Tuesday, July 16, 2013

በቅድስት ሥላሴ መ/ኮሌጅ ጉዳይ ቋሚ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

  • ደቀ መዛሙርቱ ቅ/ሲኖዶሱ ከመንግሥት በመነጋገር የደኅንነት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል
  • የልዩ ጽ/ቤቱን ለቃችኹ ውጡ ትእዛዝ ‹‹ሕግን የጣሰና ለከሳሽ ያደላ›› በሚል ተቃውመውታል
  • የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ እና የጠ/ቤ/ክህነቱ ዋ/ሥራ አስኪያጅ ደቀ መዛሙርቱን እያረጋጉ ነው
  • የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ ከደቀ መዛሙርቱ ጎን ቆመዋል ተብሏል
  • ኹኔታው ያሳሰባቸው የማታ ተማሪዎች ተወካዮች ከቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ጋራ ተወያይተዋል
  • የኮሌጁ መምህራን አቡነ ጢሞቴዎስ ከበላይ ሓላፊነታቸው እንዲነሡ መጠየቃቸው ተሰምቷል
  • በሕገ ቤተ ክርስቲያን ኮሌጁን በበላይነት የመቆጣጠር ሥልጣን የዋ/ሥ/አስኪያጁ ነው
  • የኮሌጁ ቦርድ እና አስተዳደሩ ብቃት ባላቸው ባለሞያዎች እንዲደራጅ የጠየቀው አጣሪ ኮሚቴው ቦርዱ ተጠሪነት ከቅ/ሲኖዶስ ይልቅ ለጠ/ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲኾን በሪፖርቱ መክሯል
  • ‹‹ኮሌጁ እንደ ሀ/ስብከቴ ነው፤ በኮሌጁ ጉዳይ ጣልቃ አትግቡብኝ!›› /አቡነ ጢሞቴዎስ/
  • ‹‹የኮሌጁን ጉዳይ ለኔ ተዉት!›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር እስከ መጪው ፳፻፮ ዓ.ም መስከረም ወር አጋማሽ ድረስ እንደተዘጋና ደቀ መዛሙርቱ ኮሌጁን እስከ ዛሬ ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ‹‹በሰላማዊ መንገድ›› ለቀው እንዲወጡ የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት በትላንትናው ዕለት በይፋ ያወጣውን ማስታወቂያ የተቃወሙ የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ቅ/ሲኖዶሱ ለአስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ መስማማታቸው ተገለጸ፡፡
ሐራዊ ምንጮች ከመንበረ ፓትርያሪኩና ውዝግቡ አፋጣኝ እልባት እንዲያገኝ በበጎ ፈቃድ ከሚንቀሳቀሱ አካላት እንደተረዱት÷ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና አራቱ ተተኪ/ተለዋጭ የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔና ያወጣውን ማስታወቂያ በመቃወም በኮሌጁ ወቅታዊ ኹኔታ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ ለቅ/ሲኖዶሱ አባላት አድርገዋል፡፡ ስብሰባው እስከ መጪው ዐርብ፣ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ድረስ ሊጀመር እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
EOTC_HeadQuarter
ቅ/ሲኖዶሱ በአስቸኳይ ስብሰባው÷ ልዩ ጽ/ቤቱ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ያሳለፈው ውሳኔና ያወጣው ማስታወቂያ ከሕገ ቤተ ክርስቲያንና ውዝግቡን ለማጣራት የተቋቋመው ኮሚቴ ካቀረባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች አንጻር ያለው አግባብነት ይፈተሻል፤ ኮሚቴው ከአጭርና ከረጅም ጊዜ አኳያ የዘረዘራቸውን የማስተካከያ ርምጃዎች መርምሮ ተፈጻሚ እንዲኾኑ መመሪያ ይሰጣል፤ ከዚህም ባሻገር አካላዊ ጤንነታቸው ለያዙት ሓላፊነት ብቁ አያደርጋቸውም የተባሉትን የኮሌጁን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ የማንሣት ርምጃም ሊወስድ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
የቋሚ ሲኖዶሱ ሰብሳቢ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ቢኾኑም በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፲/፪/ሀ መሠረት የቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይና ድንገተኛ ጉባኤ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ወይም ቋሚ ሲኖዶሱ በሚያደርጉት ጥሪ ሊካሄድ ይችላል፡፡ በሕመምና በልዩ ልዩ ከአቅም በላይ በኾነ ምክንያት አንዳንድ አባላት ባይገኙ እንደ አጀንዳው ዐይነት /የሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ወይም የአስተዳደር መኾኑ/ ተለይቶ ከዚህ አኳያ የምልአተ ጉባኤው መሟላት ተወስኖ ስብሰባው ሊደረግ እንደሚችል በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ ፫/ሀ እና ለ ላይ ተደንግጓል፡፡

No comments:

Post a Comment