Tuesday, July 30, 2013

የግብፅ ፖለቲካዊ ትርምስ


የግብፅ ፖለቲካዊ ትርምስ

የአዉቶማቲክ ጠመንጃ ተኩስ ይሰማናል።ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ (እኛ እንዳንመታ) ዙሪያችንን ከበዉ ሠብአዊ ጋሻ ሠሩ።ጥይቶችና የሲ ኤስ ጋሶች ይተኮሱብናል።አየሩ በጢስ ታፍኗል።ሰዎች ያስታዉካሉ።የመስክ ሆስፒታሎቹ ወለል ደም ተንጣሎባቸዋል።---"
የዩናይትድ ስቴትሱን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪን፥ ቅዳሜ እንዳሉት «በጣም አሳስቧል።» የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ካትሪን አሽተንን ዛሬ እንዳደረጉት ወደ ካይሮ አስጉዟል።ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ለፓን ጊ ሙን፥ ያስደነግጣል።ገሚስ ግብፆችን ሲያስፈነጠዝ ሌሎቹን ዋይታ ያስረግዳል።የግብፅ የግድያ፥ የጥፋት፥ ዉድመት ጉዞ።

ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ሲሲ የሚመሩት ጦር ከዓረብም፥ ከአፍሪቃም ሐገራት አቻዉ በቁጥር፥ በታጠቀዉ መሳሪያ ብዛት፥ ጥራት፥ ዘመናይነትም አንደኛ ነዉ።አንደኛዉ ፈርጣማ ጦር የሰለጠነ፥ የተቀጠረ፥ የተደራጀዉ ከድሮ እስከ ዘንድሮ በይፋ እንደሚታወቀዉ ባብዛኛዉ እስራኤልን እንዲወጋ ነዉ።ምናልባት ከወር በፊት ከካይሮና ከአዲስ አበባ እንደተሰማዉ ኢትዮጵያን ሊሆን ይችላል፥ ምናልባት ገማል አብድናስር የመን ላይ እንዳደረጉት ከሶሪያ ተፋላሚዎች አንዱን ደግፎ ለመዋጋት ይዘምትም ይሆናል።ወይም ተመሳሳይ ነገሮች።

ብቻ በብዙዉ ዓለም ብዙ ጊዜ እንደሚባለዉ የታላቅ፥ ታሪካዊ፥ ጥንታዊ ሐገር፥ ሕዝቡን ከዉጪ ጠላት ጥቃትና ወረራ ለመከላከል ነበር።ባለፈዉ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ግን «ጀግናዉ» የግብፅ ጦር ርዕሠ-ከተማ ካይሮ መሐል የሱን ጥበቃና ከለላ በሚፈልጉ፥ የሱን ደሞዝ፥ ቀለብ የሚከፍሉ ሲቢል ዜጎች ላይ ጀግንነቱን አሳየ።
Supporters of deposed Egyptian President Mohamed Mursi throw stones from behind a makeshift barricade they built as they take cover from the police during clashes in Nasr city area, east of Cairo July 27, 2013. At least 70 people died on Saturday after security forces attacked supporters of deposed President Mohamed Mursi in Cairo, Muslim Brotherhood spokesman Gehad El-Haddad said, adding the toll could be much higher. REUTERS/Asmaa Waguih (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST TPX IMAGES OF THE DAY) ግችት


ያልታጠቀ ተቃዉሞ ሠልፈኛኝ ግንባር ደረቱን እያፈለሰ ጣለዉ።ከካይሮ ሆስፒታሎች የአንዱ ሐኪም ያርዳሉ ወይም ያስረዳሉ።


«ሁሉም የቆሰሉት ጭንቅላታቸዉ፥ ወይም ደረታቸዉ ላይ ነዉ።አንድ ሰዉ ብቻ ጀርባዉ ላይ ተመትቷል።እስካሁን ሃያ ስምንት (አስከሬን) ተረክበናል።ሌሎች ደግሞ አሁን መጥተዋል።ሁለቱ ሰዎች ጭንቅላታቸዉ ሙሉ በሙሉ ተፈርክሷል። አንጎላቸዉ ተበትኗል።ሁሉም የተመቱት በአይኖቻቸዉ መሐል-ግንባራቸዉን ነዉ።ከከፍታ ቦታ ቁልቁል በተተኮሰ ጥይት ነዉ የተመቱት።ሁሉም ጭንቅላቱን፥ ደረቱን ወይም ልቡን ተመታል።»


የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ለጦርነቱ ቆስቋሽ፥ ዋና ተፋላሚዎች፥ ለአዉሮጳ-አሜሪካኖች የሰላም ብልፅግናቸዉ ጅምር፥ በኮሚንስት ካፒታሊስት የመከፋፈል፥ መነታረካቸዉ ሠበብ፥ የነሱን ግጭት ጦርነት ወደተቀረዉ ዓለም የመላክ፥ መግፋታቸዉ ብልሐት ዉጥን ነዉ።በጦርነቱ ወቅት ማርሻል ሞትጎመሪ፥ ከጄኔራል ሮሚዎ ጋር ለተፋለሙበት ግብፅ ባንፃሩ እንደ ብዙዉ የአፍሪቃና የዓረብ ሐገራት ሁሉ የጦርነቱ ፍፃሜ የሌላ ጦርነት ዉጊያ ሰበብ ምክንያት ነዉ።


የግብፅ ጦር፥ የመጀመሪያዉ የአረብ እስራኤሎች ጦርነት፥ የሲዊስ ቦይ ወይም (የብሪታንያ፥ የፈረንሳይ፥ የእስራኤል እና የግብፅ) ጦርነት፥ የስድስቱ ቀን ጦርነት፥የየመኖች ጦርነት፥ የዮም ኩፑር ጦርነት እየተባለ ከጦርነት ተለይቶ አያዉቅም።በዚሕ ሁሉ ጦርነት መሐል ያለፈዉ የአረብ፥ አፍሪቃዉ ሐያል ጦርን እንዲያዙ ባለፈዉ ዓመት በፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ የተሾሙት ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል-ሲሲ ወታደራዊ ትምሕርት፥ ሥልጠናዉን ከግብፅ እስከ አሜሪካ፥ ብሪታንያ ድረስ ሔደዉ ተምረዉታል።



A member of the Muslim Brotherhood and supporter of deposed Egyptian President Mohamed Mursi hides from tear gas thrown by police during clashes in Nasr city area, east of Cairo July 27, 2013. The Muslim Brotherhood said at least 31 people were killed on Saturday when security forces opened fire on a protest by supporters of deposed President Mohamed Mursi in Cairo. REUTERS/Asmaa Waguih (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST) አስለቃሽ ጢስ
ጦርነት እንዳደረዉ የጦር ጄኔራል ግን አንድም ጦርነት ተዋግተዉ፥ አዋግተዉ አያዉቁም። አሌክሳንደሪያ የሠፈረዉን ክፍለ-ጦር ላጭር ጊዜ ከማዘዝ በስተቀር ብዙ ጊዚያቸዉን በግብፅ ኤምባሲዎች በወታደራዊ አታሼነት ከርዕሠ-ከተማ ርዕሠ-ከተማ ሲያቀያይሩ ነዉ-ያሳለፉት።


በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ መጀመሪያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በአደባባይ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ከሥልጣን የተወገዱትን ፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክን የተካዉ የጦር ሐይሎች ላዕላይ ምክር ቤት አባል ሆነዉ የታሪካዊቱን ሐገር ትልቅ ቤተ-መገንስት ወጣ ገባ ይሉበት ያዙ።የሙባረክ መወገድ ብዙም ለማይታወቁት ጄኔራል ሳይደግስ-አይጣላም እንደነበረ ሁሉ የሙርሲ መመረጥም የመሾም-መሸለማቸዉ ብሥራት ነበር።
እንደ ወታደራዊ አታሼ ዲፕሎማሲዉን፥ እንደ ወታደራዊ ገዢ የምክር ቤት አባል ቤተ-መንግሥትን የለመዱት አል-ሲሲ አንዴም ሳይዋጉ፥ ከጦርነት ተለይቶ የማያዉቀዉን ጦር የአዛዥነት ሥልጣን በያዙ በአስራ-አንደኛ ወራቸዉ የማያዉቁትን ጦርነት በሚያቁ ሹዋሚያቸዉ ላይ ከፈቱ።
ጀግናዉ ጄኔራል በሕዝብ የተመረጡትን ግን ተቃዋሚዎቻቸዉ ባደባባይ ሠልፍ የሚያወግዟቸዉን ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲን ከስልጣን አስወግዱ።ሐምሌ ሰወስት።ሕዝብ በአብላጫ ድምፅ ያፀደቀዉን ሕገ-መንግሥት ሻሩ።በሕዝብ የተመረጠዉን ምክር ቤት በተኑ።እና ያደረጉት ሁሉ መፈንቅለ መንግሥት አይደለም አሉ።
ዳኛ አዲሊይ መንሱርን እንደ መጋረጃ ዘርግተዉ ታሪካዊቷን ሐገር ከጀርባ ይዘዉሩ ገቡ።መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃወሙ ወገኖችን አስገደሉ።መፈንቅለ መንግሥቱ ከተደረገበት እስካለፈዉ ቅዳሜ በተቆጠረዉ ሃያ-ሰወስት ቀናት ዉስጥ ብቻ መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃወሙ ሁለት መቶ ሠዎች ተገድለዋል።በሺ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በመቶ የሚቆጠሩ ታስረዋል።እርምጃዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ በጣም አሳስቧቸዉ ነበር።
«ባለሥልጣናት ከሁለት መቶ በላይ የሙስሊም ወንድማማቾች አባላትን ማሠራቸዉ በጣም አሳስቦኛል።ይሕ የብቀላ እና የመቀጣጫ ጊዜ አይደለም።ጊዜዉ ሁሉንም አሳታፊ እና የእርቀ-ሠላም ጊዜ ነዉ።»
ከአፍሪቃ ሕብረት በስተቀር «ዓለም አቀፍ» የሚባለዉ ማሕበረሰብ መፈንቅለ መንግሥቱን በግልፅ ቋንቋ አለወገዘም።አለመወገዙን ጄኔራል ሲሲ እና ተከታዮቻቸዉ ለእርምጃቸዉ እንደ ትክክለኛ ማረጋገጪያ ሰርቲፊኬት ቢቆጥሩት አይፈረድባቸዉም።በመግደል-ማሰሩ ቀጠሉበት።አላረካቸዉም። መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃወሙ ተጨማሪ ሰዎችን ለማሠር እና ምናልባትም ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳደረጉት ባደባባይ ለመግደል ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ እንዲደግፋቸዉ ጠየቁ።

Supporters of deposed Egyptian President Mohamed Mursi run from tear gas fired at them by police during clashes in Nasr city area, east of Cairo July 27, 2013. At least 70 people died on Saturday after security forces attacked supporters of deposed President Mohamed Mursi in Cairo, Muslim Brotherhood spokesman Gehad El-Haddad said, adding the toll could be much higher. REUTERS/Asmaa Waguih (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST TPX IMAGES OF THE DAY) አስለቃሽ ጢስ

ጄኔራሉ ሰዉን ለማሰር እና ለመግደል ሕግ እንዲወጣ አልጠየቁም።አቃቤ-ሕግ እንዲከስ፥ ጠበቆች እንዲከራከሩ፥ ዳኞች እንዲፈርዱ አልፈቀዱም።ትዕዛዛቸዉን የሚፈፅመዉ ጦርና ከየሥፍራዉ ለቅመዉ የሾማቸዉ የጊዚያዊ መንግሥት አባላት የሚወስዱትን እርምጃ፥ ሕዝብ ባደባባይ መፈክርና ጫጫታ እንዲያፀድቅላቸዉ በይፋ ጠየቁ።
«አሸባሪዎችንና አመፀኞችን ለመቅጣት (ሕዝቡ) በሠልፍ ሐላፊነቱን እንዲሰጠን እጠይቃለሁ።»
መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም በተከታታይ አደባባይ የሚወጣዉን ሕዝብ የሚያስተባብረዉ የቀድሞዉ ፕሬዝዳት የመሐመድ ሙርሲ የቀድሞ ማሕበር ሙስሊም ወንድማማቾች የጄኔራል ሲሲን ጥሪ ከእርስ በርስ ጦርነት አዋጅ ነዉ የቆጠረዉ።ይሁንና የጄኔራሉን አዋጅና እርምጃ እንደሚፈግፉ በጭብጨባ ከገለፁት ታዛዥ ወታደሮቻቸዉ በተጨማሪ ጄኔራሉን ፈርቶም ይሁን ወድዶ ፍላጎታቸዉን ለማሟላት ባለፈዉ አርብ በርካታ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ነበር።እሱ አንዱ ነዉ።
«እዚሕ የመጣነዉ የጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ አብዱል ፈታሕ አል-ሲሲን ለመደገፍ ነዉ። አሸባሪዎችን እንዲመነጥሩ አረንጓዴ መብራት ለማሳየት ነዉ።ብዙ መጠበቅ አንችልም።ሐገሪቱ እየተቃጠለች ነዉ።»
ሐገሪቱ በርግጥ እየጋየች ነዉ።ሐገሪቱን የሚያጋየዉ ማነዉ ነዉ-ነዉ እንጂ ጥያቄዉ።ታንክ መትረየስ የታጠቀዉ ወይስ መስገጂያ ምንጣፍና መፈክር ያንጠለጠለዉ?የጄኔራል አል-ሲሲ ጦር ዳግም መልስ ሰጠ።
አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ፥-የቢቢሲዉ ጋዜጠኛ ካይሮ ነበር።
«ጥቃቱ ከትናንት ማታ እስከ ጠዋት ቀጥሏል።የአዉቶማቲክ ጠመንጃ ተኩስ ይሰማናል።ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ (እኛ እንዳንመታ) ዙሪያችንን ከበዉ ሠብአዊ ጋሻ ሠሩ።ጥይቶችና የሲ ኤስ ጋሶች ይተኮሱብናል።አየሩ በጢስ ታፍኗል።ሰዎች ያስታዉካሉ።የመስክ ሆስፒታሎቹ ወለል ደም ተንጣሎባቸዋል። አብዛኞቹ ቁስለኞች ጭንቅላታቸዉ ተበጥርቋል።አንድ በግምት አስራ-ሁለት ዓመት የሚሆነዉ ሕፃንም እዚያ ነበር።ሰዉነቱ በደም ተሸፍኗል።---» እያለ ይተርካል።

Egypt's Defense Minister Abdel Fattah al-Sisi is seen during a news conference in Cairo on the release of seven members of the Egyptian security forces kidnapped by Islamist militants in Sinai, in this May 22, 2013 file picture. To match Special Report EGYPT-PROTESTS/DOWNFALL REUTERS/Stringer/Files (EGYPT - Tags: MILITARY HEADSHOT POLITICS) አል ሲሲ
የተገደሉትን ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር የሚያዉቅ የለም።ሲበዛ-ሁለት መቶ ሲያንስ ሰማንያ ይገመታል።ይሕ ካይሮ ነዉ።አሌክሳንደሪያ ደግሞ በትንሽ ግምት አስር ሰዉ ተገድሏል።በሌሎች ከተሞችም እንዲሁ።የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር ቃል አቀባይ የወታደራዊ ሁንታ እርምጃ መጥፎ ገፅታ ይሉታል።
«የምናየዉ የወታደራዊ ሁንታዉን አስጠሊታ ገፅታ ነዉ።ከአንድ መቶ ሐምሳ በላይ ሠዎች ተገድለዋል።በሺ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።የከፋ ሠብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ ነዉ።ሰዎች በዘፈቀደ ይታሰራሉ።ወታደራዊ አገዛዝ በአንድ ሐገር ላይ ሊፈፅም የሚችለዉን መጥፎ ነገር ሁሉ እያየን ነዉ።ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ ወደ ቀድሞዉ የሙባረክ ሥርዓት እየመለሰን ነዉ።»
የሁለት ሺሕ አምስቱን የዓለም ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤልን የተሸለሙት ዶክተር መሐመድ አል-በራዳይ ጄኔራል ሲሲ ከጀርባ የሚያዙት ጊዚያዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸዉ።ግብፅ ግን የሠላም ኖቤልን ሜዴሊያ ያንጠለጠለ ምክትል ፕሬዝዳት እንጂ ሠላም አይደለችም።ግብፅ ሠላም አለመሆኗ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ እንዳሉት ሐገራቸዉን ያሳስባታል።«(ለግብፅ ሹማምንት) ሰላማዊ ተቃዉሞ ሰልፍ የማድረግ መብትን እንዲያከብሩ ነግሬያቸዋለሁ።» አሉ አሜሪካዊዉ ትልቅ ዲፕሎማት።
የአዉሮጳ ሕብረቷ የዉጪ ጉዳይ የበላይ ሐላፊ ካትሪን አሽተን አሳሳቢዉን ጉዳይ በቅርብ ለማየት ወደ ካይሮ ተጉዘዋል።«አሳሳቢ፥ በጣም አሳሳቢ፥ በጥልቀት አሳሳቢ» ከሚለዉ የዲፕሎማሲ ሽርደዳ ባለፍ ቅዳሜ የተፈፀመዉን ግድያ በግልፅ ያወገዘ-የሐያል ሐገር ባለሥልጣን የለም። ግድያዉን ለማዉገዝ ትንሽም ቢሆን የደፈሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን ብቻ ናቸዉ።
ጄኔራል ሲሲ፥ መሐመድ ሙርሲን ካስልጣን ካስወገዱ ወዲሕ ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ በትንሽ ግምት ሰወስት መቶ ሰዎች ተገድለዋል።የቆሰሉትን የቆጠራቸዉ የለም።በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል።ምጣኔ ሐብቷ ደቋል።ከሁሉም በላይ አምና ይሄኔ ብልጭ ብሎ የነበረዉ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ጅምር ባይጠፋ ተዳፍኗል።የሙስሊም ወድማማቾች ማሕበር ቃል አቀባይ ከዚሕም አልፈዉ ተዘርፏል ባይ ናቸዉ።

Protesters cheer and dance with flares as they gather for a mass protest to support the army in front of the presidential palace in Cairo July 26, 2013. At least seven people were killed and hundreds wounded in scattered violence across Egypt during mass rallies for and against the army's overthrow of Islamist President Mohamed Mursi, who was placed under investigation for murder. REUTERS/Asmaa Waguih (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST) ካይሮ «ትነዳለች»


«ዴሞክራሲያችን ተወስዶብናል።የመረጥናቸዉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በሙሉ ተወስደዉብናል።እዚሕ የምገኘዉ መጀመሪያ ግብፃዊ በመሆኔ ነዉ።የሙስሊም ወንድማማቾች ተወካይነቴ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠዉ ነዉ።ትናንት-ቅዳሜ አደባባይ የወጡት በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩት ሰዎች የሙስሊም ወንድማማቾች ደጋፊዎች ብቻ አልነበሩም።ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የቆሙ ሁሉ ነበሩበት።»

ምዕራባዉያን መገናኛ ዘዴዎች «እስላማዉያን» የሚሏቸዉ መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃወሙትና ባንፃራቸዉ የቆሙት የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች ግጭት፥ዉዝግብ የሰለቻቸዉ ግብፃዉያን «ሰወስተኛ ግንባር» የሚባል ሥብስብ ፈጥረዋል።ባብዛኛዉ የዩኒቨርስቲ መምሕራንና ባለሙያዎች የመሠረቱት ስብስብ ሙርሲንም፥ ጄኔራሉንም ይቃወማል።በዚሕም ብሎ በዚያ ግብፅ ቁልቁል እየተንደረደረች ነዉ፥ባፍጢሟ ሳትደፋ አዳኝ ታገኝ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ
source... http://www.dw.de

No comments:

Post a Comment