Tuesday, July 16, 2013

እስራኤልና አፍሪቃዉያን ስደተኞች

አፍሪቃ

እስራኤልና አፍሪቃዉያን ስደተኞች

እስራኤል በምድሯ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂ አፍሪቃዉያንን ወደየመጡበት አስገድዳ መመለሷን የመብት ተሟጋቾች አወገዙ። ከትናንት በስተያ እስር ላይ ካቆየቻቸዉ ሁለት ሺህ ኤርትራዉያንና ሱዳናዉያን መካከል 14 ኤርትራዉያንን ወደአስመራ መላኳን አንድ የእስራኤል የመብት ተሟጋች ድርጅትና ሂዉማን ራይትስ ዎች ይፋ አድርገዋል።
ድርጊቱን ሲቃወም መቆየቱን ያመለከተዉ ዓለም ዓቀፉ የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች ስደተኞቹ ክስና ቁም ስቅል ይፈጸምብናል ብለዉ ወደሚሰጉበት መመለሳቸዉ ዓለም ዓቀፍ ህግን የጣሰ መሆኑን አመልክቷል።
እስራኤል ዉሃ ጥምና ረሃቡን ታግሰዉ ከበደዊን ዘላኖች እገታ ነፍሳቸዉንና አካላቸዉን አትርፈዉ የሲና በረሃን አቋርጠዉ ወደግዛቷ የሚገቡ ስደተኞችን ወደየመጡበት እመልሳለሁ ስትል ብትቆይም ከዛቻ የሚያልፍ ያልመሰላቸዉ በርካቶች ነበሩ። በርከት ያሉ የደቡብ ሱዳን ዜጎችን አገራቸዉ ነፃነቷን ባወጀች ማግስት ጥቂት ገንዘብ በእጃቸዉ እያስያዘች ስትመልስ፤ የራሷ ዜጎች ሳይቀሩ «እኛም ስደተኞች ነን» ሲሉ አደባባይ ወጥተዉ ድምጻቸዉን አሰሙ። ርምጃዉ ጋብ ያለ መሰለ። ከትናንት በስተያ ደግሞ እስራኤል ዉስጥ ከሚገኙት በርካታ ኤርትራዉያን ወጣቶች መካከል እስሩና ከእስርም እንደማይለቀቁ በሚቀርባለቸዉ ማሳሰቢያ የመጣዉ ይምጣ ያሉ 14 ኤርትራዉያንን በኢስታንቡል በኩል አድርጋ ለእያንዳንዳቸዉ 1,500 ዶላር እያስያዘች ወደአስመራ ሸኘች። እስራኤል ዉስጥ የሚገኙትም ሆነ ዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋቾች ድርጊቱን ሲያወግዙ ቢቆዩም የእስራኤልን መንግስት አቋም ማስቀየር አልቻሉም። የሂዉማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ የስደተኞች ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ጄሪ ሲምፕሰን ጥገኝነት የመጠቂያ ሰነዱን እንኳ የመሙላት እድል ያላገኙት ተሰዳጆች ይህን አማራጭ ለመቀበል በስልት ተገደዋል ይላሉ፤
የስደተኞች ኑሮ
«እስራኤል በታሠሩ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራዉያን እና ሱዳናዉያን በፈቃዳቸዉ ወደአገራቸዉ ለመመለስ ተስማምተናል በሚል እንዲፈርሙ ጫና ማድረግ እንድታቆም ስንጠይቅ ቆይተናል። እስራኤል ባለፉት ዓመታት ወደአገሯ የገቡ  በግብጽ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘዉ ጣቢያ ያሰረቻቸዉን 2ሺ የሚሆኑ ኤርትራዉያንና ሱዳናዉያን የጥገኝነት ጥያቄ መዝግባ ጉዳያቸዉን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንደመልቀቅ ለሶስት ዓመታት እንደሚታሰሩ ታስፈራራለች። እናም በመጨረሻ ከዓለም እጅግ እመቃ/ጭቆና/ ወደበዛባት አገራቸዉ የተመለሱት 14 ኤርትራዉያን በዚህ ግፊትና ታስራችሁ ትቆያላችሁ በሚለዉ ማስፈራሪያ ምክንያት ነዉ።»
በዚህ ምክንያትም እስራኤል የጥገኝነት ጥያቄያቸዉን እስክታጣራ ድረስ ጥገኝነት ጠያቆዎቹን እንድትፋታና በከተሞች እንዲኖሩ እንትፈቅድ ጥያቄ ማቅረባቸዉን እንደቀጠሉም ይገልጻሉ።   
እስራኤል ዉስጥ 60 ሺህ አፍሪቃዉያን ስደተኞች እንዳሉ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህ መሃል ደግሞ 35ሺዉ ኤርትራዉያን ናቸዉ። ጥገኝነት ጠያቂዎቹ አፍሪቃዉያን በሚኖሩባቸዉ አካባቢዎች በሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ምክንያት እና በብዛታቸዉ እስራኤላዉያኑ ስጋት እንዳደረባቸዉ ነዉ የሚነገረዉ። ከኤርትራ የተሰደዱት ወጣቶች በአገራቸዉ ካለዉ ወታደራዊ አገልግሎት ሽሽት መሰደዳቸዉን ይገልጻሉ የእስራኤል ባለስልጣኖች ደግሞ ህገወጥ ስራ ፈላጊዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። በዘገባዉ እንደተገለጸዉ እሁድ እለት እንዲመለሱ ከተደረጉት መካከል ቢያንስ አንዱ ከብሄራዊ ዉትድርናዉ የሸሸ መሆኑን ገልጿል። ያን ግን ከግምት አልገባለትም። በሱዳን ህግ ደግሞ እስራኤልን የረገጠ እስከአሰር ዓመት በእስራት እንደሚቀጣ ነዉ የተገለጸዉ።  ጄሪ ሲምፕሰን እንደሚሉት እስራኤል ወደየአገራቸዉ ለመመለስ የምትዝትባቸዉ እነዚህ ተሰዳጆችን እያሰረች እንዲመለሱ የማስገደድ እቅድም መኖሩንም ሂዉማን ራይትስ ዎች መቃወሙን ነዉ የሚገልጹት፤
«ከፍተኛ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ 50 ሺዎቹን በሙሉ ለመጠረዝ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ሰኔ 24ቀን እስራኤል በተከታታይ ስትወስድ ከነበረዉ ርምጃ አንዱን አጽድቃለች፤ ይኸዉም ዝቅተኛ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች እንዲታሰሩ የሚያዝ ነዉ፤ ለምሳሌ ሞባይል ስልክ ወይም ብስኪሌት የሠረቀ ወይም ሌላ ዝቅተኛ ወንጀል የፈጸመ ማለት ነዉ። በተጨማሪም የታሠሩት ከአገሪቱ እንዲወጡ ጫና ማድረጉም ይቀጥላል። እናም እስራኤል ይህን ህግ በመጠቀም በከተሞች የሚኖሩትን 50ሺ ስደተኞች ወደማሰር እና እንዲወጡላት ጫና ወደማድረግ ታመራለች ብለን እናስባለን። ጥገኝነትን በሚጠይቁ ሰዎች ላይ ይህን ማድረግ ህገወጥ ነዉ።»
ስደተኞች መጠለያ ዉስጥ

እሳቸዉ እንደሚሉትም እስራኤል ስደተኞችን በእስር የምታቆይባቸዉ ቦታዎች በአንድ ጊዜ ከአምስት እስከ ስድስት ሺህዎቹን ብቻ ነዉ መያዝ የሚችሉት። ባለስልጣኖች ከሰጡት መግለጫ በመነሳት የሚናገሩት ሲምፕሰን ስደተኞቹ ላይ ጫናዉን ለማጠናከር ሲባል የተጠቀሰዉን ህግ ተጠቅሞ በርካቶቹን ለማሰር በአስር ሺዎችና በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለማዉጣት ዝግጅት መኖሩንም ያመለክታሉ። በእርግጥ ይህ መቼ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም ነዉ ያሉት። ባለፈዉ ሰሞን የወጡ ዘገባዎች እስራኤል በርከት ያሉ ስደተኞችን ወደሶስተኛ አገር ለመስደድ ካልተጠቀሱ የአፍሪቃ ሃገሮች ጋ መስማማቷን አመልክተዋል። ጄሪ ሲምፕሰን የተባለዉ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ቢሰማም እስካሁን የሃገሮቹ ማንነት እንዳልተጠቀሰ፤ ገልጸዉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ቢሆን እንኳን በተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መስፈርት መሰረት ሊከናወን እንደሚገባ ነዉ ያመለከቱት፤
«እስራኤል ይህን ስምምነት ተፈራርማም ከሆነ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከአንድ አገር ወደሌላዉ የሚተላለፉበት ግልጽ መስፈርት አለዉ። እኛም እስራኤል ሸክሙን ወደሌላ እንዳታዛዉር ማለትም በሺዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ፈላጊዎችን ወደሌላ አገር እንዳትጭን በግልፅ ተናግረናል። UNHCRም ጥገኝነት የመስጠት ግዴታቸዉን ለመሸሽ ሲሉ ይህን ማድረግ እንደማይገባቸዉ ግልጽ አድርጓል። ስለዚህ እስራኤል እነዚህ ሰዎች ወደሌላ አገር ማዛወር አይኖርባትም፣ ይልቁንም ጥገኝነት የሚያገኙበትን ሂደት በማመላከት ጥያቄያቸዉን በበቂና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ልታይላቸዉ ይገባል።» 
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ


source.... http://www.dw.de

No comments:

Post a Comment