሥራት አልቻልንም፡፡ በቅርቡ ግን ከጤና ቢሮው ጋር
ተነጋግረን በዚያ ልንሠራ የምንችልበትን መንገድ እያመቻቸን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፈው ሰሞን 8044 ላይ ደውዬ መስመሩ አይሠራም ነበር፡፡ መስመሩ የተመደበለት አገልግሎት ካለ ብልሽቱን እንዴት ነው የምታዩት?
አቶ አበበ፡- ላለፉት አራት ወራት መስመሩ አልሠራልንም፡፡ ብልሽቱ በምን ምክንያት እንደተፈጠረ እርግጠኞች ባንሆንም ችግሩ ግን የቴሌ ይመስለናል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም ከእነርሱ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በጥሪ ማዕከሉ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡት እነማን ናቸው?
አቶ አበበ፡- አማካሪዎቹ አምስት ነርሶችና አንድ ሶሻል ወርከር ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ወጣቶቹ 8044 ላይ ሲደውሉ በብዛት የሚጠይቁት ጥያቄ ምንድን ነው?
አቶ አበበ፡- በጣም የሚገርምሽ ነገር እኔ እንደዜጋም እንደ ባለሙያም
ያስደነገጠኝ ነገር ስለድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ወጣቶቹ ያላቸው የተዛባ መረጃ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ
ደረጃ ተማሪዎች፣ እንዲሁም ወጣቶች ስለወሊድ መከላከያው ያላቸው መረጃ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ መልኩ የተዛባ ነው፡፡
ሌላው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የት ነው የሚገኘው የሚል ጥያቄን ለማቅረብ ይደውላሉ፡፡ ሦስተኛው ጥሪ ደግሞ
አርግዣለሁ፣ እርግዝናው የተፈጠረው ደግሞ አስቤበት ሳይሆን በአጋጣሚ ነው፡፡ ስለዚህ ምን ላድርግ የሚል የመፍትሔ
ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስለአባለዘር በሽታና ስለፍቅር ግንኙነት ይጠይቁናል፡፡ ደዋዮቻችን ከሁሉም ክልል
የተውጣጡ ናቸው፡፡ የአብዛኛዎቹ ዕድሜም ከ19 እስከ 20 ዓመት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ስንወያይ ሜሪስቶፕስ ፅንስ ማቋረጥን አያስተዋውቅም ብለውኛል፡፡
ነገር ግን ተቋሙ ባለው የፅንስ ማቋረጥ እውቅና ሴቶች ፅንስን ማቋረጥ ሲፈልጉ የመጀመርያው አማራጫቸው ሜሪስቶፕስ
ነው፡፡ ድርጅቱ በዚህ መጠን እንደ አማራጭ የሚወስድ ከሆነ ፅንስ ማቋረጥን የሚያበረታታ አይመስሎትም?
አቶ አበበ፡- እዚህ ላይ ሁለት ነገር ማንሳት እንችላለን፡፡ አንደኛ
በመረጃ እጥረት ምክንያት የሚፈጠሩ ያልተፈለጉ እርግዝናዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የመረጃ እጥረት ሲባል አንዲት እናት
የረዥም ጊዜ ፅንስ መከላከያ ብትወስድ መሃን ትሆናለች ወይም ማህፀኗ ውስጥ የተቀመጠው ሉፕ ወደ ጭንቅላቷ ይሄዳል
የሚሉ የተሳሳቱ አመለካካቶች አሉ፡፡
ስለዚህ እነዚህን አማራጮች ላለመጠቀም በየጊዜው ወደሚወሰዱ ኪኒኖች ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ኪኒኖቹን
አይዋጡ ሳይሆን ያለውን አማራጭ በሙሉ አይተው ይጠቀሙ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድም በሌላም መንገድ ሴቶቹ
የሚፈልጉትን አማራጭ ማግኘት ካልቻሉ ያልተፈለገ እርግዝና ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ የተሻለ መረጃና ግንዛቤ ካለ
አማራጮችን በመጠቀም ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል ይቻላል፡፡ እርግዝናው ከመጣ ግን ችግሩን ለማስወገድ
አገልግሎቱን ለረዥም ጊዜ ስንሰጥ ስለነበረ ወደ ሜሪስቶፕስ ይመጣሉ፡፡ እኛ ስለ ፅንስ ማቋረጥ ባናስተዋውቅም ከፍተኛ
የነበረውን ፅንስን በማቋረጥ ሒደት የሚሞቱ የእናቶችን ቁጥር እንዲቀንስ እየሠራን ነው፡፡ መንግሥትም ሁኔታውን
ለመታደግ በሁሉም ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ፅንስን ለማቋረጥ የሚመጡት ሴቶች ተደፍረው፣ ከቤተሰብ አባል ወይም በሌላ መጥፎ አጋጣሚ አርግዘው ሊሆን ይችላል፡፡ እናንተ ጋ ሲመጡ በምን ምክንያት እንዳረገዙ ትጠይቋችኋላችሁ?
አቶ አበበ፡- ይህ ጥያቄ የመጀመሪያ ጥያቄ ባይሆንም በማማከር ሒደት
ግን መልሱ ሊገኝ ይችላል፡፡ ትልቁ ነገር እርግዝናው ተፈጥሯል፡፡ በምንሰጠው የማማከር አገልግሎት ለምን
እንደተጋለጠች ለምሳሌ በዕውቀት ማነስ ነው? በአገልግሎት እጥረት ምክንያት ነው? የሴቶቹ መወሰን አለመቻል ነው?
ባልና ሚስት መካከል የግልፅነት ውይይት አለመኖር ነው? ወይስ ምንድን ነው? የሚለውን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ሌላው
ነገር አሁን ያልተፈለገ እርግዝና ካጋጠማት ለሚቀጥለው ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠር ጥሩ አገልግሎት
እንሰጣለን፡፡ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት ለማግኘት ከሚመጡት ውስጥ 97 በመቶ የሚሆኑት ፅንስ መከላከያ ይዘው ነው
የሚሄዱት፡፡ እና የምንፈልገው አንዴ ፅንስ ለማቋረጥ የመጣች ሴት በቂ መረጃ አግኝታ ድጋሚ ያልተፈለገ እርግዝና
አጋጥሟት እንዳትመጣ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ሴቶቹ ያረገዙበትን ምክንያት በማማከር ሒደት ውስጥ የምታገኙት ከሆነ አብዛኛዎች ሴቶች እርግዝናው የሚያጋጥማቸው እንዴት ነው?
አቶ አበበ፡- እኔ እንደግለሰብ ያለኝ ድምዳሜ ለእርግዝና የሚዳረጉት
በመረጃ እጥረት ነው፡፡ ለምሳሌ የድንገተኛ ወሊድ መከላከያን ለአንድ ወር የምትወስድ አለች፡፡ ኪኒኑን በየወሩ ወስጄ
አረገዝኩ የምትል አለች፡፡ ስለዚህ የመረጃ እጥረት አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ሴቶቹ የመረጃ እጥረት ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ለእርግዝና የሚዳረጉት በምን ምክንያት ነው?
አቶ አበበ፡- ይህን መመለስ የሚያስችል የተጠናቀረ ነገር የለንም፡፡
ነገር ግን ከአንድ ድርጅት ጋር በጥምረት ለመሥራት አቅደናል፡፡ ለእኔ ግን ቸልተኝነት ይመስለኛል፡፡ እንደሚያረግዙ
ያውቃሉ፡፡ እርግዝናውን የማይፈልጉ ከሆነ መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ የእርግዝናዎቹ ምክንያቶች ወደ አዲስ አበባና ገጠር
ሲኬድ ይለያያል፡፡
ሪፖርተር፡- ፅንስ ለማቋረጥ የሚመጡ ሴቶች የዕድሜ ክልላቸው ስንት ነው?
አቶ አበበ፡- በአማካይ ከ16 እስከ 24 የሚገኙ ናቸው፡፡
አብዛኛዎቹም ያላገቡ ናቸው፡፡ እንደ አገር በሥነ ተዋልዶና በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ወጣቶች ላይ አልደረስንም፡፡
በተለይ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ላሉት ወጣቶች፡፡ ለእነሱ ተመጣጣኝና ከእነርሱ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል መረጃና
ትምህርት እየተሰጠ እንዳልሆነ እኔ በግሌ መረዳት ችያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ትምህርቱንና መረጃውን ለመስጠት በየትኛው የዕድሜ ክልል ውስጥ ቢሆኑ ነው ተመራጭ የሚሆነው?
አቶ አበበ፡- በዕድሜ ከተወሰደ ቢቻል ከ15 ዓመት በታች አሊያም
በ15 ዓመታቸው ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ዕድሜያቸውን ያማከለና የተንተራሰ የሥነ ተዋልዶ ጤና
ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከፍ እያሉ ሲመጡ ወደ 19ኝ እና 24 ዓመት ሲጠጉ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ
ማድረግ ነው፡፡ ወላጆችም በግልፅነት ለልጆቹ ስለሁኔታው የማስረዳት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በዓመት ምን ያህል ሴቶች ፅንስ ለማቋረጥ ይመጣሉ?
አቶ አበበ፡- በ31ዱም ክሊኒኮቻችን የምንሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ለመጠቀም በወር ወደ 266 ሺሕ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 16 በመቶ የሚሆኑት ፅንስ ለማቋረጥ የሚመጡ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ፅንሱ ስንት ጊዜ ሲሆነው ነው ለማቋረጥ የሚመጡት?
አቶ አበበ፡- በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት 28 ሳምንት ድረስ ፅንስን ማቋረጥ ይቻላል፡፡ እኛ የምንሠራው ግን ከ16 እስከ 18 ሳምንት ለሆነው ፅንስ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ እስከ አምስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ይመጣሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ፅንስ ማቋረጥን በተመለከተ የተከሰተ ሞት ወይም ሌላ ችግር አለ?
አቶ አበበ፡- እስካሁን ያጋጠመን ችግር የለም፡፡
ሪፖርተር፡- የራሳችሁ በሆኑት 31ዱም ክሊኒኮችና አብራችሁ በምትሠሯቸው 570 ክሊኒኮች በሙሉ ፅንስ የሚቋረጥ ሥራ ትሠራላችሁ?
አቶ አበበ፡- በእኛ ክሊኒኮች ውስጥ አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ በሌሎቹ ክሊኒኮች ውስጥ ግን የማይሠሩ አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አርኤች ኔጌቲቭ የሆኑ ሴቶች የመጀመርያ ልጃቸውን ሲያስወርዱ መወጋት ያለባቸው
መድኃኒት አለ፡፡ መድኃኒቱን ካልተወጉ ዳግም ቢያረግዙ ፅንሱ ላይ ወይም የሚወለደው ልጅ ላይ ችግር ሊፈጠር
ይችላል፡፡ እናንተ ጋር ፅንስ ለማቋረጥ የሚመጡ ሴቶች ስለ አርኤች የሚነገራቸው ነገር እንደሌለ ካነጋገርኳቸው
ሴቶችና አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች መረዳት ችያለሁ፡፡ ይሄ ክፍተት እንዴት ሊኖር ቻለ?
አቶ ደበበ፡- እኔ መረጃው እንደማይነገራቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የጥራት ክፍላችን የሚሰጡት ምክሮች ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው ወይ የሚለውን ያያል፡፡
ሪፖርተር፡- ያለኝ መረጃ የዛሬ ስምንት ዓመት፣ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማና ከሁለት ዓመት
በፊት ፅንስ ያቋረጡ ሦስት ሴቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሦስቱም ሴቶች አር ኤችን በተመለከተ የተነገረን ነገር
የለም ነው ያሉት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዷ አሁን ላይ ብታረግዝም
ድጋሚ ለተፀነሰው ልጅ ችግር ሊሆን የሚችለውን አንቲቦዲ ሰውነቷ እንዳመረተ ተነግሯታል፡፡ እናንተም የምክር
አገልግሎቱን ባለመስጠታችሁ የሚፈጠረውን ችግር በተቻለ መጠን ለመቀነስ ከሐኪሟ ጋር እየተወያየ ነው፡፡ የደም
ዓይነትን የመለየት ሒደት ሲሠራ የአርኤች ውጤት ፖዘቲቭ ወይም ኔጌቲቭ መሆኑንም በዚያው ማወቅ ይቻላል፡፡ ሥራው
ደግሞ ትንሽ ብር የሚያስከፍልና አጭር ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ ይህንን አቀናጅታችሁ ለሴቶቹ ያሉበትን ሁኔታና
የሚያጋጥማቸውን ነገር ለመንገር እንዴት እስከዛሬ አላሰባችሁበትም?
አቶ አበበ፡- እንደ ድርጅት ይህንን አገልግሎት ስንሰጥ እነዚህ ነገሮች ተካተውበታል፡፡
ሪፖርተር፡- በተግባር ላይ ግን እንዴት ሊውሉ አልቻለም?
አቶ አበበ፡- እኔ ባለኝ መረጃ መሠረት ተግባራዊ እየሆነ ነው
ያለው፡፡ የማማከር አገልግሎቱ ያልተሰጣቸው ሰዎች ቀደም ብለው ቢነግሩን ኖሮ ዕርምጃ እንወስድ ነበር፡፡ ጥሩ ይሆን
የነበረው አገልግሎቱን የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎቻችንን ብታናግሪ ደግሞ ይበልጥ መረጃው ይኖርሽ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ትክክል ነው፡፡ ልዩነቱ ግን አገልግሎቱን የሚሰጠውን አካል ባናግርም ሁኔታው
የሕክምና ስህተት ስለሆነ የማማከር አገልግሎቱን አንሰጥም ማንም አይልም፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱ ይሰጣል አይሰጥም
የሚለውን ነገር በትክክል ማወቅ የሚቻለው ለሕክምና ከመጡም ታካሚዎቻችሁ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ አልተነገረንም የሚሉ
ከሆነ ክፍተቱ አለ ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ሁኔታው ምን እንደሆነ እንኳን ከናካቴው ሊያውቁ ይችላሉ፡፡
አቶ አበበ፡- የተባለው ነገር ካለ እንደግብዓት ወስጄ አረጋግጣለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ባላችሁ አንድ ክሊኒክ በቀዶ ሕክምናና በምጥ ስታዋልዱ ክፍያው ስንት ነው?
አቶ አበበ፡- በአማካይ ከ1500 እስከ 2000 ብር አካባቢ እናስከፍላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ፅንስን ለማቋረጥ ስንት ታከፍላላችሁ?
አቶ አበበ፡- እስከ 150 ብር አካባቢ ልናስከፍል እንችላለን፡፡ ፅንስ ለማቋረጥ ሌላ ቦታ ሄደው እየደሙ የሚመጡ አሉ፡፡ ለእነሱ ደግሞ የነፃ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡
ethiopian reporter
No comments:
Post a Comment