Saturday, July 27, 2013

ፍርድ ቤቱ በእነ ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ሰጠ

ፍርድ ቤቱ በእነ ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 19 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 5ኛ የወንጀል ችሎት ዛሬ ከሰአት በኋላ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት እና ሁለት የስራ ባልደረቦቻቸው ላይ በተመሰረተው ከባድ የማታለል ወንጀል ላይ ተካሂዶ በነበረው የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ሰጠ።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ፣ ዋና ጸሃፊው አስር አለቃ ሰጥአርጌ አያሌው እና የአስተዳደር ሃላፊው አቶ በቀለ ሻረው ፥ በከባድ የማታለል ወንጀል የፌደራሉ አቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸው እያንዳንዳቸው የ25 ሺህ ብር ዋስ ጠረተው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ይታወሳል።
የማህበሩ አባላት ሆነው አቅመ ደካሞች እና ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ የሆኑት ብቻ ተረጋግጦ ኑሯቸውን ለመደጎም በ1998 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 25 የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በማህበሩ አማካኝነት እንዲተላለፍላቸው ሰጥቷቸው ነበር።
አመራሮቹ ተጠርጥረው ከተከሰሱባቸው ወንጀሎች አንዱ ቤቶችን ባልተገባ መንገድ ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው አውለውታል የሚል ነው።
ከአበል ግዥና ከሌሎች የሂሳብ አርስቶች ጋር በተያያዘ ባክኗል የተባለውን ገንዘብ ሳይጨምር ያለፈው አመት የማህበሩ ገቢ ሲወራረድ በጉድለት ታይቷል የተባለው ከ98 ሺህ ብር በላይ የሚሆነው በተጠርጣሪዎቹ የተመዘበረ ነው መባሉም ሌላኛው ክስ ነው።
ግምቱ ከፍተኛ የሆነ ብር ተመዝብሯል በሚል ተጠርጥረው በተከሰሱበት ወንጀል ግለሰቦቹ ከ25 በላይ ገጽ የራስ መቃወሚያ አቅርበው አቃቤ ህግም ምላሽ በመስጠቱ ነው ዛሬ ፍርድ ቤቱ በግራ ቀኙ ክርክር ላይ ብይን የሰጠው።
 በከባድ የማታለል ወንጀል ልንከሰስ አይገባም የሚል ጥቅል ይዘት ያለው የተከሳሾቹ የራስ መቃወሚያን ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
በሌላ በኩል ሌሎች ያልተከሰሱ የማህበሩ አመራሮች ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ እስካሁን በፕሬዝዳንትነታቸው እያገለገሉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በክሱ ያልተካተተ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ መዝብረዋል በሚል ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ፥ ችሎቱም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ትክክለኛ ማስረጃቸውን ይዘው ከመጡ የጉዳዩ እውነትነት ተጣርቶ የዋስትና መብታቸው ሊነሳ እንደሚችል አስታውቋል።
የራስ መቃወሚያ ክርክሩ በማብቃቱ ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግን ማስረጃ ለመስማት ለጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
ሊቀትጉሃን አስታጥቄ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሃገር እንዳይወጡ መታገዳቸው ይታወሳል።

በጥላሁን ካሳ

fanabc

No comments:

Post a Comment