Thursday, July 18, 2013

አንድ በያይነቱ ቲማቲም የሌለው…


507679721_c4fff4f2ec-copy
 
አንድ በያይነቱ ቲማቲም የሌለው…

ይሄ ጨዋታ በያይነቱ ነው፡፡ የሌለው ቲማቲም ብቻ ነው… ለምን ቲማቲም የለውም ከወደ ማብቂያው መልሱ አለ፡፡ በነገራችን ላይ እንደው ለርዕስ እንዲመቸኝ ብዬ እንጂ ሌሎቹ አይነቶች ተገኝተው ቲማቲሙ ቢጠፋ ችግር አልነበረውም ሌሎቹም ጠፍተው ቲማቲሙም ጠፍቶ ነው የተቸገርነው፡፡ ዘንድሮ አልጠፋ ያለው የኑሮ ውድነት መንስኤው ብቻ ነው፡፡ ፍካሬ እየሱስ ላይ ድንገት ይመጡና ርስ በርስ ተባልተው ይጠፋሉ…! የሚል ነገር አለ ሲሉ ሰምቼ ነበር እስቲ ይቺን ነገር አጣሩልን… ሼህ ሁሴን ጅብሪልም በዚህ ጉዳይ ላይ የሆነ ነገር ሳይሉ አይቀሩም! ብዙ ትንቢት ሰምተን ነበር ጭራሽ ትንቢት የተነገረባቸው ትዕቢት በትዕቢት እየሆኑ አስቸገሩን አንጂ! (ለነገሩ ትዕቢታቸወም የትንቢቱ አካል ነው)
ለማንኛውም ብሎግ ያፈራውን በያይነቱ እንቃመስ፤
አንድ
ትላንት አለሌዋን የእንግሊዝ ፀሀይ “ስቦጭቃት” ሃያ ሰዓት ሙሉ ሰማይ ላይ ተሰቅላ ሙስሊም ወዳጆቻችንን ፆሙን አከበደችባቸው ብዬ አውግቼዎ ነበር ታድያ ለማነፃፀሪያ የገናን ጀንበር ጠቅሻት አልነበር…
ለካስ የገና ጀንበር ጭራሽ ቶሎ ነው ወደቤቷ ክትት የምትለው፡፡ እኔኮ ዱርዬዋ እርሷ መስላኝ ነበር… ወዳጆቼ በሰጡኝ ማስተካከያ መሰረት የኢትዮጵያ ጀንበር አምሽታ እና ሞቅ ብሏት የምትገባው በሰኔ ነው፡፡ ወይ ጉድ ሰኔን መቼ በዚህ ጠረጠራኳት… ሰኔ መሸታ ቤት አላት ብዬስ በወየት በኩል ላስብ…! (የሆነ ሆኖ ስህተትም መስራትም ማስተካከያ መስጠትም ብርቄ አይደለምና የትላንቱ የፌስ ቡክ ጨዋታ ላይ ታህሳስ የሚለው ሰኔ በሚል ተተክቶ ይነበብ!)
ሁለት
ሃይሌ ገብረ ስላሴ ፕረዘዳንት ለመሆን ፈልጋለሁ ያለው የምሩን ነው አንዴ… እኔ እኮ አቶ ግርማ ወልደጊዜርጊስን ሲያሽሟጥጣቸው መስሎኝ ነበር፡፡ አሁን ብዙዎች እንደሚያወሩት ግን ሀይሌ አስር ሺውንም ትቶ ማራቶኑንም ትቶ ለፕረዘዳንትነት እየሮጠ መሆኑን ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ በዚህኛው ሩጫ ካሸነፈ ግን ሜዳሊያ አይሸልምም፡፡ ጀግናም አይባልም፡፡ ራሱ ጀግና አርሶ አደሮችን ሜዳሊያ ይሸልማል እንጂ! ለካስ ደግሞ ህጉ እንደሚለው ሃይሌ ፓርላማ ሳይገባም ፕረዘዳንት የመሆን እድል አለው፡፡ ምናለበት አሁን እኒያ ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ባይመቀኛቸው…
ዶክተርዬ በቃ ለፕረዘዳንትነት ካልተመረጡማ ምን አለፋዎትና በግል ተወዳድረው አሸንፈው፤ “ታላቁ መሪያችን ታላቋ ድርጅት የተባረከው መንግስት…” ምናምን ይላሉ… ዝም ብለው የልብዎን ይናገሩ… የልቦን ብቻም አይደለም የቦንጋን ህዝብ የልብ ይናገሩለት፡፡ እና የመጣው ይምጣ እንዴ ምን በወጣዎ ከህዝብዎም ሳሆኑ ከኢህአዴግም ሳይሆኑ…
የምር ግን ሃይሌ ፕረዘዳንት ሆኖ ምን ሊያተርፍ ነው! አንድ ወዳጄ እንዳሉት ልብ ካለው ጠቅላይ ሚኒስትርነት አይወዳደርም…! እኛ የተቸገርነው ያልተዝረከረከ እና በቅጡ የሚጠቀልለን ጠቅላይ ሚኒስትር ነው እንጂ እንግዳ እየሸኘ እንግዳ እየተቀበለ ወራትን እየሸኘ ደሞዙን እየተቀበለ የሚኖር ፕረዘዳንት መቼ ቸገረን!
ሶስት
የአውሮፓ ፓርላማ ህብረት አባላት ለኢትዮጵያ መንግስት ልክ ልኩን ነገሩት አሉ፤ የጸረ ሽብር አዋጁ በቅኔ የአፃፃፍ ዘዴ አሻሚ በሆኑ ትርጉሞች የተሞላ እና ከህገመንግስታዊ ድንጋጌው ጋር የሚላተም መሆኑንም ተናገረዋል ነው የተባለው፡፡ መንግስታችን አንድነቶች እና የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ሲጠይቁት “ይህ አዋጅ በቀጥታ የዳበረ ልምድ ካላቸው ሀገራት ቃል በቃል እደግመዋለሁ ቃል በቃል የተቀዳ ነው… ” እያለ ሲመልስ ነበር፡፡ አሁን ራሳቸው የዳበረ ልምድ ያላቸው ሀገራት አዋጁ እንደ ውጫሌ ህግ አሻሚ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው ሲሉት ጦር ያነሳባቸው ይሆን…!
ሌላው ቢቀር ግን “እነዚህ የኒዮ ሊበራሊዝም አራማጆች ናቸው” ይለናል ተብሎ ይጠረጠራል፡፡ እኔ የምለው ኒዮ ሊበራሎችን እና ሽብርተኞችን መንግስታችን አበልጅ አደረጋቸው አይደል…!
አራት
የአዲሳባ መንግዶች ክረምቱ እና የባቡር መንገድ ዝርጋታው እንዲሁም ፍሳሽ አልባው አስፋልት (በቅንፍም አንዳንዱ ቦታ የተሰራልን አስፋልት ብረት ምጣድ በሉት ይሄ ገላ መታጠቢያ ጎድጓዳው ምጣድ የለም… ልክ እንደሱ ውሃ አቁሮ ስታዩት ቻይናዎቹ የገነቡልን ለጀልባ ነው ለመኪና ያሰኛል) ብቻ ይሄ ሁሉ ተደራርቦ ከፍተኛ የመንገድ ችግር አጋጥሟል፡፡ እንደውም አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ በደህናው ጊዜ ሄድክ እንጂ አሁን ቢከፋህ እንኳ ማምለጫ መንገድ የለም ብሎኛል፡፡
አምስት
እኔ የምለው ቲማቲም እንዲህ የተቀናጣችው ምን ልሁን ብላ ነው… ለአንድ ኪሎ ሃያ ስድስት ብር… አይደብራትም እንዴ…! አቶ ሃይለማሪያም በዚህ ጉዳይ ላይ ደግሞ ያላግጡ አሎት፤ እንደባለፈው ጊዜ “ቲማቲም በልቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ቲማቲም መብላት ስለጀመረ ነው የተወደደው” ቢሉ አባ…ዬ ህዝቡ መሮታል “ራስዎ ቲማቲም መብላት ስለጀመሩ ነው” ብሎ ያስቀይሞታል! እና ሲመልሱ ይጠንቀቁ!

No comments:

Post a Comment