Monday, July 22, 2013

‹‹በእንቁላሉ ጊዜ›› ያልተቀጣው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን

‹‹በእንቁላሉ ጊዜ›› ያልተቀጣው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ በቢሊዮን የሚገመት ሀብት ለኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ ይውላል፡፡ ‹‹ከዚያም ከዚህም›› ተለምኖ በብድር ተፈልጎ ለኬብል ዝርጋታ፣ ለገጠር ኤሌክትሪፊኬሽንና መሰል ሥራዎች ርብርብ ይደረጋል፡፡ ያም ሆኖ ኮርፖሬሽኑ የሕዝብ እርካታና አመኔታን ያገኘ እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በዓል ሲሆን፣ የውጭ እንግዶች ከተማውን ሲጎበኙ፣ በትልልቅ አገራዊና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ወቅት ሕዝቡ እንዲያገኝ የሚያደርገው ከአቅም ማነስና ከአስተዳደር ችግር ብቻ አለመሆኑ ይታወቃል ይላሉ፡፡ ‹‹ሙስናና ብልሹ አሠራር የነገሠበት ተቋም ስለሆነ ነው›› በማለት በድፍረት ይናገራሉ፡፡‹‹እስካሁን ድረስ የፈለጉት አካባቢ ኃይል እየቆረጡ በጉቦ ጥቂት ሠፈሮችን ነጥለው የሚሰጡ የበታች ሙያተኞች የሉም?›› የሚሉት ነዋሪዎች፣ ደሴ፣ አርባ ምንጭ፣ ድሬዳዋን በመሰሉ ከተሞች የፖልና የመስመር ግዥ ላይ ከፍተኛ ምዝበራ ተፈጽሞ የተከሰሱ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞችን እንደሚያውቁም አልሸሸጉም፡፡ ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ በኮንዶሚኒየም ወይም በአዲስ ሠፈር ቆጣሪ ለማስገባት እንደ ሕጋዊ አካል ነዋሪው ገንዘብ ሰብስቦ ጉቦ እንዲሰጣቸው የሚያስጠይቁ ሠራተኞች አሉ በማለት ይናገራሉ፡፡የአባባሉን ተጨባጭነት የሚያረጋግጠው ራሱ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከወራት በፊት ያወጣው ሥነ ምግባር መጽሔት (ቅጽ 12፣1) ነው፡፡ እንደ መረጃው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከ45 በላይ የሚሆኑ ግዥዎች ገቢ ከተደረጉና ክፍያ ከተፈጸመባቸው በኋላ ሥራ ላይ ሲውሉ ችግሮች ማጋጠማቸው ታይቷል፡፡ ለዚህ የማረጋገጥ ሥራ ሲከናወን የጥራት ችግር ያለባቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ከ45 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ፒኖች የቴክኒክ ችግር ያለባቸውና ከአምስት ዓመታት በላይ ሥራ ላይ ሳይውሉ ተቀምጠው መገኘታቸውን አብራርቷል፡፡
እንግዲህ አስቡት እነዚህ በአሥር ሚሊዮኖች ዶላር የሚገዙ ንብረቶች ለምን ተቀመጡ? የበላይ አመራሩስ አያውቅምን? የቦርድ ኃላፊዎችና ከፍተኛ የመንግሥት አካላትስ የት ነበሩ? የሚሉት ደምቀው የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከዓመታት በፊት ከሥራ ተባረርን ያሉ የመሥሪያ ቤቱ የቴክኒክ ሠራተኞች በአንድ የግል ጋዜጣ ላይ ይህንኑ መረጃ ሕዝብና መንግሥት ይስማው ብለው ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ እነሆ ቢዘገይም ጉዳዩ ሰሚ አግኝቶ ለፍርድ መቅረቡ፣ እነዚያ የተገፉ ዜጎች ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡
ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከዓመት በፊት በለቀቀው መረጃ የኮርፖሬሽኑን የንብረት አስተዳደር ችግሮች በሚገባ አጋልጧል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ውስጥ ተገዝተው የሚመጡ መለዋወጫ ዕቃዎች በንብረት ክፍል በአደራ መረከቢያ ቅጽ ተመዝግበው የገቢ ሰነድ ሳይሠራላቸው ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የሚቆዩ በመሆናቸው ዕቃዎቹ ችግር ቢኖርባቸው እንኳን በወቅቱ ለማስመለስ የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ ተችሏል፤›› ሲል ያስረዳል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የተዝረከረከ ጥቂቶችን ለማበልጸግ የተመቸ አሠራር፣ በዚች ውስን ሀብት ባላት አገር ላይ ሲፈጸም መኖሩ እጅግ የሚያስቆጭ ነው፡፡
የኮርፖሬሽኑ የቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የመሥሪያ ቤቱ ስም በክፉ አይነሳ ባይ ተከላካይ ነበሩ፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር ኮርፖሬሽኑን እየወረረው ነው ብሎ የጻፈ አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄን ስድብና ዛቻ አድርሰውበት እንደነበር ሳይሸሽግ አጫውቶኛል፡፡
አምባገነንነት ለሙስና የተመቸ በመሆኑ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ ሙስና ይነግሣል መባሉም ለዚህ ነበር፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የሕዝብ ሀብት አውድመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ያሉ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ጉዳይ ይቆየንና ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ለምን አልተፈተሸም የሚለው ያስቆጫል፡፡ መንግሥትም በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነት አጠናክሮ በሄደ ነበር፡፡ ምንም ሆነ ምን አሁን እየተወሰደ ያለው ዕርምጃም ቢሆን ይበል የሚያሰኝ እንጂ የሚናቅ አይደለም፡፡
ፀረ ሙስና ኮሚሽን በጥናት ጊዜ መብላቱን ያቁም
አሁን እየተወሰዱ ያሉ የፀረ ሙስና ዕርምጃዎችና ሙስናን የመታገል ጥረቶች በጥናትና ምርመራ የተገኙ ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡ የአገራችን ማኅበረሰባዊ ልማድ ድብቅነት ሆኖ ሳለ፣ በድብቅ የሚፈጸምን ድርጊት በቀላሉ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ታዛቢዎች ግን ጥናቱ ጊዜ የሚበላና ሀብት እስኪሰወር የሚታገስ መሆን የለበትም ይላሉ፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አሠራር ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጡ ድርጊቶችና የሥራ ክፍሎችን ብልሹ አፈጻጸም ፀረ ሙስና ኮሚሽን መግለጽ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንም የግዥና ንብረት አያያዝ ችግር በኮሚሽኑ ከተጋለጠ ከአምስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ዕርምጃ ሳይወሰድ ንቅናቄ የታየው አሁን ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም ፈጣን ጥናት፣ ቀልጣፋ ዕርምጃና በሕግ የማስቀጣት ሥራ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡
ከዚህ አንፃር ሲታይ ራሱ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ጥናት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ያላግባብ የተከመቹና በላያቸው ላይ የተፈጸሙ ግዥዎች ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ በ1995 ዓ.ም. የተገዙ የሃይቴንሽን ኬብሎች (ኤቢሲ ኬብል ብዛት 255 ሺሕ፣ 20 ኬ.ቪ ብዛት 74 ሺሕ፣ 30 ኬ.ቪ ከ25 ሺሕ በላይ) ሥራ ላይ ያልዋሉ፣ ለፀሐይና ዝናብ ተጋልጠው እየተበላሹ ያሉ፣ በ2000 ዓ.ም. የተገዙ ፒን ቦልትድ ብዛት 106,275 ሥራ ላይ ያልዋሉ፣ በ2001 ዓ.ም. ዋየር ባለ 6 ሚ.ሜ 1,285,200 ሜትር፣ ዋየር ባለ 4 ሚ.ሜ 518,200 ሜትር ሥራ ላይ ያልዋሉ፣ የተለያዩ ቆጣሪዎች ከ4,000 በላይ፣ ወዘተ ሥራ ላይ ያልዋሉ መሆናቸውና በአሠራር ምክንያት ንብረቶች በየሜዳው እንዲከማቹና ለብልሽትና ለሥርቆት እንዲጋለጡ መደረጉን ከወራት በፊት አጋልጧል፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ኮርፖሬሽኑ ‹‹መሬት በገፍ በሞላበት ዘመን›› በስፋት የያዛቸው ግቢዎች ሁሉ እንደ መጋዘን እያገለገሉት ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ በውድ ዋጋ የተገዙ የአገር ሀብቶችን በወጉ መሥራታቸውን ሳያረጋግጥ፣ በአግባቡ በማይጠበቁበት ሁኔታ እያራገፈ ማስቀመጡ ተገቢነት የለውም፡፡ ይኼው ጊዜው ደርሶ እውነቱ ሲገለጥም የሌብነትና የትልልቅ ሙስና ምንጮች መሆናቸው እየታየ ነው፡፡ እነዚህ ሀብቶች ለምን ያህል ከተሞች ኤሌክትሪክ ማዳረስ ያስችሉ ነበር ተብሎ ሲጠየቅ አደጋው በልማት ላይ የተቃጣ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
በቀረው ጊዜስ ምን ይበጃል?
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ‹‹እሰይ! አበጀህ! በርታ!›› ከሚሉ ወገኖች መካከል አይደለሁም፡፡ ደግሞ ምንም ሲሠራ እንዳልከረመ ተቋም ‹‹ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ›› ተነስቼ ላጣጥለው አልሻም፡፡ ራሱ ተቋሙ ባወጣው መረጃ እስካሁን ከ5.2 ሚሊዮን ለማያንሱ ዜጎች የቀጥታ ትምህርትና ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ እየዘገየም ቢሆን ብዙዎቹን የአገራችንን የሙስና ወንጀለኞች ክስ አስቀጥቷል፡፡ ባስመለሰው ንብረት ረገድ መሬት ላይ ከታየው ስኬት ውጪ እዚህ ግባ የሚባል የሕዝብ ሀብት አልታደገም፡፡ አሁንም በአዲስ ጉልበት (የመንግሥት ቁርጠኝነትም ተጨምሮበት) እየተጋ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ትግሉን የተውት መሆኑን አስቦ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡
ከዚህ አንፃር ኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን 9ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ሲከበር ‹‹በትልልቅ የሙስና ወንጀሎች ላይ አተኩረን እንሠራለን›› ያሉትን አባባል አጠናክሮ መፈጸም ይገባል፡፡
በወቅቱ ያስቀመጧቸው በሒደት ላይ ያሉ ድርጊቶች በግልጽ ታውቀው መልካም እየታዩባቸው ነው፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተፈጸመው የ94.3 ሚሊዮን ብር የሙስና ወንጀል ምርመራ ተጠናቆ ክስ ተመሥርቷል፡፡ ውጤቱን ቶሎ እንፈልጋለን፡፡
በተንዳሆ ፕሮጀክት ከግብር ጋር በተያያዘ በመንግሥት ላይ የ5.8 ሚሊዮን ብር ጉዳት በመድረሱ ምርመራው ተጠናቆ ክሱ ተመሥርቷል፡፡ የተባለውን ማወቅ እንናፍቃለን፡፡
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በተደረገ የ100 ሚሊዮን ብር የእህል ግዥ ጨረታ ግለሰቦች በፈጸሙት ወንጀል ጨረታው ተሰርዞ ክስ መመሥረቱን ሰምተናል፡፡ ምን ሆነ?
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሐራጅ ሽያጭ ጋር የተያያዘ የ46 ሚሊዮን ብር ሕገወጥ ብድር ምርመራዎች ተጠናቅቀዋል የተባለው የት አለ?
በቀድሞው የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ከመመርያና ከአሠራር ውጪ ለግለሰቦች የስልክ መስመር እንዲዘረጋ በማድረግ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር ስልክ በማስደወል በመንግሥት ላይ በደረሰው የ14.4 ሚሊዮን ብር ጉዳት ማን ተጠየቀ?
በሼባ የብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ፍጆታ ጋር በተያያዘ በመንግሥት ላይ የደረሰ የ65.3 ሚሊዮን ብር ጉዳትስ? በተመሳሳይ በደብረ ዘይት ለሚገኘው የአቢሲኒያ ስቲል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተመሳሳይ ችግር ተመርምሮ ዕርምጃው ይፋ እንደሚደረግ ኮሚሽነሩ አስታውቀው ነበር፡፡
ከ10 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ከጫት ኤክስፖርት ጋር በተያያዘ 44 የሚሆኑ ግለሰቦችን ያካተተ የክስ ጉዳይ፣ ለብሔራዊ ባንክ በሕገወጥ መንገድ በሽያጭ ከቀረበ ወርቅ ጋር በተያያዘ የ17 ሰዎች ክስ ከዳር መድረሱ ይታወሳል፡፡ የሕዝብ ሀብት ምን ያህሉ ተመለሰ? ከተቀጡ ዜጐች ምን ያህል ትምህርት ለመስጠት ጥረት ተደረገ ማለትም ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙዎቹ የአገራችን ከተሞች ያለው የመሬት ሙስና፣ በረጂ ድርጅት ስም የሚገባ ሀብት (የኤችአይቪ/ኤድስ፣ የእናቶችና ሕፃናት ሞት፣ ለትምህርትና መሰል ተግባራት) የሚነሳበት የሙስና ጉምጉምታና የሚደርሳቸው ጥቆማ የት ደረሰ? ባንኮች አካባቢ እየተባለ ያለው ዓይን ያወጣ ድርጊትና የኮንስትራክሽን ዘርፉ ፈተና ሁሉ ሃይ ባይ ይፈልጋሉ፡፡
በቅርቡ በፓርላማ በስንት ጭቅጭቅና እግዚኦታ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ግለሰብ ከአገር መውጣት ጉዳይስ? ግለሰቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመሬት ጉዳይ ጋር በተያያዘና በሌሎችም ምክንያቶች ይጠየቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ በባሌ ሳይሆን በቦሌ የወጡበትን ምክንያት ማስረዳት ካልተቻለ የሙስና ገመናችን ጉዳይ አጠያያቂ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለበት ሥርዓት መነጋገር ካልቻልን የሙስና ገመናችንን ብዙ ቦታ የሚያደራርሰን ይመስላል፡፡
Source: Reporter http://www.freedom4ethiopian.wordpress.com

No comments:

Post a Comment