አስከፊው ስርዓት ከውስጥም ከውጭም ተወጥሯል።
አበራ ሽፈራዉ /ከጀርመን/
የኢትዬጵያን ሕዝብ ሰብአዊና ቁሳዊ መብቶች በነፆነት ትግል ሰበብ ሕወሐት ለአለፉት 39 ዓመታት ሲረግጥ
ቆይቷል።በመግቢያዬ ላይ ሀሳቤን በዚህ መልክ እንዳጠቃልል ያደረገኝ ደግሞ ባለፉት 39 ዓመታት የተከናወኑትን መለስ
ብዬ ሳያቸው ከሰመሗቸው፣ካየሗቸውና ካነበብኳቸዉ እንደተረዳሁት በእርግጥም ኢትዬጵያውያን በነዚህ ዓመታት በሕወሐት
የለየለትና መሰሪ ተግባር የተነሳ ሲገደሉ፣ሲታሰሩ፣ሰብዓዊ መብታችን ሲረገጥና፤በነፆነት ሥም ብዙዎች በቀጥታም ሆነ
በተዘዋዋሪ ለሕወሐት ጥቅም አስፈፃሚነት ሲሞቱ አልያም የጥቅሙ ተቀናቃኞች በሙሉ ሕይወታቸዉን ሲያጡ ቆይተዋል፤አለፍም
ካለ ደግሞ ያፈሩትን ንብረትና ሀብትም ለማጣት ተገደዋል፣ተዘርፈዋል፣ ተነጥቀዋል ፤እምቢ ካሉም ለአንዴና ለመጨረሻ
ጊዜ ከዚህ አለም በጥይት ተገድለው በሞት ተለይተዋል ።
ከደርግ መንግስት ዉድቀት በኋላም ለ22 ዓመታት የታየው ተጨባጭ ሁኔታ በርግጥም እነዚህ ሕወሐቶች የኢትዬጵያ
ቀንደኛ ጠላቶች መሆናቸውን አለምንም እፍረትና ይሉኝታ ሲያቅዱና ሲተገብሩ ቆይተዋል፤አሁንም ቀጥለዋል፤ተዉ ያለም
የሚጠብቀው እስር፣ግርፋት፣መሰደድና ሞት መሆኑ ለሁሉም ኢትዬጵያውያን ብቻ ሳይሆን ዓለም እያወቀው ያለ ጒዳይ ሆኗል።
የውጭ ሀገራት የዲኘሎማሲና የውጭ ግንኙነቱም በተወሰኑ የጥቅም ግንኙነት ላይ ብቻ ባተኮረና የኢትዬጵያን ሕዝብ
ጥቅም ወደጐን በተወ መልኩ የተከናወነ ሆኖ ቆይቷል፤በውጭ ሀገራት የዲኘሎማሲ ማህበረሰብ የሠብአዊና የፍትሕ ጥያቄ
ሲቀርብ ግን እርሱ የእኔ ጒዳይ ነው ተዉት እያለ የሰው ልጆችን ከሰብዓዊነት ውጭ በመጨቆን በዚህ ዘመን የማይጠበቅ
የጭቆናና የብዝበዛ ስርዓት በመሆን ቀጥሏል፤በየትኛውም የዓለም ሀገራት የማይፈፀም ግፍ ዛሬ በኢትዬጵያ ይፈፀማል።
የኢትዬጵያ ሕዝብ የሚያታግለው ስለአጣ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ያካበተው ርህሩሕነት፣ቸርነት፣ቻይነት፣ይቅር
ባይነት፣በመቻቻል አብሮ በጋራ መኖርንና መስማማትን ይዞ የኖረ ሕዝብ በመሆኑ ዛሬ ሕወሐት/ኢሕሐዴግ እነዚህን ጠቃሚ
የማህበራዊ አኗኗር እሴቶች ለመጣል እየሞከረ ይገኛል፤ይሁንና በሕዝቡ ላይ ከልክ ያለፈ ግፍ በመፈፀሙና እነዚህን
ለአገሪቷም ሆነ ለመሪዎቿ የሚጠቅሙ የማህበራዊ አኗኗር እሴቶችን ከሕዝቡ ላይ ለመሸርሸር በመሞከሩ ዛሬ
ሕወሐት/ኢሕሐዴግን ለመጋፈጥ ብዙዎች ወደ ትግሉ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ሕወሐት/ኢሕሐዴግ ከለየለት ጥፋቱ ለመመለስ ባለመፈለጉና የሕዝብን ትግስት እንደፈሪ በመቁጠሩ ዛሬ ውጥረቱ
በራሱ በሕወሐት/ኢሕሐዴግ ላይ ነግሷል፤ ወደደም ጠላም ተወጥሯል፤ሕዝቡ በድፍረት በሠላማዊ ሠልፍ ብቻ
ለሕወሐት/ኢሕሐዴግ ጥላቻዉን እየገለፀ ይገኛል፤ይህም በሕወሐት/ኢሕሐዴግ ሠፈር ትልቅ ድንጋጤን በመፍጠሩ የዉጥረቱን
መጠን ለመቀነስ የሚደረጒ ልዩልዩ ስብሰባዎችም ቢሆኑ ሌላ ተጨማሪ ድንጋጤን በገዢዎቻችን ሠፈር እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ሕወሐት/ኢሕሐዴግ የዲሞክራሲና የፍትህ ፅንሰ ሐሳቦች በፍፁም የማይገባዉና በ60ዎቹ የሶሻሊስት አስተሳሰቦች
ተተብትቦ ፤በሰብአዊ ፍጥረት ላይ ባለዉ ንቀት የተነሳና ይኸዉ አሮጌ አስተሳሰቡ ዓለም ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር
አብረዉ ሊጓዙ የሚችሉ ወጣቶችን ለመሰብሰብ ባለመቻሉ፣የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ባለመፈለጉና በዚሁ አሮጌ
አስተሳሰቦችና በጥላቻ ፖለቲካ በተመረዙ ሰዎች እየተመራ በመሆኑ ዛሬ ውጥረቱ በራሱ በድርጅቱ ዉስጥ እየሰፋ መምጣቱን
ከራሱ ከድርጅቱ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ዛሬ ኢትዬጵያ ግልፅ ባልሆነ መልኩ በተደራጁ ማፍያዎች እንደምትመራ ኢትዬጵያን ብቻ ሳይሆኑ የአለም መሪዎች ጭምር እያወቁ የመጡ ይመስላል።
በቅርቡ እንኳን በዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ በጁን 20,2013 በኮንግረስ ማን የተከበሩ ስሚዝ ሰብሳቢነት
በኢትዩጵያ ባለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ከመለስ በኋላ የምስክርነት ቃል መስማት በተከናወነበት ወቅት
የተሰነዘሩት አስተየቶችና ለኢትዬጵያ መሪዎች ማነቆ የሚሆኑ ሕጐችን ለማውጣት ቃል መግባታቸዉን ስንመለከት አሜሪካ
ከዚህ ስብሰባ በስተጀርባ በኢትዩጵያ ጉዳይ ላይ ያላትን ዕቅድ ለመተግበር መነሳቷን አልያም የሕወሐት/ኢሕሐዴግ
መሪዎች አካሄድ እንዳላስደሰታቸው ያመለክታል።
ባለፈው ሰሞን የኢትዩጵያ የልማት ድጋፍ ስጪ አገሮች አምባሳደሮች የሰማያዊ ፖርቲ አመራርን ለማነጋገርና
አንዳንድ መረጃ ለመለዋወጥ ማቀዳቸውና መተግበራቸው ከሕወሐት/ኢሕሐዴግ የይስሙላ ዴሞክራሲ ጋር ቅራኔ አንዳላቸውና
በሕዝብ እንቅስቃሴም ዙሪያ የተለየ እይታ ይዘው መቅረባቸውን ፤እንዲሁም ለዘለቄታ ግንኙነታቸውና ጥቅሞቻቸው ሕዝብ
ከጠላው ጋር መስራታቸው በታሪክ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል የገባቸውና ፤እነሱም ለውጥ ፈላጊ መሆናቸውን ማየት
ይቻላል።
አውሮፓ ሕብረት የፖርላማ ተወካዬች በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ለመነጋገር በኢትዩጵያ ያደረጉትን ጉብኝት
ብንመለከት ደግሞ «ኑና እዪ» የተባሉ ይመስል ሕዝቡ ላይ ያለዉን ችግር እራሳቸው በቅርበት ያዩትና እራሳቸውን
ጭምር ያሳዘናቸው መሆኑና ፤የኢትዩጵያ ችግር እምን ደረጃ እንደደረሰ ለመረዳት ችለዋል። እነዚህ የአውሮፓ ህብረት
የፖርላማ አባላት ኢትዩጵያ በምን አይነት ሰዎች እንደምትመራ ለመረዳት እንደቻሉና የተለየ አግራሞት እንደፈጠረባቸዉ
በቀላሉ መረዳት ይቻላል ፤ ከዚህም የተነሳ ይመስላል የህብረቱ አባላት የታሰሩ ጋዜጠኞችና የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ
አባላት ከስር እነዲለቀቁ ፣ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበር ፣የእምነትና የሀይማኖት ተቋማት መብትና
ነፆነት እንዲከበር መግለጫ እስከማዉጣት የተገደዱት።
ይህ ብቻ አይደለም በሃገራችን በሁለቱ ትልልቅ የሐይማኖት ተቋማት አካባቢ ያለዉ « የፍትህ ያለህ » ጥያቄዎች
በኢትዩጵያ መሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ባይነት ችግሩ እየተባባሰ ለመፍታት ወደሚቸግር አቅጣጫ እየመጡ መሆኑ የየዕለት
ዜናዎች ሆነዋል።
ሌላው የሕወሐት/ኢሕሐዴግ ባለስልጣናት በመላው ዓለም ከኢትዩጵያን ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር
በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የሚገጥማቸዉ ተቃዉሞ በሌሎች አገሮች ህዝቦች የሌለ በመሆኑ ህወሃቶች ምን ያህል በአገራቸዉ
ዜጎች ዘንድ የተኮንኑ ለመሆናቸዉና አመኔታ የማይጥልባቸው መሆኑ እየታወቀ መምጣቱና በኢትዩጵያ አስክፊዉ ስርአት
መሪዎች አካባቢ ትልቅ ድንገጤን እየፈጠረ መምጣቱ የቅርብ ጊዜያት እዉነታዎች ናቸዉ።
በቅርብ ደግሞ በሶስቱ ዋናዋና በአገር ውስጥ የስላማዊ ትግል አራማጅ ፓርቲዎች ማለትም በሰማያዊ
ፓርቲ፣በአንድነትና በመድረክ ላይ እየደረሰ ያለው የስም ማጥፋት ዘመቻ በህዝቡ ተቀባይነት ባይኖርዉም እንደለመደዉ
ለጥቃት መዘጋጀቱንና በነዚህም ፓርቲዎች አባላተ ላይ እየደረሰ ያለዉ እስራትና ማዋከብ በሕወሐት/ኢሕሐዴግ ፓርቲ ላይ
ትልቅ ውጥረትና ድንጋጤ መፍጠሩን ያመለክታል።
ሌላው በተለያዩ ጊዜያት ሕወሐት/ኢሕሐዴግ ለኤርትራ መንግስት የሚያቀርባችዉ በስጦታ የታጀቡ የንታረቅ ልምምጦች
ድንገት ሊነሳ የሚችል ጦርነት በስልጠናቸው ላይ የሚፈጥረዉ ችግር ትልቅ ፍርሃት እንደፈጠረባችውና ለስልጠናቸዉ ሲሉ
የትኛውንም ነገር ለመስጠት መዘጋጀታቸዉን ያሳያል።
እነዚህ በገዢዉ ፓርቲ አካባቢ ያሉት ዉጥረቶች በስለላ መዋቅር ብዛት ፣ በስር ቤቶች ብዛት ፣ በወታደራዊ
ትጥቅና ስልጠና ብዛት መፍትሄ የማያገኙባቸዉ ዋናዋና ምክንያቶች ህዝቡ ክልክ ያለፈ ጭቆና ዉስጥ መዉደቁ ፣ግልጽ
ዘር መድሎ መኖሩ፣ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በሙስና መዘፈቃቸዉና የገዢዉ ፓርቲ ንግድ ተቋማት የንግድ ብዝበዛና
ሌሎችም ህዝቡን ስላስመረረዉ ትግሉ የማይቆም ትግል መሆኑን ሁሉም ኢትዮዽያዊ እየተረዳ ያለው ሀቅ መሆኑም ጭምር
ነው።
በአለፉት ዓመታት በዝርፊያ ፣በዘር ማጥፋት ተግባር ፣ ህዝቡን በማሰርና በመግደል፣በዘረኝነት መድሎ፣ በከፍተኛ
ሙስና ተግባርና በሌሎችም ሀገርንና ህዝብን ሊጎዱ በሚችሉ ተግባራት ላይ መሰማራቱ ሊቀጥል እንደማይችል ሁሉም
የተረዳዉ ሀቅ ሆኗል ።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የስቪክ ማህበራትና ሌሎች የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ አሁን ኢትዩጵያ ካለችበት ሁኔታ
አንፃር ኢትዩጵያን ከለየለት ጭቆና ለማላቀቅ በሚደርገዉ ትግል ይበልጥ መስባስብ ፣መመካከርና የመፍትሄ አቅጣጫን
አስቀምጦ መንቀሳቀስ ጊዜዉ የሚጠይቀዉ ጉዳይ በመሆኑና የሕወሐት/ኢሕሐዴግ ውጥረት በህዝቡና በሃገሪቷ ላይ ሌላ
ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጥር አስቀድሞ መከላከል ጠቃሚ ነው እላለሁ።
እግዚአብሔር ኢትዩጵያን ይባርክ!
Short URL: http://www.zehabesha.com/
No comments:
Post a Comment