Saturday, July 27, 2013

ዘንድሮ ከቀረቡት የሙስና ጥቆማዎች መካከል ከግማሽ በላይ ኮምሽኑን የሚመለከቱ አይደሉም

ዘንድሮ ከቀረቡት የሙስና ጥቆማዎች መካከል ከግማሽ በላይ ኮምሽኑን የሚመለከቱ አይደሉም

በጋዜጣው ሪፖርተር
ለፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን በ2005 በጀት ዓመት ከቀረቡት የሙስና ጥቆማዎች መካከል በኮምሽኑ ሥልጣን ሥር የሚወድቁት ከግማሽ በታች መሆናቸው ተጠቆመ።
ከኮምሽኑ የተገኘ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንዳመለከተው በበጀት ዓመቱ ለኮሚሽኑ የቀረቡት 3ሺ710 ጥቆማዎች ሲሆኑ ጥቆማዎቹን የመመዝገብና የመለየት ስራ ተከናውኗል። ከቀረቡት ጥቆማዎች 1ሺ670 (45 በመቶ)በኮሚሽኑ ሥልጣን ሥር የሚወድቁ ሲሆኑ 2ሺ40 (55 በመቶ) ከኮሚሽኑ ስልጣን ክልል ውጪ ሆነዋል። በተጨማሪም ከቀረቡት ጥቆማዎች 42ቱ የከለላ አቤቱታዎች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 21ቹ የመጀመሪያ ከለላ ሲሰጣቸው 16ቱ ከለላ የማያሰጣቸው ሆነው ተገኝተዋል፤ ቀሪዎቹ 5ቱ በመጣራት ላይ ይገኛሉ። ከቀረቡት ጥቆማዎች መካከል ከግማሽ በላይ ኮምሽኑን የሚመለከቱ ሊሆኑ ስላልቻሉበት ምክንያት በሪፖርቱ የተጠቀሰ ነገር የለም።
በበጀት ዓመቱ 508 የምርመራ መዝገቦችን በራስ ኃይል መርምሮ ለማጠናቀቅ ታቅዶ 449 ተመርምረው ተጠናቀዋል። ክንውኑ ዝቅ ሊል የቻለው የበጀት ዓመቱ የአዲስ ሰራተኞች ቅጥር በወቅቱ ባለመፈጸሙ ምክንያት ነው ብሏል።
በራስ ኃይል ከተመረመሩ የሙስና ወንጀል መዝገቦች መካከል 60 በመቶ በሚሆኑት ላይ በማስረጃ የተደገፈ የ“ያስከስሳል” ውሳኔ ለማሳረፍ ታቅዶ በራስ ኃይል ከተመረመሩ 336 መዝገቦች መካከል ለ163 መዝገቦች የያስከስሳል ውሳኔ ተሰጥቷል። (81 በመቶ) ተዘጋጅተው ከቀረቡ 380 የክስ ቻርጆች መካከል 362 የክስ ቻርጆች በበቂ ማስረጃ ተደግፈው ተዘጋጅተዋል።
በኮሚሽኑ ስልጣን ክልል ስር ከሚወድቁት ቀላል የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች መካከል ስልጣን ባላቸው መርማሪ አካላት እንዲመረመሩ ከተላኩ ጥቆማዎች መካከል ክትትል በማድረግ በበጀት ዓመቱ የሚመለሱትን ሽፋን ከ71 በመቶ ወደ 80በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ ሥልጣን ባላቸው መርማሪ አካላት እንዲመረመሩ ከተላኩ 246 ጥቆማዎች መካከል ክትትል በማድረግ 231(94 በመቶ) ተመልሰዋል።
በኮሚሽኑ ስልጣን ክልል ስር ከሚወድቁት ቀላል የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች መካከል የሚመለከታቸው መ/ቤቶች አጣርተውና እርምጃ ወስደው ከተላኩ ጥቆማዎች መካከል ክትትል በማድረግ በበጀት ዓመቱ የሚመለሱትን ሽፋን ከ71 በመቶ ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ  የሚመለከታቸው መ/ቤቶች አጣርተውና እርምጃ ወስደው እንዲያሳውቁን ከተላኩ 230 ጥቆማዎች መካከል ክትትል በማድረግ ቀደም ሲል የተላኩትን ጨምሮ 278 ተመልሰዋል።
ምርመራ ከሚካሄድባቸው የሙስና ወንጀል ጉዳዮች መካከል 60 በመቶ የሚሆነውን የያስከስሳል ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ ውሳኔ ካገኙ ምርመራቸው የተጠናቀቀ መዝገቦች 336 ሲሆኑ 163ቱ የያስከስሳል ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል።
በበጀት ዓመቱ 1ሺ 488 የምርመራ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ በ880 መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል። ክንውኑ ዝቅ ሊል የቻለው የበጀት ዓመቱ የአዲስ ሰራተኞች ቅጥር በወቅቱ ባለመፈጸሙ ምክንያት ነው።
በ900 የችሎት መዝገቦች ላይ ክርክር ለማድረግ ታቅዶ በ638 መዝገቦች ላይ ክርክር ተደርጓል። ክንውኑ ዝቅ ያለው ወደ ችሎት የቀረቡ ጉዳዮች በማነሳቸው ነው።
(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 411 ሀምሌ 17/2005) freedom4ethiopian.wordpress.com

No comments:

Post a Comment